አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 09 April 2018

አዲስ አበባ  ሚያዚያ 1/2010  የኤርትራ ስደተኞች በዘላቂነት የማቋቋምና መደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ "በጋራ መስራት ይገባል" ስትል ድምጻዊት ብሩክታዊት ጌታሁን (ቤቲ ጂ) ገለጸች።

የመንግሥታቱ ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን አጋር የሆነችው ድምጻዊት ብሩክታዊት ጌታሁን (ቤቲ ጂ) በትግራይ ክልል የሚገኘውን የሽሬ እንዳ ሥላሴ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ጎብኝታለች።

ድምጻዊት ብሩክታዊት ለሁለት ቀናት ባደረገችው ጉብኝት የኤርትራ ስደተኞች ያሉበትን ሁኔታ የተመለከተች ሲሆን፤ ከስደተኞቹም ጋር ለመወያየት እድል ማግኘቷን ኮሚሽኑ ገልጿል።

እነዚሁ የኤርትራ ስደተኞች አብዛኞቹ ከቤተሰባቸው ወይም ከአሳዳጊዎቻቸው ተለይተው በትግራይ ክልል በአራት የስደተኞች ጣቢያ ወስጥ ተጠልለው ይገኛሉ።

ስደተኞቹም ከድምጻዊት ብሩክታዊት ጋር ለሁለት ቀናት በነበራቸው ቆይታ ያለፉበትን የህይወት ውጣ ውርድ አጋርተዋታል።
በጉብኝቷ ወቅት በደረሳበቸው የመፈናቀል አደጋ በርካታ ሰዎች ለተለያዩ አእምሮአዊ ችግር ውስጥ መግባታቸውን የታዘበችው  ሙዚቀኛዋ የሞራል ድጋፍ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልጻለች።

"እነሱን ለመደገፍ የምንችልበትን ሁኔታ ማሳብ አለብን፤ ከእነርሱ ጋር እንዴት እንሰራለን ብለን እራሳችንን መጠየቅ አለብን፤ ይህን የምናደርግ ከሆነ እነርሱን በቀላሉ ማቋቋም እንችላለን" ብላለች።

ድምጻዊት ብሩክታዊት እንዳለችው "እዚህ የተወለዱትንም ወይንም ያደጉትን ስደተኞች ስትመለከት እጅግ ያሳዝናል፤ በአይናቸው ውስጥ ተስፋ ይታያል፤ በድምጻቸው ቁርጠኝነታቸው ይሰማል፤ አጋርነታችንን ካሳየናቸው ደግሞ ሁሉም ይሳካል"።

"እንዲህ አይነቱ መስዋዕትነት የሚከፈለውም ህይወትን ስትረዳ ነው፤ እነዚህ ልጆች ይህን ሁሉ እያወቁ ወደ እዚህ መጥተዋል፤ ህልማቸውን ለማለም እንዲችሉና ተስፋቸውንም ለማስቀረት ትልቅ ስራ ይጠብቀናል" ብላለች።   

ስደተኞቹ በአገራቸው ለውትድርና ላለመመልመልና ተያያዥ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመሸሽ የተሰደዱ ናቸው። ወደፊት በተለያዩ የውጭ አገሮች ከሚኖሩ ቤተሰቦቻቸው ጋር ለመቀላቀል ተስፋ ያደርጋሉ።

ስደተኞቹ የሥራ እድልና መተዳደሪያ እንዲያገኙ እድሎች ማመቻቸት ከተቻለ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብትም በአዎንታዊ መልኩ ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉም ነው ያመለከተችው።

ድምጻዊት ብሩክታዊት የመንግሥታቱ ድርጅት ከፍተኛ አጋር በመሆን ይህንን ጉብኝት ያደረገችው ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

በአሁኑ ወቅት ከ900 ሺ በላይ ስደተኞች በኢትዮጵያ የሚገኙ ሲሆን፤  ከነዚህ መካከል 165 ሺ የሚሆኑት ከኤርትራ የመጡና 22 በመቶ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ባሉ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ናቸው።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 1/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር ግምት ያላቸው ሁለት ዘመናዊ የእቃ መፈተሻ ማሽኖችን ከአሜሪካ ትራንስፖርት ደህንነት አስተዳደር (ቲ ኤስ ኤ) በእርዳታ አግኝቷል።

መፈተሻ ማሽኑ የአየር መንገዱን የደህንነት ጥበቃ ስራ ያሳድጋል ተብሏል።

ቲ ኤስ ኤ ከአሜሪካ ጋር አጋርነት ካላቸው ዓለም ዓቀፍ አየር መንገዶች ጋር በመስራት ዘመናዊውን የመፈተሻ ማሽን የሚያቀርብ ሲሆን ከኢትዮጵያ ጋር ባለው የተሻለ ግንኙነት መነሻነት ነው መሳሪያዎቹን ሊያበረክት የቻለው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም አየር መንገዱ የመፈተሻ ማሽኑን ማግኘቱ ያለውን አገልግሎት ከማፋጠኑም በላይ ደህንነቱን ይበልጥ ያረጋግጣል ብለዋል።

የብዙ አየር መንገዶች መዳረሻና መተላለፊያ የሆነውን የአዲስ አበባን አየር ማረፊያ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ሚናው ከፍተኛ እንደሚሆንም አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሚካኤል ራይኖር አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግዙፍ የአየር ንግድ ከስጋት የፀዳና ሰላማዊ እንዲሆን ለማስቻል መሳሪያው የተበረከተ መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አየር ትራንስፖርት ቀዳሚ መሆኗን የተናገሩት አምባሳደሩ ቴክኖሎጂው በአፍሪካ አህጉር ሲተከል የመጀመሪያው እንደሆነ ጠቁመዋል።

ድጋፉ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የአየር ትራንስፖርት ትስስር ያጠናክራልም ብለዋል።

የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው የዕቃ መፈተሻ መሳሪያ በቀን ከ15 እስከ 17 ሺህ መንገደኞችን የእቃ መያዣ ሻንጣ ፈትሾ ማሳለፍ የሚችል ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህ ቀደም የሰውና የእቃ መፈተሻ ሁለት መሳሪያዎች የነበሩት ሲሆን የአሁኖቹ ግን በዘመናዊነትና ሻንጣ ውስጥ ያሉ ከ65 በላይ አይነት እቃዎችን በመመርመር የላቀ ነው።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 1/2010 የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ "የእንኳን ደስ አለዎት" መልዕክት አስተላለፉ።

ፕሬዝዳንት ፑቲን ዶክተር አብይ አህመድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመመረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ዶክተር አብይ ሁለቱ አገሮች በተለያዩ መስኮች ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በማሳደግ "የአገራቱን ህዝቦች ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ገንቢ ሚና ይወጣሉ" ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ፕሬዝዳንት ፑቲን ገልጸዋል።

የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በጋራ መከባበርና ለረጅም ጊዜ በቆየ ወዳጅነታቸው ላይ እንደተመሰረተና ይህንንም ሩሲያ እንደምታደንቅ አንስተዋል።

አገሮቹ በጸጥታና ደህንነት ያላቸው ግንኙነት እንዲጠናከርና በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚደረገውን ጥረትም ያግዛሉ ብለው እንደሚጠብቁም ነው ቭላድሚር ፑቲን የገለጹት።

ፑቲን በደስታ መግለጫቸው ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መልካም ጤንነትና በስራቸው ስኬታማ ጊዜ እንዲያሳልፉ መመኘታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ከዚህ ቀደም የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኬቻንግ፣ የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን፣ የእንግሊዝ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፣ የሳዑዲ አረቢያው ንጉስ ሰልማን ቢን አብዱልአዚዝ አልሳውድ፣ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲና የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ና የሌሎች አገሮች መሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ"እንኳን ደስ አለዎት" መልዕክት ማስተላለፋቸው የሚታወስ ነው።

 

Published in ፖለቲካ

አዳማ ሚያዝያ 1/2010 በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲጠናከር ከኦህዴድ ጎን እንደሚቆሙ በምስራቅ ሸዋ ዞን የሚገኙ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ገለጹ።

 የምስራቅ ሸዋ ዞንና አዳማ ከተማ የብአዴን፣ደህዴንና ህወሓት አስተባባሪዎች የኦህዴድን 28ኛ ዓመት ምስረታን ምክንያት በማድረግ በሰጡት መግለጫ  ኦህዴድ የጠራ ዓላማ አንግቦ በርካታ ፈተናዎችን በማለፍ ለውጤት የበቃ መሪ ድርጅት መሆኑን ገልጸዋል።

 በዞኑ የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) አስተባባሪ አቶ ጌታ በላቸው እንደገለጹት ኦህዴድ ባለፉት 28 ዓመታት የሀገረቱ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የተመዘገቡ ድሎችን ለማስቀጠል የላቀ ሚና አለው።

 በአሁኑ ወቅት አስተማማኝ ሰላም በማስፈን፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ለማረጋገጥ ድርጅቱ የተሰጠውን ክልላዊና ሀገራዊ ኃላፊነት በላቀ ደረጃ እንዲወጣ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከጎኑ እንደሚቆሙ ተናግረዋል ።

 በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚኖሩ መላው የአማራ ህዝብ ለልማቱ እያደረጉ ያሉት ተሳትፎ እንደተጠበቀ ሆኖ የህዝቡን አንድነት የሚሸረሽሩ አመለካከቶችን በማረም የኦህዴድ ዕቅድና ተልዕኮን ለማሳካት እንደሚረባረቡም አስገንዝበዋል።

 ኦህዴድ በሀገሪቱ የነበረው የጭቆና አገዛዝ በህዝቦች እልህ አስጨራሽ ትግል ተወግዶ በሀገሪቱ ብርሃን እንዲፈነጥቅ ካስቻሉ መሪ ድርጅቶች አንዱ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የምስራቅ ሸዋ ዞንና የአዳማ ከተማ የህወሓት አስተባባሪ አቶ አብረሀ ሐጎስ ናቸው።

 ኦህዴድ ከእህት ድርጅቶች ጋር ሆኖ የከፈለው መስዋዕትነት ሀገሪቷ አሁን ለደረሰችበት ሁሉን አቀፍ ልማት፣ እድገትና የዴሞክራሲ ለውጦች ወሳኝ ሚና እንደነበረውም ተናግረዋል።

 በዞኑ የሚገኙ የህወሓት አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ከኦህዴድ ጎን ሆነው ሙስናን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን፣ ጠባብነትና ትምክህትን በመታገል ሀገሪቷ የጀመረችውን የለውጥ ምዕራፍ ማሳካት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

 የምስራቅ ሸዋ ዞን የደህዴን አስተባባሪ ወይዘሮ ሙና ሚልኪሶ በበኩላቸው  ኦህዴድ ሀገሪቷ ከገባችበት ዘርፈ ብዙ ችግር እንድትላቀቅ የያዘውን መስመር ድርጅታቸው ለመደገፍ ከጎኑ ሆኖ እንደሚንቀሳቀስ ገልጸዋል።

 በዞኑ የሚኖሩ የደቡብ ክልል ተወላጆች፣ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ኦህዴድ በሚያከናውናቸው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሥራዎች ንቁ ተሳታፊ በመሆን ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያጎለብትም አመልክተዋል።

 የምስራቅ ሸዋ ዞን ኦህዴድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ታምራት በበኩላቸው እንዳሉት ድርጅቱ ባለፉት ዓመታት በሀገሪቷ ሁሉን አቀፍ ልማት፣መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ አንዲጠናከር ሲሰራ ቆይቷል።

 በአሁኑ ወቅት በክልሉም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ የህዝቡ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በአፋጣኝና በተገቢው ምላሽ እንዲያገኙም በሙሉ አቅሙ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

 በሀገሪቱ አስተማማኝ ዴሞክራሲ እውን እንዲሆን የህዝቡ የፍትህ ጥማትና እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ድርጅቱ ራሱንና ውስጣዊ አሰራሩን በመፈተሽ አዲስ የትግል ምዕራፍ መጀመሩን አስረድተዋል።

 በዚህም እህት ድርጅቶች፣በክልሉ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች መላው የክልሉ ህዝብ ከጎኑ በመቆም  የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ትግል ከዳር ለማድረስ እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 1/2010 የትንሳዔ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር መከበሩን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በደማቅ ሁኔታ በተከበረው የትንሳዔ በዓል በመዲናዋ ምንም አይነት የጸጥታ ችግር አለመከሰቱን አሳውቋል።

በሌላ በኩል በዓሉ በተከበረበት በዋዜማና በእለቱ  በአራት ሰዎች ላይ ከባድ የትራፊክ አደጋ የተከሰተ ሲሆን፤ በንብረት ላይ አስራ አምስት አደጋዎች መድረሱን ገልጿል።

በሰው ህይወት ላይ ምንም ዓይነት የሞት አደጋ አለመመዝገቡን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ ይህም ከበዓል ወቅት እና በመደበኛው ጊዜ ከሚደርሰው አደጋ ጋር ሲነጻጸርም ዝቅተኛ መሆኑን በመልካም አንስቷል።

በበዓል ወቅት የሚከሰተውን ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ አደጋ ለመከላከልም ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ በተመረጡ 12 ስፍራዎች የቁጥጥር ስራ መሰራቱንም ገልጿል።

በተሰራው የቁጥጥር ስራም 65 አሽከርካሪዎች ከመጠን በላይ ጠጥተውና ከፍጥነት በላይ  ሲያሽከረክሩ መያዛቸውን የኮሚሽኑ መግለጫ ያመለክታል።

ከወንጀል ድርጊት ጋር ተያይዞ ከሚሽኑ ከሚመለከታቸው አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በመስራቱ ከወትሮ የተለየ የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙና በዓሉ በሰላም መከበሩን በላከው መግለጫ አስታወቋል።

በዓሉ በሰላም እንዲከበርም ህብረተሰቡ ላደረገው ቀና ትብብር የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምስጋናውን አቅርቧል። በቀጣይም ህብረተሰቡ ያልተቆጠበ ትብብሩን እንዲቀጥል መልዕክቱን አስተላልፏል።

በከተማዋ ከትንሳዔ በዓል ጋር ተያይዞ ምንም አይነት የእሳት አደጋ አለመከሰቱን የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጣር ባለስልጣን ማስታወቁ ይታወሳል።

 

Published in ማህበራዊ

ጅግጅጋ ሚያዝያ 1/2010 በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት መዘጋጀታቸውን  የሶማሌ ክልል የጎሳ መሪዎች ገለጹ፡፡

 የጎሳ መሪዎቹ ይህን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ህዝቡን  በጅግጅጋ ከተማ ባወያዩበት ወቅት ነው።

 በአዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለመፍታት እያደረጉት ካለው ጥረት በተጨማሪ ከመንግስት ጋር ተቀራርበው ለመስራት ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

 የሀገር ሽማግሌና የአበስኩል ጎሳ መሪ አቶ አብዲከሪም ቀሊንሌ የሰላሞ ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባና የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች ለዘመናት ተከባብረውና ተሳስበው የመኖር ባህሎቻቸውን ወደነበረበት መመለስ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

 የነበረው ቅራኔ ተወግዶ በህዝቦች መካከል ሰላምን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

 የብሰሜ ጎሳ መሪ የሆኑት ገራድ ኩልሚየ ገራድ መሐመድ ሁለቱም ክልሎች ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው ገልጸው፣ ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የመፍትሄ ሂደቱ አካል ለመሆን መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

 የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው በመድረኩ  ባደረጉት ንግግር በሁለቱም ህዝቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭትና አለመግባባት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለመፍታትና ሰላም ወደነበረበት እንዲመለስ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

 መንግስት ለዘላቂ ሰላም በትኩረት እንደሚሰራ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በተለይ የጎሳና የሀገር መሪዎች ለሰላም ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው እንዲንቀሳቀሱ አስገንዝበዋል።

 ቀደም ሲል የኦሮሚያና  ሶማሌ አጎራባች ክልሎች ልማት ጉዳይ ቢሮ ሲሰራ እንደነበር ያስታወሱት የክልሉ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ አብዱላሂ ሐሰን ቢሮው አሁንም መመለስ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

 ለሁለቱ ክልል ህዝቦች ዘላቂ ሰላም ተግተው እንደሚሰሩ የገለጹት ደግሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐሙድ ዑመር ናቸው፣

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ተወካዮችና ከፌደራል የሥራ ኃላፊዎች ጋር በሰላም ጉዳይ ለምክክር ወደጅግጅጋ ከተማ መምጣታቸውን አድንቀዋል።

 የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት  አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው " አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሁለቱ ክልሎች ጊዜያዊ ግጭት እልባት ማግኘት አለበት በሚል ለችግሩ ቀዳሚ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀሳቸው ትልቅ ትርጉም አለው" ብለዋል።

 "ሰላምን ለማግኘት እናንትን ፍለጋ መጥተናል" ያሉት አቶ ለማ የሶማሌና የኦሮሚያ ክልል ህዝቦች የሚያስተሳስራቸው የባህል፣ የሃይማኖትና የታሪክ ትውፊት እንዳላቸው አመልክተዋል።

 

 

 

 

 

 

Published in ፖለቲካ

ምንይችል አለማየሁ (ኢዜአ)

ኢትዮጵያ ባሳለፍነው ሳምንት ሁለት አንኳር ጉዳዮችን አስተናግዳለች። አንደኛው በአህጉረ አፍሪካ ብዙም ያልተለመደና ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት ቁልፍ ሚና የሚጫወተው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ የአሁኑ ትውልድ ላሊበላን ከፈለፈሉና አክሱምን ያቆሙ የቀደምት አያቶቹን ወኔ ታጥቆ እየገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሰባተኛ ዓመት ክብረ በዓል ነው።

ኢትዮጵያ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ እዚህም እዚያም "ብቅ እልም" በሚሉ አለመረጋጋቶች ስትታመስ መቆየቷ እሙን ነው። አነዚህ አለመረጋጋቶች በተለይ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በስፋት ተንጸባርቀዋል። በአንዳንድ አካባቢዎችም የተፈጠሩት አለመረጋጋቶች ወደ ለየላቸው ግጭቶች ተሸጋግረው ከንብረት ማውደም ባለፈ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት ቀጥፈዋል።

የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እነዚህን አለመረጋጋቶች እንደጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ ቀድመው ባስቀመጡት አጀንዳ ልክ በሚፈልጉት ሁኔታ ተንትነውታል፤ "ኢትዮጵያ አበቃላት" እስከማለት የደረሱ መገናኛ ብዙሃን ነበሩ። በተለይ የግብጽ መገናኛ ብዙሃን በዚህ ፕሮፓጋንዳ ተጠምደው እንደነበረ አይዘነጋም። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የግብጽ መገናኛ ብዙሃን ስለ አለመረጋጋቱ ሲዘግቡት የነበረውን መረጃ ለህዝብ ይፋ እስከ ማድረግ መድረሱም ይታወሳል።

ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ማንነታቸው በቅጡ የማይታወቅ፤ ከየትኛው ጎራ መሆናቸው የማይለይ፤ ነገር ግን የነበረውን አለመረጋጋት ወደ ደም አፋሳሽ እልቂት ለመቀየር የተለያዩ ምስሎችን በማስደገፍ (በአመዛኙ የተቀነባባሩ) "ግፋ በለው" ሲሉ ከርመዋል።

ይህ አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ የሚለው አለመረጋጋት ለዘመናት ተቻችለውና ተከባብረው ሲኖሩ የነበሩ ማህበረሰቦች እርስ በርስ እንዲጠራጠሩ ከማድረጉም በላይ፤ አገሪቷ በታሪኳ አይታው በማታውቀው መንገድ በርካታ ዜጎችን ከሞቀ ቀያቸው አፈናቅሏል። በሱማሌና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን የዜጎች መፈናቀል ለአብነት ማንሳት ይቻላል።

መንግስት በበኩሉ እነዚህ አለመረጋጋቶች ምንጫቸው ብሶቶች ናቸው። አመራር አባላት በሙስና፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመዘፈቃቸው የተፈጠረ ነው ሲል በትዕይንተ መስኮት ቀርቦ በተደጋጋሚ ተናግሯል። አገሪቷን የሚመራው  የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ከአለመረጋጋቶቹ ማግስት "ህዝብ የጣለብኝን  ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት" በሚል በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ የጀመረ ሲሆን፤ የተሃድሶ ሂደቱንም በየጊዜው እየገመገመ፣ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን በተደጋጋሚ ይፋ አድርጓል።

የወቅቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት  ከህዝብ የተነሱ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ሰላም ለመፍጠር ሲልም  በመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም ለስድስት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል። አዋጁ በተቀመጠለት ጊዜ ገቢራዊ ሆኖ የተነሳ ሲሆን፤ በእነዚህ ጊዜያት መንግስት ህዝቤን በድላችኋል ያላቸውን አመራር አባላት ተጠያቂ ከማድረግ በተጨማሪ አዲስ ካቢኔ እስከማዋቀር የደረሰ ውሳኔ አሳልፏል።

እንዲህ እንዲህ እያለ የመጣው የኢትዮጵያ የሰላም ሁኔታ ከመሻሻል ወደ ባሰ ክስተት በመሄዱ እና በአንዳንድ አካባቢዎች አለመረጋጋቶች በመፈጠራቸው አገሪቷ ድጋሚ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥላ ስር እንድትወድቅ ዳርጓታል።

የኢህአዴግ አራቱ እህት ድርጅቶች ችግሩን ከስር መሰረቱ መፍታትን ያለመ ግምገማ መጀመሪያ በተናጥል፤ ከዚያ በጋራ ያካሄዱ ሲሆን፤ ከግምገማው በኋላ የድርጅቶቹ ሊቃነ መናብርት እርስ በርስ የተፈጠረባቸውን መጠራጠር እንደፈቱ፤ ከስልጣን በፊት ለአገርና ህዝብ የሚል አቋም እንደያዙና ኪራይ ሰብሳቢነትን በቁርጠኝነት ለመታገል  እንደተነሱ መግለጫ ሰጡ።

ከመግለጫው ጥቂት ቀናቶች በኋላ የኢህአዴግና ደኢህዴን ሊቀመንበር እንዲሁም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ "ለወቅታዊ ችግሮች የመፍትሄ አካል ለመሆን" በማለት የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ በይፋ አቀረቡ። በእርሳቸው የመልቀቂያ ጥያቄም  የተለያዩ አመለካከቶች ተንጸባርቀዋል።

አንዳንዶቹ ማን ይተካቸዋል ሲሉ፤ ሌሎች በተለይ ከአገር ውጭ የሚኖሩ የተለያዩ አካላት የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢህአዴግ)  "አብቅቶለታል፤ መንግስት ሊፈርስ ነው" ሲሉ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮችን በመጠቀም ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም ምክር ቤቱ ቀናቶችን የፈጀ ግምገማ ካካሄደ በኋላ የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጥያቄ ተቀብሎ የኦህዴድ ሊቀመንበር የሆኑትን ዶክተር አብይ አህመድን የግንባሩ ሊቀ መንበር አድርጎ መሾሙን አስታወቀ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በዚህ ሳምንት መባቻ ባካሄደው ስብሰባ አዲሱን የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድን የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰየመ።

የስልጣን ሽግግሩን አምባሳደሮች እንዴት ገለጹት?

በኢትዮጵያ የተካሄደው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ከኢትዮጵያውያን እስከ ውጭ አገሮች ዲፕሎማቶች አድናቆት ተችሮታል። በተለይ የሽግግሩን ሂደት በምክር ቤቱ ሲከታተሉ የነበሩ የተለያየ አገር አምባሳደሮች ሁኔታው በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ እንደነበር ሲገልጹ ተስተውለዋል።

ሽግግሩ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ምሳሌ የሚሆንና አገሪቷ ለገባችበት ወቅታዊ ችግር ትክክለኛ መፍትሄ እንደሆነ የተናገሩም ነበሩ።

በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ቫነት ሉስድሬች አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ካለፉት ስህተቶች ተምረው ለአገሪቷ ጥሩ ነገር ይዘው እንደሚመጡ እንደሚያምኑ ሲገልጹ፤ በኢትዮጵያ የቬንዙዌላ አምባሳደር ሊዊስ ማሪኖ ማታ "ኢትዮጵያ የየትኛውንም አገር ጣልቃ ገብነት ሳትፈልግ የራሷን ችግር በራሷ መፍታት እንደምትችል ያሳየችበት ሂደት" እንደሆነ ተናግረዋል።

"ሰላማዊ የስልጣን ሽግግሩ በአገሪቷ ዴሞክራሲ አዲስ ምዕራፍ እንደከፈተ" የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ የሲሪላንካ አምባሳደር ሲመት ዳስናይክ ናቸው።

በኢትዮጵያ የባንግላዴሽ አምባሳደር ሞኒራል ኢስላም በበኩላቸው "ሰላማዊ ሽግግሩ ለኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው" ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ የስልጣን ሽግግሩን አስመልክቶ በድረ-ገጹ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሰረት ዶክተር አብይ አህመድን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መሾሙ የሚያስደስትና በአዎንታዊ መልኩ የሚቀበሉት እንደሆነና  አሜሪካም ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በቅንጅት እንደምትሰራ መግለጫው አትቷል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በዚህ ሳምንት መባቻ አንድ መሪ በህይወት እያለ፤ አዲሱ የቀደመውን አሞግሶ፤ የቀደመው ደግሞ አዲሱን ተሿሚ  "ህዝቤን አደራ" በማለት ህገ መንግስትና የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አስረክቦ፤ ለበርካታ አፍሪካውያን እንደ ህልም የሚቆጠር የነበረና በአህጉሪቷ ባልተለመደ መልኩ መሪዎች ተቃቅፈው ስልጣን ሲረካከቡ ለዓለም አሳይታለች።

ይህ ብቻ አይደለም፤ ኢትዮጵያ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራና ላብ ያረፈበት፤ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም ብቻ እየገነቡ ያሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተበሰረበትን ሰባተኛ ዓመት ልደት አክብራለች። የግድቡ ግንባታ አሁን ባለበት ደረጃ 65 በመቶ ደርሷል፤ በዚህ ዓመት መጨረሻም በሁለት ዪኒቶች  ኃይል ማመንጨት በመጀመር ኢትዮጵያውያንን እራት የማብላቱን ተግባር አሃዱ እንደሚል ይጠበቃል።

ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ግድቡ እዚህ እንዲደርስ እስካሁን ባሉት ሰባት ዓመታት ውስጥ 10 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ማዋጣታቸውን ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

በአጠቃላይ ሳምንቱ የኢትዮጵያ ህዝቦች ለዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጎልበት የሄዱበት ርቀት የታየበትና  ሁሉም በአንድነት ከተባበረ የሚያቅታቸው ነገር እንደሌለ ለዓለም ያሳዩበት ነበር።

ወትሮም ኢትዮጵያ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት እና የሰው ዘር ሁሉ መገኛ መሆኗን ለዓለም በምታሳይበት ጊዜ የጨዋና ታላቅ ትውልዶች ቅብብሎሽ ሁባሬነቷን ከሚታስመሰክርበት አጋጣሚዎች አንዱ የሳምንቱ ታላላቅ ሁነቶች ዓይነት ነውና የአገራችንን ህዳሴ በተግባር እናስመስክር።

ሰናይ ጊዜ!

Published in ዜና ትንታኔ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 1/2010 የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን / ሉሲዎቹ / ከሊቢያ አቻቸው ጋር ያለባቸውን የመልስ ጨዋታ ነገ አዲስ አበባ ላይ ያካሄዳሉ።

ሉሲዎቹ በ2011ዓ.ም. በጋና ለሚካሄደው 11ኛው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታቸውን ከሜዳቸው ውጭ ከሊቢያ ጋር ተጫውተው 8 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፈው መምጣታቸው ይታወቃል።

በአሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ ዋና አሰልጣኝንት የሚመሩት ሉሲዎቹ ባለፈው ሳምንት እሮብ እለት ከሊቢያ ጋር ግብጽ ላይ ጨዋታቸውን አድርገው  በረሂማ ዘርጋው ፣ ሎዛ አበራ፣  ቤተልሄም ከፍያለው፣ ብዙአየው ታደሰና ምርቃት ፈለቀ ጎሎች አሸንፈው ተመልሰዋል።

በሰፊ የጎል ልዩነት ያሸነፉት ሉሲዎቹ የመልሱን ጨዋታ ደግሞ ነገ  በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርጉ ይሆናል።

በርከት ያሉ ወጣት ተጫዋቾችን በቡድኑ ስብስብ ውስጥ ያካተተችው አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ በአፍሪካ ዋንጫ አንድም ጊዜ የመሳተፍ እድል ያላገኙትን ሊቢያዎችን በቀላሉ አሸንፋ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፏን እድል አስፍታ ነው የተመለሰችው።

የአፍሪካ ሴቶች  ዋንጫ እንደ አዲስ ከተጀመረ ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሶስት ጊዜ ማጣሪያውን አልፈው በውድድሩ መካፈል ችለዋል።

 

Published in ስፖርት

መተማ ሚያዚያ 1/2010 በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳውኃ ከተማ የፋሲካን በዓል ምክንያት በማድረግ ችግረኛ ለሆኑ  300 ሰዎች ትላንት የምሳ ግብዣና የአልባሳት ድጋፍ ተደረገ።

የዝግጅቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢና የከተማዋ ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ወጣት ደጀን ቢራራ እንዳለው  ድጋፉ የተደረገላቸው እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የትንሳኤ በዓልን በደስታ እንዲያሳልፉ ታስቦ ነው፡፡

በከተማዋ ወጣቶች ተነሳሽነት ከህብረተሰቡና ከተቋማት በተሰባሰበ 80 ሺህ ብር ወጪ ለአረጋውያን፣ ወላጆቻቸውን  ላጡ  ህፃናትንና አካል ጉዳተኞች ምሳ ተጋብዘዋል።

ከመካከላቸውም የደሃ ደሃ የሆኑና ደጋፊ ለሌላቸው 70 ሰዎች የብርድ ልብስ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።

በዝግጅቱ ተጋባዥ የሆኑት የ62 ዓመት እድሜ ባለፀጋ  አቶ ፈንታ አለሙ በሰጡት አስተያየት በተደረገላቸው ድጋፍ በዓሉን በደስታ ማሳለፍ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።

"የወጣቶቹ በጎ ተግባርም ለአባቶችና ለደሃ የህብረተሰብ ክፍሎች ያላቸውን አሳቢነት ያሳዩበት ተግባር በመሆኑ  ምስጋና ይገባቸዋል" ብለዋል፡፡

ሌላው የዝግጅቱ ተሳታፊና የ72 ዓመቱ የእድሜ ባለፀጋ አቶ ሞገስ መንግስቱ በበኩላቸው  ወጣቶቹ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸውና በዚህም ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ወጣቶች ገንዘብ አሰባስበው ባደረጉላቸው የምሳ ግብዣና የብርድ ልብስ ድጋፋ መደሰታቸውን በመግለጽ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ደግሞ እማሆይ የልፍኝ ደረሰ ናቸው።

በዝግጅቱ የተገኙት የከተማው አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ተስፋሁን ሲሳይ የወጣቶች በጎ ተግባር ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ተስፋ ያጫረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ የድሃ ድሃ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት ቤቶችን ገንብቶ ለተወሰኑት የሰጠ ቢሆንም ቀጣይ በቋሚነት የሚታገዙበትን  ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 

በዝግጅቱ ስነስርዓት የኃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 1/82010 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት በአውሮፓ ከተሞች በተካሄዱ የማራቶን ውድድሮች አሸንፈዋል።

 በጣልያን ሮም በሴቶች ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ረሂማ ቱሳ ሁለት ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ46 ሴኮንድ አሸናፊ ሆናለች። አትሌቷ የማራቶን ውድድሩን ለሶስት ተከታታይ ዓመት በማሸነፍ የፍሬህይወት ዳዶን ታሪክ መጋራት ችላለች።

 በተጨማሪም ረሂማ የገባችበት ሰዓት በርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቷ ሆኖ ተመዝግቦላታል።

 የባህሬኗ ዳሊያ አብዱልቃድር ሁለት ሰዓት ከ26 ደቂቃ ከ46 ሴኮንድ ሁለተኛ፤ ኬንያዊቷ አሊስ ቼፕኬምቦይ ኪቦር ሁለት ሰዓት ከ28 ደቂቃ ከ19 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

 አትሌት ጀሚላ ዎርቴሳ፣ አትሌት መሰራ ሁሴን፣ አትሌት ጎደፋይ አፈራና አትሌት ብዙአየሁ ሞሐመድ በቅደም ተከተል ከአምስት እስከ ስምንት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

 በወንዶች ኬንያዊው ኮስማስ ቢሬች፣ ባህሬናዊው ኢብራሂም አብዶ አብዲና ሌላኛው ኬንያዊው ፖል ካንጎጎ ከአንድ እስከ ሶስት ገብተዋል።

 አትሌት ግርማይ ብርሃኑ አምስተኛ፣ አትሌት ደጀኔ ደበላና አትሌት ዳንኤል አስጨንቅ ሰባተኛና ስምንተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

 በጀርመን ሀኖቨር ማራቶን በወንዶች ኢትዮጵያዊው አትሌት ሰቦቃ ንጉሴ ሁለት ሰዓት ከዘጠኝ ደቂቃ ከ44 ሴኮንድ አሸናፊ ሆኗል።

 ኬንያዊው ማይክል ኩንዩጋ ሁለት ሰዓት ከ10 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ ሁለተኛ ሲወጣ፤ ሌላኛው ኬንያዊ ዱንካን ኮኤች ሁለት ሰዓት ከ10 ደቂቃ ከ19 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

 በሴቶች ኬንያዊቷ አግነስ ኪፕሮፕ፣ ካዛኪስታናዊቷ አክማራል ሜርማንና ጀርመናዊቷ አይዳ ስታልሁት በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

 በጣልያን የሚላን ማራቶን በወንዶች ኢትዮጵያዊው አትሌት ሰይፈ ቱራ ሁለት ሰዓት ከዘጠኝ ደቂቃ ከአራት ሴኮንድ አሸናፊ መሆን ችሏል።

 ኬንያውያኖቹ ጀስቱስ ኪፕኮስጄይና በርናባስ ኪፕቱም ሁለተኛና ሶስተኛ ወጥተዋል።

 በሴቶች ኬንያውያኖቹ ሉሲ ካቡ፣ ቪቪያን ጄሮኖ ኪፕላጋትና ሸይላ ኬፕኬች ከአንድ እስከ ሶስት በመውጣት የበላይነቱን ይዘዋል።

 በፓሪስ ማራቶን ኬንያውያኖቹ ፓል ሎያንጋታ፣ ማቲው ኪሶሪዮና አርነስት ንጌኖ ከአንድ እስከ ሶስት ሲወጡ ኢትዮጵያዊው አትሌት ይታያል አጥናፉ አራተኛ ደረጃን ይዟል።

 በሴቶች ኬንያውያኖቹ ቤትሲ ሳይናና ቼፕጌቲች አንደኛና ሁለተኛ ሆነው ተከታትለው ሲገቡ ኢትዮጵያውያኖቹ ጉሉሜ ጫላና አሽቴ በቀለ ሶስተኛና አራተኛ ወጥተዋል።

 በቱርክ ኢስታንቡል የግማሽ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች አሸንፈዋል።

 በወንዶች ኢትዮጵያዊው ዋለልኝ አምደወርቅ 59 ደቂቃ 50 ሴኮንድ ሲያሸንፍ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አሰፋ ተፈራ አንድ ሰዓት ከዜሮ ዜሮ ሴኮንድ ከሰባት ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ ወጥቷል።

 በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ አባብል የሻነህ አንድ ሰዓት ከስድስት ደቂቃ ከ22 ሴኮንድ አንደኛ፤ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ሮዛ ደረጀ አንድ ሰዓት ከሰባት ሴኮንድ ከዜሮ ዜሮ ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች።

 ኬንያዊቷ ዲያና ኪፕዮኪ   አንድ ሰዓት ከሰባት ሴኮንድ ከ55 ማይክሮ ሴኮንድ ሶስተኛ ወጥታለች።

 ኢትዮጵያውያኖቹ እታገኝ ወልዱና ዘርፌ ልመንህ አምስተኛና ስድስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

 በአጠቃላይ ትናንት የተካሄዱት ሁሉም ውድድሮች በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር እውቅና የተሰጣቸው ናቸው።

 

Published in ስፖርት

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን