አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Saturday, 07 April 2018

ሀዋሳ መጋቢት 29/2010 በዓሉ የደስታና የተስፋ በመሆኑ ለሃገር ሰላም በማሰብ ማክበር እንደሚገባ  የኃይማኖት አባቶች አሳሰቡ፡፡

የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ መልዕክታቸውን  ያስተላለፉት የሲዳማ፣ ጌዲኦ ዞኖችና አማሮና ቡርጂ ወረዳዎች ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል " የትንሳኤ በዓል የአብሮነትና የፍቅር  በመሆኑ በጋራ መደሰት ያስፈልጋል " ብለዋል፡፡

በዓሉ ከመንፈሳዊ ስነ-ስርዓቱ ባለፈ ለሀገር ሰላም በመጸለይና በማሳብ  ከመቼውም ጊዜ በላይ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

"ለሃገር ሰላም ጠንቅ የሆነው ሙስናና አለአግባብ መክበር ነው ፤ ሙስናን  የሚጸየፍና ከሃገሩ የማይሰርቅ ትውልድ ልንፈጥር ይገባል " ብለዋል፡፡

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም ገና በወጣትነት እድሜ ሃገሪቱን የመምራት ሃላፊነት መቀበላቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡

የመጀመሪያ ንግግራቸው የሃገሪቱን ቀጣይ ተስፋ ያመላከተ በመሆኑ ያነሷቸው ትላልቅ ጉዳዮች በገቡት ቃል ልክ ተግባራዊ እንዲሆኑ ሁሉም መተባበር እንዳለበት አቡነ ገብርኤል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በሃዋሳ ሃገረ ስብከት የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹእ አቡነ ሮቤርቶ ቤርጋማሲኪ በበኩላቸው በዓሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች መዳን የከፈለውን መስዋዕነት በማስታወስና አስተምህሮቱን በመከተል የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት መከበር አለበት ብለዋል፡፡

"እርስ በርስ በመከባበርና በአንድነት አዲስ ከተመረጡት ጠቅላይ ሚኒስቴር ጋር መስራት ይኖርብናል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ህብረት ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ መጋቢ አስፋው አሻግሬ  ትንሳኤ በክርስቶስ ሞት እርቅ የወረደበት  መሆኑን አውስተዋል፡፡

"በዓሉ ሲከበር ከሰዎች ሁሉ ጋር በእርቅና በይቅርታ መከበር አለበት "ያሉት መጋቢ አስፋው የተቸገሩትን መርዳት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት ትልቅ ሃገር እንደመሆኗ በቅርቡ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የመጡት ዶክተር አብይ አህመድ እኩልነትና ፍትህ በሃገሪቱ እንዲሰፍን መስራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡

ሃገሪቱን  የመምራት ኃላፊነት ከተሰጣቸው መሪዎች ጋር መስራት ደግሞ የህዝቦች ግዴታና ኃላፊነት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

መጋቢ አስፋው እንዳመለከቱት በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች በእርቅ እንዲፈቱ እየሰሩ ናቸው፡፡

የኃይማኖት አባቶቹ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

 

 

Published in ማህበራዊ

መቀሌ መጋቢት 29/2010 በትግራይ ክልል ከድህነት ወለል በታች የሚኖረውን ህዝብ ቁጥር ለመቀነስ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር ለማካሄድ እየተሰራ መሆኑን  የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ።

በተለያዩ ተቋማት በምርምርና ጥናት ሥራዎች ከተሰማሩ የክልሉ ተወላጅ ምሁራን ጋር በመቀሌ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የምክክር መድረክ ተጠናቋል፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕስ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ከምሁራን ጋር መግባባት ላይ የተደረሰባቸውን ጉዳዮች አስመልክተው ትላንት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

እንደምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ፣ በክልሉ በየዓመቱ በተከናወኑ የልማት ሥራዎች የድህነት ምጣኔው እየቀነሰ መጥቷል፡፡

"ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ባካሄደው የጥልቅ ተሀድሶ ግምገማ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራና በሌሎች የልማትና የአገልግሎት ዘርፎች የሚስተዋሉ ችግሮች እንዳሉ ታውቋል"  ብለዋል፡፡

በግምገማ ወቅት የተለዩ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ጥልቅ ጥናትና ምርምር በማድረግ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይ በክልሉ ያለውን የድህነት ምጣኔ ለማውረድና የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራውን በጥናትና ምርምር ለመደገፍ በአሁኑ ወቅት 15 የጥናትና ምርምር መነሻ ሀሳቦች ተለይተው ጸድቀዋል።

እንደዶክተር ደብረጽዮን ገለጻ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን የሚያከናውኑ 62 ከአገር ውስጥና 25 በአሜሪካና አውሮፓ የሚገኙ የክልሉ ተወላጅ ተማራማሪዎች ተደልድለዋል፡፡

የምርምር ሥራዎቹ በግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ በጤናና ትምህርት ጥራትና አገልግሎት አሰጣጥ፣ በቱሪዝም፣ በመልካም አስተዳደርና መአድን ዘርፎችና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ሚድያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፉም የህዝብ አገልጋይ በሚሆንበት መንገድ እንዲሰራ ማድረግ ትኩረት ከተደረገባቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑንም ዶክተር ደብረጽዮን ገልጸዋል፡፡

የጥናትና ምርምር ሥራዎች ውጤት ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ እስከ ሦስትኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የሚያገለግሉ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

በግብርና ዘርፍ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል የጥናትና ምርምር መነሻ ሀሳብ በመድረኩ ላይ ካቀረቡ ምሁራን መካከል ዶክተር ጉዑሽ ብርሀነ በጥናታቸው የክልሉን መልክአምድርና ከባቢያዊ ጸጋ መሰረት ያደረገ ሥራዎችን ለማካሄድ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምክክር መድረክ  በርካታ ጠቃሚ ሀሳቦች ከመገኘታቸው ባለፈ ምሁራን ለክልላቸው እድገት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ሲሉ ዶክተር ጉዑሽ አያይዘው ገልፀዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ባህርዳር መጋቢት 29/2010 ለመጪው የመኽር ወቅት ግብአት 600 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እየተከፋፈለ መሆኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን  ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የግብዓት አቅርቦትና ስርጭት ቡድን መሪ አቶ አያሌው ያረጋል ለኢዜአ እንደገለጹት እየተከፋፈለ ያለው ማዳበሪያ በምርት ወቅቱ ከሚያስፈልገው አንድ ሚሊዮን 200ሺህ ኩንታል ውስጥ ነው፡፡

እስካሁንም 120 ሺህ ኩንታል ለአርሶ አደሩ ደርሶ ቀድሞ ለሚደርስ ሰብል ልማት በግብአትነት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

 ቡድን መሪው እንዳሉት ባለፈው ዓመት ማዳበሪያ በወቅቱ ባለመቅረቡ በእርሻ ስራ ተፈጥሮ የነበረው አሉታዊ ተፅእኖ ዘንድሮ እንዳይደገም በተያዘው አቅጣጫ መሰረት ወቅቱን ጠብቆ እየቀረበ ነው።

ማዳበሪያው የቀረበው  የአርሶ አደሩን ፍላጎት መሰረት በማድረግ መሆኑን  ተናግረዋል።

 ቀሪውን ማዳበሪያ በወቅቱ ከወደብ ወደ ዞኑ የማጓጓዙ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ነው ቡድን መሪው ያስረዱት።

 በዞኑ ጃቢጠህናን ወረዳ የማና ውስጠጉልት ቀበሌ አርሶአደር ብርሃኔ ካሴ ባለፈው ዓመት ማዳበሪያ በወቅቱ ባለመቅረቡ ቀድሞ ለሚዘራ ሰብል  እጥረት በማጋጠሙ ተቸግረው እንደነበር አስታውሰዋል።

 በተያዘው  ዓመት ግን ቀድሞ መግባት በመጀመሩ ያላቸውን ሶስት ሄክታር መሬት ስምንት ኩንታል ማዳበሪያ ገዝተው ለመጠቀም ከወዲሁ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 ማዳበሪያ ዘንድሮ ለየህብረት ስራ ማህበራት ቀድሞ በመድረሱ 11 ኩንታል ለመግዛት ቀጠሮ መያዛቸውን የተናገሩት ደግሞ በደንበጫ ወረዳ በእግዚአብሔር አብ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር አብራራው ፈንቴ ናቸው።

በወንበርማ ወረዳ የማርቁማ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ቸኮል ሁሉቃ በበኩላቸው የራሳቸውንና የተከራዩትን ሰባት ሄክታር መሬት በበቆሎ፣ስንዴና በርበሬ ሰብሎች ለማልማት የእርሻ ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 የተሻለ ምርት ለማግኘትም 20 ኩንታል ማዳበሪያ ሰሞኑን እጅ በእጅ ለመግዛት ዝግጅት ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል። 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 29/2010 በአፍሪካ ህዝቦች መካከል ልዩነትንና ጥላቻን የሚያስፋፉ ድርጊቶችን ለመከላከል የአህጉሪቷ ወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ መሓማት አሳሰቡ።

 እ.ኤ.አ በ1994 በሩዋንዳ የተከሰተውን የጅምላ ጭፍጨፋ በማስመልከት ዛሬ በአፍሪካ ኅብረት 24ኛ ዓመት የመታሰቢያ መርኃ ግብር ተካሄዷል።

 በሩዋንዳ በተከሰተው የጅምላ ጭፍጨፋ በመቶ ቀናት ውስጥ ከ800 ሺ በላይ ዜጎች ህይወታቸው አልፏል። ከነዚህም ሲሶ የሚሆኑት ህጻናት መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።   

 የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር  ሙሳ ፋቂ መሓማት ባደረጉት ንግግር "በሩዋዳ የተከሰተውን የጅምላ ጭፍጨፋ በማሰብ ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ ጥፋት እንዳይደገም መንቃት አለብን"

ኮሚሽነሩ በአፍሪካ የተለያዩ ዓይነት ግጭቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ለዚህም ደግሞ በርካታ የመከላከያ ሥልቶች ገቢራዊ ቢሆኑም የአተገባበር ክፍተቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

 በአህጉሪቱ ወደ ጭፍጨፋና ግጭቶች የሚያመሩ አመለካከቶችና ድርጊቶችን ለመከላከል  የወጡ ሕጎችን ማክበርና ማስከበር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

 በህዝቦች መካከል  ከአንድነት ይልቅ ጥላቻን የሚያስፋፉ አመለካከቶች ለመመከት ወጣቶች የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ነው የጠቆሙት። 

 በኢትዮጵያ የሩዋንዳ አምባሳደር ሆፕ ቱሙኩንዳ በተመሳሳይ በሩዋንዳ የተከሰተው የጅምላ ጭፍጨፋ በሀገሪቱም ሆነ በአፍሪካ ላይ "ጥቁር ጥላ ያጠላ ታሪክ" መሆኑን ገልጸዋል።

 በመሆኑም ማንኛውም ቡድን ወይንም ግለሰብ እንዲህ ያለውን ኢ - ሰብዓዊ ድርጊት ለመፈጸም "የሚገፋፋ ምክንያትን አልያም ደግሞ አሉታዊ አመለካከቶችን መታገል አለበት" ብለዋል።  

 በአፍሪካውያን ያለው የተለያየ ማንነት "ጠንካራ አገር ለመገንባት አቅም ይፈጥራል እንጂ ለመለያየት ምክንያት የሚሆንበት ሁኔታ የለም" በማለት ነው ያሳሰቡት።

 በአፍሪካ 'የተለያየ ጎሳ፣ ኃይማኖትና ቋንቋ አለ፤ ይህም ስጦታ ነው፤ ይህንንም በአግባቡ መጠቀም አለብን' የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮች፣ የኃይማኖት አባቶችና የተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።

 

 

 

Published in ፖለቲካ

ሀዋሳ መጋቢት 29/2010 የሀዋሳ ሃይቅ  ዓሳ ምርት በተለያዩ ምክንያቶች እየቀነሰ መምጣቱን  ዓሳ አቅራቢዎችና ተጠቃሚዎች ገለጹ፡፡

 የሃዋሳ ሃይቅ ሁለገብ ዓሳ አቅራቢዎች ማህበር ሊቀ መንበር አቶ ዳዊት አብርሃም ለኢዜአ እንዳሉት ለሀይቁ እንክብካቤ ማነስና ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር የተያያዙ ችግሮች የሚፈጥሩት ተጽእኖ ለምርቱ መቀነስ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

 " በቀን  እስከ 4ሺ ዓሳዎችን ከሃይቁ እያወጡ እንደየመጠናቸው በአማካይ ከ10 ብር እስከ 25 ብር ለደንበኞቻቸው ቢሸጡም ከዓመታት በፊት የምርቱ መጠን  ከዚህ ቁጥር የተሻለ ይገኝ ነበር "ብለዋል፡፡

 የፊደል መዝናኛ ማህበር አባል ወጣት ዮሐንስ አየለ በበኩሉ የምርት መጠኑ በመቀነሱ  አስጋሪዎች የሚያቀርቡላቸው ዓሳዎች ትንንሽ እየሆኑ መቸገራቸውን ተናግሯል፡፡ 

 የዓሳ ምርት በቁጥርም በመጠንም በመቀነሱ ደንበኞቻቸው የጥራትና የዋጋ ቅሬታ እንደሚያቀርቡ ጠቁሟል፡፡

 በመንጠቆ የሚያጠምዱ ዓሳ አጥማጆች መኖራቸውም በዓሳ ምርት ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ 

ዓሳ ተጠቃሚዎችና  የመመገብ ባህል እያደገ ቢመጣም ፍላጎትና አቅርቦቱ የተመጣጠነ አለመሆኑን የገለጹት ደግሞ የሃዋሳ ሳውዝ ኢንተርናሽናል ሆቴል ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ሃሰን ሙክታር ናቸው፡፡

በዚህም ምክንያት በዓሳ ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ ተጠቃሚዎችን ቅር እያሰኘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 የማህበራት  ዓሳ ምርት አቅርቦትና ጥራት ችግር ስላለበት ከዝዋይ፣ መቂ፣ አርባምንጭና አጎራባች አከባቢዎች እንደሚያስመጡም አመልክተዋል፡፡

 በሆቴል ስራ የተሰማሩት አቶ ዳንኤል ደስታ እንዳሉት  የዓሳ ምርት አቅርቦት እየቀነሰ ነው፡፡

 በቀን እስከ 450 ዓሳዎችን ከማህበራት ገዝተው ከ20 እስከ 25 ብር እንደሚሸጡም አመልክተዋል፡፡

 የሀዋሳ ከተማው ነዋሪው  አቶ አሸብር ግርማ ከሶስት ዓመታት በፊት ከሰባት እስከ አስራ አምስት ብር የሚከፈልበት ዓሳ አሁን   እስከ  60 ብር  መድረሱን ተናግረዋል፡፡

 ተገቢው የዓሳ ምርት እንዲኖር የሀይቁ ሀብት በሚመለከተው አካል  ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

 በሃዋሳ ከተማ አስተዳዳር እንሰሳትና ዓሳ ሃብት መምሪያ የኤክስቴንሽን ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ብንቤ ስለጉዳዩ ተጠይቀው ከዚህ በፊት በዓመት ከ800 ቶን በላይ የነበረው የሀይቁ ዓሳ የማምረት አቅም  አሁን ከግማሽ በታች መውረዱን ገልጸዋል፡፡

 በአሁኑ ወቅት እስከ 390 ቶን ዓሳ ብቻ በዓመት እየተመረተ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በሀይቁ ዙሪያ የሚሰሩ መስኖዎች ተፅዕኖና፣ ከከተማና ከኢንዱትሪዎች የሚለቀቁ ቆሻሻዎችና ኬሚካሎች ለዓሳ ምርት መቀነስ ዋነኛ ምክንያች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የህገ ወጥ አስጋሪዎች መበራከትና ያልደረሱ ዓሳዎችን ማስገርም ለችግሩ ሌላው ምክንያት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

 በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲና በሌሎች ባለድርሻ አካላት የተካሄዱ  ጥናቶችን መነሻ በማድረግ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ  መሆኑን አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡

ለግንባታ ስራና ለከተማ ውበት አገልግሎት ከሀይቁ የሚወሰደው ውሃ እንዲቆም መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡

" በዋናነት በሀይቁ አካባቢ የሚከናወኑ የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በማጠናከር ከደለል ለመከላከል እየሰተራ ነው"ብለዋል፡፡

ከሀገሪቱ የውሃ  አካላት በዓመት ማምረት ከሚቻለው ከ51 ሺህ ቶን ዓሳ ውስጥ የደቡብ ህዝቦች ክልል ከ17 ሺህ በላይ ቶን በመሸፈን ድርሻ እንዳለው ጥናታዊ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

180 በላይ የዓሳ ዝሪያዎች በሀገሪቱ እንደሚገኙና ከእነዚህ ውስጥ 30 በመቶው በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 29/2010 በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጊዜያዊ የእስረኞች ማቆያ ወይም በተለምዶ "ማዕከላዊ" ተብሎ የሚታወቀው የወንጀል ምርመራ ማዕከል ተዘጋ።

የፌደራል የወንጀል ምርመራ ጽሕፈት ቤት የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ አቶ ነጋ አደሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ካለፉት ስርዓቶች ጀምሮ በማዕከላዊ የተለያዩ የወንጀል ምርመራዎች ሲከናወኑበት ቆይቷል።

በመሆኑም ማህበረሰቡ በምርመራ ማዕከሉ ከነበረው ኢ ሰብአዊ አያያዝ ጋር በማዕከላዊው እስር ቤት ላይ ጥላቻ አሳድሯል።

ይህን የህብረተሰቡ የጥላቻ አመለካከት ከመቀየር አኳያ ማዕከሉን እንደሚዘጋ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ቀደም ሲል ውሳኔ ማሳፉ ይታወሳል።

"ውሳኔውን ሁላችንም የሰማነው ጉዳይ ነው" ያሉት ኃላፊው፤ ይህን ውሳኔ ተግባራዊ በማድረግ ከመጋቢት 28 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ማዕከሉ እንዲዘጋ መደረጉን አረጋግጠዋል።

በዚህም እስር ቤቱ ይሰጥ የነበረውን እስረኞችን የማቆየትና የመመርመር ስራም ከትናንት ጀምሮ ሙሉ በሙሉ አቁሟል።

እዚያ ውስጥ  የነበሩ ተጠርጣሪ እስረኞችም ወደ አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲዘዋወሩ መደረጉንም ገልጸዋል።

የተጠርጣሪዎች ቤተሰቦች ለመጠየቅ ከፈለጉ አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት በመሄድ መጠየቅ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

የወንጀል ምርመራ ጽሕፈት ቤት ለጊዜው ካዛንቺስ ዮርዳኖስ ሆቴል አጠገብ ወደሚገኝ ቢሮ መዘዋወሩን ጠቁመው፤ ኅብረተሰቡ ማንኛውንም ጥቆማ ለማቅረብ እንደሚችል አመልከተዋል።

አዲሱን የምርመራ ቢሮውን የዝውውር ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ ይፋ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

Published in ማህበራዊ

ማይጨው መጋቢት 29/2010 በትግራይ ክልል በመጪው መኽር ወቅት ከ1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር ለመሸፈን ዝግጅት እየተደረገ ነው።

 በዝግጅቱ ለ400 የግብርና ባለሙያዎች ለአምስት ቀናት በማይጨው ከተማ የተሰጠው ስልጠና ተጠናቋል።

 የትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የእርሻ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የአዝርዕት ልማትና አፈር ለምነት ማሻሻያ ቡድን መሪ አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ እንደገለጹት በክልሉ በመጪው የመኽር ወቅት 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት ግብ ተይዟል።

 " በክልሉ በሚገኙ ስድስት ዞኖች አርሶ አደሩን በቡድን በማደራጀት ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላና ሰሊጥ በኩታ ገጠም ማሳ ላይ ለማልማት ዝግጅት ተደርጓል " ብለዋል ።

 በመኽር ወቅቱ ለምርት ማሳደጊያነት የሚያስፈልገው ከ300 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና 52 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለወረዳዎች እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

 በተጨማሪም በአርሶ አደሩ ደረጃ  የተመረተ  ምርጥ ዘር አሰባስቦ በማሰራጨት ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ አቅጣጫ መያዙን አመላክተዋል ።

 "ክልሉ ለሰብል ልማት ተግዳሮት የሆነውን የአፈር እርጥበት ችግር ለመፍታት በምርት ወቅቱ የእርሻ ልማት ፓኬጅ ተግባራዊ ይደረጋል " ብለዋል ።

 እንደ ቡድን መሪው ገለጻ በምርት ወቅቱ ከመደበኛው የሰብል ልማት ጎን ለጎን የዝናብ እጥረትን ተቋቁመው በአጭር ጊዜ ለምርት በመድረስ ምርታማነትን የሚያሳድጉ አዳዲስ ምርጥ ዘሮችን የማባዛት ሥራ ይካሄዳል፡፡

 "ለግብርና ባለሙያዎቹ በእርሻ መሬት ዝግጅት፣ በመስመር መዝራት፣ በማዳበሪያና ምርጥ ዘር አጠቃቀምና በተሻሻሉ የግብርና አሰራሮች የንድፍ ሃሳብና የተግባር ስልጠና ተሰጥቷቸዋል " ብለዋል፡፡

 ባለሙያዎቹ ከስልጠናው ያገኙትን ግንዛቤ ወደ አርሶ አደሩ በማውረድ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል። 

 የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ፍስሃ በዛብህ እንደገለፁት በክልሉ የአርሶ አደሩን የግብርና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ግንዛቤ በማሳደግ በሰብል ልማት ዘርፍ የተሻለ ለውጥ ማምጣት የግብርና ባለሙያዎች ድርሻ መሆኑን አስገንዝበዋል።

 በክልሉ የሚገኙ የሰርቶ ማሳያዎችና የገበሬ ማሰልጠኛ ማዕከላትን በመጠቀም የሙሉ ፓኬጅ ትግበራን በሁሉም አርሶ አደሮች ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ ስልጠና እንደሚሰጥም አመልክተዋል።

 በክልሉ ስድስት ዞኖች በመጪው የመኽር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከሚለማው መሬት 26 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ዕቅድ መያዙን ነው የተናገሩት።

 ከሰልጣኞች መካከል የአፅቢ ወንበርታ ወረዳ የስነ-አዝርዕት ባለሙያ ወይዘሪት ልዕልቲ መሀሪ በሰጡት አስተያየት "ስልጠናው የተሻሻሉ ሰብል ዝርያዎችና የግብርና አሰራሮችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚቻልበት መንገድ ላይ ተጨማሪ አቅም ፈጥሮላቸዋል ።

 እንደ ባለሙያዋ ገለጻ ያገኙትን ግንዛቤ ወደ አርሶ አደሩ ለማካፈልና በቅርበት የሙያ እገዛ ለማድረግ ተዘጋጅተዋል ።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 29/2010 እንግሊዝ በጦርነት ወቅት ከመቅደላ የወሰደቻቸውን የኢትዮጵያ ቅርሶች ለማስመለስ መንግስት የተጠናከረ ጥረት እያደረገ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

"ቅርሶቹ በረጅም ጊዜ ውሰት ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው" እየተባለ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚወራው ትክክለኛ ያልሆነና መንግስት የማያውቀው መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ቅርሶቹ በአጼ ቴዎድሮስ  ዘመነ መንግስት ኢትዮጵያና እንግሊዝ መቅደላ ላይ ባካሄዱት ጦርነት ወቅት የተወሰዱ ናቸው።

ይህን በማስመልከት የባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው ንብረትነታቸው የኢትዮጵያ የሆኑ ከአስር በላይ ታቦታት፣ ከአምስት መቶ በላይ ታሪካዊ መጻህፍት እንዲሁም ሌሎች ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች "በእንግሊዛዊያን ተወስደው በሙዚየሞችና ግለሰቦች እጅ ተይዘው ይገኛሉ" ብለዋል።

እነዚህ ቅርሶች ንብረትነታቸው የኢትዮጵያ በመሆኑ ለማስመለስ የኢትየጵያ መንግስት ለእንግሊዝ መንግስት ጥያቄ አቅርቦ ድርድሮችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ከመቅደላ የተወሰዱት ቅርሶች በእንግሊዝ አገር በሚገኘው ቪክቶሪያ አልበርት ሙዚየም ለአንድ ዓመት ለተመልካች ክፍት መደረጋቸውንም ዶክተር ሂሩት ተናግረዋል።

ቅርሶቹ ለእይታ መቅረባቸው የኢትዮጵያን ባህል፣ ታሪክና ወግ ለዓለም ከማስዋወቁ ባለፈ ጎብኝዎቹ፤ "ለዕይታ የቀረቡት ቅርሶች የኢትዮጵያ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ እንዲያገኙ እድል ይፈጥራል" ብለዋል።

በተመሳሳይ "የእንግሊዝ መንግስት እነዚህን ቅርሶች በረጅም ጊዜ ውሰት ወደ ኢትዮጵያ ሊያመጣ ነው" እየተባለ የሚናፈሰው ወሬ ትክክለኛ አለመሆኑን ገልጸዋል ሚኒስትሩ።

የቪክቶሪያ አልበርት ሙዚየም ሃላፊ ቅርሶችን ለኤግዚቢሽን እይታ በከፈቱበት ጊዜ ያነሱት "የግል ሃሳብ እንጅ የእንግሊዝና የኢትዮጵያ መንግስት አቋም አይደለም" ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ሚኒስቴሩ ቅርሶች በውሰት ወደ አገሪቷ እንዲመጡ ያደረጉት ውይይት አለመኖሩንና ይሄም ሊሆን እንደማይችል ገልጸዋል።

ቅርሶች ከተወሰዱበት መቅደላ አካባቢ እስከ ቋራ ድረስ ያለውን ስፍራ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በጎንደር ዩኒቨርስቲና በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም  ቢሮ በኩል ጥናቶች እየተደረጉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

የአጼ ቴዎድሮስ 200ኛ ዓመት የልደትና 150ኛ ዓመት የሙት ዓመት በዓል አከባበር ከሚያዝያ 2 እስከ 8 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር የሚዘከር መሆኑንም ተናግረዋል።

የእንግሊዝና የኢትዮጵያ ጦርነት በ1868 ዓ.ም መቅደላ ላይ መካሄዱ ይታወሳል።

Published in ማህበራዊ

ሶዶ መጋቢት 29/2010 መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች አቅርቦት እጥረትና የስርጭት ፍትሃዊነት ችግር እንደገጠማቸው በወላይታ ሶዶ ከተማ  አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የከተማዋ  ንግድና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት በበከሉ ችግሩን ለመፍታት አፋጣኝ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ወይዘሮ አስቴር ታደሰ በከተማዋ ፋና ቀበሌ የመምህራን አምባ መንደር ነዋሪ ሲሆኑ  በመንግስት ድጎማ ሲቀርቡ የነበሩ የስኳርና የዘይት ምርት እጥረት ከዛሬ ነገ ይስተካከላል ቢባልም  ችግሩ እንዳልተፈታ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ምክንያት በግል ቸርቻሪዎች በከፍተኛ ዋጋ ለመግዛት መገደዳቸውን ወይዘሮ አስቴር በተለይ በዓል ወቅት ችግሩ ባለመፈታቱ ቅር መሰኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከእጥረቱም ባሻገር ከዚህ በፊት በቤተሰብ ልክ በኩፖን ይቀርብ  የነበረው የፍጆታ ምርት  በግማሽ መቀነሱ ፍትሃዊ እንዳልሆነ  የገለጹት ደግሞ የአራዳ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ካሰች ገብረ ሚካኤል ናቸዉ፡፡

እንደ ወይዘሮዋ ገለጻ ችግሩ ባለመፈታቱ  ላልተፈለገ ወጪ እየተዳረጉ ናቸው፡፡

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ አበበች አንጁሎ እንዳሉት  የስኳርና ዘይት ዋጋ በማሻቀቡ ከመንግስት የሚቀርበውን ሲጠብቁ እንደቆዩ ተናግረዋል፡፡

ዘይት በሊተር ከ23 ብር  ወደ 60 ብር ስኳር ደግሞ 18 ብር ከ50 ሳንቲም  ወደ 55 ብር ከፍ ብሎ ከቸርቻሪ ነጋዴዎች ለመግዛት እየተገደዱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የሚመለከተው የመንግስት አካል ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እልባት እንዲሰጣቸው የሚፈልጉ መሆናቸውን  አመልክተዋል፡፡

ስለጉዳዩ የተጠየቁት የከተማዋ ንግድና ኢንዳስትሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታጋይ ቶማስ በበኩላቸው በመንግስት ድጎማ የሚመጣው ስኳርና ዘይት ከዚህ በፊት ለ45 ቀናት ይመጣ የነበረው  አሁን ለ15 ቀናት ታስቦ በመምጣቱ እጥረቱ መከሰቱን ገልጸዋል፡፡

ይህም ከሚጠብቀው በግማሽ በማነሱ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ችግሩን በአፋጣኝ ለመፍታት የመጣውን ከ744 ኩንታል በላይ ስኳርና 242 ሺህ 784 ሊትር ዘይት  እንዲከፋፍል እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከስርጭት ፍትሃዊነትና አዲስ የኮታ ድልደላ ጋር ተያይዞ ከማህበረሰቡ እየተነሳ ያለው ቅሬታ ለመፍታት ከነዋሪው ቁጥር ጋር የሚመጣጠን የኮታ ማሻሻያ በአጭረ ጊዜ ለመስራት  ጥናት በማድረግ ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ውስን ቢሆንም የመጣውን በአግባቡ ለማህበረሰቡ ለማዳረስና በዓሉን በተረጋጋ ሁኔታ እንዲያከብር ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በከተማዋ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 30 የንግድ ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይ እርምጃ መውሰዱን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የተወሰደው እርምጃም  21 የንግድ ድርጅቶች ማሸግና ቀሪዎቹ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ነው፡፡

በበዓሉ  ምክንያት የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት ቁጥጥር የሚያደርግ ልዩ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ታጋይ አብራርተዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ጅግጅጋ መጋቢት 29/2010 አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመጀመሪያ የስራ ጉብኝታቸውን በሱማሌ ክልል ጀመሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጅግጅጋ አውሮፕላን ጣቢያ ሲደርሱ በርካታ ህዝብ ደማቅ አቀባበል ያደረገላቸው ሲሆን፤ በዚያውም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መልካም የስራ ዘመን እንዲሆንላቸው ያላቸውን ምኞት ገልጸውላቸዋል።

በአቀባበሉም በርካታ የጅግጅጋ ነዋሪዎች ልዑካን ቡድኑን ግራና ቀኝ ሆነው አጅበዋቸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመሪያ የስራ ጉብኝት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና  የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ሽፈራው ሽጉጤን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ከፍተኛ አመራር ያካተተ የልዑካን ቡድን አባላት ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጀመሪያ የስራ ጉብኝታቸው በክልሉ የተከናወኑትን የመሰረተ ልማት ስራዎችን ይጎበኛሉ፤ ከህዝቡ ጋርም ውይይት ያደርጋሉ።

በውይይቱም ከህብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን