አርዕስተ ዜና

የቆቃ-አዱላላ-ቢሾፍቱ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ የተሽከርካሪዎችን ብልሽትና ጊዜ ቀንሷል - አሽከርካሪዎች

565 times

ደብረዘይት መጋቢተ 4/2010 ከጠጠር ወደ አስፋልት ኮንክሪት ደረጃ ያደገው የቆቃ-አዱላላ-ቢሾፍቱ መንገድ ይደርስባቸው የነበረውን የተሽከርካሪ ብልሽትና የጊዜ ብክነት እንዳስቀረላቸው የመንገዱ ተጠቃሚዎች ገለጹ።

መንግስት በመደበው ከ711 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የቆቃ-አዱላላ-ቢሾፍቱ 52 ኪሎ ሜትር መንገድ በአገር በቀሉ አሰር ኮንስትራክሽን ድርጅት ነው የተሰራው።

መንገዱ በአስፋልት ኮንክሪት ተገንብቶ ለአገልግሎት በመብቃቱ በመንገዱ አስቸጋሪነት ያባክኑት የነበረውን ጊዜ እንደቀነሰላቸውና ተሸከርካሪዎቻቸውን ከብልሽት እንደታደገላቸው በመስመሩ በጉዞ ላይ የነበሩ አሽከርካሪዎች ለኢዜአ ገልጸዋል።

አሽከርካሪ ንጉስ ዳዲ "ከዚህ በፊት ፒስታ በነበረበት ሠዓት ሶስት ሠዓት ነበር የሚያስኬደው፤ አሁን ደግሞ አንድ 50 አርባ ደቂቃ ነው የሚፈጀው ፒስታ በነበረበት ሠዓት ጎማ ይተኛል አሁን በጣም ሰላም ነው" ብለዋል።

"አስፋልት ከገባ በኋላ ሠዓታችንን ቆጥቦልናል፤ በሞጆ ነበር የምንዞረው፤ የመንገድ አሰራሪም ጥራት ያለው ነው ያሉት ደግሞ ሌላው አሽከርካሪ ኤፍሬም ተስፋዬ ናቸው"።

በፊት ኮረኮንች በመሆኑ  ሰው ራሱ ሲታመም ወደ ከተማ ለመሄድ በጣም ያስቸግረን ነበርያሉት አሽከርካሪ መንግስቱ ጉደታ አሁን መንገዱ በአስፋልት ስለተሰራ እንደልባቸው መሄድ መቻላቸዉን ተናግረዋል፡፡

አሽከርካሪው እንዳሉት በፊት ሶስት ሠዓት ይፈጅባቸው የነበረው መንገድ አሁን ግን 20 ደቂቃ ባልሞላ አዱላላ ደርሰው  እንደምመለሱና በየመንገዱ ሁሉ በክረምት በጎርፍ ክምችት ሞተር በማበላሸት ንብረት ሲወደም መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ የመንገዱ ግንባታ በ2007 ዓ.ም መጀመሩንና በተያዘለት 36 ወራት ማጠናቀቅ እንደተቻለ ገልጸዋል።

መንገዱ ጥራቱን ጠብቆ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ ተጠቃሚዎችና የአካባቢው ህብረተሰብ ለመንገዱ እንክብካቤና ጥበቃ እንዲያደርጉም አቶ ሳምሶን አስገንዝበዋል።

የትራፊክ ደህንነትን ለማሳለጥ የሚተከሉ የትራፊክ ምልክቶች ሊጠበቁ እንደሚገባም አክለዋል።

 

 

Last modified on Tuesday, 13 March 2018 19:24
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን