አርዕስተ ዜና

በሰሜን ሽዋ ዞን 3 ሚሊዮን ሊትር የሚጠጋ ወተት ለገበያ ቀርቧል

426 times

ደብረብርሀን መጋቢት 4/2010 በሰሜን ሽዋ ዞን ባለፉት ስምንት ወራት ከወተት አምራች ማህበራት 3 ሚሊዮን ሊትር የሚጠጋ የወተት ምርት ለገበያ መቅረቡን የዞኑ ሕብረት ሥራ ማህበራት ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በጽህፈት ቤቱ የሀገር ውስጥ የገበያ መረጃ ትንተና ባለሙያ አቶ ግዲሳ ኦልጅራ ለኢዜአ እንደገለጹት ምርቱን ለገበያ ያቀረቡት 3 ሺህ 129 አባላት ያሏቸው 20 የወተት አምራች ሕብረት ሥራ ማህበራት ናቸው።

ማህበራቱ ለአዲስ አበባና ለአካባቢው ገበያ ለሽያጭ አቅርበው ካገኙት ገቢ ውስጥ ከ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ አግኝተዋል ።

እንደ ባለሙያው ገለጻ የማህበራቱ አባላት ቁጥር በማደጉና የሚያቀርቡት የወተት መጠን በመጨመሩ አቅርቦቱ ከቀዳሚው ዓመት በ700 ሺህ ሊትር ብልጫ አሳይቷል ።

ከእዚህ በተጨማሪ አባላቱ የተሻሻሉና የውጭ ዝርያ ያላቸውን የወተት ላም ዝርያ በማርባት የሚያመርቱትን የወተት መጠን ማሳደግ መቻላቸው አመልክተዋል።

በባሶና ወራና ወረዳ የኮርማረፊያ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ፍቃዱ ግዛው በሰጡት አስተያየት በማህበር ተደራጅተው የወተት ምርታቸውን ለገበያ ማቅረብ ከጀመሩ ወዲህ ብክነትን መቀነስ ችለዋል።

"ባለፉት ስምንት ወራት ለገበያ ካቀረብኩት 4ሺህ 800 ሊትር ወተት ሽያጭ 62 ሺህ 400 ብር ገቢ አግኝቻለሁ" ብለዋል ።

በወረዳው የደሊላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ብርሃኑ መኩሪያ በበኩላቸው ከሚያረቧቸው የወተት ላሞች በቀን ከ30 ሊትር በላይ ወተት እያመረቱ   ለማህበራቸው እያስረከቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"አንድ ሊትር ወተት በ13 ብር በማስረከብ በወር ከ11 ሺህ ብር በላይ ገቢ እያገኘሁ ነው" ብለዋል።

የወተት ማቀዝቀዣና መናጫ ማሽን ለመግዛት የሚያስችላቸው የገንዘብ ብድር ቢመቻችላቸው የማህበሩን አቅም በማሳደግና የወተት ብክነቱን በመቀነስ የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አመላክተዋል ።

ከግብርና ሥራዬ ጎን ለጎን ላሞች እያረባሁ ከወተት ምርት ሽያጭ በወር ከ20 ሺህ ብር በላይ በማግኘት ችያለሁ ያሉት ደግሞ የአንጎለላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ከፈለኝ ተሾመ ናቸው።

የወተተ ማህበራቱ ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል እንዳላቸውና እስከ በጀት አመቱ መጨረሻ ከ4 ሚሊዮን 500 ሺህ ሊትር በላይ ወተት ለገበያ ለማቅረብ እየሰሩ መሆናቸው ታውቋል ።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን