ከኢትዮጵያ ድንበር እስከ ጅቡቲ ያለው የባቡር ፕሮጀክት ተመረቀ Featured

10 Jan 2017
1441 times

ጂቡቲ ጥር 2/2009 የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ለሁለቱ አገራት ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የጎላ ሚና እንደሚኖረው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ።

ከኢትዮጵያ ድንበር እስከ ጅቡቲ ያለው የ 100 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ዛሬ በይፋ ተመርቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ መስመሩን መርቀው ከፍተውታል።

የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር 758 ኪሎ ሜትር አጠቃላይ ርዝመት ሲኖረው በኢትዮጵያ በኩል መስከረም 25 ቀን 2009 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ በተገኙበት መመረቁ ይታወሳል።

ዛሬ ደግሞ በጅቡቲ በኩል የፕሮጀክቱ ምርቃት ሲከናወን ከጅቡቲ ነጋድ እስከ ሆልሆል ባቡር ጣቢያ ድረስ የሁለቱ አገራት ባለሥልጣናትን ያካተተ የሙከራ ጉዞ ተደርጓል።

በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒሰትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በኤሌክትሪክ የሚሰራው ዘመናዊ ባቡር ለሁለቱም አገራት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

ዘላቂነት ላለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የዘመናዊ መሰረተ ልማት ሚና የጎላ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቡሩ ኤሌክትሪክን የሚጠቀም በመሆኑ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የላቀ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ 95 ከመቶ በላይ የሚሆነው የገቢና ወጪ ንግድ የሚከናወነው በጅቡቲ በኩል እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

የባቡር መስመሩ ሥራ መጀመር ይህን አገልግሎት ከማቀላጠፉም በላይ ምርቶችን ለማጓጓዝ ከሦስት ቀናት በላይ ይወስድ የነበረውን ጊዜ ወደ 12 ሰዓታት ዝቅ ያደርገዋል።

የሁለቱን እህትማማች አገራት ግንኙነትም ይበልጥ ያሳድገዋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

"የጅቡቲ ማደግ የኢትዮጵያ ማደግ ነው፤ የኢትዮጵያ ማደግም የጅቡቲ ማደግ ነው፤ በመሆኑም ተያይዘን እንጓዛለን አብረንም እናድጋለን" ብለዋል።

መስመሩ ከጅቡቲም አልፎ እስከ ሴኔጋል ዳካር የሚዘልቅ በመሆኑ አፍሪካን በማስተሳሰር በኩል የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለውም አውስተዋል።

የአፍሪካ ኅብረት የያዘው አንዱ ዕቅድ በፈጣን ባቡር አፍሪካን ማስተሳሰር በመሆኑ ፕሮጀክቱ ዕቅዱን ተግባራዊ ያደረገና ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው ብለዋል።

የፕሮጀክቱ ወጪ ከቻይና ኤግዚም ባንክ በተገኘ ገንዘብ የተሸፈነ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቱን ለቻይና አፍሪካ ትብብር ዕድገት አንዱ ማሳያ አድርገው ጠቅሰውታል።

የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ለሁለቱ አገራት የዕድገት ሽግግር ዋስትና ከመሆኑም ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

በኢትዮጵያና ጅቡቲ መካከል ዘመናዊ የትራንስፖርት ሥርዓት እውን መሆን ትስስራቸውን በማሳደግ ብቻ ሳይገደብ ቀጣይ ዕጣ ፋንታቸውንም የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በቀጣዩቹ 10 ዓመታትም አገራቱ ኃያል የመሆን ተስፋ እንዳላቸው እምነታቸውን ገልጸዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ