አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Thursday, 05 April 2018

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2010 በመንግስት የጤና ተቋማት መከናወን የሚገባቸውን የላቦራቶሪ ምርመራዎችና የመድሐኒት ግዢ አገልግሎት በግል ተቋማት ማድረግ  መወገድ  አለበት ተገለጸ ፡- የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም

 የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በሀገር አቀፍ ደረጃ በተመረጡ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ 16 የጤና ተቋማት በመልካም አስተዳደር እና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ቁጥጥር አካሂዷል፡፡

 ተቋሙ ቁጥጥር ባደረገባቸው ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች የለያቸውን ጠንካራ ጐኖች፣ ዋና ዋና የሕግና የአሰራር  ክፍተቶችና የመፍትሄ ሃሳቦች ዙሪያ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

 በተቋሙ የቁጥጥርና ጥናት ዳይሬክተር አቶ አዳነ በላይ እንደገለጹት፤ አንዳንድ የህክምና ባለሙያዎች የግል ጥቅማቸውን በማሰብ በመንግስት የጤና ተቋማት መሰራት የሚችሉ የላብራቶሪ ምርመራዎችና የመድሀኒት ግዥዎች በግል የጤና ተቋማት እንዲሰጡ ይደረጋል።

 ይህም ተገልጋዮችን አላስፈላጊ ላልሆነ ወጪና እንግልት የሚዳርግ በመሆኑ ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ሊወገድ ይገባል ብለዋል፡፡

የተፈላጊ ሙያተኞችና የህክምና ቁሳቁሶች ያለመሟላት ተኝተው ለሚታከሙ ህሙማን በተለይም ልዩ ክብካቤ ለሚሹ ጨቅላ ህፃናትና እናቶች የክፍል ጥበትና የአልጋ ቁጥር ማነስና በአንዳንድ ባለሙያዎች የሚታይ የስነ ምግባር ጉድለቶች በቁጥጥሩ ወቅት መስተዋሉን ጠቅሰዋል።

በደም አቅርቦት እጥረት ምክንያት ህይወታቸው የሚያልፉ  ወላድ እናቶችና ድንገተኛ ህሙማን በርካታ መሆናቸዉ፣ በመጀመሪያ ደረጃና በጤና ጣቢያ ሊታከሙ የሚችሉ ህሙማን ወደ ሪፌራል ሆስፒታሎች በመላካቸው ያልተገባ መጨናነቅና የሥራ ጫና እየፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች የአንቡላንስ እጥረትና በጤና ተቋማት ፍትሃዊ ስርጭት ያለመኖር ችግርም አለ ብለዋል።

በክልል ጤና ቢሮዎችና በሆስፒታሎች ከሰው ኃይል ቅጥር፣ ከደመወዝና ጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ልዩነቶች  ባለሙያውን የሥራ ተነሳሽነት በመጉዳት ለመልካም አስተዳደር ችግር መንስኤ እንደሚሆነ አቶ አዳነ ገልጸዋል፡፡ 

የጤና ተቋማት ሀላፊዎች ከተገልጋዮች የሚነሱ ቅሬታዎችን  አፋጣኝ ምላሽ መስጠት  በሚፈለገው ደረጃ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃን በበኩላቸው በህክምና ባለሙያዎች  የሚታዩ የስነ-ምግባር ጉድለቶችን ለመፍታት የብዙ አካላት ርብርብ በመጠየቁ ከቤተሰብ ጀምሮ  ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።

ከመድሃኒቶች ግዢ ጋር በተያያዘ ያሉ ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ በተለይም ውድ የሆኑ መድሃኒቶች ከሆስፒታል ሀላፊዎች ፈቃድ ውጭ እንዳይሸጡ  ቁጥጥር መደረጉን ጠቅሰዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የአምቡላንስ ችግር ለመፍታት በማቀድ የሶስት ሺህ አምቡላንሶች ግዢ በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

 በቅርቡ 68 አይነቶች የህክምና መሳሪያዎች ለክልሎችና ለዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች መሰራጨታቸውን አስታውሰዋል።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ህሙማን የሚያስተናግዱ ሆስፒታሎች ላይ የማስፋፊያ ስራዎች በተጓዳኝ ተንቀሳቀሰው ደም ለመሰብሰብ የሚያገለግሉ ስምንት ተሽከርካሪዎች በቀጣዩ አመት ለመግዛት መታቀዱን ገልጸዋል።

 የሪፈራል ሆስፒታሎችን ጫና ለመቀነስና የህሙማንን ቅብብሎሽ ለማሻሻል የጤና ተቋማትን በኢንተርኔት የማገናኘት ስራ መጀመሩንም አንስተዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

Published in ማህበራዊ

ዲላ መጋቢት 27/2010 በጌዴኦ ዞን ሙሉ በሙሉ የጠፋውን የጂጎ የተፈጥሮ ቀርከሃ ደን መልሶ ለማልማት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ አካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ጽሕፈት ቤት ገለፀ ፡፡

ጽሕፈት ቤቱ ለ80 አርሶ አደሮችና የልማት ባለሙያዎች በመልሶ ማልማት ሥራ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አክሊሉ በደቻ እንዳሉት፥ ከ342 ሄክታር በላይ ሽፋን የነበረው የጂጎ የተፈጥሮ ቀርከሃ ደን በዞኑ ቡሌ ገደብ እና ይርጋጨፌ ወረዳዎችን ያዋስናል፡፡

የቀርከሃ ተክል በባህሪው ከ40 እስከ 120 ዓመት ጊዜ ውስጥ አብቦ ፍሬውን ካራገፈ በኋላ እንደሚጠፋ ያብራሩት ኃላፊው፥ የጂጎ ቀርከሃ ደንም ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ በ2008 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ መጥፋቱን አስረድተዋል ፡፡

አቶ አክሊሉ እንዳሉት የደኑ መጥፋት በውስጡ ይኖሩ ለነበሩ የዱር እንስሳት መሰደድ፣ ከ32 በላይ ለሚሆኑ ምንጮች መድረቅ እና ለአካባቢው የአየር ንብረት መለወጥ ምክንያት ሆኗል፡፡

በአሁኑ ወቅት ደኑን መልሶ ለማልማት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ አምና ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በተካሄደ የንቅናቄና ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ውጤት መገኘቱን አብራርተዋል፡፡

ደኑ ከመጥፋቱ በፊት በዙሪያው ለሚገኙ አርሶ አደሮች የገቢ ምንጭ ከመሆኑም ባሻገር ለአካባቢው የአየር ንብረትና ብዝሀ ሕይወት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ነበረው፡፡

"የአካባቢው አርሶአደሮች በተፈጠረላቸው ግንዛቤ መሬት ከረገፈው የቀርከሃ ፍሬ የሚበቅሉ ትናንሽ ችግኞችን ከመንከባከብ ባለፈ የደኑን ክልል ከህገ ወጥ የመሬት ወረራ በጋራ እየተከላከሉ ይገኛሉ" ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በቡሌ ወረዳ የቀርከሃ ችግኝ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልፀው፥ በዘመናዊ የቀርከሃ ችግኝ አፈላልና አበዛዝ ዘዴዎች ላይ አርሶ አደሮች መሰልጠናቸውን አስረድተዋል፡፡

ደኑ በተፈጥሯዊ መንገድ ከመጥፋቱ በፊት አካባቢው ደጋማ የአየር ንብረት እንደነበረው የገለጹት ደግሞ በቡሌ ወረዳ የላባ ጋሻ ቀበሌ የተፈጥሮ ልማት ባለሙያ አቶ ስሜ ታደሰ ናቸው። 

በአሁኑ ወቅት አካባቢው ወደ ወይና ደጋ የአየር ፀባይ እየተቀየረ በመሆኑ ከጊዜ ወደጊዜ የአካባቢው ሙቀት እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አርሶአደሩ በራሱ ተነሳሽነት የእንክብካቤና ጥበቃ ሥራ እየሠራ መሆኑን የጠቀሱት ባለሙያው "በእኛ በኩልም በአርሶ አደሩ ላይ ያሉ የክህሎት ክፍተቶችን በመሙላት ኃላፊነታችንን እየተወጣን እንገኛለን" ብለዋል ፡፡

አርሶ አደሮች በበኩላቸው በደኑ ክልል ላይ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ እንዳይካሄድ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2010 የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ባለ በጀት የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚፈልጓቸውን እቃዎች በጥራት፤ በፍጥነትና በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ አለመሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።

ምክር ቤቱ የእቃ አቅራቢ ድርጅቶችንና ተጠቃሚ የመንግስት ተቋማትን በመደገፍ፣ በመከታተልና በመቆጣጠር ረገድ የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጠንካራ የአሰራር ስልቶችን ሊተገብር እንደሚገባ አሳስቧል።

በምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌደሬል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ባቀረበው የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የማዕቀፍ ግዥ የኮንትራት ውል አፈጻጸም፤ የክዋኔ እና የሒሳብ ኦዲት ሪፖርት ላይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር መክሯል።

የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ከተሰጠው ተልዕኮና ራዕይ አኳያ ለባለ በጀት የመንግስት ተቋማት  በጥራት፣ በፍጥነትና  በተመጣጣኝ ዋጋ እቃዎችን እያቀረበ አይደለም ብሏል ምክር ቤቱ። 

ባለ በጀት የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚፈልጓቸውን እቃዎች አስቀድመው እንዲያሳውቁና በዚያውም ልክ እንዲቀርቡላቸው ከማድረግና እቃ አቅራቢዎችን ከመደገፍና ከመከታተል  አኳያ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴም ደካማ መሆኑ በኦዲት ግኝቱ ተመላክቷል።

ከፍተኛ የትምሕርት ተቋማት አስፈላጊ እቃዎች በድርጅቱ አማካኝነት በጥራት፣ በፍጥነት፣ በአይነትና በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡላቸው እንዳልሆነ የሚናገሩት በትምሕርት ሚኒስቴር የውስጥ አዲተር አቶ መኮንን ጩንቻ "በበርካታ ዩንቨርሲቲዎች ውስጥ በማዕቀፍ ግዢ እጥረት ምክንያት ከፍተኛ እጥረት አለ" ይላሉ።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ወይንእሸት ገለሶ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት "እኛ የጠየቅነው ሌላ፤ የቀረብልን እቃ ሌላ" በሚል በተደጋጋሚ ቅሬታ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።

በርካታ ገንዘብ የፈሰሰባቸው እቃዎች በእቃ አቅራቢዎችና በተጠቃሚዎች መካከል ተናቦ መስራት ባለመቻሉ ለብክነት እየተዳረጉ እንደሆነም ገልጸዋል።

የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የክትትልና የቁጥጥር ስርዓቱን በማጠንከር ጉልሕ ሚናውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በእቃ አቅራቢዎችና በመንግስት መስሪያ ቤቶች መካከል ያለውን የላላ ግንኙነት ማጠናከርና በጥምረት በመስራት ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

'ተቋማቱ የግዥ እቅድ አለማቅረባቸው ለድርጅቱ እንደ እንቅፋት ሊጠቀስ አይገባም' ያሉት ዋና ኦዲተሩ እቃ ለማቅረብ ውል የገቡ አቅራቢዎች ውላቸውን በሚያፈርሱበት ጊዜ መቅጣትና እርምጃ መውሰድ እንደነበረበት ይገልጻሉ።

ወደፊትም ውል የሚያፈርሱ እቃ አቅራቢዎችን መቅጣትና እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ የጠቆሙት አቶ ገመቹ የግዢ ፍላጎትና እቅዳቸውን ለማያሳዉቁ ተቋማት እቃ የማቅረብ ግዴታ አለመኖሩን አመልክተዋል።

የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ አቅራቢዎች በገቡት ውል መሰረት እንዲያቀርቡ የማስተካከያና የቅጣት እርምጃም ጭምር እየተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።

ከ2008 እስከ 2010 ዓም ባለው የማዕቀፍ ግዥ ስምምነት የግዥ ፍላጎታቸውን ያቀረቡት ዩኒቨርሲቲዎች 16 ብቻ መሆናቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ 'ተቋማት የሚፈልጓቸውን እቃዎች በዝርዝር የማቅረብ ስንፍና አለባቸው' ብለዋል።

የግዥ መጓተት መኖሩን ያልካዱት አቶ ይገዙ ጨረታ ማውጣት፣ የቴክኒክ ግምገማ ማድረግ፣ ሪፖርት ማቅረብና ሌሎች ውስብስብ ቢሮክራሲዎች የመጓተቱ መንስዔ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የንግድ ስምምነቱ ከበርካታ አካላት ጋር የሚፈጸም በመሆኑ ጊዜው ሊጓተት እንደቻለም ይገልጻሉ።

ከባለ በጀት መስሪያ ቤቶች፣ ከአቅራቢዎች፣ ከተጠቃሚ መስሪያ ቤቶችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በየጊዜው በመገናኘት ምክክር እየተደረገ በጊዜ፣ በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ እቃ ለማቅረብ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር መጋቢት 27/2010 በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰከላ ወረዳ አርሶ አደሮች የሚያከናውኑት የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ የማሳቸውን የአፈር ለምነት በማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ እንዳስቻላቸው ተናገሩ።

በወረዳው የኮለል ለቻ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ስሜነህ ሞላልኝ እንደገለጹት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ከመጀመሩ በፊት ጋራ የበዛበት አካባቢያቸው የአፈር ለምነቱ የተሟጠጠ ነበር። 

በተሰራው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ የአካባቢው ልምላሜ በመመለሱ የማሳቸው አፈር ለምነት እንዲሻሻል አድርጓል፡፡

ጥቅሙን በመረዳታቸውም ባለፈው ጥር ወር በተጀመረው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ያለማንም ቀስቃሽ መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለአንድ ወር ያካሄዱትን የልማት ስራ አጠናቀው ለቀጣዩ የመኽር ልማት የእርሻ ስራ በማከናወን ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

በወረዳው የአባይ ሳንግብ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ወንድም ተሻለ በበኩላቸው በየዓመቱ የሚሰሩት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች የማሳቸው አፈር ለምነት መጨመር የሰብል ምርት መጠኑን እንዳሳደገላቸው ነው ያነሱት።

ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በ551 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ባለሙያ አቶ ፈጠነ መኮንን ተናግረዋል።

ስራው የተከናወባቸው 2 ሺህ 192 ተፋሰሶችም የአፈር ክለትን ከ77 ቶን ወደ 34 ቶን ዝቅ እንዲልና የውሃ ፍሰቱ እንዲጨምር ማስቻሉ በጥናት መረጋገጡን ጠቁመዋል።

ይህም የአፈር ለምነቱ እየተሻሻለ በመምጣቱ በሄክታር በአማካኝ ዘጠኝ ኩንታል የምርት ጭማሪ እንዲኖር ማድረጉን አስረድተዋል።

በዘንድሮው የበጋ ወራትም ከግማሽ ሚሊየን የሚበልጡ የዞኑ አርሶ አደሮች 40 ሺህ ሄክታር በሚጠጋ የማሳና የጋራ ላይ ዕርከን ስራዎች መከናወናቸውንም አስታውቀዋል። 

4 ሺህ 452 ሄክታር የተራቆተ መሬትን በመከለል ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ እንዲጠበቅ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።  

Published in አካባቢ

ባህር ዳር  መጋቢት 27/2010 ከተሞች ያሉባቸውን የመሰረተ ልማት ችግሮች ለይቶ በመፍታት የህዝቡን ዘላቂ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መርሀ ግብር ቀርጾ እየሰራ መሆኑን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አስታወቀ።

 ለመርሃ ግበሩ ማስፈፀሚያም ከዓለም ባንክና ከኢትዮጵያ መንግስት 859 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መመደቡ ታውቋል።

 በአማራ ክልል በመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ከሚሆኑ 32 ከተሞች የተውጣጡ አመራሮች በመርሃ ግበሩ አተገባበር ላይ በባህር ዳር ከተማ መክረዋል።

 የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ ዶክተር አምባቸው መኮንን በእዚህ ወቅት እንዳሉት በሀገር ደረጃ 117 ከተሞች በዓለም ባንክ መርሃ ግብር ታቅፈው ተጠቃሚ እንዲሆኑና የመሰረተ ልማት ስራቸውን እንዲያፋጥኑ እየተሰራ ነው።

 ከነዚህ ከተሞች መካከል 44ቱ ቀደም ባሉት ዓመታት በመርሃ ግብሩ ታቅፈው ተጠቃሚ መሆን የጀመሩ ሲሆን 73ቱ በአዲስ ተመልምለው ተጠቃሚ የሚሆኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 ይህም ከተሞች በፕላን እንዲመሩ፣ የመሰረተ ልማት ስራቸውን እንዲያሟሉ፣ ውብ፣ ፅዱና አረንጓዴ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ ገፅታቸውን ለመቀየርና የወጣቶችን ኑሮ ለማሻሻል ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል።

 ከተሞች በአምስት ዓመት ውስጥ ልማቱን እንዲያንቀሳቅሱ ምቹ ሁኔታ በመፍጠርና የራሳቸውን የፋይናንስ ምንጭ አቅም ኖሯቸው ልማቱን ተረክበው እንዲያስቀጥሉ ማድረግ የመርሃ ግብሩ ዓላማ መሆኑንም አስረድተዋል።

 "የመርሃ ግብሩ ተግባራዊ መሆን ለከተሞች ፈጣን ዕድገት፣ ለበርካታ ወጣቶችና ሴቶች የስራ ዕድል መፍጠሪያ ከመሆኑ በተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለማመንጨት የሚያግዝ ነው" ብለዋል።

 አዲስ ተጠቃሚ በሚሆኑ ከተሞች የሚገኙ አመራሮች በፍጥነት ዕቅዳቸውን አዘጋጅተው ወደተግባር በመግባት ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት መስራት እንሚኖርባቸውም አሳስበዋል።

 የአማራ ክልል ከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ የከተሞች የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ አስተባባሪ አቶ አሻግሬ አቤልነህ በበኩላቸው እንዳሉት በክልሉ 32 ከተሞች በዓለም ባንክ መርሃ ግብር ተጠቃሚ ይሆናሉ።

 ተጠቃሚ ከሚሆኑ ከተሞች መካከልም 10ሩ ቀደም ካሉት ዓመታት ጀምሩ ተጠቃሚ እየሆኑ የሚገኙ ሲሆን 22ቱ በመርሃ ግብሩ ለመታቀፍ መስፈርቱን አሟልተው የተመረጡ ናቸው።

 የህዝብ ቁጥር፣ የመፈጸም አቅም፣ የገቢ አሰባሰብ፣ ዕቅድና ሌሎች መስፈርቶችን በተሻለ ያሟሉ ከተሞች ተለይተው የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መመረጣቸውን ተናግረዋል።

 "በልማት ሥራው የኮብል ስቶን፣ የጠጠር መንገድ ጥገናና የአዳዲስ መንገድ ሥራ እንዲሁም የመብራትና የውሃ መስመር ዝርጋታና ሌሎች ስራዎች ይከናወናሉ" ብለዋል።

 ቀደም ብለው ተጠቃሚ በሆኑ ከተሞች 70 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ያስታወሱት አቶ አሻግሬ፣ አዲሶቹ ወደሥራ ሲገቡ ከዕጥፍ በላይ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።

 ከተማቸው የዓለም ባንክ መርሃ ግበር ተጠቃሚ እንድትሆን ሲያቀርቡት የነበረው ጥያቄ መልስ በማግኘቱ መደሰታቸውን የተናገሩት ደግሞ የአዲስ ዘመን ከተማ አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ አቶ አዘዘ ሞላ ናቸው።

 ሥራውን ለመጀመር የሚያስችሉ ግብዓቶችን ማሟላታቸውንና በቅድሚያም የመንገድና የጎርፍ ማፋሰሻ ሥራዎችን ቀድመው ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

 የተመደበው 859 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለቀጣይ አምስት ተከታታይ ዓመታት ለመርሃ ግብሩ ማስፈፀሚያ የሚውል ሲሆን በውይይቱም በአማራ ክልል በመርሃ ግብሩ የተቀፉ ከተሞች አመራር አካላት መሳተፋቸውን የዘገው ኢዜአ ነው።

Published in ኢኮኖሚ

ደሴ መጋቢት 27/2010 የ11 ዓመቷ ታዳጊ ዶሮ በጨረታ ሸጣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ ስትታትር ከረመች። ጥረቷም ተሳክቶ አንድ አውራ ዶሮ በሀገሪቱ ታሪክ ባልተለመደ ሁኔታ በ17 ሺህ ብር በመሸጥ  ለግድቡ ግንባታ አበርክታለች።

ሰሚራ ኢብራሂም በደቡብ ወሎ ዞን  ከላላ ከተማ   የአራተኛ ክፍል ተማሪ ነች፤ አባቷ የሰጧትን አውራ ዶሮ ለጨረታ አቅርባለች ፡፡

ለሶስት ዙር ያጨረተችው የዚችው ታዳጊ ቀና ዓላማን የተረዱት የአካባቢው ህዝብም በመሳተፍ ዶሮውን 17ሺህ ብር  ገዝተውታል፡፡ ፡

"አባይ የሀገሬ ሃብት በመሆኑ ጥቅም እንዲሰጥ እፈልጋለሁ" የምትለው ታዳጊ ሰሚራ አሁንም አቅሟ በፈቀደ ከቤተሰቧ የተበረከተላትን ዶሮ በመሸጥ ያገኘችውን 17ሺህ ብር ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ እንዲውል ማበርከቷን ለኢዜአ ተናግራለች፡፡የግደቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅም ድጋፏን እንደምትቀጥልም በመጥቀስ፡፡

ወላጅ እናቷ ወይዘሮ ወሰን ደምስ ልጃቸው  ለአባይ ያላትን ተቆርቋሪነት አድንቀው ፍላጎቷን ለማሳካት የአቅማቸውን ያህል ወደፊትም ለመደገፍ መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል፡፡በደሴ ከተማ ሰኞ ገበያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ  ሰላም አያሌው በበኩሏ ወላጆቿ ለትራንስፖርት የሚሰጧትን ገንዘብ በማጠራቀም የመቶ ብር ቦንድ መግዛቷን ገልጻለች፡፡

"ገንዘቡ ጥቂት ቢሆንም የቦንድ ግዥው እኔና እኔን መሰል ታዳጊዎች  ለሀገራችን ያለንን ተቆርቋሪነት የምናሳይበት እድል ስለፈጠረልን ደስተኛ ነኝ" ብላለች፡፡

በዞኑ የተሰበሰበ ገንዘብ  

የደቡብ ወሎ ዞን መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ የህዝብና ሚዲያ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ሉሌ ተክሌ እንዳሉት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ እንዲውል በተያዘው ዓመት 35 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡የህዳሴው ችቦ ዘንድሮ አቀባበል በተደረገበት ወቅት በዞኑና በደሴ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ የህብረተሰብ ከፍሎች ከአራት ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ  ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል፡፡ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ  የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ አንስቶ ከ172 ሚሊዮን ብር በላይ ከዞኑ ህብረተሰብ ድጋፍ መደረጉም ተመልክቷል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ 7ኛ ዓመት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበቅን ቀን ምክንያት በማድረግም በደቡብ ወሎ ዞን  ፡የተለያዩ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች እየተካሄዱ እንደሚገኙ  ታውቋል።

  የግድቡን ከደለል ለመታደግ

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው በበኩላቸው በደቡብ ወሎ  ከሚገኙ ሦስት ሺህ 542 ተፋሰሶች ውስጥ 82 በመቶ የሚሆኑት ከአባይ ተፋሰስ ጋር ቀጥታ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

 ግባታው  ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ በተፋሰሶቹ ላይ በህብረተቡ ተሳትፎ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መከናወኑን አመልክተዋል፡፡

 የተከናወነው ስራም 791ሺህ  ሄክታር መሬት የሸፈነ መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊው  ተፋሰሶቹን በስነ ህይወት የማጠናከር ስራ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2010 የመንግሥት የልማት ድርጅት የነበረው የአሰላ ብቅል ፋብሪካ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ዋጋ ለኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ፌዴሬሽን በግል ይዞታነት ተላለፈ።

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴና የፌዴሬሽኑ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ትርፌሳ ነጋሳ የርክክብ ስምምነቱን ዛሬ ተፈራርመዋል።

ፋብሪካው የካቲት 5 ቀን 2010 ዓ.ም ለጨረታ ቀርቦ አራት ድርጅቶች የተሳተፉ ሲሆን፥ ፌዴሬሽኑ በ1 ቢሊየን 343 ሚሊየን 660 ብር ጨረታውን አሸንፏል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ በፊርማ ስነስርዓቱ ወቅት እንደገለጹት፥ በፕራይቬታይዜሽን አዋጁ መሰረት ፌዴሬሽኑ የጨረታውን 35 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ ፈጽሟል።

ቀሪውን 65 በመቶ ደግሞ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ከፍሎ ለማጠናቀቅ መስማማታቸውን ነው የተናገሩት።

ፋብሪካው ከዚህ ቀደም የገብስ ግብዓት ከአካባቢው አርሶ አደሮች ይቀርብለት እንደነበር አስታውሰው፥ እነዚህ አርሶ አደሮች በፌዴሬሽኑ ተሰባስበው የፋብሪካው ባለቤት መሆናቸውን አድንቀዋል።

በሀገሪቱ የቢራ ፋብሪካዎች መስፋፋት የብቅል አቅርቦት ፍላጎት እንዲጎለብት በማድረጉ ፌዴሬሽኑ ይህንን ፍላጎት ለማሟላት ይሰራል ያሉት ሚኒስትሩ፥ አርሶ አደሮቹ ምርትና ምርታማነታቸውን በማስፋት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ፌዴሬሽን ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ትርፌሳ ነጋሳ በበኩላቸው፥ አርሶ አደሮች ከፋብሪካው ጋር በተፈጠረው የገበያ ትስስር ተጠቃሚነታቸውን ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ያለውን የገበያ ፍላጎት ለማሟላት ፋብሪካውን የማስፋፋትና አደረጃጀቱን ጠንካራ የማድረግ ስራ በፌዴሬሽኑ ይሰራል ብለዋል።

ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ከ370 በላይ ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታነት በማዘዋወር ከ40 ቢሊየን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ መደረጉን መረጃዎች ያሳያሉ።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ  መጋቢት 27/2010 የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን ለማሳካት ያለው አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገመገመ።

ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በበኩሉ በበጀት ዓመቱ የተሻለ ሥራ መስራቱንና ሀሳቡን እንደማይቀበለው ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

የምክር ቤቱ የገቢዎችና ጉምሩክ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት፤ ባለስልጣኑ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የግብር ገቢው ከጠቅላላው የአገሪቷ ምርት 17 ነጥብ 9 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው ለማስቻል ያቀደ ቢሆንም ያለው አፈጻጸም 12 ነጥብ 4 በመቶ ነው።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ ናፈቁሸ ደሴ እንደተናገሩት፤ የአገሪቷን ገቢ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የኢትዮጵያ ግብር አሰባሰብ ከሰሀራ በታች ከሚገኙ ዝቅተኛ ደረጃ ካላቸው ታንዛኒያና ኡጋንዳን ከመሳሰሉ አገሮች ተርታ እንዲመደብ አድርጎታል።

የኮንትሮባንድ ንግድን በሚመለከት፣ ከወደብ ጋር የተያያዙ ስራዎችን በማከናወንና "ሕጋዊ የግብይት ደረሰኝ ሥራን በሚመለከት ባለስልጣኑ ድክመቶች ተስተውለውበታል" ብለዋል።

የፌዴራልና የክልል ገቢዎች ተቋማት ወጥ በሆነ አሰራር ተናቦ በመስራትና ችግሮች ተፈፅመው ሲገኙ እርምጃ በመውሰድ በኩልም ክፍተት መኖሩ ለአፈጻጸሙ ማነስ እንደምክንያት ጠቅሰዋል።

ባለስልጠኑ በበኩሉ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን ለማሳካት ያለው አፈፃፀም ዝቅተኛ ነው መባሉን አልተቀበለውም።

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞገስ ባልቻ፤ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን ለማሳካት 'ባለስልጣኑ ያለው አፈፃፀም ዝቅተኛ ነው' የሚለው የቋሚ ኮሚቴው እይታ ጥቂት ሰዎችን በመጠየቅ የተሰራ ሪፖርት በመሆኑ ተቋሙ እንደማይቀበለው ተናግረዋል።

"የተሰበሰበው መረጃ የባለስልጣኑን የዕቅድ አፈጻጸም ዝቅተኛ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ የሚያደርስ አይደለም" ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ሞግተዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ባቀረበው ሪፖርት ባለስልጣኑ በሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያዎችና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆን መንስዔ እየሆነ ነው።

በሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያዎችና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የሚስተዋሉ ችግሮች እየተበራከቱ መምጣታቸውም በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል

ወይዘሮ ናፈቁሸ ደሴ እንደተናገሩት፣  በመስክ ምልከታ፣ ቅሬታዎችን በመቀበልና ከጥናት የተገኙ ሰነዶችን በመመርመር የተገኙ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት የባለስልጣኑ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ አቅርቦት የደንበኞችን ፍላጎት ማሟላት አልቻለም።

የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ እንዲጠቀሙ ህጉ ከሚፈቅድላቸው የደረጃ ሀ እና የደረጃ ለ ግብር ከፋዮች መካከል ተጠቃሚ የሆኑት 65 በመቶ ብቻ ናቸው።

አገልግሎት ላይ ያሉት የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያዎች አብዛኛዎቹ ከባለስልጣን መስሪያ ቤት ጋር የተሳሰሩ አለመሆናቸው፣ በየጊዜውም ክትትልና ድጋፍ አለመደረጉና ዓመታዊ የቴክኒክ ምርመራ ወቅቱን ጠብቆ አለመካሄዱ ክፍተት እንደሆነ ቋሚ ኮሚቴው በሪፖርቱ አመልክቷል።

ዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ እንዲኖር በማድረግ በኩልም የተሻሉ ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም በተደጋጋሚ የአገልግሎት (ሲስተም) መቆራረጥ ችግር ስለሚስተዋል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ተጠይቋል።

ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በበጀት ዓመቱ የተሻለ ሥራ መስራቱን ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

በሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያዎችና በዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂዎች በኩል የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ አሰራሮች መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

ለዚህም ስኬት ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር፣ ከከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር፣  ከባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አቅርቦት ድርጅት፣ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከንግድ ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢዎችና ጉምሩክ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባለስልጣኑን የበጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀም በሚመለከት የቀረበውን መነሻ ጽሁፍ ተከትሎ ባለድርሻ አካላት ሀሳባቸውን አቅርበዋል።

ከንግድ ሚኒስቴርና  ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን የመጡ የውይይቱ ተሳታፊዎች በሽያጭ መመዝገቢያና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም በኩል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አሰራሩን ማሻሻል እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከርና በጋራ ለመስራት ማቀዱም ችግሩን እንደሚፈታው እምነታቸውን ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ ገቢ በመሰብሰብ ከዓመት ዓመት የተሻሉ ተግባራትን ቢያከናውንም የአገሪቷን የፋይናንስ ወጪ ከራስ ገቢ ለመሸፈን የተያዘው ዕቅድ ኃላፊነት የተጣለበት በመሆኑ የበለጠ ሊሰራ እንደሚገባ ተገልጿል።

Published in ኢኮኖሚ

ሃዋሳ መጋቢት 27/2010 በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርት የተሰማሩ ባለሀብቶች በመጋቢት ወር ወደ ውጪ ከላኩት ምርት ከ3 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ከሰባት ሳምንት በፊት በፓርኩ ውስጥ ቲሸርት በማምረት ሥራ የተሰማራው ቤስት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ካምፓኒ የመጀመሪያ ምርቱን ትናንት ወደ አሜሪካ ልኳል፡፡ 

ካምፓኒው የመጀመሪያ የወጪ ንግዱን በላከበት ስነስርዓት ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍጹም አረጋ ለኢዜአ እንዳሉት በፓርኩ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ መሆን ባለሀብቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጪ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ አድርጓል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኩ ሥራ ከመጀመሩ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የገባ አንድ ኩባንያ ሥራ ለመጀመር መሬትና የኃይል አቅርቦት ለማግኘትና ለሌሎች  ውጣ ውረዶች የተወሰኑ ጊዜያት ያለስራ ሊያሳልፍ ይችል ነበር ብለዋል፡፡

ከሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ቀደም ሲል በወር ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በታች ወጋ ያለው ምርት ኤክስፖርት ሲደርግ መቆየቱንና ከታህሳስ እስከ የካቲት በአማካይ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ምርት ኤክስፖርት ማድረግ ተችሎ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በተያዘው መጋቢት ወር ከሦስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው ምርት መላኩንና በሚቀጥለው ወርም ገንዘቡ ወደ አራት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍ እንደሚል ኮሚሽነር ፍጹም በእርግጠኘነት ገልጸዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኩ ከሰባት ሳምንት በፊት ሥራ የጀመረው ቤስት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ካማፓኒ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ጎተም ሬዲ የውጭ ባለሀብቶችን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ጥሩ ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በተለይ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ኢሚግሬሽንና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ባለሀብቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማምጣት የጎላ ሥራ ሲሰሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከመሰረተ ልማት አቅርቦት አንጻር የሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በዓለም ተመራጭ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ካምፓኒው በቀጣይ በየሳምንቱ አንድ ኮንቴነር ቲሸርት ወደ አሜሪካ በመላክ በወር እስከ 500 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ለማስገኘት ግብ ይዞ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ካምፓኒው በአሁኑ ወቅት ከ650 በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ ተጨማሪ ማሽኖችን በማስመጣት የሠራተኛ ኃይሉን በሁለት እጥፍ እንደሚያሳድግ ተጠቁሟል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ 27/2010 በውቅሮ ከተማ ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የቆየው  የመላው ትግራይ ወጣቶች የአትሌቲክስ ዓመታዊ ሻምፒዮና ውድድር ትናንት ተጠናቀቀ።

በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች፣ ከተሞችና ክለቦች መካከል በተካሄደው ሻምፒዮና በሩጫ፣ዝላይና ውርወራ ውድደሮች ከ600 በላይ ወንድና ሴት ስፖርተኞች ተሳትፈዋል።

በከተሞችና ወረዳዎች  መካከል በተካሄደ አጠቃላይ አትሌቲክስ ውድድር በሴቶች ውቅሮ ከተማ አንደኛ በመሆን ዋንጫ ሲያነሳ፥ ማይጨውና አክሱም ከተሞች ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን አጠናቀዋል።

በወንዶች አጠቃላይ አትሌቲክስ ውድድር ሽሬ እንደስላሴ አንደኛ በመሆን ዋንጫ ሲያገኝ ማይጨውና እንደመሆኒ ከተሞች ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነዋል።

በተመሳሳይ በወንዶች የግማሽ ማራቶን ሩጫ እንደርታ ወረዳ ውደደሩን በበላይነት ሲያጠናቅቅ፥ ዓዲግራት ከተማና ኦፍላ ወረዳ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ይዘዋል።

በሌላ በኩል በክለቦች መካከል በተደረገ አጠቃላይ አትሌቲክስ ውድድር በሁለቱም ፆታ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ በአንደኛነት ዋንጫ ሲያነሳ፥ በሴቶች ትራንስ ኢትዮጵያና ጉና እንዲሁም በወንዶች መሰቦ ስሚንቶና ጉና ሁለተኛና ሶሰተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቀዋል።

ውድድሩ በዘርፉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ክልሉን የሚወክሉ ምርጥ ስፖርተኞችን ለመምረጥ ያለመ መሆኑን የክልሉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ማሞ ገልፀዋል።

ከመጋቢት 19 ቀን 2010 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በተካሄደው ውድድር በሁለቱም ፆታዎች ጥሩ ፉክክር መታየቱንና ተሰፋ ሰጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር አቶ ወልደገብረኤል መዝገቡ ለአሸናፊዎች ዋንጫና ሌሎች ሽልማቶችን  አበርክተዋል።

Published in ስፖርት
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን