አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ኢትዮጵያ ለተመድ የ2017 የዘላቂ የልማት ግቦች አፈጻጸም ሪፖርት እየተዘጋጀች ነው Featured

17 Feb 2017
459 times

አዲስ አበባ የካቲት 10/2009 ኢትዮጵያ በመንግስታቱ ድርጅት የፖለቲካ መድረክ ለምታቀርበው የ2017 ዘላቂ የልማት ግቦች የፈቃደኝነት የአፈጻጸም ሪፖርት ዝግጅት መጀመሯን የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ ከማዕከላዊ ስታትስቲክስና ከኢትዮጵያ ካርታ ስራዎች ኤጀንሲዎች ጋር በትብብር ያዘጋጀው የአገራዊና የክልል የልማት ዕቅድ፣ ክትትልና ግምገማ የጋራ ምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

"ኢትዮጵያ የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችን ከመቀበል አልፋ ከ2ኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዷ ጋር አስተሳስራዋለች" ይላሉ የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ይናገር ደሴ።

"ድህነትን ማጥፋትና እየተለወጠ ባለ ዓለም ውስጥ ብልፅግናን ማስፋፋት" በሚል መሪ ሃሳብ በመጪው ሰኔ 2017 በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ የአፈጻጸም ሪፖርት ከሚያቀርቡ 40 አገራት መካከልም አንዷ ናት ኢትዮጵያ።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተነደፉ የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችን እንደየ አገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ ገቢራዊ ለማድረግ የአባል አገራት መሪዎች ቃል ገብተዋል።

የልማት ግቦቹን አፈጻጸም ለመከታተልና ለመገምገም የ2017 ዘላቂ የልማት ግቦች የፈቃደኝነት ዝግጅትና አገራዊ የግምገማ ሪፖርት ለማቅረብም እንዲሁ።

የዘላቂ የልማት ግቦቹ የፈቃደኝነት ዝግጅትና ግምገማ ሪፖርት በጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመር ሰኔ 7 ቀን 2017 በተመድ የፖለቲካ መድረክ ነው የሚቀርበው።

የመንግስታቱ ድርጅት መስራች አባል የሆነችው ኢትዮጵያም ለ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችና ለድህረ 2015 የአፍሪካ የልማት አጀንዳዎች ቀረጻ ከተመረጡ አገራት አንዷ ናት።

በመሆኑም "እንደ ኢትዮጵያ ሁኔታ የዘላቂ የልማት ግቦች አፈጻጸም ሲወራ የ2ኛው የዕድገትና ትራንሰፎርሜሽን ዕቅድ የሁለት ዓመት አፈጻፅም ሪፖርት ማለት ስለሆነ ይህንኑ የሚያሟላ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ጀምረናል" ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

በተመድ የፖለቲካ መድረክ የሚቀርበው ሪፖርት አገሪቷ ራሷን በፈቃደኝነት የምታስገመግምበት በመሆኑ ለቀጣይ ስራዎች ጠቃሚ ግብዓት የሚገኝበት እንደሚሆን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያም የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች እንዳሳካች ሁሉ ዘላቂ የልማት ግቦቹን እንደምታስቀጥል ለማሳየት መድረኩን መጠቀም እንደሚኖርባትም ነው ያብራሩት።

በመንግስታቱ ድርጅት የፖለቲካ መድረክ የሚቀርበው የዘላቂ የልማት ግቦች የፈቃደኝነት የአፈጻጸም ሪፖርት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ሪፖርቱ አገራዊ እንደመሆኑ የመንግስት አካላት ብቻ ሳይሆኑ በ2ኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዝግጅት ወቅት እንደሆነው ሁሉ  በግምገማው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉም ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የግል ድርጅቶችና የሃይማኖት ተቋማት በዕቅድ አፈጻጸሙ ዙሪያ የራሳቸውን አስተያየትና ግምገማ የሚሰጡባቸው መድረኮች እንደሚዘጋጁ በመጠቆም።

የጋራ ምክክር መድረኩ ዓላማ የፌዴራል አካላት፣ የክልል መንግስታትና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ባለድርሻ አካላት በሪፖርት ዝግጅቱ ስለሚኖራቸው ተሳትፎ ለመወያየት ነው ብለዋል።

በዕቅድ ዝግጅት፣ ትግበራና ግምገማው ወቅት ትክክለኛና ተዓማኒነት ያለው የስታትስቲክስ መረጃና የጂኦ ስፓሻል መረጃ በማስፈለጉ የማዕከላዊ ስታትስቲክስና የኢትዮጵያ ካርታ ስራዎች ኤጀንሲዎች በምክክር መድረኩ እንዲሳተፉ መደረጉን አክለዋል።

በምክክሩ በህዳር 2010 ዓ.ም ስለሚካሄደው አገር አቀፍ የህዝብና ቤት ቆጠራ ቅድመ ዝግጅት ግምገማና አጠቃላይ የአገር ምርት ግንባታ ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር ዝርዝር ውይይት እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የአገራዊና የክልል የልማት ዕቅድ፣ ክትትልና ግምገማን የተመለከተ የጋራ የምክክር መድረክ ረቂቅ የመተዳደሪያ ሰነድ የተዘጋጀ ሲሆን ነገ ለውይይት እንደሚቀርብ ይጠበቃል።

በብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን የበላይነት የሚመራው የ2017 ዘላቂ የልማት ግቦች የፈቃደኝነት አፈጻጸም ሪፖርት ውይይት ከተደረገበት በኋላ በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጥር ሰኔ 1 ቀን 2017 በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚጸድቅ ይሆናል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ