አርዕስተ ዜና

የባቡር መስመሩ አፍሪካን በማስተሳሰር የራሱ ሚና ይኖረዋል-አምባሳደር ብርሃነ Featured

11 Jan 2017
577 times

አዲስ አበባ ጥር 3/2009 የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር አፍሪካን በማስተሳሰር የራሱ ሚና እንደሚኖረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ መልዕክተኛ ተናገሩ።

ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ እንዳሉት የባቡር መስመሩ ትልቅ፣ ዘመናዊና በታዳሽ ኃይል (በኤሌክትሪክ) የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ዓለምን በማይበክል መልኩ የተገነባና ለሌሎችም ምሳሌ የሚሆን ነው።

ለሁለቱ አገሮች ካለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር በአህጉር ደረጃ የተያዘውን አፍሪካን የማስተሳሰር ዕቅድም ዕውን የሚያደርግ ነው።

አፍሪካ በ50 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በኢኮኖሚም ሆነ በመሰረተ-ልማት ጠንካራና የተባበረች አንድ አህጉር እንድትሆን ዕቅድ ተይዟል።

የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ዕቅዱ ዕውን እየሆነ እንደሚሄድ "አንዱ ማሳያና በቀጣይም የአካባቢውን አገሮች የሚያስተሳስር ነው" ብለዋል።

ቀጣዩ መስመር ለአፍሪካ ከተሞች በሚመች መልኩ በቅብብሎሽ የሚዘረጋ በመሆኑ "የአካባቢውን አገሮች የመሰረተ-ልማት፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የሰላም ትስስር ያጠናክራል ነው" ያሉት።

ፈጣን ባቡሩ ሰው፣ ዕቃና እንስሳትን የሚያመላልስ በተለያየ ደረጃ የመጫን አቅም ያላቸው ሲሆን፤ 2 ሺህ 760 መንገደኞችን በመያዝ በሰዓት 120 ኪሎ ሜትር ሲጓዝ፤ 3 ሺህ 500 ቶን በመጫን በሰዓት 80 ኪሎ ሜትር የመጓዝ አቅም አለው።

ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ለመግባት ተሽከርካሪዎች ከሶስት ቀን እስከ አንድ ሳምንት ይወስድባቸው የነበረውን ጊዜ ወደ 12 ሰዓት ዝቅ ማደረጉ ደግሞ ይበልጥ ተመራጭ ያደርገዋል።

ይህም የአገሪቷ ኢኮኖሚ ይበልጥ እንዲያድግና "ምርቶቻችን በዓለም ገበያ አዋጪ በሆነ መንገድ እንዲሸጡ፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎችና ቴክኖሎጂዎችም አዋጭ በሆነ መልኩ እንዲገቡ ያደርጋል" ነው ያሉት አምባሳደር ብርሃነ።

አገሪቷ የጀመረችውን ፈጣን ዕድገት ወደፊት የሚገፋና "የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠርም አስተዋጽኦው የጎላ ነው" ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ "በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን በመተሳሰብና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ወዳጅነት የበለጠ ጠፍሮ የሚይዝ ትልቅ ገመድ ነው" በማለት ገልጸዋል።

የሁለቱ አገሮች ህዝቦች መጻኢ ዕድል አንድ ላይ እንዲሆን የሚያደርግና የአገራቱን የዕድገት ደረጃም ከፍተኛ ቦታ የሚያደርስ መሆኑን በማሳየት።

ከኢትዮጵያ ድንበር እስከ ጅቡቲ ያለው የ100 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር በትናንትናው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ በተገኙበት ተመርቋል።

ከሶስት ወራት በፊትም በኢትዮጵያ በኩል ያለው የ656 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ሁለቱ መሪዎችና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት መመረቁ ይታወሳል።

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ