አርዕስተ ዜና

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት የሚፈጸምባቸውን አዳዲስ ቅርንጫፎች ሊከፍት ነው

11 Jan 2017
791 times

ነቀምቴ ጥር 3/2009 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ  በስድስት ከተሞች የኤሌክትሮኒክስ ግብይት የሚፈጸምባቸውን አዳዲስ ቅርንጫፎች እንደሚከፍት አስታወቀ።

ምርት ገበያው ተቋቁሞ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንሰቶ እስካሁን ድረስ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ማገበያየቱንም ገልጿል።

በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የስትራቴጅክ ዕቅድ ባለሙያ ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ዋሲሁን እንዳሉት ቅርንጫፎቹ የሚከፈቱት በነቀምቴ፣ ሀዋሳ፣ ሁመራ፣ ጎንደር፣ አዳማና ኮምቦልቻ ከተሞች ነው።

በአሁኑ ወቅት በከተሞቹ ለግብይት ሥራው የሚሆኑ ማዕከላት ግንባታቸው በመፋጠን ላይ መሆኑን የገለጹት ባለሙያዋ፣ የኤሌክትሮኒክስ ግብይቱ  አገልግሎቱን ለማዘመን፣ ቀልጣፋና ተደራሽ  ለማድረግ  የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ሻጭና ገዥ በአንድ መድረክ በግንባር ለመገናኘት ያባክኑት የነበረውን ጊዜ ከማስቀረት ባለፈ የግብይት ሥርዓቱን ይበልጥ  ግልጽና ተአማኒ በማድረግ  ሊፈጠሩ የሚችሉ  አለመግባባቶችን እንደሚያስቀር ጠቁመዋል።

እንደ ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ገለጻ፣ ለደንበኞች በአጭር ጊዜ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የኤሌክትሮኒክስ የመገበያያ ዘዴን ከማስፋት ባለፈ ከዋናው መስሪያ ቤት ጋር በመረጃ መረብ  የማስተሳሰር ሥራ እየተሰራ ነው።

አገልግሎቱን ለማስተዋወቅ በየከተሞቹ ለሚገኙ ደንበኞችና ባለድርሻ  አካላት የግንዛቤ  ማስጨበጫ  መርሃግብር እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው  በነቀምቴ ከተማ ለግብይት ፈጻሚዎችና ለባለድርሻ አካላት ትናንት የተዘጋጀው መድረክም የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ  የሚሰጣቸው አገልግሎቶች፣ የምርት ገበያው አባል ለመሆን መሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎችና  የኤሌክትሮኒክስ  ግብይት  ስለሚኖረው ጠቀሜታ  ማብራሪያ  መሰጠቱን ወይዘሮ ኤልሳቤጥ አመልክተዋል።

ባለሙያዋ እንዳሉት፣ አዲሶቹ ቅርንጫፎች ሥራ ሲጀምሩ የሚገበያዩ አካላት በተመሳሳይ ሰዓትና ጊዜ ከሁሉም ቅርንጫፎች  ጋር እኩል መገበያየት ይችላሉ።

የኢትዮጵያ  ምርት ገበያ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሥራውን ከሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ መጀመሩን አስታውሰው፣ ይህንንም ለማቀላጠፍ  ከ990 በላይ የግብይት ተዋንያንን  አሰልጥኖ ብቁ ለሆኑት 761 ሰልጣኖች  የምስክር  ወረቀት መስጠቱን ጠቅሰዋል።

ምርት ገበያው ሥራውን ከጀመረ ወዲህ እስካሁንድረስ ከ50 ሺህ በላይ ግብይቶችን ያካሄደ ሲሆን ይህም ከ316 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ እንዲሁም ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ በገንዘብ የሚተመን መሆኑን አስረድተዋል።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የምዕራብ ወለጋ ዞን የቡናና ሻይ ልማት ግብይት ባለስልጣን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወጋሪ ነገራ፣ የግብርና ምርት ዕድገት እያሳየ በመምጣቱ ምርቱ ዋጋ እንዲያገኝ ገበያ ያስፈልገዋል።

ቀደም ሲል የምርት ግብይቱ በማዕከል ደረጃ ብቻ የሚካሄድ መሆኑ ሕብረተሰቡንና  አምራቹን ሲያጉላላ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁን ወቅት የኤሌክትሮኒክስ ግብይቱ  ወደ አምራቹና ነጋዴው ይበልጥ ተደራሽ መሆኑ ቀልጣፋ  አገልግሎት ለመስጠት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

በቄለም ወለጋ  ዞን ዳሌ ዋበራ ወረዳ  በቡናና በሰሊጥ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ተመስገን ተርፋ በበኩላቸው፣ በስልጠናው በዘመናዊ የግብይት ሂደት አሰራርና ባሉበት ሆነው መገበያየት  እንደሚችሉ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የግብይት ሂደቱ ጊዜያቸውን የሚቆጥብ በመሆኑ ባሉበት ሆነው ሥራቸው ሳይጉላላ ለማከናወን አንደሚያስችላቸው ከስልጠናው መረዳታቸው ተገልጿል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ