አርዕስተ ዜና

በኢንዱስትሪ ፓርኮች የፍሳሽ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ ለመገንባት ስምምነት ሊደረግ ነው Featured

19 Jun 2017
318 times

ሐዋሳ ሰኔ 12/2009 አርቪንድ ኢንቪሶል የተሰኘ የህንድ ኩባንያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የፍሳሽ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ ለመገንባት የመግባቢያ ሰነድ ሊፈራረም ነው።

ሰነዱን ከኩባንያው ጋር የሚፈራረሙት የኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ናቸው።

በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያካበተው ኩባንያው በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገነቡ 10 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ግንባታ ያካሂዳል ተብሏል።  

መንግሥት የአገሪቱን ምጣኔ ኃብት ለማሳደግ ከሚሰራባቸው ዘርፎች መካከል የአምራች ኢንዱስትሪውን ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጓል።

ይህን ለማቀላጠፍም የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ለውጭም ሆነ ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው።

ይህም ከፍተኛ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ለማስቻል ፓርኮቹ በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ ውጤቶችና መሰል ዘርፎች ላይ እንዲያተኩሩ እየተሰራ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የወጪ ንግድ ላይ ትኩረት ያደረ የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴም በትኩረት እየተሰራበት ያለ መስክ ነው።

የሚገነቡት ፋብሪካዎች ደግሞ በአካባቢ ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድሩ በተለይም ከፋብሪካዎቹ የሚወጣ የፍሳሽ ውሃን ማጣራት ቅድሚያ ይሰጠዋል።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ሥልትን ተግባራዊ አድርጋ በመንቀሳቀስ በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ ለመቀነስ እየሰራች ነው።

በአሁኑ ወቅትም በአዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የፍሳሽ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ በመግጠም በቀን 11 ሚሊዮን ሌትር ፍሳሽ ውሃ እየተጣራ ይገኛል።

ይህም ከአፍሪካ ቀዳሚ ሲሆን ለግንባታው የወጣው ወጪ ደግሞ አነስተኛ መሆኑ ነው የተጠቆመው።

ፓርኩ በቀን የሚመነጨውን ቆሻሻ ውሃ ሙሉ በሙሉ መልሶ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑ ተገልጿል።

ይህን ተሞክሮ ወደ ሌሎች ፓርኮች ለማስፋት ነው አርቪንድ የተሰኛው ኩባንያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ነገ የመግባቢያ ሰነድ የሚፈራረመው።

ይህም በመርዛማ ፍሳሾች ምክንያት በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በእጅጉ እንደሚቀንስ ታምኖበታል።

በዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ የሚገነቡት የውሃ ማጣሪያ መሳሪያዎችን በሌሎች ፋብሪካዎችም ለመተግበር ነው ሥምምነት ላይ የሚደረሰው። 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ