አርዕስተ ዜና

በመስኖ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን የሰሜን ሸዋና ምስራቅ ወለጋ ዞን አርሶ-አደሮች ገለጹ

17 Feb 2017
382 times

ፍቼ/ነቀምቴ የካቲት 10/2009 በገበያ ተፈላጊነት ያላቸውን ሰብል፣ ፍራፍሬና አትክልት በመስኖ በማልማት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን በሰሜን ሸዋ ዞን የደብረ ሊባኖስ እና ግራር ጃርሶ ወረዳ አርሶአደሮች ገለጹ።

በምስራቅ ወለጋ ዞን በዘንድሮ የበጋ ወራት 80 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ መሆኑም ተመልክቷል።

በመስኖ ልማት ሥራው ከተሳተፉት አርሶአደሮች አንዳንዶቹ ለኢዜአ እንዳሉት በመስኖ አልምተው ከሚሸጡት ምርት በዓመት ከ7ዐ ሺህ ብር በላይ ገቢ አግኝተዋል።

በደብረ ሊባኖስ ወረዳ የሚኖሩት አርሶ አደር ጌታቸው ገብሬ በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት የመስኖ ልማቱ ከቤተሰብ ቀለብ ባለፈ ቋሚ የገቢ ምንጭ እየሆናቸው ይገኛል።

በሁለት ሄክታር መሬታቸው ላይ ከአትክልት በተጨማሪ ገብስና ስንዴን በመስኖ እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዓመታዊ የመስኖ ልማት ገቢያቸው ከ70 ሺህ ብር በላይ መሆኑን ገልጸው፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከመስኖና ከሌላ የገቢ ምንጭ 300 ሺህ ብር የሚጠጋ ሀብት ማፍራታቸውን ተናግረዋል።

ዘንድሮ እያካሄዱት ላለው የመስኖ ልማት ሥራ ከባለሙያ ምክር ባለፈ የራሳቸውና የቤተሰባቸውን ጉልበት በመጠቀም ውጤታማ ሥራ እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በወረዳው የአማራ አፍጥን ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ሲሳይ አያሌው በበኩላቸው "ባለፈው ዓመት በመስኖ ልማት ነጭ ሽንኩርትና በርበሬ በማምረት 50 ሺህ ብር ገቢ አግኝቺያለሁ" ብለዋል።

የመስኖ ልማቱን ከጥቅምት ወር ጀምሮ በውሃ መሳቢያ ሞተር ታግዘው በማከናወን ላይ መሆናቸው የተናገሩት ደግሞ በግራር ጃርሶ ወረዳ የቶርባን አሼ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ጉርሜሳ ጉቱ ናቸው።

ባለፈው ዓመት አትክልት፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም በማምረት በአንድ ዙር 71 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

 የሰሜን ሸዋ ዞን መስኖ ልማት ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ምትኩ እንደገለጹት በዘንድሮው የመስኖ ልማት ሥራ በ13 ወረዳዎች የሚገኙ ከ141 ሺህ በላይ  አርሶአደሮች እየተሳተፉ  ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ 121 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ በመጀመሪያው ዙር የመስኖ ልማት 84 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን ገልጸዋል።

ከልማቱም 12 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቁመው፣ ይህም ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በአንድ ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።

ለልማቱ ዘጠኝ መካከለኛ ግድቦችን ጨምሮ በባህላዊና በዘመናዊ መንገድ የተጠለፉ 71 ወራጅ ወንዞች፣ የከርሰ ምድር ውሃና ጉድጓዶች ጥቅም ላይ ውለዋል።

በመስኖ ከሚለሙት መካከል ገብስ፣ ስንዴ፣ ነጭና ቀይ ሽንኩርት፣ ፍራፍሬና አትክልት የሚገኙባቸው ሲሆን ለእዚህም ከ45 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ቀደም ብሎ መሰራጨቱን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና በምስራቅ ወለጋ ዞን በዘንድሮ የበጋ ወራት 80 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ ነው።

የዞኑ መስኖ ልማት ባለስልጣን ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊና የመስኖ ውሃ አቅርቦት የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ሚልኬሳ ወርቅነህ እንዳሉት የመስኖ ልማት ሥራው እየተካሄደ ያለው ስቡስሬ፣ ዋዮቱቃ፣ ጎቡፈዮን ጨምሮ በ17 ወረዳዎች ነው።

በመስኖ ልማት ሥራው 135 ሺህ የሚሆኑ አርሶአደሮች በግልና በማህበር ተደራጅተው እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸው፣ እስካሁን 274 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ መዋሉን አስታውቀዋል።

በመጀመሪያው ዙር በባህላዊና ዘመናዊ መስኖ እየለሙ ካሉት መካከል ድንች፣ ቲማቲም፣ ካሮት፣ ሽንኩርት፣ በርበሬ፣ በቆሎና ቦሎቄ ይገኙበታል።

ከመስኖ ልማቱም ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ሚልኬሳ ተናግረዋል።

ከዞኑ አርሶአደሮች መካከል በዋዩቱቃ ወረዳ የቦነያሞሎ ቀበሌ አርሶአደር ሰንበቶ ተመስገን በሰጡት አስተያየት ዘንድሮ በአንድ ሄክታር መሬታቸው ላይ ያለሙትን ድንችና ሽንኩርት ለገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

እስካሁን ከ100 ኩንታል በላይ ምርት ለገበያ በማቅረብም 43 ሺህ ብር የሚጠጋ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በሲቡ ወረዳ የለሊሳ ቀበሌ አርሶአደር አዱኛ ሐምቢሳ በዘንድሮ የበጋ ወራት በአንድ ተኩል ሄክታር መሬት ላይ በቆሎና ሽንኩርት ዘርተው በመንከባከብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑወቅት ሊሰበሰብ ከደረሰው የሽንኩርት ምርታቸው ብቻ ሃምሳ ሺህ ብር ገቢ እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ