አርዕስተ ዜና

በዞኑ በ66 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ በመካሄድ ላይ ነው

11 Jan 2017
391 times

ደብረ ብርሃን ጥር 3/2009 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በ66 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተጠናከረ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ተጀመረ።

በዞኑ የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ በይፋ የተጀመረው በመርሀቤቴና ምንጃር ወረዳዎች ነው።

በመርሀቤቴ ወረዳ በተዘጋጀው መርሀግብር ላይ የተገኙት የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ እንዳሉት፣ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራዎች የአካባቢያቸው ምርታማነት እያደገ መጥቷል።

የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል ዘንድሮም በ962 ተፋሰሶች 66 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተጠናከረ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ ከጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጅምሮ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ከሚከናወንባቸው አካባቢዎች የተወሰኑትን ከእንስሳትና ከሰው ንኪኪ ነጻ በማድረግ አርሶ አደሩ በእንስሳት ማድለብ፣ በንብ ማነብ፣ በአትክልትና ፍርፍሬ፣ በእንስሳት መኖና በሌሎች የኢኮኖሚ አማራጮች እንዲሰማራባቸው የሚደረግ መሆኑንም አቶ ደረጀ አመልክተዋል።

በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ከ30 እስከ 40 ቀን በሚካሄደው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ውሃን አሰባስቦ ለመያዝ የሚያስችሉ የተለያዩ የውሃ ማቆሪያዎችና የአፈር መከላትን የሚከላከሉ የእርከን ሥራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።

በተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራው በ11 ሺህ 814 የልማት ቡድኖች የተደራጁ ከ492 ሺህ 990 በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከጥር አንድ ቀን ጀምሮ በመሳተፍ ላይ ናቸው።

በቅድመ ዝግጅት ሥራው 28 ሺህ 782 ቀያሽ አርሶ አደሮችን የማሰልጠንና የመስሪያ ቁሳቁስ የማቅረብ ሥራ መከናወኑንም አስታውሰዋል።

የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራው ተገቢ ትኩረት አግኝቶ በጥራትና በፍጥነት እንዲከናወን በመራሀቤቴና ምንጃር ወረዳዎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ሥራው እንዲጀመር መደረጉንም አቶ ደረጀ ተናግረዋል።

በመርሀቤቴ ወረዳ የጌቨ ዘሞይ ቀበሌ አርሶአደር ወልደኪዳን ደመቀ እንደገለጹት፣ ባለፉት ዓመታት በአካባቢያቸው በተሰራው ሥራ ለዘመናት ተራቁቶ የነበረው የዞማ ተራራ በማገገሙ  ምርታማነታቸው ጨምሯል።

በተራራው ሥር ካለው አንድ ሄክታር መሬታቸው አምስት ኩንታል የማይበልጥ ምርት ያገኙ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ላይ የአፈሩ ለምነት በመመለሱ ከሃያ ኩንታል በላይ ምርት እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ እንዳሉት፣ በአካባቢው የውሃ ፍሰቱ እየጨመረ በመምጣቱ በመስኖ ተጠቅመው ማንጎ፣ አፕል፣ ብርቱካንና ቀይ ሽንኩርት በማልማት ተጨማሪ ገቢ በማግኘት ላይ ናቸው።

ደሳለኝ ግዛው የተባሉ ሌላው አርሶ አደር በበኩላቸው፣ ባለፉት ዓመታት በሁለት ሄክታር መሬታቸው ላይ የድንጋይ እርከን ሰርተው በመንከባከባቸው ምርታማነታቸውን ከእጥፍ በላይ ማሳደግ ችለዋል።

በወረዳው የጊደብ ወረጎ ቀበሌ አርሶአደር ከፈለ ተሾመ፣ ቀደም ባሉት ዓመታት በአካባቢያቸው በክረምት ወራት የሚከሰተው ጎርፍ የርሻ መሬታቸውን ከመጉዳቱ ባሻገር በየዓመቱ ስጋት ይፈጥርባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

ባለፉት ዓመታት በዞኑ በ931 ተፋሰሶች ውስጥ በሚገኝ 278 ሺህ ሄክታር መሬት የተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች መከናወናቸው ተገልጿል፡፡

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ