አርዕስተ ዜና

የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ከሞጆ ደረቅ ወደብ ጋር መገናኘት በአጭር ጊዜ ውጤት እያስገኘ ነው

498 times

አዲስ አበባ የካቲት 5/2010  አዲሱ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ከሞጆ ደረቅ ወደብ ጋር በተገናኘ በሁለት ወር ጊዜ ከሁለት ሺህ በላይ ኮንቴነሮችን ከውጭ ወደ ወደቡ ማመላለስ እንዳስቻለ ተገለፀ።

የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበርና የኢትዮጵያ ባህርና ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የባቡር መስመሩ ከወደቡ ጋር መገናኘት ለአገሪቷ የኢኮኖሚ እድገት አንድ ምዕራፍ እንደሚከፍት አመላክተዋል።

የአክሲዮን ማህበሩ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሳርካ እንደተናገሩት የባቡር መስመሩ ከወደቡ ጋር መገናኘቱ ቀጥታ የወጪ ንግድ ግንኙነቱን ለማሳለጥ አይነተኛ ሚና ይኖረዋል።

የአገልግሎቱ መጀመር ለአገሪቷ ሁለት ጠቀሜታዎች እንዳሉትም ነው ኢንጂነሩ ያስረዱት።

ባቡሩ በአንድ ጊዜ 106 ኮንቴነሮችን ከጅቡቲ የማመላለስ አቅም እንዳለው የተናገሩት ኢንጂነር ጥላሁን በሁለት ወር ጊዜ ከ2 ሺህ በላይ ኮንቴነሮችን ወደ አገር ውስጥ ማመላለስ ተችሏል ነው ያሉት።

ይህም ጅቡቲ ወደብ ላይ ለረጅም ጊዜ ተጠራቅሞ የነበረውን ኮንቴነር የቆይታ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ባህርና ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ካፒቴን ተፈራ በዳሶ በበኩላቸው የባቡር መስመሩ ከወደቡ ጋር ቀጥታ እንዲገናኝ መደረጉ ለአገሪቷ የኢኮኖሚ እድገት አንድ ምዕራፍ ይከፍታል።

አገልግሎቱ ከተጀመረ ወዲህ የአገሪቷን የሎጂስቲካል አገልግሎት አሰጣጥ የበለጠ ቀልጣፋ አድርጎታልም ብለዋል።

ያለአግባብ ይባክን የነበረውን ጊዜና ጉልበት በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ አሰራሩን ቀልጣፋ እንደሚያደርገውም ነው ካፒቴኑ የገለጹት።

ኮንቴነሮችን በቶሎ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት እየተቻለ ቢሆንም ግን አስመጪዎች ኮንቴነሮችን ከወደቦች በቶሎ ያለመንሳት ችግር እያጋጠመ መሆኑን ሳይጠቁሙ አላለፉም ካፒቴኑ።

በተለይም በመንግስት መስሪያ ቤቶች በኩል ግዥ ተፈጽሞ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ኮንቴነሮች ላይ ችግሩ እንደሚጎላ አመልክተዋል።

በመስሪያ ቤቱ አሰራር መሰረት በጊዜው በማያነሱ ባለሃብቶች ላይ ንብረቶችን የመውረስ እርምጃ እንደሚወሰድም አክለዋል።

ከጅቡቲ የሚመጡ ኮንቴነሮችን በደረቅ ወደቡ በፍጥነት ማራገፍ የሚያስችል አር.ኤም.ጂ የተሰኘ ዘመናዊ መሳሪያም በቅርቡ አገልግሎት ለማስጀመር ዝግጅት መጠናቀቁም ተገልጿል።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን