አርዕስተ ዜና

የኤሌክትሪክ ኃይል እጦት ሊፈታ ያልቻለ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖብናል-የዱከም ከተማ ነዋሪዎች

11 Jan 2017
528 times

አዲስ አበባ ጥር 3/2009 የኤሌክትሪክ ኃይል እጦት ሊፈታ ያልቻለ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሆነባቸው የኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን የልማት ተነሺዎች ገለጹ።

የዱከም ከተማ የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው የከተማዋ የኤሌክትሪክ ኃይል ችግርን መፍታት ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ አባላት ሰሞኑን ከኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን የልማት ተነሺዎችና ከዱከም ከተማ የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

በዚሁ ጊዜ የኤሌክትሪክ ኃይል እጦት እስካሁን ሊፈታ ያልቻለ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሆነባቸው የልማት ተነሺዎቹና የስራ ኃላፊዎቹ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት አንስተዋል።

እንደ ነዋሪዎቹ ገለፃ በተለይም ለኢንዱስትሪ ዞኑ ልማት ከቦታቸው ሲነሱ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት እንደሚያገኙ ቃል የተገባላቸው ቢሆንም እስካሁን ተግባራዊ አለመሆኑ ለምሬት ዳርጓቸዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት እንዲሟላላቸው ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ አለማግኘታቸውንም ነው የልማት ተነሺዎቹ ያመለከቱት።

ለኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ለቀን ስንነሳ ይሟላላችኋል ተብሎ እስካሁን ድረስ አልተሟላም።ጭለማ ውስጥ ነው ያለነው ሌባ እየዘረፈን ነው። ከብቶቻችንንም ሌባ እየዘረፈ ነው። ስለዚህ በመንግስት በኩል በአፋጣኝ መብራት እንዲገባልን  እንጠይቃለን'' ብለዋል፡፡

የዱከም ከተማ የስራ ኃላፊዎች በበኩላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ችግር የኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን የልማት ተነሺዎች ብቻ ሳይሆን የከተማዋ የመልካም አስተዳደር ችግር በመሆኑ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተወካይ አቶ መከተ ነጋ ከልማት ተነሺዎች የተነሱ ጥያቄዎችን ከሚመለከታቸው አስፈጻሚ አካላት ጋር በመወያያት መፍትሄ ለማምጣት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ጉዳዩን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት መረጃ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ