አርዕስተ ዜና

ኢንስቲትዩት የኤክስፖርት አፈጻጸሙን ለማሻሻል በተግባር መንቀሳቀስ አለበት

19 May 2017
711 times

አዲስ አበባ ግንቦት11/2009 የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኤክስፖርት አፈጻጸሙን ለማሻሻል ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢንስቲትዩቱን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ላይ ተወያይቷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ መኩዬ እንዳሉት የኢንስቲትዩቱ የዘጠኝ ወራት የኤክስፖርት ዘርፍ አፈጻጸም እጅግ ዝቅተኛ ነው።

ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የቆዳ ውጤት ፋብሪካዎች በሚፈለገው ደረጃ አለመጠናከር መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ላይ ጠንካራ ሥራ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

"በመስኩ የሚሰማሩ የውጭ ባለሃብቶች በሚፈለገው ደረጃ እየመጡ አይደለም" ያሉት ሰብሳቢው ችግሩን ለመፍታት የኢንቨስትመንት ኮሚሽንን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

"የግብዓት አቅርቦት፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረትና የፋብሪካዎች አቅም ውስንነት የሚሉ ተደጋጋሚ ምክንያቶች በቀጣይ መነሳት የለባቸውም፤ ኢንስቲትዩቱም ይህን ተገንዝቦ ተጨባጭ ሥራ ሊያከናውን ይገባል" ነው ያሉት።

የቆዳ ፋብሪካዎች አካባቢን እየበከሉ ስለመሆኑ ከኀብረተሰቡ ጥቆማ እየመጣ መሆኑን የተናገሩት አቶ ብርሃኑ ብክለቱን ለመከላከል ፋብሪካዎቹ አገር አቀፉን መስፈርት ተከትለው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግሩን ለማቃለል ኢንስቲትዩቱ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማትና ከዩኒቨርስቲዎች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑ በአንጻሩ የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ተቋሙ በበጀት ዓመቱ በዘርፉ ከ15 ሺህ በላይ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ቢያቅድም ያሳካው አራት ሺህ  ብቻ በመሆኑ በቀጣይ ትኩረት እንዲሰጠው አመልክተዋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዱ ለገሰ በሰጡት ማብራሪያ የኤክስፖርት አፈጻጸሙን ለማሻሻል ባለሃብቶች በሌሎች አገራት ኤግዚቢሽኖችና መሰል ዝግጅቶች ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል። 

የቆዳ ውጤት ዓለም አቀፍ የገበያ መዳረሻዎችን ከማስፋት አኳያም ጥረት መደረጉን ጠቅሰው የውጭ ባለሃብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ የማግባባት ሥራ መሰራቱን አክለዋል። 

የቆዳ ፋብሪካዎች አካባቢ እንዳይበክሉ ለማድረግ ኢንስቲትዩቱ ተከታታይ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ