አርዕስተ ዜና

በትግራይ የእጣን ዛፍ ሀብትን ለመጠበቅ ምርምር እየተደረገ ነው

20 Mar 2017
578 times

መቀሌ መጋቢት11/2009 በትግራይ ክልል የእጣን ዛፍን ከጥፋት ለመታደግ በምርምር የተደገፈ ጥረት እየተደረገ መሆኑን  የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ገለጸ።

በቢሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ እንክበካቤና ደን ልማት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሀፍቱ ኪሮስ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብና ማዕከላዊ ዞኖች 384 ሺህ 200 ሄክታር   መሬት  በእጣን ዛፍ የተሸፈነ ነበር፡፡

በሂደት በደረሰበት ጉዳት እየተመናመነ ሽፋኑ አሁን ላይ ወደ  267ሺህ 88 ሄክታር ዝቅ ብሏል።

የህገ ወጥ እርሻ መስፋፋት፣ ልቅ ግጦሽ፣ ደን ጭፍጨፋ፣  ቃጠሎና ስርዓት የሌለው የምርት አጠቃቀም ለተክሉ መመናመን በምክንያትነት ከተጠቀሱት ውስጥ ይገኙበታል፡፡

"በየዓመቱ ይገኝ የነበረው 50 ሺህ ኩንታል ምርት በማሽቆልቆሉ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢም እየቀነሰ መጥቷል "  ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ሀፍቱ ገለፃ አሁን ያለውን የእጣን ዛፍ ሀብት ባለበት ደረጃ ለማቆየትና በሂደት ሽፋኑን ወደ ነበረበት ይዞታ ለመመለስ ዝርያዎቹን በሳይንሳዊ ዘዴ በማባዛት  ለመጠበቅና ለማልማት  የሚያስችል ምርምር እየተካሄደ ነው።

በተጓዳኝም  ከ20 እስከ 30 አባላት ያሏቸው  86 ማህበራት ተቋቁመው የእጣን ዛፍ ይዞታዎችን በመረከብ እንዲንከባከቡና ችግኝ እንዲተክሉ እየተደረገ መሆኑንም አስተባባሪው  አመልክተዋል።

"የእጣን ዛፍ ሀብቱ ለመጪዎቹ ሶስት ዓመታት ከምርት ነፃ ሆኖ እንዲቆይ ይደረጋል፤ በይዞታው ላይም የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች እየተካሄደ ነው  "ብለዋል ።

በትግራይ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ምርምር ምክትል አስተባባሪ አቶ ክንፈ መዝገበ በበኩላቸው የእጣን ዛፉን ከጥፋት ለመታደግ  በዘርና በግንድ ቆረጣ ዘዴ ዝርያዎችን ለማራባት የሚያስችል ምርምር እየተካሄደ  መሆኑን ገልጸዋል።

የማይፀብሪና ሽሬ ግብርና ምርምር ማዕከላት ተክሉን በሰርቶ ማሳያዎች  ቆርጠው በመትከል ባደረጉት  የሙከራ ምርምር ተስፋ ሰጪ ውጤት መገኘቱንና ይህንኑ የማስፋፋት ስራ መጀመሩን ጠቅሰዋል ።

በአየር ሁኔታ ለውጥ ምከንያት በተክሉ እድገትና ምርታማነት ላይ የሚፈጠር አሉታዊ ተፅእኖ እንዳይኖር ቀጣይነት ያለው ጥናትና ምርምር እንደሚካሄድ ጠቅሰዋል፡፡

የበዝሒ ህብረት ሸርክና ማህበር ምክትል ሊቀመንበር አቶ ንጉሰ ነጋ  ከዚህ ቀደም 150 ሄክታር የእጣን ዛፍ ይዞታ በመረከብ  በየዓመቱ  እስከ 300 ኩንታል ምርት በመሰብሰብ ለገበያ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

የእጣን ምርቱን ለሀገር ውስጥ ገበያ ኩንታሉን እስከ 4000 ብር ይሸጡ እንደነበርም  አስታውሰዋል ።

ይሁንና የሚገኘው ምርት በሂደት እየቀነሰ በመምጣቱ ባለፈው ዓመት 60 ኩንታል ብቻ ማግኘታቸውን ጠቁመው  ዘንድሮ  ማምረቱን  በማቆም ለሶስት ዓመታት የሚቆይ  እንክብካቤ የማድረግ ስራ መጀመራቸውን  አመልክተዋል፡፡

የዕጣን ዛፍ  ለመድኃኒት፣ ለመስታወት፣ ለፕላስቲክ ቀለም፣ ለሽቶና ለተለያዩ ኬሚካሎች መስሪያ እንደሚውል ከትግራይ  የግብርና ምርቶች  ገበያ ፕሮሞሽን ኤጀንሲ  የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ