አርዕስተ ዜና

ሮሆቶ የተባለ የጃፓን መድሃኒት አምራች በኢትዮጵያ የመሰማራት ፍላጎቱን ገለፀ

432 times

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2010 ሮሆቶ የተሰኘ ግዙፍ የጃፓን መድሃኒት አምራች ኩባንያ መዋዕለንዋዩን በማውጣት በኢትዮጵያ መሰማራት እንደሚፈልግ አስታወቀ።

በኩባንያው ከፍተኛ አመራሮች የተመራው ልዑክ በኢትዮጵያ ኢንቨስት በሚያደርግበት ሁኔታ ላይ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል ጋር ተወያይቷል።

የኩባንያው ምክትል ኃላፊ ሽዋን ሃን ያን እንዳሉት ኩባንያው በኢትዮጵያ የቆዳና የዓይን ጤናን ለመጠበቅ የሚያገለግሉ መድሃኒቶችን ማምረት ይሻል።

ኢትዮጵያ ለአምራች በተለይም ለፋርማሲውቲካል ዘርፍ የሰጠችውን ትኩረትም አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገሮች ጋር የፈረመችው ነጻ የንግድ ስርዓት /ኤፍ.ቲ.ኤ/ በኢትዮጵያ ለሚያመርቱት ምርት ገበያ ተደራሽነት መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ምክትል ሃላፊዋ ተናግረዋል።

ልዑካኑ ከሚኒስትር ዴኤታው ጋር በነበራቸው ውይይት በኢትዮጵያ ስላለው ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ማብራሪያ እንዳገኙ ጠቁመዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቢዝነስ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ አርአያ ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው እንደገለጹት ኩባንያው ስራውን ከኢትዮጵያዊያን ባለሃብቶች ጋር በመቀናጀት ማከናወን ይፈልጋል።

ይህን እቅዱን ለማሳካት ከኢትዮጵያዊያን ባለሃብቶች ጋር መነጋገሩንና በኢትዮጵያ የሚያመርታቸውን ምርቶች ወደ ጎረቤት አገሮች ለመላክ ማቀዱን ተናግረዋል።

ኩባንያውን በቶሎ ወደስራ ለማስገባት ቂሊንጦ በሚገኘው የፋርማሲውቲካል ኢንዱስትሪ ፓርክ ቦታ እየተመቻቸ መሆኑን የገለጹት አቶ አርአያ በዘርፉ ያለውን የካበተ ልምድ ለኢትዮጵያዊያን ለማስተማር ቃል መግባቱንም አውስተዋል።

Last modified on Tuesday, 13 March 2018 19:22
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን