አርዕስተ ዜና

በግብርና ኢንቨስትመንት ውጤታማ የሆኑ ባለሃብቶችና ድርጅቶች ተሸለሙ

20 Mar 2017
416 times

ባህርዳር  መጋቢት 11/2009  በአማራ ክልል በግብርና ኢንቨስትመንት ተሰማርተው ውጤታማ የሆኑ 19 ባለሃብቶችና ድርጅቶች ተሸለሙ፡፡

ሽልማቱ የተሰጠው በጎንደር ከተማ ለሁለት ቀናት የተዘጋጀው የግብርና ኢንቨስትመንት ኮንፈረንስ ትናንት ሲጠናቀቅ ነው፡፡

የክልሉ መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ሃላፊ አቶ ጸጋ አራጌ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የክልሉ መንግስት የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት የሆነውን የግብርና ኢንቨስትመንት ለመደገፍ እየሰራ ነው።

በዚህም በዘርፉ ከተሰማሩ 1ሺህ 915 ባለሃብቶች መካከል ውጤታማ ለሆኑ 19 ባለሃብቶችና ድርጅቶች የምስክር ወረቀትና የልማት አርበኝነታቸውን የሚገልጽ ስጦታ እንደተበረከተላቸው ተናግረዋል፡፡

የእውቅና ሽልማት መስጠቱ ሌሎችም ተበረታተው ለግብርናው መዘመን የበኩላቸውን እንዲወጡ የሚያነሳሳ ነው።

ውጤታማ የሆኑ ባለሃብቶችን በማደረጃትም ሆነ በግል እንደየአቅማቸው በቀጣይ በሚገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመረጡት የስራ ዘርፍ እንዲገቡ ለማበረታታት እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

ከተሸላሚዎቹ መካከል በሰሜን ጎንደር መተማ ወረዳ የመጡት አቶ ተስፋ ወርቁ በሰጡት አስተያየት ከ1ሺህ  ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ሰሊጥ፣ ጥጥና  ማሽላ  በማምረት ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለ40 ቋሚና ከእርሻ ዝግጅት እስከ  ሰብል መሰብሰቢያ ወቅት ደግሞ ከ700 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች  ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠራቸውን  ተናግረዋል።

" ኢንቨስትመንቴ በሁለተኛና መጀመሪያ ዲግሪ ባላቸው የሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዲመራ ማድረጌ ለውጤት እንድበቃና በክልሉ መንግስት እውቅና እንዲሰጠኝ አብቅቶኛል" ብለዋል።

በቀጣይም የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ልማት ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለላቸውም ጠቁመዋል፡፡

በአራት ሄክታር መሬት በጥምር ግብርና በመሰማራታቸው ውጤታማ ሆነው ለመሸለም መብቃታቸውን የገለጹት ደግሞ ከኦሮሞ  ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ደዋ ጨፋ ወረዳ የተመረጡት ባለሃብት አቶ መስፍን ክፍሉ ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት ያለው የገበያ ሁኔታ ያልተረጋጋ በመሆኑ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ በመሰማራት እሴት ጨምረው ወደ ውጭ በመላክ ተወዳዳሪ ለመሆን  በአካባቢያቸው ከሚገኙ ሌሎች ባለሃብቶች ጋር እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

በምዕራበ ጎጃም  የጃቢጠናን ወረዳ ነዋሪው ወጣት ተስፋሁን የኔዓለም እንዳለው ከ12 የዩንቨርሲቲ ተመራቂዎች ጋር ተደራጅተው በ2004 ዓ.ም በ25 ሄክታር መሬት ላይ የግብርና ልማት ጀምረዋል፡፡

" ከራሳችን በማዋጣት በ60ሺህ ብር የጀመነው ልማት በየዓመቱ በርበሬ፣ በሎቄ፣ አኩሪ አተርና በቆሎ አምርተን በመሸጥ ዛሬ ላይ ከ2 ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር በላይ በባንክ ማስቀመጥ ችለናል" ብሏል።

ወረዳውና ዞኑ የብድር አቅርቦትና ሌሎችንም ድጋፎች ካደረጉላቸው በአጭር  ጊዜ ውስጥ ወደ ከፍተኛ ባለሃብትነት በማደግ ተሸላሚ ለመሆን እንደሚጥሩም ተናግሯል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ