አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Friday, 06 April 2018

ሐረር መጋቢት 28/2010 የአካባቢያቸውን ሰላም ጠብቀው በማቆየት የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸውን ለማስቀጠል እንደሚንቀሳቀሱ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የሚገኙ የኦህዴድ/ኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ተናገሩ። 

አባላቱና ደጋፊዎቹ ድርጅቱ የተመሰረተበትን 28ኛ ዓመት የምስረታ በዓል " በኦህዴድ መስመርና በህዝባችን ርብርብ የማይፈታ ችግር የማናስመዘግበው ድል አይኖርም" በሚል መሪ ቃል በሐረር ከተማ በፓናል ውይይት አክብረዋል።

በዓሉ ሲከበር ድርጅቱ ያስመዘገባቸው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውጤቶችን ለማጠናከር በአንድነት እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል።

ከተሳታፊዎቹ መካከል የአፈረን ቀሎ ሁምበና አባገዳ ሙሳ ሮባ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የልማት ሥራዎች እርሳቸውን ጨምሮ የዞኑ ህዝብ ተጠቃሚ ሆኗል ።

በቀጣይም ኦህዴድ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎችን በማከናውን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያደርጋቸው ጥረቶች የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል።

"መንግስት ከወጣቱ በርካታ የልማትና የሰላም ሥራዎችን ይጠብቃል" ያለው ወጣት ፋሚ ዩሱፍ በበኩሉ ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎ በሀገሪቱ የተረጋገጠውን ሰላምና ልማት ጠብቆ ለማቆየት እንደሚሰራ ተናግሯል።

የልማት ተሳታፊም ሆነ ተጠቃሚ መሆን የሚቻለው ሰላም ሲኖር መሆኑን ገልጾ፣ "በአካባቢያችን ሰላምን በዘላቂነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የዜግነት ግዴታዬን ለመወጣት ዝገጁ ነኝ" ብሏል።

ወይዘሮ ፈርያ አልይ በበኩላቸው ብዙዎች የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው በተገኘው ድል ሴቶች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እኩል የመሳተፍና የመጠቀም መብትን መጎናጸፋቸውን ገልጸዋል።

"በእዚህም የሴቶች ተጠቃሚነት እያደገ በመምጣቱ ሰላምና አንድነትን አጠናክረን እንቀጥላለን" ብለዋል።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በበኩላቸው "ኦህዴድ /ኢህአዴግ ከምስረታው ጀምሮ ባከናወናቸው ተግባራት ብዙ ውጣ ውረዶች ቢያጋጥሙትም በህዝብና በድርጅቱ ቁርጠኛ አመራሮች በድል እየተጓዘ ይገኛል" ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት ያስመዘገባቸውን አንጸባራቂ ድሎች ህዝቡ በተለይ ደግሞ ወጣቱ ትውልድ ከድርጅቱ ጎን በመሰለፍ የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

በከተማው በሚገኘው አሚር አብዱላሂ መሰብሰቢያ አዳራሽ በተከበረው በዓል ላይ የዞኑና የወረዳ አመራር አካላት፣ የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ አባገዳዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በዓሉን በማስመልከት የተለያዩ ስነጽሁፎች፣ ሙዚቃዎችና ሌሎች ዝግጅቶች ለታዳሚው ቀርበዋል፡፡

 

Published in ፖለቲካ

መጋቢት 27/2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሸጎሌ አካባቢ ለፋሲካ በዓል በቂ   የበሬና የበግ አቅርቦት መኖሩና ዋጋውም ተመጣጣኝ መሆኑን  ሪፖርተራችን  በስፍራው ተዘዋውሮ ያናገራቸው ገዥዎችና ሻጮች ተናገሩ።   

መንገዱ  ሰላም   በመሆኑ  የሽያጭ   በጎችን  ይዘው  ከአምቦ   መስመር   ጥቁር   እንጭኒ፣ ከጉደርና  ባቢቻ  ያለምንም ችግር  ወደ   አዲስ አበባ  ማምጣት መቻላቸውን  የተናገሩት  አቶ ጌታቸው ገብረአምላክ ናቸው።

እንደ  አቶ ጌታቸው ገለፃ  ሀገር ሰላም  በመሆኑ   ከየአቅጣቸው  የሚመጡ  የበግ ነጋዴዎች  እንደልባቸው   ወደ   መዲናዋ   እንዲገቡ  በመቸላቻቸው    ገበያው  የተረጋጋ   እንዲሆን  አስችሏል፡፡

የበግ ዋጋ ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር  መጠነኛ ቅናሽ  ማሳየቱን የተናገረችው ደግሞ በግ ስትገዛ ያገኘናት ወይዘሪት  እመቤት  ሃይለስላሴ  ናት። 

ወይዘሪት እመቤት እንደምትለው  ለባለፈው ዓመት የፋሲካ በዓል  በ5ሺ ብር የገዛችውን የበግ ሙክት  ዘንድሮ  በ4ሺ  መግዛቷን ገልፃለች።

በግ  ሲሸጡ ያገኘናቸው  አቶ   አሸናፊ  ወልደሰንበት በበኩላቸው  በዚህ  አመት   ድርቅ  ባለመኖሩ  ለእንስሳት እርባታ አመቺ  ወቅት  ስለነበር  በቂ የበግ  አቅርቦት  በመኖሩ ዋጋው ሊቀንስ ችሏል ይላሉ፡፡

 የበግ ዋጋ ከ1ሺህ 500- 4ሺህ ብር ፤ ፍየል  ደግሞ  ከ1500- 5000  ብር እየተሸጠ መሆኑን  ነው የተናገሩት።  

“እኛ  አቅርበናል  እስከ   በዓሉ   ድስ  ባሉት  ጥቂት  ቀናት  በርከት ያለ ገዥ  ይመጣል  ብለን  ተስፋ  እኛደርጋለን”  በማለትም  ገልፀዋል።

በተመሳሳይ በሬ ከ13ሺህ  እስከ 35 ሺ ብር  እንደሚሸጥና   መለስተኛ  በሬ  በ12 ሺ  ብር እየተሸጠ መሆኑን በሥፍራው  መመልከት ተችሏል።   

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 28/2010 አዲሱ አመራር የሚጠበቅበትን የመሪነትና የአስተባባሪነት ሚና በአግባቡ እንደሚወጣ ሁሉ ኅብረተሰቡም የተሟላ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ መንግስት ጥሪ አቀረበ።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት "ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር ለህዳሴያችን ስኬት!" በሚል ርዕስ ያወጣውን ሳምንታዊ መግለጫ ልኳል።

በመግለጫውም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሰየም በአገራችን ታሪክ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር እውን መሆኑን በተግባር ማረጋገጡን አውስቷል።

ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግሩ በአንድ በኩል ዛሬ ኢትዮጵያ የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ የሚያመላክት ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለቀጣይ የአገሪቷ ሰላምና ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የሚያሳይ መሆኑን መግለጫው አትቷል።

የስልጣን ሽግግሩ ለዴሞክራሲ ኃይሎች፣ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ብሎም በአፍሪካና በዓለም አደባባይ ላይ ኢትዮጵያ ለሚኖራት ተሳትፎ በአርዓያነት የሚጠቀስ ተግባር መሆኑንም እንዲሁ።

ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ በተግባር ሊረጋገጡ የሚችሉት፣ በመንግሥት ጥረት ብቻ ባለመሆኑ መላው ህዝብ በቡድንና በተናጠል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መንግስት ጥሪውን አስተላልፏል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል!

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ

መጋቢት 28 ቀን 2010 ዓ.ም

ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር ለህዳሴያችን ስኬት!

የኢትዮጵያ ህዳሴ ስኬት የሚረጋገጠው፣ አንደኛው ትውልድ በዘመኑ የጀመረውንና ያስመዘገበውን ውጤት ከቀጣዩ ትውልድ ጋር በመቀባበል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሂደቱም ከመናቆር ይልቅ መደጋገፍን፣ ከመጠላለፍ ይልቅ መተባበርን የሚጠይቅ ነው፡፡

የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሰየም በአገራችን ታሪክ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር እውን መሆኑን ዳግም በተግባር አረጋግጧል፡፡ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግሩ በአንድ በኩል ዛሬ አገራችን የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ የሚያመላክት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ለቀጣይ ሰላማችንና ዕድገታችን ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም፣ አገራችን በተያያዘችው የህዳሴ ጉዞ ሂደት ውስጥ እመርታዊ ለውጥ ተደርጎ የሚወሰድ እና ለቀጣይ የዕድገት ጉዞም ትልቅ መሠረት የሚጥል ሲሆን፣ ለዴሞክራሲ ኃይሎች፣ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ብሎም በአፍሪካና በዓለም አደባባይ ላይ ለሚኖረን ተሳትፎም በአርዓያነት  የሚጠቀስ ተግባር ነው፡፡

እንደሚታወቀው፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የማይነጣጣሉ የአንድ ሳንቲም ገጽታዎች ናቸው፡፡ እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች በተግባር ሊረጋገጡ የሚችሉት፣ በመንግሥት ጥረት ብቻ እንዳልሆነም ይታወቃል። ይልቁንም፣ መላው ህዝባችን በቡድንና በተናጠል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ በመሆኑም፣ መንግሥት የመሪነት እና የአስተባባሪነት ሚና ቢኖረውም የዜጎች ህይወት በመሠረቱ የሚቀየረው በዋነኝነት በዜጎች ጥረትና ልፋት መሆኑን መገንዘብ እና በዚህ በኩል ራሳችንን ለለውጥ ማዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡

በዚህ አጋጣሚ፣ አዲሱ አመራር የሚጠበቅበትን የመሪነትና የአስተባባሪነት ሚና በአግባቡ እንደሚወጣ፣ ሕዝባችንን በባለቤትነት የማሳተፍ ነባር መርሆዎቻችንን ተከትሎም ከድህነት ለመላቀቅ የተያያዝነውን ራእይ ለማሳካት ጠንክሮ እንደሚሰራ ለማረጋገጥ ይወዳል።

አገራችን ኢትዮጵያን በ2017 ዓ.ም. መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ የያዝነው ዕቅድ የሚሳካው በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የተሟላ እና ንቁ ተሳትፎ መሆኑን አጥብቆ የሚገነዘበው የኢፌዴሪ መንግሥት፣ ትውልዱ አሁን ያስመዘገበውን ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር ድል እየተንከባከበ ለቀጣይ ተደማሪ ውጤቶች ርብርብ ማድረጉን እንዲቀጥል ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Published in ፖለቲካ

ሶዶ/አክሱም/ ነቀምቴ መጋቢት 28/2010 በወላይታ አካባቢ የፋሲካ በዓል ገበያ የተረጋጋ መሆኑን፣ በአክሱም እና በነቀምቴ ከተሞች ደግሞ  በእርድ ከብትና  የፍጆታ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡

በወላይታ ሁምቦ ጣባላ ገበያ የበግና ፍየል ነጋዴ የሆኑት አቶ አበራ አይዛ ለኢዜአ እንዳሉት በበዓሉ ገበያ የእንስሳት አቅርቦት እጥረት እንደሌለና ዋጋውም  ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ሲነጻጸር ጭማሪ አላሳየም፡፡

ፍየል ከ1300 እስከ 3500 እንዲሁም በግ 1500 እስከ 4000 ድረስ እንደየአቅምና ፍላጎት እየተገበያየ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ከሸማቾች መካከል አቶ ገናለ ገዙሜ  በሰጡት አስተያየት በገበያው  ፍየል በ2600 ብር መግዛታቸውን ጠቅሰው በቂ አቅርቦት እንዳለ  መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

አማርጦ ለመግዛት ዕድል የሚሰጥ ገበያ በመሆኑ  ሻጩም ሆነ ሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ  ለመገበያየት የሚያስችልና የተረጋጋ ሆኖ እንዳገኙትም ጠቅሰዋል፡፡

በዳልቦ ገበያ የእርድ ከብት ለመግዛት የተገኙት አቶ ላምበቦ ዳና በበኩላቸው ገበያው በአቅርቦትም ሆነ በዋጋ የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የእርድ ከብት  ከ7 ሺህ ብር ጀምሮ እስከ 12 ሺህ ብር መግዛት እንደሚቻል በገበያው ተዘዋውረው መመልከታቸውን ያመለከቱት አቶ ላምበቦ ገበያው እንደአቅም ለመጠቀም አማራጩ እንዳለ አውስተዋል፡፡

በሶዶ ከተማ መርካቶ ገበያ የዶሮ ነጋዴው አቶ አሸናፊ ወርቁ ምርቱና አቅርቦቱ እንዳለ ጠቅሰው የዶሮ ዋጋ መጠነኛ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡

የዶሮ ዋጋ  ዝቅተኛው እስከ 220 ብር እና ከፍተኛው ደግሞ እስከ 430 መሆኑን ጠቁመው ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀር ከ30 ብር እስከ 50 ብር  ጭማሪ ማሳየቱን አስረድተዋል፡፡

በዓሉ ከወዲሁ የደመቀና ገበያውም የተረጋጋ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ አሸናፊ ለዚህ ሁሉ የሃገሪቱ ሰላም ወደነበረበት መመለሱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ 

ወይዘሮ ሠላማዊት ናና በበኩላቸው የሀገሪቱ  መረጋጋት ተስፋን በሰነቀ መንፈስ በዓሉን ለማክበር ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የሰላምና መረጋጋት መኖር ነጋዴው፣   አምራቹና ሸማቹ  ወደሚፈልገው  ተዘዋውሮ ለመገበያየት ዕድልና  አማራጭ እንደሚኖረው አመልክተዋል፡፡

ቅቤ የተወሰነ ጭማሪ አሳይቶ በኪሎ በ250 ብር ቢሆንም የምርት አቅርቦት ችግር ያለመኖሩን ጠቅሰው ቀይ ሽንኩርት ካለፈው ዓመት በአምስት ብር ቀንሶ  ኪሎ በ10 ብር ነጭ ሽንኩርት ደግሞ እስከ 40 ብር እየተሸጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩልም ዛሬ በአክሱም ከተማ የገበያ ማዕከል የተዘዋወረው የኢዜአ ሪፖርተር ሙክት ፍየል ዋጋ በአማካይ ሦስት ሺህ ብር ወጠጤ ከ1 ሺህ 500 እስከ 2 ሺህ ብር ድረስ ሲሸጥ ተመልክቷል፡፡

ሲሸምቱ ከነበረት የከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ በርሄ ኃይሌ እንዳሉት ሙክት ፍየል በ2 ሺህ 800 ብር መግዛታቸውንና  ይህም ዋጋው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ጨምሯል።

በአማካይ በአንድ የሙክት ፍየል ዋጋ ላይ   እስከ 800 ብር ጭማሪ ማሳየቱን ነው የተናገሩት።

ወጣት ግደይ ተስፋዬ  በበኩሉ፣" ፍየል በ1 ሺህ 500 ብር ገዝቻለሁ ፤ዋጋው በጣም የተጋነነ ነው" ብሏል።

በተመሳሳይ በከተማው በዶሮ ዋጋ ላይ የተጋነነ ጭማሪ መታየቱን የተናገሩት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ዳዊት ኃይሌ ናቸው።

አቶ ዳዊት " ባለፈው ዓመት በ150 ብር ዶሮ እንደገዙ አስታውሰው ዘንድሮ በ250 ብር ገዝቻለሁ፣በጣም ውድ ነው"ብለዋል።

ወይዘሮ አወጣሽ ኪዳነ የተባሉት የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው ዶሮ በ200 ብር እንደገዙትና ዋጋው ካሰቡት በላይ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ይህም በበዓል  ወቅት የሚኖር አይነት ጭማሪ እንደሆነ  ነው ወይዘሮ አወጣሽ የተናገሩት።

የአክሱም ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ  ገብረመስቀል ተካ ስለዋጋ ጭማሪው አስመልክተው በሰጡት ምላሽ ጭማሪው  ከዶላር ጭማሪ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ  የግንዛቤ ክፍተት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በገበያው የአቅርቦት ችግር እንደሌለ  ፣ ነጋዴውና ሸማቹ የተሳሳተ አመለካከት በመያዝ ራሱ የፈጠረው ተጽእኖ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፍትሓዊ ግብይት እንዲኖር  ጽሕፈት ቤቱ በቀጣይነት ገበያውን የማረጋጋት ስራና በነጋዴው የሚስተዋለው የገበያ ግንዛቤ ክፍተት ለማስተካከል እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡

በተመሳሳይ ከነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል  አቶ አመንቴ ኩምሳ በሰጡት አስተያየት የዘንድሮ ፋሲካ በዓል የገበያ  ዋጋ ከባለፈው ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡

አቶ አመንቴ እንዳመለከቱት ከሁለት ሳምንት በፊት እስከ አንድ ሺህ  ብር ይገዛ የነበረው  በግ  አሁን ላይ በአምስት መቶ ጭማሪ  እየተሸጠ ነው፡፡

የምግብ ቤት ባለቤት  የሆኑት አቶ አሰፋ ድንሳ በበኩላቸው ቀደም ሲል 12ሺህ ብር ይገዛ የነበረው  በሬ ዛሬ ከ 17 ሺህ  ብር በላይ እየተሸጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አንለይ ኃይሉ በበኩላቸው ቀደም ሲል ሶስት ብር የነበረው እንቁላል በአንድ ብር ጭማሪ ማሳየቱንና  150 የነበረው ዶሮ እስከ 300 ብር ሲገበያይ  መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

ነገሌ መጋቢት 28/2010 በነገሌ ከተማ  በማህበር ለተደራጁ  150 መምህራን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ መስጠቱን የከተማው ማዘጋጃ ቤት ገለፀ፡፡

ማዘጋጃ ቤቱ ለመምህራኑ በነብስ ወከፍ  160 ካሬ ሜትር  ቦታ ትላንት አስረክቧል ።

በማዘጋጃ ቤቱ የመሬት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባነታ ዴላ ለኢዜአ እንዳሉት  መምህራኑ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ የተሰጣቸው ያለውድድር በሊዝ ጨረታ መነሻ ዋጋ ነው፡፡

መምህራኑ በተሰጣቸው ቦታ ላይ ቤት ለመስራት እንዲቻላቸው እያንዳንዳቸው 4 ሺህ 500 ብር እንዲሁም በቡድን እስከ  675 ሺህ ብር መቆጠባቸውን ተናግረዋል።

"መምህራኑ የግለሰብ ቤት ተከራይተው በመኖራቸው የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና እያጋጠማቸው መሆኑን በመግለፅ ባቀረቡት  ጥያቄ መሰረት የቤት መስሪያ ቦታ ተሰጥቷቸዋል " ብለዋል ።

የተሰጣቸው ቦታም  24 ሺህ ካሬ ሜትር መሆኑን አመልክተው ይህም ተከፋፍሎ በነብስ ወከፍ  160 ካሬ ሜትር መዳረሱን ጠቅሰዋል።

የቤት መስሪያ ቦታ ከተሰጣቸው መካከል መምህር ደመቀ ደገፋ በሰጡት አስተያየት  ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለከተማው ማዘጋጃ ቤት የቦታ ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

"ማዘጋጃ ቤቱ ለመምህራን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ መስጠቱ ለህዝቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ያሳያል" ብለዋል፡፡

የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለማግኘት ጥያቄ ካቀረቡበት ጊዜ ጀምሮ በግላቸው  4 ሺህ 500 ብር እንደቆጠቡ መምህር ደመቀ ተናግረዋል፡፡

የቤት መስሪያ ቦታ ማግኘታቸው ለዓመታት በኪራይ ቤት ሲደርስባቸው የነበረውን ችግር እንደሚፈታላቸው  የገለፁት ደግሞ መምህር አሰግድ አየለ ናቸው።

"የቆጠብኩት ገንዘብ ቤት ሰርቶ ስለማይጨርስልኝ በማዘጋጃ ቤቱ በኩል ከደመወዝ የሚቆረጥ የብድር ገንዘብ እንዲመቻችልኝ ጥያቄ አቅርብያለሁ " ብለዋል።

የቤት መስሪያ ቦታ በማግኘታቸው ጥያቄያቸው መመለሱን ያመለከቱት አስተያየት ሰጪዎቹ የራሳቸውን ቤት በመስራት  ተረጋግተው ለተማሪዎቻቸው ተገቢውን እውቀት እንዲያስጨብጡ የሚያበረታታቸው መሆኑን ተናግረዋል ።

Published in ማህበራዊ

ነቀምት መጋቢት 28/2010 በምሥራቅ ወለጋ ዞን በዘንድሮው የበጋ ወራት በመጀመሪያ ዙር በተካሄደ የመስኖ ልማት 11 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን የዞኑ መስኖ ልማት ባለሥልጣን አስታወቀ ፡፡

የባለሥልጣኑ የመስኖ ልማት ኤክስቴንሽን የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አብዱ ኢፋ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት ምርቱ የተገኘው በ17 ወረዳዎች በባህላዊና በዘመናዊ ዘዴ በመስኖ ከለማው 88 ሺህ 217 ሄክታር መሬት ላይ ነው።

የመስኖ ልማቱ የተካሄደው በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በአገዳ፣ በጥራጥሬና ስራስር ሰብሎች መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

የተገኘው ምርት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ ማሳየቱን አስተባባሪ ገልጸዋል።

"ዘንድሮ የተሻለ የውሀ አማራጭ መኖሩ፣ የአርሶ አደሩ የምርት ማሳደጊያ ግብአት አጠቃቀም ልምድ መጎልበት አበላጫ ምርት እንዲገኝ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው " ብለዋል።

ለመስኖ ልማቱ ከ4ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና 154ሺህ 39 ኩንታል የተለያየ የሰብል አይነቶች ዘር ቀርቦ ጥቅም ላይ መዋሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በልማቱ ከተሳተፉ 143ሺህ 726 አርሶ አደሮች መካከል 14ሺህ 57ቱ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል ።

በዞኑ የሲቡ ስሬ ወረዳ የለሊሣ ቀበሌ አርሶ አደር በቀለ ቱሉ በሰጡት አስተያየት በመጀመሪያው ዙር በ1 ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት ሽንኩርት፣ትማቲምና ጥቅል ጎመን ሽያጭ 38ሺህ ብር ገቢ አግኝተዋል ።

"አሁን ላይ የመሰኖ ምርት ያነሳሁበት ማሳ ላይ በመኸር ቀድሞ ለሚዘራ በቆሎ ዝግጅት እያካሄድኩ ነው" ብለዋል ።

ሌላው የቀበሌው ወጣት ሸለማ ምትኩ በበኩሉ በሩብ ሄክታር መሬት ላይ ካለማው ቲማቲምና ሽንኩርት ሽያጭ 28ሺህ ብር ገቢ ማግኘቱን ተናግሯል።

በመጀመሪያ ዙር በሩብ ሄክታር መሬት ላይ ካለማሁት ድንችና ቲማቲም ሽያጭ ከ11ሺህ ብረ በላይ በላይ ገቢ አግኝቻለሁ ያሉት ደግሞ በዋዩ ቱቃ ወረዳ የቦነያ ሞሎ ቀበሌ አርሶ አደር ጋሮምሣ ዋቅጅራ ናቸው።

በዞኑ በሁለተኛው ዙር የመስኖ ልማት መርሀ ግብር ለማልማት ከታቀደው 62 ሺህ 509 ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን 54ሺህ 390 ሄክታሩ ታርሶ በዘር የተሸፈነ ሲሆን ከሁለተኛው ዙር የመስኖ ልማት 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል ።

Published in ኢኮኖሚ

ባህርዳር መጋቢት 28/2010  በባህር ዳር ከተማ  የፋሲካ በዓል ገበያ  የእርድ እንስሳት ዋጋ ካለፈው የገና በዓል ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን   ሸማቾችና ነጋዴዎች ገለጹ።

የኢዜአ ሪፖርተር በባህር ዳር ከተማ የፋሲካ በዓል የእርድ እንስሳት፣ የዶሮና እንቁላል ዋጋን  ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

የበሬ ነጋዴው አቶ አየነው ቦሌ እንደገለፁት አንድ የደለበ በሬ 30 ሺህ ብር ለመሸጥ እየተደራደሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ባለፈው ገና ተመሳሳይ በሬ 19 ሺህ ብር እንደሸጡ አስታውሰዋል።

በተመሳሳይ ባለፈው ገና 10 ሺህ ብር የሸጡትን አይነት ተመሳሳይ በሬ ዛሬ 13 ሺህ ብር ለመሸጥ እንደተስማሙ ተናግረዋል።

በሬ ሲገዙ ያገኘናቸው አቶ ጥላሁን አበበ በበኩላቸው  የበሬ ዋጋ  ከፍተኛ  እስከ 40 ሺህ ፣ዝቅተኛ እስከ 15 ሺህ ድረስ እንደሚጠራ ገልፀዋል፡፡

በአቅርቦት በኩል ከገና በዓል ያልተናነሰ ቢሆንም በዋጋ ግን ከ5 ሺህና ከዛ በላይ ጭማሬ እንዳሳየ ተናግረዋል።

የፍዬል ዋጋም በተመሳሳይ ከገና በዓል ዋጋ ጋር ሲነጻጸር 500 ብርና ከዛ በላይ ጭማሬ አሳይቷል።

የበግ ነጋዴው አቶ ካሳሁን ዘውዴ እንደተናገሩት በግ  እስከ 3 ሺህ አነስተኛው ደግሞ በ1 ሺህ 500 ብር እየሸጡ  ነው።

በግ ሲገዙ ያገኘናቸው አቶ ምናለ ዳምጤ የበግ ዋጋ  አቅርቦቱ በበቂ ሁኔታ ያለ ቢሆንም  ከገና በዓል ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ከ 300 እስከ 500 ጭማሬ ማስተዋላቸውን ነው ያስረዱት።

አቶ ኤርሚያስ ተድላ በበኩላቸው የፍየል ዋጋ ከፍተኛ እስከ 4ሺህ 400 ብር መካከለኛ 3 ሺህ ብርና ዝቅተኛ ደግሞ 1ሺህ 500 ብር እየሸጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ይህም ከገና በዓል ዋጋ  እስከ 1ሺህ ጭማሬ መኖሩን ገልፀዋል።

ዶሮ  300 ፣ 200ና 180 እየተሸጠ ሲሆን ካለፈው በዓል ዋጋ ሲነጻጸር ከ 50 እስከ 80 ብር ጭማሬ መኖሩን ሸማቾችና ነጋዴዎች ገልፀዋል፡፡

እንቁላል  ከሦስት ብር እስከ ሦስት ብር ከሠላሳ ሳንቲም እየተሸጠ ሲሆን ከገና በዓል ዋጋ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን  ኢዜአ ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 28/2010 የሶዶ-ሳውላ ሸፊቴ መንገድ ግንባታ መጀመር ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ ለማቅረብ እንደሚያስችላቸውና ማህበራዊ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝላቸው የአካባቢው ነዋሪዎችና መስተዳድር አካላት ገለፁ።

140 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍነው የሶዶ - ሳውላ - ሸፍቴ የአስፓልት መንገድ ግንባታ የመጀመሪያ ምዕራፍ ስራዎች ተጀምረዋል።

ከአዲስ አበባ 516 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሳውላ ከተማና አጎራባች ወረዳዎቿ የቡና፣ ነጭ ሰሊጥ፣ ኮረሪማ፣ ዝንጅብል፣ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችና የሰብል ምርቶች አምራች ቢሆኑም፤ በመንገድ እጥረት ምክንያት ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ ለማቅረብ ይቸገሩ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የአካባቢው ነዋሪ አቶ ሳሙኤል አፃ እና የአስር አለቃ አልቤ አፋ እንዲሁም የሳውላ ከተማ ከንቲባ ምንተስኖት ተሰፋዬ እንደተናገሩት፤ በአካባቢው የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመሟላቱ ምክንያት ህብረተሰቡ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተዳርጎ ቆይቷል።

የሳውላ ከተማ ከንቲባ አቶ ምንተስኖት ተሰፋዬ አካባቢው ለአገሪቷ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ በሚያስገኙ በቁም እንስሳትና በሰብል ምርቶች የሚታወቅ ቢሆንም፤ የመንገድ መሰረተ ልማት እስካሁን ባለመሟላቱ ለችግር ተዳርገው መቆየታቸውንም ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ አሁን የተጀመረው 140 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍነው የሶዶ - ሳውላ ሸፍቴ አስፓልት መንገድ ግንባታ ሲጠናቀቅ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝላቸው ነው የአካባቢው ነዋሪዎች የገለጹት።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ግርማይ በበኩላቸው  መንግስት የከተሞችን እድገት ታሳቢ ያደረገ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ነው።

ካለፉት ሃያ ዓመታት ጀምሮ በአገሪቷ የነበረው የመንገድ መሰረተ ልማት 20 ሺ ኪሎ ሜትር የነበረ ሲሆን፤ አሁን ግን ይህ ቁጥር ወደ 110ሺ ኪሎ ሜትር አድጓል።

የሶዶ-ሳውላ መንገድ ግንባታ የተጀመረ በመሆኑ የአካባቢው ህብረተሰብና አስተዳደር አካላት ለመንገዱ ግንባታ መፋጠንና እውን መሆን በወሰን ማስከበርና በሌሎች ሥራዎች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

በጠጠር መንገድ ደረጀ ይገኝ የነበረና ስፋቱም ከአምስት እስከ ሰባት ሜትር ብቻ የነበረው መንገዱ አሁን በአስፓልት ኮንክሪት ደረጃ የሚገነባና መንገዱ በሚያልፍባቸው ከተሞች አካባቢን ጨምሮ 19 ሜትር ስፋት ኖሮት እንደሚገነባ ይጠበቃል።

ለግንባታው የሚውለው ገንዘብ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ብድርና በኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚሸፈንም ታውቋል።

'ቻይና ሬልዌይ ሰቨን ግሩፕ' 86 ኪሎ ሜትር  ከሶዶ እስከ ዲኒቄ የሚሸፍነውን የሚገነባ ሲሆን፤ ከድንቄ-ሳውላ 54 ኪሎ ሜትር መንገድ የሚገነባው ደግሞ 'ቤጂንግ አርባን ኮንስትራክሽን ግሩፕ' ነው።

መንገዱን ገንብተው ለማጠናቀቅ ኮንትራክተሮቹ የአራት ዓመት ጊዜ እንደተሰጣቸውም ለማወቅ ተችሏል።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ መጋቢት 28/2010 እናቶች ለእናቶች የተባለ አገር በቀል ማህበር በመቀሌ ከተማ ለሚኖሩ ጧሪ ለሌላቸው አረጋውያን እናቶች ለዓመት በዓል መዋያ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።

የማህበሩ  ፈጻሚ ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ አስመላሽ እንዳሉት ማህበሩ ዛሬ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገላቸው እናቶች ቁጥር 55 ሲሆኑ ለእያንዳንዳቸው በነፍስ ወከፍ ብር 400 ሰጥቷቸዋል። 

የበዓሉ ዕለት እናቶች በለመዱት ባህልና ወግ  መሰረት በዓሉን በደስታ በቤታቸው ውስጥ ማሳለፍ እንዲችሉ በሚል እሳቤ የገንዘብ ድጋፍ  መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የገንዘብ ድጋፍ ከተደረገላቸው እናቶች መካከል ወይዘሮ ጥበቡ ገብረውበት እንዳሉት በጉርምስና ዕድሜያቸው በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ልጅ ባለመውለዳቸው አሁን በእርጅና ጊዜ ደጋፊና ጧሪ ማጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

ማህበሩ ለበዓል መዋያ ያደረገላቸው ድጋፍ ዶሮ ገዝተው ለፋሲካ በዓል ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር ለማሳለፍ እንደሚያስችላቸውና በእዚህ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

"በዓሉን በደስታ ማሳለፍ እንድንችል እናቶች ለእናቶች ማህበር ላደረገልን ድጋፍ  ምስጋና ይገባዋል" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሀዳስ ገብረእግዚአብሔር ናቸው፡፡

" ማህበሩ በሰጠን ገንዘብ ለበዓሉ የሚያስፈልገውን እንደአቅማችን ገዝተን እንደሌላው ተደስተን እንውላለን "ብለዋል፡፡

የእናቶች ለእናቶች ማህበር በተመጣጠነ ምግብ አዘገጃጀት፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከለልና አረጋውያን እናቶችን በመንከባከብ ይሰራል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ማህበሩ ከኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቫይረስ ጋር ለሚኖሩ ወገኖች ወርሃዊ የምግብ ድጋፍ በማድረግና የኢኮኖሚያዊ  አቅማቸውን በማጎልበት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ፡፡

Published in ማህበራዊ

ሀዋሳ መጋቢት 28/2010 በደቡብ ክልል እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ ተከትሎ በመጪው ግንቦትና ሰኔ ወር ወባ በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰት አስቀድሞ ለመከላከል የፀረ ትንኝ ኬሚካል ርጭትና የአጎበር ስርጭት መካሄዱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና በሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ አቅናው ካውዛ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት ሊቀሰቀስ የሚችለውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎች ተከናውነዋል ።

የመከላለሉ ሥራ የተካሄደው ለበሽታው ተጋላጭ በሆኑ ጋሞጎፋ፣ ደቡብ ኦሞና ሰገን ህዝቦች አካባቢ መሆኑን ተናግረዋል። 

በቅድመ መከላከሉ ሥራ በዞኖቹ በ448 ሺህ  በ1 ነጥብ 4  ቤቶች ላይ የፀረ ትንኝ ኬሚካል መረጨቱን ተጠቅሰዋል ።

"በኬሚካል ርጭቱ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከበሽታው መታደግ ተችሏል " ብለዋል ።

ከኬሚካል ርጭቱ ጎን ለጎን በ2007 ዓ.ም የተሰራጩና በአሁኑ ወቅት ያረጁ ከ3 ሚሊዮን በላይ አጎበሮችን በአዲስ መተካት ተችሏል" ብለዋል ።

በዞኖቹ ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የአካባቢ ንጽህናና ቁጥጥር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አቶ አቅናው አስታውቀዋል ።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን