አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Sunday, 08 April 2018

ጅግጅጋ መጋቢት 30/2010 በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት የበርካታ ዜጎችን ህይወት ነጥቋል ፤ ብዙዎች ተወልደው ካደጉበት ቀዬ እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።

ድርጊቱ ኢትዮጵያዊያንን ያሳዘነ "ለምን እንዲህ ሆነ? የአብሮነት ትስሰራችን፤ ለዘመናት የተገነባው ፍቅራችንና መተሳሰባችን ወዴት ገባ? ምንስ ነካን?" በማለት እንዲጠይቁ ያደረገ ነው።

የሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በውይይቱ ወቅት አጽንኦት የሰጡት ሀሳብ፤ የግጭቱ መንስዔ የሌላ ሶስተኛ አካል ክፉ ሀሳብ የመራው ክስተት መሆኑ ነው።

ድርጊቱን በቁጭት እያነሱ፤ በመካከላቸው ወንድማማችነትና የአብሮነት ታሪካቸውን እያስታወሱ ፤ ችግሩን የመፍታት አቅማቸውን በመተማመን ተስፋ ያደርጋሉ።

የሕዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት የሚያናጉ የሰላም እጦቶች ከወዴት መጡ ምንጫቸው ምን ይሆን?" በማለት ነው የጠየቁት የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጅግጅጋ ተገኝተው ባወያዩበት ወቅት።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበዓለ ሲመታቸው ዕለት ባደረጉት በንግግር ''መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ የእርቅና የይቅርታ ጊዜ ነው'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት አንገት የሚያስደፋ መሆኑን ነው የገለጹት።

የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በእለቱ የተለያዩ ሀሳቦችን ሰንዝረዋል::

30222290_1882287358469798_2430060116318355456_n.jpg

የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እንደገለጹት ቀድሞውኑ መከሰት ያልነበረበት ችግር መሆኑና በቶሎ እርቀ ሰላም እንዲወርድ ተግተው እንደሚሰሩ ይናገራሉ።

ይህ ክፉ ክስተት በሰላማዊ መንገድ ተፈቶ የተፈናቀሉትም ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው ሰላማዊው ኑሮ እንዲቀጥሉ የበኩላቸውን ለመወጣት ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በበኩላቸው፤ ስራ በጀመሩ በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ ስፍራው ያቀኑት ሰላምን ከማስፈን በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ባለመኖሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በሁለቱም ህዝብ በኩል የዳበረና የትኛውንም ዓይነት ግጭት መፍታት የሚያስችል የሽምግልና ባህል መኖሩን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሁሉም ሰላምን ለማምጣትና ለማረጋገጥ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅረበዋል።

ስለሆነም ችግሩ በአፋጣኝ ተፈትቶ ሁሉም ወደ ጋራ ልማት በመግባት እንደሚሰሩም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ እና የሱማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ሙሀመድ ስለችግሩ ተወያይተው በራሳቸው ለመፍታት የየክልላቸው መንግስትና ህዝቦችን ዝግጁነት ጠቁመዋል።

ይሄንንም ለማከናወን የሚያስችል ባህላዊ እሴቶች እንዳሉ ጠቁመዋል።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመጀመሪያ የስራ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ትናንት ጅግጅጋ አውሮፕላን ጣቢያ ሲደርሱ በርካታ ህዝብ ደማቅ አቀባበል አድርጎላቸዋል። በአቀባበሉም በርካታ የጅግጅጋ ነዋሪዎች ልዑካን ቡድኑን ግራና ቀኝ ሆነው አጅበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት በዚሁ ጉብኝት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ከፍተኛ አመራር አካላት ተገኝተዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 30/2010 በከተማዋ ከትንሳዔ በዓል ጋር ተያይዞ እስካሁን ምንም አይነት የእሳት አደጋ አለመከሰቱን የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጣር ባለስልጣን አስታወቀ።

በመላ አገሪቱ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የትንሳዔ በዓል እየተከበረ ይገኛል።

በተመሳሳይ ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ በአንድ ሰው ከባድና በአምስት ሰዎች ቀላል የትራፊክ አደጋ ከመድረሱ ውጭ በህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለኢዜአ እንደተናገሩት ከበዓሉ ጋር ተያይዞ በከተማዋ እስካሁን ድረስ  ምንም አይነት የእሳት አደጋ አልተከሰተም።

ባለስልጣኑ አደጋዎች እንዳይከሰቱ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የግንዛቤ መስጫ ስራ በስፋት መስራቱን አስታውሰዋል።

ድንገት አደጋ ቢከሰት በ939 ነጻ የስልክ መስመር በመደወል ለባለሰልጣኑ ማሳወቅ እንደሚገባም አቶ ንጋቱ አስገንዝበዋል።

በሌላ በኩል ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ያለው የትራፊክ እንቅስቃሴም ሰላማዊ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግነኙነት ባለሙያ ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ እንደተናገሩት አንድ ተሽከርካሪ ከባቡር መስመር አጥር ጋር ተጋጭቶ አንድ አደጋ ከማድረሱ ውጭ ሰላማዊ የትራፊክ እንቅስቃሴ መኖሩን ገልጸዋል።

በአደጋው አንድ ሰው ከባድና አምስት ሰዎች ቀላል አደጋ እንደደረሰባቸው ኢንስፔክተር አሰፋ ተናግረዋል።

በዓሉን በሰላም ለማክበር አሽከርካሪዎች በጥንቃቄ እንዲሽከረክሩና ጠጥተው ከማሽከርከር እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

እግረኞች ራሳቸውን ከትራፊክ አደጋ መጠበቅ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።  

Published in ማህበራዊ

ሱማሌ ክልል መጋቢት 29/2010  በቅርቡ በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ ህዝቦችን ያጋጨው ያልተገባ ክስተት በአፋጣኝ በእርቀ ሰላም እንዲፈታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ።

በዛሬው ዕለት በሱማሌ ክልል የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከክልሉ ህዝብ ጋር ውይይት እያካሄዱ ነው።

በውይይቱ  ላይ ባደረጉት  ንግግር በቅርቡ የኦሮሚያና ሱማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት "ያልተገባ፣ ከኢትዮጵያዊነት ባህል ያፈነገጠና የሁላችንንም አንገት ያስደፋ የሽንፈት ታሪካችን ነው" ብለዋል።

በግጭቱ ሁለቱም ወገን ተሸናፊ እንደነበር የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ያለፈውን ችግር የምንቋቋምበት የዳበረ የአብሮነት ባህል እንዳለም ጠቁመዋል።

ከአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ የሱማሌ ጎሳ ጋራዶችና የሃይማኖት አባቶች በሽምግልና ሰላም ለማውረድ የዳበረ ባህል እንዳላቸው ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሁሉም በጋራ ሰርቶ ችግሩን በአፋጣኝ እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል።

እነዚህን የአብሮነት እሴት በመጠቀም በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው የሚመለሱበት ቀን "ሁላችንንም ሊናፍቀን ይገባል" ሲሉ ነው የገለጹት።

ይህ እንዲሆን ደግሞ ሁሉም የሚጠበቅበትን መስራት እንደሚገባው አመልክተው፤ የፌዴራል መንግሥትና እርሳቸውም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሀሙድ በበኩላቸው፤ ክስተቱ እንደሚያሳፍራቸውና በወቅቱም የደረሰውን ጉዳት አለመከላከልም እንዳስቆጫቸው ተናግረዋል።

በቀጣይም የሁለቱን ወንድማማቾች የቀደመ ሰላምና አብሮነት ለመመለስ የክልሉ መንግስት ያለውን ዝግጁነት ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሾሙበት ጥቂት ቀናትም ወደ ክልሉ በመምጣት የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታትና ለአገር አንድነት ያላቸውን ዝግጁነትን እንደሚያሳይም ጠቁመዋል።

ዶክተር አብይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ተብለው በተሰየሙበት ዕለት ባደረጉት የመጀሪያው ንግግራቸው "መጪው ጊዜ በኢትዮጵያችን የፍቅርና የይቅርታ ጊዜ ነው" ማለታቸው ይታወሳል። 

Published in ፖለቲካ

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን