አርዕስተ ዜና

የምግብና መጠጥ አውደ ርዕዩ ለገበያ ትስስርና ለምርት ማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ ነው

21 Apr 2017
326 times

አዲስ አበባ ሚያዝያ 13/2009 አገር አቀፉ የምግብና መጠጥ አውደ ርዕይ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርላቸው የአውደ ርዕዩ ተሳታፊዎች ገለጹ።

ሶስተኛው አገር አቀፍ የምግብና መጠጥ አውደ ርዕይ ዛሬ በኤግዚቢሽን ማዕከል ተከፍቷል።

የቅባት እህሎች አስመጪና ላኪ ድርጅት የኤክስፖርት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አዲሱ ጌትነት በኤግዚቢሽኑ ሲሳተፉ የመጀመሪያቸው መሆኑን ገልጸው ገበያ ለማግኘት መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።

የባልትና ምርቶች ማከፋፈያ የምርት ሽያጭ ባለሙያዋ ወጣት መስከረም ታደለ በበኩሏ አውደ ርዕዩ ምርቶቻቸውን ለሌሎች ተሳታፊዎች ለማስተዋወቅና የገበያ ተደራሽነታቸውን ለማስፋት እንደሚረዳ ተናግራለች።

ሸማቾችና ሻጮችን በአንድ ቦታ የሚያገናኝ በመሆኑ የገበያ ትስስር ለመፍጠር መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ነው ያስረዳችው።

"አውደ ርዕዩ ምርቶቹን ከመሸጥ ባሻገር የሚፈጥረው የገበያ ትስስር ለቀጣይ ስራ የሚያስገኘው ጥቅም የጎላ ነው" ያለው ደግሞ የአንድ አልኮል መጠጦች ፋብሪካ ተወካይ ኢንጂነር ሳምሶን ጉዲሳ ነው።

የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ምርቶችን ለኅብረሰቡ ለማስተዋወቅ አውደ ርዕዩ ምቹ መሆኑንም አክሏል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መብራህቱ መለስ አውደ ርዕዩ ሸማቾችና ሻጮችን በማገናኘት፣ የተሳታፊዎችን ምርቶች በማስተዋወቅና የገበያ እድል በመፍጠር ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

የዘርፉን ኢንዱስትሪዎችና አቅራቢዎች በማገናኘት ትስስራቸውን እንዲያጎለብቱ እንደሚረዳና ዘርፉ የደረሰበትን ደረጃ የማሳየት አጋጣሚ እንደሚፈጥርም ጠቅሰዋል።

የምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና ኤስ.ፒ ጄኔራል ቢዝነስ አውደ ርዕዩን በጋራ አዘጋጅተውታል።

ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ቀናት የሚቆየው አውደ ርዕይ "ጥራት ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት" በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል።

በአውደ ርዕዩ በምግብና መጠጥ ማምረት እንዲሁም ማሸግ ስራ የተሰማሩ 66 ድርጅቶች፣ አስመጪዎችና አቅራቢዎች እየተሳተፉ ነው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ