አርዕስተ ዜና

የቆቃ-አዱላላ-ቢሾፍቱ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታው ተጠናቀቀ

573 times

ቢሾፍቱ መጋቢት 3/2010 በኦሮሚያ ክልል የቆቃ-አዱላላ-ቢሾፍቱ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ተጠናቀቀ፡፡

በፌደራል መንግስት በጀት ከ711 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው ይህ መንገድ 52 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሲሆን በአገር በቀሉ አሰር የኮንስትራክሽን ድርጅት ተገንብቷል።

የመንገዱን ግንባታ በ36 ወራት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታስቦ በ2007 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን ግንባታው በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቁን በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ገልጸዋል፡፡

የመንገድ ግንባታው የአካባቢውን ህብረተሰብ የአስፓልት መንገድ ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ህብረተሰቡ በአካባቢው የሚመረተውን የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በቀላሉ ወደ ገበያ ለማቅረብ ያግዛል፡፡

በተጨማሪም የመንገዱ መጠናቀቅ በአካባቢው የሚገኘውንና ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ግብዓትነት የሚያገለግለውን የተለያዩ ማዕድናት በቀላሉ ወደ ፋብሪካዎች ለማድረስ አስተዋጽኦ እንዳለውም ነው አቶ ሳምሶን የተናገሩት፡፡

በአካባቢው የሚገኘውን የአሸዋ ምርት ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ለማቅረብም የመንገድ ፕሮጀክቱ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡

መንገዱ ጥራቱን ጠብቆ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ ሁሉም ተጠቃሚ ለመንገዱ እንክብካቤና ጥበቃ እንዲያደርግም አቶ ሳምሶን ጥሪ አቅርበዋል።

Last modified on Tuesday, 13 March 2018 00:02
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን