አርዕስተ ዜና

ኮርፖሬሽን የፍጆታ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ተጠቃሚ እያደረገን ነው - የሐረር ከተማ ነዋሪዎች

470 times

ሐረር መጋቢት 4/2010 የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ሐረር ቅርንጫፍ የፍጆታ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

ባለፉት 15 ቀናት ከ342 ኩንታል በላይ ፓስታ፣ ሩዝና ስኳር እንዲሁም ከ4ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለነዋሪው በተመጣጣኝ ዋጋ ማከፋፈሉን ቅርንጫፉ ገልጧል።

በከተማው የቀበሌ 16 ነዋሪ ወይዘሮ ፋንቱ ማሞ በሰጡት አስተያየት ቅርንጫፉ ከፍራፍሬ በተጨማሪ ስኳር፣ ዘይት፣ፓስታና ሩዝ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዚህም ከነጋዴ በ30 ብር እንገዛ የነበረው አንድ ኪሎ ፓስታ በ20 ብር እንዲሁም 25 ብር የሚሸጠው አንድ ኪሎ ሩዝ በ20 ብር በመግዛት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

አቶ ተስቲ ዩስፍ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ በ265 ብር የሚያቀርበው ባለ አምስት ሊትር የሱፍ ዘይት በገበያ ካለው ዋጋ የ30 ብር ቅናሽ እንዳለው ገልፀዋል፡፡

እንዲሁም በገበያ 30 ብር የሚሸጠውን አንድ ኪሎ ስኳር በ19 ብር ከ50 ሳንቲም በመግዛት ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለፃ ኮርፖሬሽኑ የፍጆታ እቃዎችን ለህብረተሰቡ ለማዳረስ የሚያደርገው ጥረት በአንድ ቦታ ላይ የተወሰነ በመሆኑ በቀጣይ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ተጨማሪ መሸጫ ሱቆች ሊከፍት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ሐረር ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም ግዛው ባለፉት 15 ቀናት ከ342 ኩንታል በላይ የፓስታ፣ ሩዝና ስኳር እንዲሁም  ከ4ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለከተማው ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ አከፋፍሏል።

የምግብ ሸቀጦቹም በከተማም ከሚገኙ የንግድ ሱቆች ከአምስት ብር አስከ 30 ብር በኪሎና በሊትር ቅናሽ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮም የዳቦ ዱቄት ለህብረተሰቡ ማከፋፈል እንደሚጀምር ተናግረዋል።

ተጠቃሚው ያነሳውን የመሸጫ ቦታ እጥረት ለመቅረፍ በከተማው በተለምዶ ሸዋበርና አራተኛ በሚባሉት ህዝብ በሚበዛባቸው ሥፍራዎች  ለመክፈት ከክልሉ ንግድ ጽህፈት ቤት ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን