አርዕስተ ዜና

ኅብረተሰቡ በቦንድ ሣምንት በንቃት ተሳትፎ ድጋፉን እንዲያጠናክር ተጠየቀ

477 times

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2010 ከነገ ወዲያ በሚጀምረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቦንድ ሣምንት ኅብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ጥሪ አቀረበ። 

መላው ኢትዮጵያዊያን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ቦንድ በመግዛት፣ በጉልበትና በሃሳብ በአንድነት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የጽህፈት ቤቱ የሚዲያ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ለኢዜአ እንደተናገሩት የህዳሴው ግድብ የቦንድ ሣምንት ከመጋቢት 10 እስከ 17 ቀን 2010 ዓ.ም በመላ አገሪቱ ይካሄዳል።

በእነዚህ ቀናት በሁሉም አገሪቷ የቦንድ ሽያጭ የሚካሄድ ሲሆን በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ድንኳን በመትከል ጭምር ይካሄዳል።

በቦንድ ሣምንት ሽያጩን በስፋት ለማከናወን ከልማትና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ጋር በጋራ እየሰራን ነው ብለዋል አቶ ኃይሉ።

ህብረተሰቡ አጋጣሚውን የተለያዩ ማህበራዊ ሁነቶችና በዓላትን ምክንያት በማድረግ ለልጆች፣ ለቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ የቦንድ ስጦታ በማበርከት አገራዊ ሃላፊነቱን መወጣት እንደሚችልም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በቦንድ ሳምንቱ በአርሶና አርብቶ አደር አካባቢዎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ተግባራትን ከቦንድ ሽያጭ ጋር በማስተሳሰር የቅስቀሳ ስራ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።

ወደ ግድቡ የሚገባውን ደለል መከላከል ከተቻለ ግድቡ እስከ 300 ዓመት ማገልገል እንደሚችል ጥናቶች እንደሚያሳዩ በመጥቀስ አርሶና አርብቶ አደሩ በአፈርና ውሃ ጥበቃና ደን ተከላ እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ የ'ይቻላል' መንፈስ እስካሁን በዓመት 30 ቀን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በማከናወን 79 ቢሊዮን ብር የሚገመት የአርሶና አርብቶ አደር ጉልበት ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ውሏል።

በ2009 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት ከቦንድ ሣምንትና ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ሩጫ ቲሸርት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል።

በአሁኑ የቦንድ ሣምንትም የበለጠ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን የገለጹት አቶ ኃይሉ ህብረተሰቡ እስካሁን ሲያደርግ እንደነበረው አቅሙ በፈቀደው ቦንድ እንዲገዛ ጥሪ አቅርበዋል።

የመሰረተ ድንጋዩ በ2003 ዓ.ም የተቀመጠለትና በሕዝብ ተሳትፎ የሚገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 64 በመቶ ስራው ተከናውኗል።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን