አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 04 April 2018

ጎንደር መጋቢት 26/2010 ከ500 በላይ የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች  በድህረ ምርት አሰባሰብ የሚታየውን የምርት ብክነት ለመቀነስ  ለአርሶ አደሩ የግብርና መካናይዜሽን አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን  የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ገለጸ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር ለኢዜአ እንደተናገሩት አገልግሎቱን እየሰጡ ያሉት  ማህበራትና ዩኒየኖች በአማራ፣ በኦሮሚያ ፣በትግራይ እና  በደቡብ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች ውስጥ ነው፡፡

ማህበራቱና ዩኒየኖቹ እየሰጡ ካሉት አገልግሎት መካከል የበቆሎ መፈልፈያና የጤፍ መውቂያ እንዲሁም የምርት ማጨጃና መሰብሰቢያ ኮምባይነሮች የኪራይ አገልግሎቶች ይገኙባቸዋል፡፡

የግብርና መካናይዜሽን አገልግሎቱ ከዚህ ቀደም አርሶአደሩ በግለሰቦች አንድ ኩንታል ስንዴ ለመውቃት ይከፍል የነበረውን 130 ብር ማህበራቱ ወደ 70 ብር ዝቅ እንዲል ማድረግ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

"የድህረ ምርት አሰባሰብ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መደገፉ አርሶአደሩ በባህላዊ መንገድ ምርቱን በመሰብሰብ ይባክን የነበረውን ከ20 እስከ 30 በመቶ የምርት ብክነት ለማስቀረት እገዛው የላቀ ነው "ብለዋል፡፡

በቅድመ ምርት የእርሻ ስራም አርሶአደሩና ቤተሰቡ ጭምር የሚያጠፉትን  ጉልበትና ጊዜን በመቆጠብ ረገድ የትራክተር እርሻን በማስፋፋት በኩል ማህበራቱ የማይተካ ሚና እየተጫወቱ ናቸው፡፡ 

ኤጀንሲው የማህበራቱን ተሳትፎ ለመደገፍና ለማጠናከር ብሎም ተደራሽነታቸውን ለማስፋት በፌደራል ደረጃ ቡድን በማቋቋም ክልሎችን የማገዝ  ስራ እያከናወነ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት በክልሎች  በሚገኙ 500 የህብረት ስራ ማህበራት የተጀመረውን የግብርና መካናይዜሽን አገልግሎት ለማስፋት የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍን በማጠናከር ቁጥራቸውን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በጎንደር ከተማ የሚገኘው የጸሃይ ገበሬዎች የህብረት ስራ ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ እንዳልክ አቤ በሰሊጥ ምርት ላይ የሚታየውን የድህረ ምርት ጥራት መጓደል ለማቃለል ዘመናዊ የሰሊጥ ማበጠሪያና ማሸጊያ ፋብሪካ ማቋቋቸውን ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው በሰዓት እስከ 70 ኩንታል የማበጠር አቅም ሲኖረው ለማህበራት ፣ለባለሀብቶችና ለአርሶአደሮች በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን እየሰጠ ነው፡፡

ከፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በሀገሪቱ 18 ሚሊዮን የሚጠጉ አርሶና አርብቶአደሮችን በአባልነት ያቀፉ 83ሺ የህብረት ስራ ማህበራትና 380 ዩንየኖች ይገኛሉ፤ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታልም አላቸው፡፡

"የህብረት ስራ ማህበራት ግብይት ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት"በሚል መሪ ሀሳብ  32 መሰረታዊ ማህበራትና 4 ዩንየኖች የተካፈሉበት ሲፖዚየም፣ አውደ ርዕይና ባዛር ባለፈው አርብ በጎንደር ከተማ ለህዝብ ክፍት መደረጉን በወቅቱ ተገልጿል፡፡   

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ድሬደዋ መጋቢት 26/2010 የህዝቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና የወጣቶችን የሥራ ዕድል ለማስፋት ቅንጅታዊ ሥራን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የድሬዳዋ ኦህዴድ አመራሮች ገለጹ፡፡

የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች በበኩላቸው የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ለኦሮሞ ህዝብ ሁለንተናዊ መብቶች መረጋገጥ ያከናወናቸው ተግባራት እንዲጠናከሩ ተሳትፏቸውን ለማጎልበት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

በሺህ የሚቆጠሩ የኦህዴድ አባላትና ደጋፊዎች፣ የድሬዳዋ የሀገር ሽማግሌዎችና አመራሮች ድርጅቱ የተመሰረተበትን 28ተኛ ዓመት በዓል በደመቀ ሥነ-ሥርዓት ትናንት አክብረዋል፡፡

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኦህዴድ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈጅረዲን ሙሣ እንደተናገሩት፣ ኦህዴድ በተበተታተነ መንገድ ሲኪያሄድ የነበረውን ትግል በማቀናጀት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።

የኦሮሞ ህዝብ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ መብቶች እንዲከበሩለት ባለፉት 28 ዓመታት ውጤታማ ተግባራት ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ ዘንድሮ የሚከበረው የምስረታ በዓል የድርጅቱ አዳዲስ አመራሮች ሀገርን የመምራት ታላቅ ኃላፊነት የተረከቡበት በመሆኑ ደስታውንና

ኃላፊነቱን ድርብ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

ኦህዴድ በድሬዳዋም ሆነ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለወጣቶች የሚፈጥረውን የሥራ ዕድል በስፋትና በተቀናጀ መንገድ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፣ የኦሮሞ ህዝብ ተጠቃሚነቱ እንዲጎለብት ከድርጀቱ ጎን እንዲሰለፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የኦህዴድ ሊቀመንበርና የኢህአዴግ ሰብሳቢ አቶ አብደላ አህመድ በበኩላቸው "ኦህዴድ ከጥልቅ ተሃድሶ ማግስት ጀምሮ ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የተቀናጀ ጥረት እያደረገ ይገኛል" ብለዋል።

ይህን እንቅስቃሴ በላቀ ውጤት በማጀብ ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ድርጅቱ በአዳዲስ ወጣቶችና ጎልማሶች መመራት መጀመሩ ወሳኝ ሚና እንዳለው ነው የገለጹት።

"የኦህዴድ አባላትና ደጋፊዎች ከሌሎች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ያለንን አንድነት በማጽናት ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግና ለወጣቱ  የተሻለ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ማጠናከር አለብን " ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን በበኩላቸው "ኦህዴድ የኦሮሞ ህዝብን ብቻ ሳይሆን የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የልማት፣ የሰብአዊና የዴሞክራሲያዊ መብት ጥያቄዎች ለመመለስ ከሌሎች እህትና አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን አኩሪ ውጤት አስመዝግቧል" ብለዋል፡፡

በ28ተኛው የኦህዴድ የምስረታ በዓል ላይ የተገኙት የድሬዳዋ ኢህአዴግ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት፣ የኢሶህዴፓ እና የሐብሊ ተወካዮች ከደርጅቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጽናት የተሸለ እድገትና ብልጽግና ለማስመዝገብ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በሀገር ሽማግሌዎችና አባቶች ምርቃትና መልዕክት ማክበር በተጀመረው በዓል ላይ የተገኙት የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች የመልካም አስተዳደርና የልማት ውጥኖቹን ከዳር ለማድረስ ከኦህዴድ ጎን በመቆም በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

በኦህዴድ የምስረታ በዓል ላይ የድርጅቱን ቀጣይ ተግባራት ለማጠናከር የሚያስችል ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።

Published in ፖለቲካ

አዳማ መጋቢት 26/2010 በኦሮሚያ ክልል ለ2010 /2011 የምርት ዘመን ምርታማነትን ለመጨመር የተዘጋጀ አዲስ የግብርና እድገት ፓኬጅ የትግበራ ንቅናቄ ዝግጅት መጀመሩን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ገለጸ።

በፓኬጁ አተገባበር ላይ ከክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች የተወጣጡ የግብርና ሴክተር ስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተዘጋጀ ስልጠና በአዳማ ከተማ አባ ገዳ አዳራሸ ተካሄዷል።

በዚህ ወቅት የቢሮው ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በተለይም ለኢዜአ እንደገለጹት በበልግና በመኸር አዝመራ ዝግጅት አርሶ አደሩ ሰለፓኬጁ ውጤታማነት በቂ ክህሎትና ግንዛቤ እንዲያገኝ ቅድሚያ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገቢውን እውቀት ለማስጨበጥ እየተሰራ ነው።

ከአርሶ አደሩ ጀምሮ ያለው ፈፃሚ አካል በእውቅትና በአመለካከት ማዘጋጀት ለምርትና ምርታማነት እድገት ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ በ2009/2010 የምርት ዘመን በዋና ዋና ሰብል ከ178 ሚሊዮን ኩንታል በላይ መሰብስብ መቻሉንም ተናግረዋል።

ለ2010 /2011 የምርት ዘመን ከ200 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለማምረት ታቅዷል።

ለእቅዱ ውጤታማነት በአዲስ የግብርና ዕድገት ፓኬጅ አተገባበር ዙሪያ በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ሴክተር የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች  ግልፅ ግንዛቤ አግኝተው ለተግባራዊነት እንዲረባረቡ የንቅናቄው ዝግጅት መጀመሩን የቢሮው ኃላፊ አስረድተዋል።

"የተጀመረው ንቅናቄ በክልሉ በዋና ዋና ሰብል  ከ25 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የምርት ጭማሪ ለማግኘት  ጭምር ነው" ብለዋል።

አቶ ዳባ እንዳሉት አርሶ አደሩ የመካናይዜሽን አገልግሎት በስፋት ተጠቃሚ እንዲሆንና ምርታማነትን የሚያሳድጉ  የግብርና ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ እንዲያገኝ እየተሰራ ነው።

ለምርት ዘመኑ በእቅድ ከተያዘው አራት ሚሊዮን 200ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር  ውስጥ እስካሁን  ከ2 ሚሊዮን 500ሺህ ኩንታል በላይ በዩኒየኖች በኩል ወደ የአካባቢው ተጓጉዞ መድረሱን አመልክተዋል።

አርሶ አደሮች ፣የልማት ጣቢያ ሰራተኞችና  ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ  ከ6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ስልጠና ይሰጣቸዋል ተብሏል፡፡

ከስልጠናው ተሳታፊዎች  መካከል የአርሲ ዞን እርሻና የፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መላኩ ታምሩ በበኩላቸው "ስልጠናው አዲሱን የግብርና ዕድገት ፓኬጅ ለመተግበር ግንዛቤና  ክህሎት የተገኘበት ነው "ብለዋል።

ለመጪው የመኸር ወቅት በግብአትነት ለማዋል በዞኑ በእቅድ ከያዙት ከ400ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ውስጥ እስካሁን ከግማሽ በላይ በየአካባቢው ዩኒየኖች መድረሱን ተናግረዋል፡፡

ያጋጠመውን የመካናይዜሽንና የዩሪያ ማዳበሪያ እጥረት ችግር  ለመፍታት ከክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ   ጋር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውንም አቶ መላኩ ጠቁመዋል፡፡

"ስልጠናው በአዲሱ የግብርና እድገት ፓኬጅ  አተገባበር ላይ  አርሶ አደሩን ማንቀሳቀስ የሚያስችል ነው"  ያሉት ደግሞ የምስራቅ ወለጋ ዞን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ምክትል  ኃላፊ አቶ ዘውዴ መኮንን ናቸው።

የአፈር ማዳበሪያ  እስካሁን 163 ሺህ ኩንታል ለአርሶ አደሩ ማቅረብ መቻሉን አመልክተው ቀሪውም በሂደት ላይ  እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡ 

ለሶስት ቀናት በተዘጋጀውና ትናንት በተጠናቀቀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በክልሉ 20 ዞኖች እና ከ300 በላይ ወረዳዎች የተወጣጡ ከ2ሺህ በላይ  የግብርና ሴክተር የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ደሴ/ደብረማርቆስ/ሶዶ መጋቢት 26/2010 አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለሰነቋቸው አገራዊ ራዕይ እውን መሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ በአማራና ደቡብ ክልል የሚገኙ የሶስት ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የከሚሴ፣ የደብረ ማርቆስና የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግሩ የአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እያበበ ለመምጣቱ ማሳያ ነው።

በከሚሴ ከተማ ቀበሌ 06 ነዋሪ አቶ ጎበዜ ወሌ በአገሪቱ የተጀመረው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የዴሞክራሲ ባህል እያደገ መምጣቱ አመልካች ነው ብለዋል።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያደረጉት ንግግርም አገራዊ አንድነትን ለማጠናከርና የህግ የበለይነትን ለማረጋገጥ ያላቸውን ቁርጠኛ አቋም ያንጸባረቁበት እንደሆነም አስታውቀዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ከብሔር ጋር ተያይዞ የሚነሱ አለመግባባቶችን በሰለጠነ አግባብ ለመፍታት ሁሉም አካላት መረባረብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በመካከለኛና ዝቅተኛ አመራር በሚፈጠረው የአፈጻጸም ክፍተት የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ የድርጊቱ ተዋናይ አመራሮች በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበት ጠንካራ አሰራር ሊዘረጋ እንደሚገባ የገለፁት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ አቶ ለማ ደጀኔ ናቸው።

በከሚሴ ከተማ የቀበሌ 06 ነዋሪ ወጣት ኢዮብ ስሜነህ በበኩሉ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች በሰለጠኑበት የትምህርት መስክ ህዝባቸውንና አገራቸውን የሚያገለግሉበትን ስልት በመቀየስ አገሪቱ የጀመረችውን እድገት ያስቀጥላሉ የሚል እምነት እንዳለው ገልጿል፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ አቶ ታሪኩ በላቸው እንዳሉት አዲሱ መሪ የአገሪቱን ህዝቦች ለዘመናት የቆየው የመተሳሰብና የመቻቻል ባህል ለማጠናከርና  የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ለማፋጠን በትጋት ይሰራሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ ዝማም ሞላ በበኩላቸው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሁሉም በላይ አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ያላቸው ቁርጠኝነት እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል፡፡

ዶክተር አብይ አገሪቱ የጀመረችውን የልማትና የእድገት ጉዞ ለማስቀጠል በሚያደርጉት ጥረት የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸውን እውቀትና ክህሎት እንዲሁም ቀና አመለካከት ተጠቅመው ሀገሪቱ ከሌሎች ሀገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት ያጠናክራሉ ያሉት አቶ እንዳለው ይርጋ በአገሪቱ የተሻለ እድገት እንዲመጣ በማድረግ በህዝብ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት ይወጣሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ለህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ችግር መነሻ የሆኑ ምክንያቶችን በመለየት እና ፈጥኖ በማስተካከል ህብረተሰቡ የሚጠብቀው ለውጥ እንዲመጣ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ስራ እንደሚጠበቃቸውም ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግሩ የአገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት እያበበ ለመምጣቱ ማሳያ መሆኑን የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡

በወላይታ ሶዶ ከተማ የኪዳነ ምህረት ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገብረሚካኤል ጉዴታ ለኢዜአ እንደገለጹት  ሰላማዊ የልጣን ሽግግር መደረጉ የተጀመረው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት እያደገ መምጣቱን ያሳያል፡፡

አዲሱ  ጠቅላይ ሚኒስትር ይከናወናሉ ብለው ላነሷቸው ተግባራት ስኬታማነት ሁሉም  ኢትዮጵዊ በየተሰማራበት የስራ መስክ ጠንክሮ በመስራት ሊደግፋቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የሰላም መንደር ነዋሪ ወጣት ተስፋዬ ዙላ በበኩሉ  የዴሞክራሲ መርህ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መተግበሩና ኢህአደግም ህዝባዊነቱን በተግባር በማረጋገጡ ደስታ እንደተሰማው ገልጿል፡፡

የስልጣን ሽግግሩ ያለምንም እንከን በጋራ መግባባት መከናወኑ በግለሰቦች የስልጣን ጥማት በአንዳንድ አካላት ላይ ተከስቶ የነበረውን ያለመተማን ስሜት ለመቅረፍ መንግስት የሄደበት በሳል እርምጃ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር መፈጸሙ ከሁሉም በላይ ሰላምን ለማስፈንና ለማረጋገጥ ሚናው ከፍተኛ ነው ያለው ደግሞ በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጤና ሳይንስ የ4ኛ ዓመት ተማሪ አቤል ዳንኤል ነው፡፡

''ሃገሪቱ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ጎዳና ላይ በመሆኗ ዜጎቿ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው'' ያለው ተማሪ አቤል ይህን ለማስቀጠል ሙስናን ከስሩ ለመስወገድ ህብረተሰብን አሳታፊ በሆነ መልኩ መሰራት እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡

የስልጣን ሽግግሩ በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ በመሆኑ ደስታና ኩራት እንደተሰማቸው የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ አበበ እማም ናቸው፡፡

''በአድዋ ወራሪውን የጣሊያን ጦር በማሸነፋችን በዓለም የገነነው ዝናችን በአዲሱ ትዉልድም ይኼው ገድል እንደተፈጸመ ይሰማኛል፤ ሂደቱ በእርግጥም ዴሞክራሲ እያበበ ስለመምጣቱ ማሳያ ነዉ'' ብለዋል፡፡

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በተለይ በታችኛው የመንግስት እርከን ህዝብን ያማረሩ የሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማስወገድ ስደትን የሚጸየፍ ትውልድ እንዲፈጠር መስራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2010 ፍቃድ ሳይኖራቸው መኪና ላይ በሚሸጡ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ምክንያት ከገበያ ውጭ እየሆንን ነው ሲሉ የመሳለሚያ አካባቢ እህል ነጋዴዎች ተናገሩ።

የአዲስ አበባ አስተዳደር ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በችግሩ ዙሪያ በከተማዋ ከሚገኙ በእህል ንግድ ስራ ላይ ከተሰማሩ ነጋዴዎች ጋር ውይይት አካሄዷል።

ምንም የንግድ ፍቃድ የሌላቸው ህገ ወጦች እየተበራከቱ መምጣት ህጋዊ ነጋዴው ላይ ጫና እያሳደረ ከመሆኑም ባሻገር መንግስት ማግኘት የሚገባውን ግብር እንዳያገኝ እያደረጉት ነው ብለዋል።

በእህል ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ሳኒ ሁሴን በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት "በርካታ ህገ ወጦች ንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው መኪና ላይ የግብይት ስራ ያከናውናሉ።"

እነዚህ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ተገቢውን ግብር ለመንግስት ስለማይከፍሉና ከዋጋ በላይ ስለሚሸጡ ችግሩ ከነጋዴው ባለፈ በመንግስትና በሸማቹ  ላይም ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ባሻ ግርማ ወርዶፋ  ህብረተሰቡ ህገ ወጥ ነጋዴዎችና ደላሎችን ለህግ አሳልፎ መስጠት ባለመቻሉና የመንግስት የቁጥጥር ስራ አናሳ መሆኑ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ እንዲሄድ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ንግድ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌታቸው ተሰማ በበኩላቸው የመሳለሚያ እህል በረንዳ የአገሪቷ አብዛኛው የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት ቦታ በመሆኑ ችግሩ ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ መልኩ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን ህገ ወጥነት ለመከላከልም ክፍለ ከተማው ህገ ወጥ ነጋዴዎች ወደ ህጋዊ መስመሩ እንዲገቡ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ነገር ግን ወደ ህጋዊ መስመሩ መግባት ያልቻሉና ካለ ንግድ ፈቃድ ሲነግዱ በተገኙ ግለሰቦች ላይ በአዋጅ 980/2008 መሰረት በወጣው የንግድ ደንብና መመሪያ መሰረት ተጠያቂ እያደረጉዋቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከዚህ መካከልም የተያዙ ንብረቶችን ከመውረስ ጀምሮ ግለሰቦችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንና በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሺሰማ ገብረ ስላሴ እንደሚሉት "በከተማዋ የህገ ወጥ ነጋዴዎች መበራከት ህጋዊ ነጋዴውን ከገበያ ውጭ እያደረገው ነው።"

ይህም ህጋዊ ሆኖ በሚሰራው ነጋዴ ላይ ጫና ከመፍጠሩ ባለፈ ግብይታቸውን በደረሰኝ ስለማያከናውኑ መንግስትን ማግኘት የሚገባውን ገቢ እያሳጡት እንደሚገኝ ገልጸዋል።

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ባለስልጣኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህም የህብረተሰቡ ሚና ወሳኝ በመሆኑ ህገወጦችን ለህግ አሳልፎ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስት ከሰባ አምስት በመቶ በላይ የሚሆነውን ገቢ የሚሰበስበው ከንግዱ ማህበረሰብ እንደሆነም መረጃዎች ያሳያሉ።

Published in ኢኮኖሚ

መጋቢት 26/2010 ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ትልቅ ዋጋ እንደምትሰጠው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አልሲሲ ተናገሩ፡፡

ፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አልሲሲ ባለፈው ሰኞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቃለ መሃላ የፈጸሙትን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በስልክ “እንኳን ደስ አለዎት” ማለታቸውን አህራም ኦንላይን የፕሬዝዳንቱን ጽህፈት ቤት ጠቅሶ በድረገጹ አስነብቧል፡፡

ሁለቱ መሪዎች በስልክ ባደረጉት ውይይትም አልሲሲ ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ትልቅ ዋጋ እንደምትሰጠው ገልጸው፣ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከርና በጋራ ጉዳዮች ላይም በትብብር ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠውላቸዋል፡፡

ዶክተር አቢይ አህመድም በቅርቡ በተካሔደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያሸነፉትን አልሲሲ እንኳን ደስ አለዎት ማለታቸውንና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማሳደግና ትብብራቸውንም ለማስፋት እንደሚሰሩ ገልጸውላቸዋል፡፡

አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ  ሀገሪቱ ለገጠማት ችግር የመፍትሔው አካል ለመሆን ከስልጣን ለመልቀቅ ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ ባለፈው ሳምንት ኢህአዴግ ዶክተር አቢይ አህመድን የግንባሩ ሊቀ መንበር አድርጎ መምረጡን ዘገባው አስታውሷል፡፡

Published in ፖለቲካ

ሰመራ መጋቢት 26/2010 የበሰቃ ሐይቅ ከአዋሽ ወንዝ ጋር እየተቀላቀለ በግብርና ስራቸው ላይ ጉዳት እያደረሰባቸው መሆኑን የአሚባራ ወረዳ ከፊል አርብቶ አደሮች ገለጹ፡፡

የአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን በበኩሉ የበሰቃ ውሃ ከወንዙ ጋር እንዳይቀላቀል በመዝጋት ችግሩን የበለጠ  ለማቃለል የሚስችል ጥናት መጠናቀቁን ፡፡

ሃይቁ በአካባቢው ህብረተሰብ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳትና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር የአንድ ቀን አውደ ጥናት በመተሃራ ከተማ ትናንት ተካሄዷል፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ የተሳተፉት በአሚበራ ወረዳ የወረር ቀበሌ ነዋሪ አቶ አሚን ኢለማ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል በበጋ ወቅት የአዋሽ ወንዝ የውሃ መጠን ስለሚቀንስ የበሰቃ ሐይቅን በመጠቀም ጥጥን ጨምሮ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ሲጠቀሙ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የሐይቁና የመሬቱ ጨዋማነት እየጨመረና የሚሰጠው ምርት እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ሙሉ በሙሉ የእርሻ መሬታቸው በጨዋማነት ተጠቅቶ ኑራቸውን ከሚደጉሙበት የግብርና ስራ እንዳይስተጓጎሉ የሚመለከተው አካል መፍትሄ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

ሌላው የወረር ቀበሌ ነዋሪ አቶ ኢናሃባ ጉረኔ በበኩላቸው የበሰቃ ሐይቅ አመቱን ሙሉ ከአዋሽ ወንዝ ጋር ተቀላቅሎ የሚፈስ ቢሆንም ጉዳት የሚያደርሰው ግን የአዋሸ ወንዝ የውኃ ይዘት በሚቀንስበት የበጋ ወራቶች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ወቅት ወንዙ  መጥፎ ሽታ የሚያመጣ በመሆኑ ለንጽህናም ሆኑ ለሰውና እንስሳት መጠጥነት አይጠቀሙበትም፡፡

እንዲሁም በወንዙ የሚገኙ የዓሳ ዝርያዎችም እንደሚሞቱ አስታውቀዋል፡፡

በተለይም ከ2008 አ.ም ጀምሮ ይህ ችግር በስፋት እየታ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት ችግሩ እንዲፈታላቸው ቢጠይቁም   እስካሁን መፍትሄ አለማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡

የገቢረሱ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጀማል አሊ በበኩላቸው የበሰቃ ሃይቅ መጠን እየጨመረ መጥቶ ከአዋሽ ወንዝ ጋር በመቀላቀሉ በአሚበራ ወረዳ ብቻ ሳይሆን ከ10 በላይ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ከፊል አርብቶ አደሮችን ኑሮ ላይ ተጽእኖ እያሳደረ ነው፡፡

በተለይም በዞኑ የአዋሽ ወንዝ በሚያቋርጣቸው አሚበራ፣ ቡሪሙዳይቱና ገዋኔ ወረዳዎች የበሰቃ ሐይቅ በህብረተሰቡ ጤናና የግብርና ስራ ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ህብረተሰቡ በየመድረኩ የሚያነሳው የመልካም አስተደደር ጥያቄ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአዉደ ጥናቱ ላይ የተገኙት የአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ግዛው በሰጡት ምላሽ  የበሰቃ ሐይቅ ከአዋሽ ወንዝ ጋር ሲቀላቀል በህብረተሰቡ የግብርና ስራም ሆነ ጤና ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የተቀመጡ አለም አቀፍ መለኪያዎችን መነሻ በማድረግ የውሃ ጥራት ቁጥጥር እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡

በዚህም የሐይቁ ጨዋማነት መጠን እየቀነሰ መምጣቱ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

ከህብረተሰቡ የሚነሳው ቅሬታ ከዚህ በፊት የውሃው ያለፈ ታሪክ የፈጠረው ተጽእኖ ውጤት እንጂ በአሁኑ ሰአት የውሃው ጨዋማነት እየቀነሰ ከስጋት ወደመልካም አጋጣሚነት እየተለወጠ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡

የህብረተሰቡን ስጋት ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ በቀጣይ የአዋሽ ወንዝ የውሃ መጠን በሚያንስበት የበጋ ወራት የበሰቃ ውሃ ከወንዙ ጋር እንዳይቀላቀል በመዝጋት ችግሩን የበለጠ ማቃለል  የሚስችል ጥናት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ በአፋር ክልል የገቢረሱ ዞንና ወረዳ  አመራሮች፣ ፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካሎች ተገኝተዋል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

ሶዶ መጋቢት 26/2010 ሰላማዊ የስልጣን ሽግግሩ በሃገሪቱ ሰላምና ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻውን እንደሚወጣ የወላይታ ዞን የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የወላይታ ሃገረስብከት ሥራ አስከያጅና የወላይታ ዞን የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ መላከ ሠላም ቀሲስ ቦክቻ ኤንጋ ለኢዜአ እንደገለጹት የተደረገው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ሃገራችን ካላት ልምድ አንጻር ያልተጠበቀ ነው፡፡

"የስልጣን ሽግግሩ የህዝብን ጥቅም ያስቀደመ በመሆኑ በሃገሪቱ ሰላምና ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማህበረሰቡን በማስተማር የሚጠበቅብንን ለመወጣት ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን" ብለዋል፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ  የወሰዱት በሳል ውሳኔ ከራስ ስልጣን ይልቅ ለህዝብ በማሰብ የአኩሪ ታሪክ ተጋሪ እንደሚያደርጋቸውም ተናግረዋል፡፡

"በፖለቲካው ረገድ ከታላላቅ ሃገሮች ጋር እንድንስተካከል ያደረገ ነው" ብለዋል ።

በሃገሪቱ ታሪክ በህይወት ባሉ መሪዎች መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ የተከናወነ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በማየታቸው መደሰታቸውን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስተባባሪ አቶ ሚልክያስ ኦሎሎ ናቸው፡፡

በመንግስት ደረጃ የታየው ቁርጠኝነት ከስልጣን ይልቅ ለህዝብ ማሰብና ሂደቱ ሰላምን ለማረጋገጥ ያለውን ፋይዳ ያሳየ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በዚህ ፈታኝ ወቅት በህዝብ መካከል ችግሮች እንዳይባባሱ በማድረግ ረገድ ጉባኤው በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን የገለጹት አቶ ሚልክያስ "በቀጣይም ህዝቡ ከመንግስት ጋር ሆኖ የልማት ተሳትፎውን እንዲያጠናክር የማስተማርና የማስተባበር ስራ ይሰራል" ብለዋል፡፡

"አድሎአዊ አሰራሮችን ማስቆም፣ የስራ ዕድል ፈጠራና በኑሮ ውድነት ላይ በተገባው ቃል መሰረት መንግስት ሊሰራ ይገባል" ብለዋል፡፡

የወላይታ ዞን የእስልምና ጉዳዮች ሰብሳቢና የጉባኤው አባል ሀጂ ናስር ዩሱፍ "ለሃገር ልማትና ሰላም በማሰብ በሃገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለተከናወነው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ላበረከቱት አስተዋጽኦ ለመሪዎቻችን ምስጋና ይገባል " ብለዋል ።

ተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስተር በተለይ ለብሄራዊ ማንነት የሰጡት ትኩረት የሃይማኖት ተቋማትና አባቶችን እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡

ልዩነትን በጠረጴዛ ዙሪያ ፈተዉ ከግል ጥቅም ይልቅ ቅድሚያ ለሃገርና ለህዝብ የወሰኑት ውሳኔ ለአፍሪካዊያን መሪዎች ምሳሌ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡

አሳታፊ የጸረ-ሙስና ትግልና እርምጃ መዉሰድ፣ ወጣቶች ወደስራ የሚገቡበት አሰራር ላይ ትኩረት ማድረግና በህዝቦች መካከል ልዩነትን ለመፍጠር የሞከሩ አደረጃጀቶችን መስመር ማስያዝ እንሚያስፈልግ ጠቁመዋል ።

የሃይማኖት ጉባኤዉ በርካታ ማህበረሰብን ያቀፈ በመሆኑ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስተር ጎን ቆመዉ የሃገራቸውን ብልጽግና ለማፋጠን በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

የወላይታ ዞን የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከ50 በላይ የተለያዩ ቤተ-ዕምነቶችን ያቀፈ መሆኑን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡

 

Published in ፖለቲካ

ፍቼ መጋቢት 26/2010 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በግራር ጃርሶ ወረዳ የንጣፍ ድንጋይና ጠጠር  ማምረት የጀመሩ ወጣቶች  ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን  ገለፁ ።

የዞኑ አስተደደር ተመሳሳይ ለሆኑ የማአድን ልማት ሰራዎች ከ500 ሄክታር የሚበልጥ መሬት ማዘጋጀቱን  አስታውቋል።

በወረዳው የሚገኙ 102 ወጣቶች ተደራጅተው ካለፈው ታኅሳስ ወር 2010 ጀምሮ “ገብርኤል “ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለኮንስትራክሸን፣ ለመንገድና ለውሃ መወረጃ  የሚያገለግል ጥርብ ድንጋይ  ማምረት መጀመራቸውን የማህበሩ ሰብሳቢ  ወጣት ደበላ የሺጥላ ገልጿል።

ወጣቶቹ ከመንግሳት  ባገኙት ግማሽ ሄክታር መሬት እስካሁን ከአምስት ሺህ ሜትር ኩዩብ  በላይ ኮብል ድንጋና ጠጠር በማምረት  ለአካባቢው ገበያ አቅርበዋል፡፡

ከዚሁ ምርት ሽያጭም በነፍስ ወከፍ በወር እንደየስራ እንቅስቃሴያቸው ከሁለት ሺህ እስከ አራት ሺ ብር ገቢ  እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል ።

የተሻለ ገበያ ትስስር፣ የማምረቻ ማሽንና የመንገድ ችግር  ቢቀረፍላቸው  የበለጠ በማምረት ለሌሎች ወጣቶች የሚተርፍ የስራ አድል  መክፈት እንደሚችሉ አስታውቋል ።

ከቴክኒክና ሙያ ከተመረቀ በኋላ ለሶስት ዓመታት ያለስራ ተቀምጦ እንደነበር የገለፀው ደግሞ  ወጣት ስንታየሁ ግርማ ነው፡፡

ወጣቱ በማሀበር ተደራጀቶ ስራ በመጀመሩ በሚያገኘው ገቢ ራሱንና ቤተሰቡን ማስተዳደር እንዳስቻለው ገልጿል፡፡

በተለይ በአሁኑ ወቅት ሰራውን እየለመደውና ገቢውም እያደገ  በመምጣቱ  ስራ የመሰራት  ተነሳሽነቱ እየጨመረ መምጣቱን ተናግሯል፡፡

ሌሎች ወጣቶችም   ተደራጅተው ወዳገኙት ስራ ቢገቡ ወጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ መክሯል።

ሌላው የማህበሩ አባል ወጣት ቶሎሳ አሰፋ በበኩሉ በማህበር ተደራጅቶ ስራ ከጀመረ ወዲህ ጊዜውን ስራ ላይ በማዋል ለተሻለ ገቢና እድገት እንዳነሳሳው አመልክቷል ።

ማህበራቸው የሚያመርተው ንጣፍ ድንጋይና ጠጠር ጥሩ ገበያ እንዲያገኝ በመንግስት በኩል የገበያ ትስስር በመፍጠሩ ለሌሎች ወጣቶች የስራ እድል ለመክፈት እንደሚያስችል ጠቁሟል ።

የወረዳው የስራ እድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸብር ጌታቸው የወጣቶቹን የገበያና የመንገድ ችግር በመፍታት  ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እንዲፈጠር እየተሰራ መሆኑን ጠቀሰዋል፡፡

በወረዳው ዘንድሮ በ132 ማህበራት የተደራጁ 3ሺህ ወጣቶች  በእደ -ጥበብ፣ በማእድን፣ በግብርና፣ በኮንስትራክሽን፣ ስራዎች ተደራጅተው ወደ ስራ መግባታቸውን አመልክተዋል ።

የዞኑ አስተዳደር  የወጣቶቹን  የስራ አጥነት  ችግር ለማቃለልና ገቢያቸውን ለማሳደግ በተፈጥሮ ሃብት የበለፀገ  ከ570 ሄክታር  የሚበልጥ መሬት በጥናት ተለይቶ መዘጋጀቱን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ወጣቶችና ሰፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ታዬ ናቸው።

በዞኑ በሂደቡ አቦቴ፣ ግራር ጃርሶ ፣  ኩዩ እና ደብረ ሊባኖስ ወረዳዎች  በጥናት የተለየው መሬት ይኸው መሬት ለአሸዋና ጠጠር፣ ሲሚንቶና ኖራ፣ ለቀለምና ብርጭቆ  ፋብሪካዎች  ግብአትነት የሚውሉ ማእድናትን የያዘ መሆኑን ተናግረዋል።

መሬቱ በዞኑ 13 ወረዳዎች በከተሞችና ገጠር ቀበሌዎች የሚታየውን የሰራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ  የሚደረገው እንቅስቃሴ  አካል መሆኑንም  ጠቅሰዋል።

በዞኑ ባለፉት ሰባት  ወራት ከ6 ሺህ 554  የሚበልጡ ወጣቶች በ381 ማህበራት ተደራጅተው በማእድል ልማት የተሰማሩ ሲሆን ከ16 ሺህ የሚበልጡት  ደግሞ የብድርና የመሰሪያ ቦታ ጠይቀው ምላሽ እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል ።

 

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር መጋቢት 26/2010 በምዕራብ ጎጃም ዞን ሽንዲ ከተማ የሚስተዋለው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኪኖሚያዊ ችግሮች እያጋለጣቸው መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

 የሽንዲ ከተማ ውሃ አቅርቦት እጥረትን ለመፍታት በ70 ሚሊዮን ብር በጀት ተግብራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ተጠቁሞል።

የከተማው ነዋሪ አቶ አብየ አድማስ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በከተማዋ የውሃ አቅርቦት ሙሉ በሙሉ የለም ማለት ይቻላል።

በውሃ አቅርቦት እጥረት ከተማዋን በተሻለ ማልማትና ማሳደግ የሚችሉ የአካባቢው ተወላጅ ባለሃብቶች በውሃ እጥርት ምክንያት አካባቢውን እየለቀቁ መሄዳቸውንም ተናግረዋል።

የውሃ እጥረቱ ሕብረተሰቡ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተጋለጠ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አብየ፣ በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶችም ለመታጠቢያ የሚሆን ውሃ ከቤታቸው እንዲያመጡ በመደረግ ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

 “ሴቶች የወንዝ ውሃ ፍለጋ ለሰዓታት እንግልት እየደረሰባቸውና አላስፈላጊ ድካም እየደረሰባቸው ነው” ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ሃብታሙ አለማየሁ ናቸው።

በሳምንት አንድ ቀን ለ30 ደቂቃ ብቻ የቧንቧ ውሃ እንደምትመጣ አመልክታ፣ አንዳንድ ጊዜ ብልሽት ሲገጥም እስከ አንድ ወር ውሃ የማይገኝበት አጋጣሚ እንዳለ አመልክተዋል።

የውሃ እጥረቱ በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶችና በትምህርት ቤት የሚማሩ ታዳጊ ልጆች ውሃ ይዘው እንዲመጡ መገደዳቸውንና ለከፋ ችግር እየተጋለጡ በመሆናቸው ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል።

በችግሩ ምክንያት ከአካባቢያቸው 17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ቡሬ ከተማ  በመሄድ ለአንድ ጀሪካን እስከ 15 ብር አውጥተው ለመግዛት መገደዳቸውን ጠቁመዋል።

የውሃ አቅርቦት ችግሩ እንዲፈታ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም መፍትሄ ማግኘት እንዳልቻሉ የገለጹት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ቢረሳው አናጋው ናቸው።

የወንበርማ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ባንቴ ታደሰ በበኩላቸው "የሽንዲ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ጥያቄን መመለስ ባለመቻሉ ከህዝቡ ጋር በልማት ዙሪያ ተቀራርቦ መነጋገር አልተቻለም" ብለዋል።

ከአሥር ዓመት በፊት በከተማው 10 ሺህ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ የተገነባው የውሃ ተቋም በአሁኑ ወቅት በሦስት እጥፍ ላደገው የነዋሪዎች ቁጥር ባለመብቃቱ ችግሩ መከሰቱን ገልጸዋል።

በውሃ እጥረት ምክንያት በግንባታ ሥራ የተደራጁ ወጣቶች በቀን ከ500 እስከ 600 ብር በላይ ለውሃ በማውጣታቸው ምክንያት ሥራቸውን ለጊዜው ማቋረጣቸውን ተናግረዋል።

የውሃ አቅርቦቱ ችግር እንዲፈታ ለክልሉ ውሃ ቢሮ በተደጋጋሚ የማሳወቅ ሥራ ሲሰሩ ቢቆዩም አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት በኩል ክፍተት መኖሩን አመለክተዋል።

የክልሉ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ይመር ሃብቴ በበኩላቸው በከተሞች ያለውን የውሃ እጥረት ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በ60 ከተሞች በተለያየ የግንባታ ደረጃ ላይ የሚገኙ የውሃ ተቋማት እንዳሉ ጠቁመው፣ ከእዚህ በተጨማሪ እስከዛሬ ውሃ ያላገኙ ከተሞችን በመለየት የዲዛይንና የጥናት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የሽንዲ ከተማ ውሃ አቅርቦት እጥረትን ለመፍታት የአንድ ውሃ ተቋም የዲዛይንና የጥናት ሥራ ተጠናቆ በ70 ሚሊዮን ብር በጀት ተግብራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩንም አስታውቀዋል።

የውሃ ተቋሙ ግንባታ በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ድረስ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ የሽንዲ ከተማንና በዙሪያው ያሉ 40 ሺህ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ አንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

የሚገነባው የውሃ ተቋም ከ10 እስክ 20 ዓመት የሚያገለግል ሲሆን ወጪውም ሙሉ ለሙሉ በክልሉ መንግስት እንደሚሸፈን ተናግረዋል፡፡

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን