አርዕስተ ዜና

የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ስርዓት ሊዘረጋ ነው Featured

17 Feb 2017
454 times

የካቲት 10/2009 በኢትዮጵያ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ስርዓት ለማስፈን አቅድ እየተዘጋጀ መሆኑን የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በሚኒስቴሩ የተፋሰስ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አስማማው ቁሜ ለኢዜአ እንደገለጹት 90 በመቶ የሚደርሰው የገጸ-ምድር የውሃ መጠን የሚገኘው በምእራባዊና ደቡብ ምእራባዊ የሃገሪቱ ክፍሎች ነው፡፡ 40 በመቶ የሚሆነው ህዝብም በዚሁ አካባቢ ይኖራል፡፡

በመካከለኛውና በመካከለኛው ምስራቅ የሃገሪቱ ክፍል ያለው የገጸ ምድር ውሃ ደግሞ 10 በመቶ የሚደርስ ሲሆን 60 ከመቶ የሚሆነው ህዝብ ይኖርበታል፡፡

በዚህም በሃገሪቱ ውስጥ ያለው የውሃ ስርጭትና ግኝቱ በተፈጥሮ የተዛባ መሆኑን ነው አቶ አስማማው ያመለከቱት፡፡

ለዚህ ደግሞ የሃገሪቱን የውሃ ሃብት በፍትሃዊነት ማከፋፈልና በፍትሃዊነት አስተካክሎ መምራት ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡

አንድ ተፋሰስ በሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ክልሎች የሚዋሰን በመሆኑ ይህን ጥራቱንም ሆነ መጠኑን ጠብቆ ማከፋፈል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የውሃ ሃብቱ በተቀናጀ መልኩ መተዳደር ፣መልማትና መጠበቅ አለበት ያሉት አቶ አስማማው ክልሎች ወንዞችና ተፋሰሶችን የሚጋሩ በመሆናቸውና የውሃ ሃብት ስርጭቱና ፍትሃዊነቱ የተዛባ በመሆኑ ይህን በመፍታት ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲኖር የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት፡፡

በተለምዶ የምንጠቀምበትን የውሃ ሃብት በእቅድና ሳይንስን መሰረት ባደረገ መልኩ የውሃ አስተዳደር ስርአት መፈጠር አለበትም ባይ ናቸው አቶ አስማማው፡፡

የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ስርአትን ለመመስረት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የተፋሰስ እቅድ የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የአባይና የአዋሽ ሸለቆ ተፋሰስ ባለስልጣናት ያዘጋጁት የተፋሰስ ስትራቴጂክ እቅዶችን አቅርበው በመታየት ላይ ሲሆን የስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ ባለስልጣን ደግሞ የተፋሰስ እቅድ ለማዘጋጀት ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

በ12 ተፋሰሶች የምትከፈለው ኢትዮጵያ 123 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የገጸ-ምድርና እስከ 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚደርስ የከርሰ ምድር ውሃ እንዳላት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ