አርዕስተ ዜና

የኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታ ወደ ሦስተኛ ምዕራፍ ተሸጋግሯል Featured

21 Apr 2017
579 times

ቤጂንግ ሚያዝያ 13/2009 የኢትዮ-ቻይና ኋጂዬን ዓለም አቀፍ የቀላል ኢንዱስትሪ ግንባታ ወደ ሦስተኛ ምዕራፍ መሸጋገሩ የኋጂዬን ግሩፕ ፕሬዚዳንት ዃሮን ጇን ገለጹ።

በጫማ ምርት የተሰማራው ኋጂዬን ግሩፕ በመስኩ የበቁ ኢትዮጵያዊያን ሙያተኞችን ለማፍራት በቻይና ሥልጠና እየሰጠ ነው።

ፕሬዚዳንቱ ዃሮን ጇን ለኢዜአ እንደገለጹት በአንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እየተካሄደ ያለው የኢትዮ-ቻይና ኋጂዬን የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ እየተፋጠነ ይገኛል።

ከሁለት ዓመት በኋላ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው የኢንዱስትሪ ፓርኩ ወደ ሦስተኛ ምዕራፍ ግንባታ መሸጋገሩን ነው ፕሬዚዳንቱ የገለጹት።

በአዲስ አበባ 137 ነጥብ 8 ሄክታር መሬት ላይ እየተገነባ ያለው የኢትዮ-ቻይና ኋጂዬን የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ፓርክ "የፋብሪካዎች፣ የመንገድ፣ የውኃና የኃይል መሰረተ ልማቶች ዝርጋታ እንዲሁም የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው" ብለዋል።

ሌሎች ሥራዎች በቀሪ ምዕራፎች እንዲከናወኑ በማድረግ የፓርኩ ግንባታ ከሁለት ዓመት በኋላ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም በዓመት 2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ የሚያስገኝ ሲሆን ከ50-60 ሺህ ለሚደርሱ ኢትዮጵያዊያን የሥራ ዕድል የማስገኘት አቅም ይኖረዋል።

በሴቶች ጫማ ምርት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው ኋጂዬን ግሩፕ በኢትዮጵያ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2012 ሥራውን የጀመረ ሲሆን ለአራት ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ያስገኘ የጫማ ፋብሪካ አለው።

በዚህ ፋብሪካው በቀን 6 ሺህ 500 ጥንድ ጫማዎችን በማምረት ለአውሮፓና አሜሪካ ገበያዎች በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በኢትዮጵያ የጀመረውን የኢንቨስትመንት ሥራ ለማስፋፋት የኢትዮ-ቻይና ኋጂዬን የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ እያከናወነ ነው።

ኋጂዬን ግሩፕ የኢትዮጵያን የጫማ ኢንዱስትሪ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በመስኩ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል ፕሬዚዳንቱ።

በዚህ ረገድ ኩባንያቸው 400 ኢትዮጵያዊያንን በቻይና ዶንጓን ከተማ በጫማ ዲዛይንና ምርት እንዲሁም በዘርፉ አስተዳደር በሦስት ዙሮች ሥልጠና መስጠቱን አስረድተዋል።

በአራተኛ ዙር ደግሞ 52 ኢትዮጵያዊያንን ተቀብሎ በቻይና ለአንድ ዓመት የተግባር ላይ ሥልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል። 

ኩባንያው በቀጣይም በየዓመቱ 2 ሺህ አፍሪካዊያንን የማሰልጠን ዕቅድ እንዳለውና ከዚህ ውስጥ የበዙት ኢትዮጵያዊያን እንደሚሆኑ ይፋ አድርጓል።

ወጣት ቅዱስ ገብረሚካኤል ከጓንጆ ኮሌጅ በጫማ ዲዛይን ትምህርት የተመረቀ ሲሆን በኋጂዬን ዲዛይን ተቆጣጣሪነት በመስራት ላይ ነው።

ኩባንያው የሥራ ዕድልና የቴክኖሎጂ ሽግግር ከመፍጠር ባለፈ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ መስራቱ "ሌሎች መሰል ኩባንያዎች እንዲሳቡ የሚያደርግ ነው" ብሏል።

ኢትዮጵያዊያን ሠራተኞች ቻይና መጥተው መሰልጠናቸው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን የሚያሳድገው መሆኑንም ገልጿል።

ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ሻሻመኔ አካባቢ የመጣችው ወጣት ጥሩወርቅ መገርሳ በ2008 ዓ.ም ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ በአግሮኖሚ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛለች።

በኋጂዬን ተቀጥራ በጫማ ዲዛይንና ምርት ለመሰልጠን ቻይና የምትገኘው ወጣቷ ወደፊት ትልቅ አቅም ፈጥራ ወደ አገሯ እንደምትመለስ ተናግራለች።

ወጣት ባይሳ ሚልኪሳ የኮሌጅ ትምህርቱን አጠናቆ ስራ ሲያፈላልግ ኋጂዬን የሥራ ዕድል እንዳስገኘለትና ለሥልጠና ወደ ቻይና መምጣቱን ገልጿል።

በቻይና ቆይታው የጫማ አሰራር፣ የአስተዳደር ሥርዓትና ለመግባባት የሚያግዝ የቻይና ቋንቋ በመልመድ የተሻለ አቅም ፈጥሮ ወደ አገሩ ለመመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑን ነው የተናገረው።

ሥልጠናው የኢትዮጵያን የጫማ ሥራ ኢንዱስትሪ ከፍ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑንም ጠቅሷል።

ኋጂዬን ግሩፕ የኢትዮጵያ ፋብሪካውን ጨምሮ በአጠቃላይ 15 ሺህ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን በዓመት 20 ሚሊዮን ጥንድ ጫማዎችን በማምረት ለዓለም ገበያ ያቀርባል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ