አርዕስተ ዜና

የጋምቤላ ክልል የመስኖ ልማት ተሳታፊ አርሶ አደሮች የገበያ ችግር እንዳጋጠማቸው ገለፁ

396 times

ጋምቤላ መጋቢት 4/2010 ከመስኖ ልማት የተሻለ ምርት ብናገኝም በገበያ እጦት ለችግር ተዳርገናል ሲሉ በጋምቤላ ክልል አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የልማቱ ተሳታፊ አርሶ አደሮች ገለፁ፡፡

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አርሶ አደሮች ያጋጠማቸውን የገበያ ችግር ለማቃለል ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

በጋምቤላ ወረዳ የፊንኪዎ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አጀና ኡጎታ በሰጡት አሰተያየት በዘንድሮው የበጋ ወራት የተለያዩ የውሃ አማራጮችን ተጠቅመው ካለሙት ቲማቲም የተሻለ ምርት ቢያገኙም በገበያ ችግር ምክንያት ለብልሽት እየተዳረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘንድው ዓመት  ካለሙት ቲማቲም ጥሩ ምርት ቢያገኙም ዋጋው በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የፊንኪዎ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ኡማን ኡቻላ ናቸው።

ቀደም ሲል ከ15 ብር በላይ ይሸጥ የነበረው የአንድ ኪሎ ቲማቲም ዋጋ በአሁኑ ወቅት ከአምስት ብር በታች እየተሸጠ መሆኑን ገልጸዋል። 

በዚሁ ወረዳ የቦንጋ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ምናሴ ከሊለ በሰጡት አስተያየት የተለያየ የጓሮ አትክልት በመስኖ በማልማት የተሻለ ምርት ማግኝታቸውን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በተለይም የቲማቲምና የሽንኩር ምርት ዋጋ በመቀነሱ ምክንያት ተጠቃሚ ሊሆኑ አለመቻላቸውን ገልጠዋል ፡፡

በመሆኑም የሚመለከተው አካል የገበያ ትስስር እንዲፈጥርላቸውና የምርት መሸጫ ቦታ እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ከአርሶ አደሮች የተነሳው የገበያ ችግር ትክክል መሆኑን ተናግረዋል።

በተያዘው የበጋ ወራት አርሶ አደሩ የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ካለፈው ዓመት በተሻለ ሁኔታ ወደ ልማት በመግባት ጥሩ ምርት ያገኘ ቢሆንም የገበያ ክፍተት ማገጠሙን ገልጸዋል።

በመሆኑም አርሶ አደሮቹ ያጋጠማቸውን የገበያ ችግር ለማቀላል ቢሮው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ገበያ የማፈላለግና የመሸጫ ቦታን የማመቻቸት ስራ ተጀምሯል ብለዋል።

በክልሉ በተያዘው የበጋ ወራት የውሃ ሸሽ፣ አነስተኛ የመስኖ ግድቦችንና ሌሎች የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብልና የጓሮ አትክልት መልማቱን አስታውቀዋል፡፡

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን