አርዕስተ ዜና

ለወጣቶች ከተመደበው 10 ቢሊዮን ተዘዋዋሪ የገንዘብ ብድር ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሥራ ላይ መዋሉ ተገለጸ

400 times

ድሬዳዋ መጋቢት 4 / 2010 በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት መንግስት ከመደበው 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ የገንዘብ ብድር 5 ነጥብ 1 ቢሊዮን የሚሆነው ሥራ ላይ እንዲውል መደረጉን የፌደራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው የኢንተርፕራይዞች ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ መንግስቱ ድሬዳዋ ተገኝተው የወጣቶችን የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው በተመለከቱበት ወቅት እንዳሉት፣ መንግስት 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ የገንዘብ ብድር መድቦ በሀገሪቱ የሚገኙ ሥራ እጥ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት የተቀናጀ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ነው፡፡

በእዚህም በየክልሉ ከሚገኙ ተቋማት ጋር በመሆን በገጠርና በከተማ የሚገኙ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 24 ዓመት የሆኑ ወጣቶች አዋጪ በሆኑ የሥራ ዘርፎች ላይ ሥልጠና አግኝተውና ክትትልና ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል።

እስካሁንም መንግስት ከመደበው 10 ቢሊዮን ብር 5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብሩ ለወጣቶች ተሰራጭቶ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰው፣ አንዳንድ ክልሎች የተመደበላቸውን ገንዘብ በአግባቡ እየተጠቀሙ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

ለአብነትም አዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከተመደበለት 167 ሚሊዮን ብር እስካሁን ጥቅም ላይ ያዋለው 67 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች እንዲሁም የድሬዳዋ አስተዳደር የመጀመሪያ ዙር ብድርን ሙሉ በሙሉ ተጠቅመው ሁለተኛው ዙር እንዲለቀቅላቸው ጥያቄ በማቅረብ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

ድሬዳዋ የገንዘብ ብድሩ በተሻለ ሁኔታ ለወጣቶች ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ከተደረገባቸው አካባቢዎች አንዱ መሆኑንም አቶ በቀለ ተናግረዋል፡፡ 

እንደ አቶ በቀለ ገለጻ፣ በብድር አጠቃቀም ላይ ችግር ያለባቸውን አዲስ አበባና አፋር ያሉ ክልሎች የተሻለ ሥራ እንዲሰሩ ከሚመለከታቸው የዘርፉ አስፈጻሚዎች ጋር በየጊዜው በመነጋገር ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ 

በእነዚህ ክልሎች ወጣቶችን ፈጥኖ ወደሥራ ከማስገባት አንጻር በራሳቸው በወጣቶችና በአስፈጻሚው አካላት ላይ የሚስተዋሉ ክፈተቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

ተዘዋዋሪ የገንዘብ ብድሩን ወስደው ወደ ሥራ ከገቡ የድሬዳዋ ኢንተርፕራይዞች መካከል 5 አባላት ያሉት የጽዮንና እስክንድር ቴራዞና ብሉኬት ማምረት ሽርክና ማህበር አንዱ ነው፡፡

የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ወጣት እስክንድር መሐመድ ለኢዜአ እንደተናገረው መንግስት ለወጣቱ ያመቻቸው ብድር ወጣቱ ባለው እውቀትና ችሎታ በመጠቀም ወደ ሥራ እንዲሰማራ የሚያግዘው ነው፡፡

በማህበር ባገኙት 3 መቶ ሺህ ብር ብድርና ቀበሌው ባመቻቸላቸው የማምረቻ ቦታ ተጠቅመው ያመረቱትን ምርት ወደ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እየሆኑ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በራሳቸው አፈላልገው ከሚያገኙት ገበያ በስተቀር በከተማው ከሚስተዋለው ሰፊ የኮንስትራክሽን ገበያ ዕድል አንጻር አስተዳደሩ የፈጠረላቸው የገበያ ትስስር አለመኖሩን አመልክቷል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ወጋየሁ ጋሻው በበኩላቸው  መንግስት ለድሬዳዋ ወጣቶች ከመደበው 55 ሚሊዮን ብር ብድር ውስጥ በመጀመሪያ ዙር የተለቀቀው 27 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በገጠርና በከተማ ለተደራጁ 187 ኢንተርፕራይዞች መሰራጨቱን ገልጸዋል፡፡

ወጣቶቹ ባገኙት ገንዘብና በተሰጣቸው ሥልጠና በመታገዝ በተለያዩ ሥራዎች እንዲሰማሩ አስፈላጊው ድጋፍና ዕገዛ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመው፣ ወደሥራ ከገቡት ኢንተርፕራይዞች አንዳንዶቹ ለውጥ እያመጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አቶ ወጋየሁ እንዳሉት፣ ወጣቶች የሚያቀርቡት የመሸጫና የማምረቻ ቦታዎች እንዲሁም የገበያ ትስስር ጥያቄዎችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በቂ አይደለም፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ፣ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብደላ አህመድ በበኩላቸው ብዙ ሚሊዮን ብር ወጥቶባቸው በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡት የመሸጫና ማምረቻ ቦታዎች ለኢንተርፕራይዞች በቅርቡ ለማከፋፈል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን