በአፍሪካ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በባዮ ቴከኖሎጂ ሰብል ተሸፍኗል

19 Jun 2017
420 times

አዲስ አበባ ሰኔ 12/2009 በአፍሪካ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በባዮ ቴከኖሎጂ ሰብል መሸፈኑን ዓለም አቀፉ የባዮቴክኖሎጂ ማዕከል ይፋ አደረገ።

ማዕከሉ ዓመታዊ ሪፖርቱን በካሜሩን ይፋ ሲያደርግ እንደገለጸው አፍሪካ በ2016 አውሮፓውያን ዓመት ሰፊ ማሳ ለባዮ ቴክኖሎጂ ሰብል አውላለች።

ያለፈው አውሮፓውያን ዓመት የባቴክኖሎጂ ሰብሎችን በማልማት ረገድ ለአፍሪካ 19ኛው ዓመት እንደነበር ሪፖርቱ አውስቶ የባዮ ቴክኖሎጂ ሰብል በ13 የአፍሪካ አገሮች በስፋት እየተመረተ መሆኑን አስታውቋል።

ደቡብ አፍሪካና ሱዳን ለባዮ ቴክኖሎጂ ሰብል ልማት መስፋፋት የሰጡትን ትኩረት አሁንም ቀጥለውበታል ነው ያለው።

በ2015 አውሮፓውያን ዓመት የባዮ ቴክኖሎጂ ሰብል ልማት በ11 የአፍሪካ አገሮች ብቻ ይመረት እንደነበር አስታውሷል።

ሶስት የአፍሪካ አገራት ከሙከራ ምርምር ተሸጋግረው የባዮ ቴክኖሎጂ ሰብሎችን ከአካባቢ ተስማሚነታቸውን ለማረጋገጥ የመስክ ሙከራ ስራ መጀመራቸውን ጠቁሟል።

ኬኒያ በጥጥና በቆሎ ልማት፣ ናይጄሪያና ማላዊ በጥጥ ልማት ባዮቴክኖሎጂን መጠቀማቸውን ጠቁሞ ይህም በእነዚህ ምርቶች ሰፋፊ የእርሻ ልማት ስራ ውስጥ ከአንድና ሁለት ዓመታት በኋላ አገራቱ እንደሚገቡ አመላካች ነው ብሏል።

ከዚያ በፊት ግን አገራቱ ዘርፉን የሚደግፍ ፖሊሲ ማውጣትና ባዮ ቴክኖሎጂን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት የሚያስችል ምርምርና አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ገልጿል።

በተጨማሪም ስድስት የአፍሪካ አገሮች በተለያዩ አካባቢዎች የባዮ ቴክኖሎጂ ሰብሎችን ለማልማት የሙከራ ስራ መጨረሳቸውን ጠቁሞ ሰብሎቹን በስፋት ለማሰራጨት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ጥጥን በስፋት ለማልማት ዝግጅታቸውን ካጠናቀቁ አገራት አንዷ መሆኗን ገልጾ ቡርኪናፋሶና ጋና ካውፒ በመባል የሚታወቀውን የአተር ዘር በባዮ ቴክኖሎጂ ለማልማት መዘጋጀታቸውን አመልክቷል።

ናይጄሪያ ማሽላና ካውፒ/አተር/ ስዋዚላንድ ጥጥ፣ ኡጋንዳ ደግሞ ሙዝና በቆሎ ለማልማት ዝግጅት ካደረጉ አገራት መካከል ይገኙበታል ሲል ማዕከሉ  ለኢዜአ በላከው መግለጫ ገልጿል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ