አርዕስተ ዜና

የአገሪቷን የልማት ፍላጎት መሸከም የሚችል አዲስ የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓት መተግበር ያስፈልጋል Featured

20 Mar 2017
1034 times

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2009 ምርትና ምርታማነትን በማረጋገጥ የልማት ፍላጎቱን መሸከም የሚችል አዲስ የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓት መዘርጋትና መተግበር እንደሚያስፈልግ ተነገረ።

የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አገሪቷ ላቀደችው የግብርና ልማት ሁሉ-አቀፍ የትራንስፎርሜሽን ስኬት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የታመነበትን አገር አቀፍ የግብርና ኤክስቴንሽን ስትራቴጂ ሰነድ ይፋ አድርጓል።

ሚኒስትሩ ዶክተር እያሱ አብርሃ “የግብርና ኤክስቴንሽን የሰውን አስተሳሰብ፣ ባህሪይና አመለካከት ከመቀየር ጎን ለጎን ኋላቀር አሠራሮችን በዘመናዊና በአዋጪ አሠራሮች በመተካት የአርሶና አርብቶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ወሳኝ ነው” ብለዋል።

ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥም የልማት ፍላጎቱን መሸከም የሚችል አዲስ የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓት መዘርጋትና መተግበር ያስፈልጋል።

ምርቶችን በሚፈለገው ጥራትና መጠን በማምረት፣ የውጭ ምንዛሪ በማሳደግ፣ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በማቅረብ፤ የሸማቹን ፍላጎት በማርካትና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል በነበረው የግብርና ኤክስቴንሽን የአርሶና አርብቶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከላትን ምርምርና ተጠቃሚውን በማገናኘት ረገድ ተገቢውን አገልግሎት የመስጠት ውስንነቶች እንደነበሩበት ተጠቅሷል።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ ከ500 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለማምረት ግብ መጣሉን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ግብርናው እየዘመነና የኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ እየተጠናከረ የሚሄድበት መዋቅራዊ ሽግግር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ለዚህም አሁን ያለውን የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓት በመቀየር አዲስ ስትራቴጂ መንደፍ የወቅቱ ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ አመልክተዋል።

አዲሱ የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓተ ፆታ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስና ሥርዓተ ምግብን በተመለከተ የተለየ ትኩረት የሰጠ እንደሆነ ተነግሯል።

በ1956 ዓ.ም 132 የነበረው የልማት ሠራተኞች ቁጥር አሁን በሁሉም ክልሎች የአርሶና አርብቶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ከ60 ሺህ በላይ የልማት ጣቢያ ሠራተኞች በቀበሌ ደረጃ አገልግሎት እየሰጡ ነው።

የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓቱን ለማዘመን በሁሉም ቀበሌዎች ከ12 ሺህ በላይ የአርሶና አርብቶ አደር ማሰልጠኛ ጣቢያዎች የተቋቋሙ ሲሆን በቀጣይም ከአምስት ሺህ በላይ ይገነባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከኢትዮጵያ አርሶ አደሮች 22 በመቶ የሚሆኑት የግብርናን ምክረ ሃሳብ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ በሞዴልነት ተፈርጀዋል፤ እነዚህ አርሶ አደሮች እያንዳንዳቸው ሁለት አርሶና አርብቶ አደሮችን በማስተማር ወደ ሞዴልነት ቢያመጡ ቁጥሩ ወደ 66 በመቶ እንደሚያድግ ጥናቶች ያመለክታሉ።

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ