አርዕስተ ዜና

በክልሉ በክረምት የሚተከል ከ15 ሚሊዮን በላይ የቡናና የፍራፍሬ ችግኝ ተዘጋጅቷል

21 Apr 2017
327 times

ባህርዳር ሚያዚያ 13/2009 በአማራ ክልል ለመጭው ክረምት የሚተከሉ 15 ነጥብ 6 ሚሊዮን የተሻሻሉ የቡናና የፍራፍሬ ችግኞች መዘጋጀታቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። 

በቢሮው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ባለሙያ አቶ ግርማ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት ችግኞቹ የሚተከሉት በ12 ሺህ 400 ሄክታር መሬት ላይ ነው ።

በተለይም ለተከላ ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል 10 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሚሆኑት በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለፍሬ የሚደርሱ የቡና ዝርያዎች ናቸው ።

በክልሉ ቡና አብቃይ በሆኑ 23 ወረዳዎች ኩታ ገጠም በሆኑ የእርሻ ማሳዎች ላይ እንደሚተከሉ ጠቅሰዋል ።

እንደ አቶ ግርማ ገለፃ በቡና ተከላው 19 ሺህ 800 አርሶአደሮች ይሳተፋሉ ።

ቀሪዎቹ 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚሆኑት የማንጎ፣ የአቡካዶ፣ የፓፓያ፣ የሙዝ፣ የዘይቱን፣ የብርቱካንና ሌሎች የቆላ ፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውን ተናግረዋል ።

አቶ ግርማ እንዳሉት ባለፈው የክረምት ወቅት ከተተከለው 13 ነጥብ 7 ሚሊዮን የቡናና ፍራፍሬ ችግኝ ውስጥ 12 ነጥብ 4 ሚሊዮን  ያህሉ ፀድቀዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ዙሪያ ወረዳ የአምባዬ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ተዋበ በቃሉ ባለፈው የክረምት ወቅት ከ200 በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን ተክለው እየተንከባከቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

"ቀደም ሲል በሩብ ሄክታር ማሳዬ ላይ ከተከልኩት ቡና በዓመት በአማካኝ ሁለት ኩንታል የተጣራ ምርት በመሰብሰብ  ከሽያጩ እስከ 13 ሺህ ብር ተጨማሪ ገቢ እያገኘሁ ነው " ብለዋል።

በመጪው ክረምት 500 እግር የተሻሻሉ የቡና ችግኞች ለመትከል ከወዲሁ የማሳ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በጃቢጠህናን ወረዳ የጎርፍ ቃውንቻን ቀበሌ ነዋሪው አርሶአደር ውበት ተስፌ ናቸው።

ከዚህ ቀደም በሩብ ሄክታር ማሳ ከተከሉት ቡና በየዓመቱ ከምርት ሽያጭ እስከ 14 ሺህ ብር እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ