አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 03 April 2018

ደብረ ብርሃን መጋቢት 25/2010 የመላው ሰሜን ሸዋ ዞን 15ኛው ባህላዊ ስፖርት ውድድር በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አጠቃላይ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቀቀ።

ለአንድ ሳምንት በተካሄደው ውድድር በክልል አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው የባህል ስፖርት ውድድር ዞኑን ወክለው የሚሰለፉ 44 ተጫዋቾች ተመርጠዋል።

በውድድሩ የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አጠቃላይ ስምንት ዋንጫዎችን በማግኘት አንደኛ በመሆን ሲያጠናቅቀ መንዝ ጌራ ወረዳ አምስት ዋንጫዎችን በማግኘት ሁለተኛ ሆኑ አጠናቋል።

የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ከላል ሳህለማሪያም እንደገለጹት የውድድሩ መካሄድ አርሶ አደሩ እየተዝናና ባህሉን ለቀጣይ ትውልድ እንዲያስተላልፍ አሰተዋጽኦ አለው።

ውድድሩ የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከርና የባህል ልውውጥ ለማድረግ ፋይዳ እንዳለው የገለጹት ደግሞ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረጻድቅ ናቸው።

ሚያዚያ 14 ቀን 2010 ዓ.ም በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ለሚካሄደው ክልል አቀፍ የባህል እስፖርት ውድድር ህብረተሰቡ እንግዶችን ተቀብሎ በማስተናገድ እንዲተባበርና ነጋደውም ጥራት ያላቸውን ምርቶች በማቅረብ ለስፖርት ቱሪዝም እድገት የበኩላቸውን ሊወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ከሚዳ ወረሞ ወረዳ ተሳታፊ ወይዘሮ አዜብ አዳምሰገድ እንደገለጹት የባህል ስፖርት ውድድር መጀመሩ አርሶአደሮች ከአባቶቻቸው የወረሱትን ባህል ጠብቀው ለትውልድ  እንዲያስተላልፉ ይረዳል።

"ውድድሩ በአረርቲ ከተማ መዘጋጀቱ በየደረጃው የሚገኘውን የንግድ ማህበረሰብ ተጠቃሚ ከማድረጉም በላይ የሌሎች ወረዳዎችን ባህልና ወግ እንድናውቅ አስችሎናል" ብለዋል።

በውድድሩ ከ24 ወረዳዎች የተውጣጡ 700 ስፖርተኞች በሰባት ባህላዊ የስፖርት ዓይነቶች መሳተፋቸው ታውቋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

 

Published in ስፖርት

አዳማ  መጋቢት 25/2010 ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ መጎልበት የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤት ጥሪ አቀረበ።

ቦርዱ ለ21 ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች በዴሞክራሲያዊ ምርጫና በመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ያተኮረ የአንድ ቀን ስልጠና በአዳማ ከተማ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፀሐፊና የጽህፈት ቤቱ ዋና ኃላፊ አቶ ነጋ ዱፊሳ በስልጠናው ላይ እንደተናገሩት በሃገሪቱ የተከናወኑት አምስት ጠቅላላና የአካባቢ ምርጫዎችን ቦርዱ በብቃት አከናውኗቸዋል።

ምርጫዎችን ነጻ ሰላማዊና ተዓማኒ ከማድረግ አኳያም የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች ተሳትፎ የላቀ መሆኑን ገልጸው ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ መጎልበት በቀጣይም ይበልጥ የተጠናከረ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችን አቅም ለመገንባት ስልጠናዎችና የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት የሚያደርገው ድጋፍ ለወደፊቱም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አቶ ነጋ ዱፊሳ አረጋግጠዋል።

በትናንቱ ስልጠና ላይ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስርዓት ምንነትና መርሆዎች እንዲሁም የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ በኢትዮጵያ የሚሉ የመነሻ ፁሁፎች ቀርበው በአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት ህገ-መንግስቱም ሆነ የምርጫ አዋጁ ግልጽ ቢሆንም በአፈፃፀም ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት መንግስትና ምርጫ ቦርዱ ብዙ ስራ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2010 የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ጄነራል ሳልቫ ኪር ማያርዲትና የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ የደስታ መግለጫ መልዕክት አስተላለፉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ጄነራል ሳልቫ ኪር ማያርዲት ዶክተር አብይ አሕመድ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሊቀመንበና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመመረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።

ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በመልዕክታቸውም፤ የሁለቱ አገሮች ታሪካዊ ግንኙነት እንዲቀጥልና የጋራ ተጠቃሚነት እንዲጠናከር ለማድረግ እንደሚሰሩ ያላቸውን ተስፋ አመላክተዋል።

በተመሳሳይም የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሴፕ ታይብ ኤርዶዋን  ዶክተር አብይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመሰየማቸው 'የእንኳን ደስ አለዎት' መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በቀጣይ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥለም ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል።

Published in ፖለቲካ

ሀዋሳ መጋቢት 25/2010 በፌዴራል ደረጃ የተካሄደው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የኢትዮጵያ ህዝቦች እኩል የማልማትና የመጠቀም መብታቸውን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡

ይህንን የገለጹት በክልሉ ምክር ቤት ስድስተኛ መደበኛ ጉባኤ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል  ትናንት አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡ አባላት ናቸው፡፡

በቤንች ማጂ ዞን ሜኤኒት ልዩ የምርጫ ክልል የተወከሉት አቶ ፋጆስ ሀፒ እንዳሉት በሀገሪቱ በሰላማዊ መንገድ የተደረገው የስልጣን ሽግግር ለአፍሪካና ለሌሎችም የዓለም  ሀገራት ትልቅ ተሞክሮ ነው፡፡

ለህዝብ ጥቅምና ሰላም ቅድሚያ በመስጠት የጠቅላይ ሚኒስትርነታቸውን ቦታ በፈቃዳቸው የለቀቁት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በአፍሪካ ቀዳሚ ያደርጋቸዋል ነው ያሉት፡፡

"ይህም ተሞክሮ ለቀጣዩ ትውልድ ጥሩ ትምህርት ሆኖ በሀገሪቱ በቀጣይ ጊዜያት የስልጣን ሽግግር እንዲህ በሰላማዊ መንገድ ይሆናል ብዬ አስባለሁ" ብለዋል፡፡

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህንን መልካም ተሞክሮ በመውሰድ የኢትዮጵያን ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩል የመልማት፣ የመጠቀም መብቱንና የስልጣን ባለቤትነቱን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ ብለው እንደሚጠብቁ አቶ ፋጆስ ገልጸዋል፡፡

ከባስኬቶ ልዩ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ ጸጋነሽ ገመዶ በበኩላቸው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸው የሀገሪቱ ዴሞክራሲ እያደገ መምጣቱን እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡

በየደረጃው በተገቢው ባለመሳራተቸው በሀገሪቱ ሰላም ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድረው እንደነበር አስታውሰው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከወጣቶችና ከሴቶች አንጻር እንዲሁም ከእኩል ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን መፍታት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

የህብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታት የመፍትሄው አካል ለመሆን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸው ጥሩ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  ከሲዳማ ዞን ቡርሳ ወረዳ ምርጫ ክልል የተወከሉት ወይዘሮ መሳፍንት ማቱሳላ ናቸው፡፡

በጥልቅ ተሀድሶ ወቅት የተነሱ የህብረተሰቡ ጥያቄዎች ምላሽ ከተሰጣቸው ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡

ከሸካ ዞን ማሻ ምርጫ ክልል የተወከሉት አቶ አዝመራ አንደሞ በበኩላቸው ባልተለመደ ሁኔታ ለሌሎች ታዳጊ ሀገራት ምሳሌ በሚሆን መልኩ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ስልጣን መልቀቃቸው ለመጪው ትውልድ ጭምር በአርአያነት የሚተላለፍ አኩሪ ታሪክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ኃይለማሪያም በመሪነት ብቻ ሳይሆን ከመሪነትም ወርዶ የመፍትሄ አካል መሆን እንደሚቻል ትልቅ ትምህርት መስጠታቸውን ጠቁመው በቀሪ ዘመናቸውም  ለዚች ሀገር ባሉበት ሁሉ መልካም አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 7/2010 የፐፕሊክ ሰርቪስ ተቋማት የሚያደርጓቸው ስብሰባዎች አላስፈላጊ የሀብት ብክነትና የመልካም አስተዳደር ችግር መንስኤ መሆናቸውን ጥናቶች አመለከቱ ።

 የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ዋና አማካሪ አቶ አሸናፊ አበራ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ስብሰባዎችን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ ኢንስቲትዩቱ ባደረገው ጥናት ተቋማቱ የሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች እያስከተሉ ይገኛሉ።

 ስብሰባዎቹ ተገቢ ጉዳይና ተሳታፊ የማያካትቱ፣ በቂ ዝግጅት የማይደረግባቸው፣ ጊዜ አባካኝ፣ አገልግሎት የሚያስተጓጉሉ፣ ውጤታማነታቸው ክትትልና ድጋፍ የማይደረግባቸውና "ቅንጅታዊ አሰራር የማይስተዋልባቸው መሆናቸው በጥናቱ ግኝት ተረጋግጧል" ብለዋል።

 የአቅም ውስንነት፣ የኪራይ ሰብሳቢ አመለካከት፣ የተጠያቂነት መጓደል ለሚደረጉ ስብሰባዎች መንስኤ መሆናቸውን የጠቀሱት አማካሪው፤ ቀልጣፋና ውጤታማ ያልሆኑ ስብሰባዎች ለአላስፈላጊ የሀብት ብክነትና የመልካም አስተዳደር ችግር እያጋለጡ መሆኑን አብራርተዋል።

 ስብሰባዎቹ ሲዘጋጁ ከምግብ ጀምሮ ምንም ጥቅም የሌላቸው አልባሳትና ባነሮች እንደሚዘጋጅ ጠቁመው፤ መሰል ተግባራት በጊዜ፣ በጉልበትና በገንዘብ ሀብት ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

 በስራ ሰዓት የመንግስት አገልግሎትን ዘግቶ ስብሰባ ማካሄድ ተገቢነት እንደሌለው ገልጸው፤ ይህም በተቋማቱ መከናወኑ ለበርካታ መልካም አስተዳደር ችግሮች መንስኤ እየሆነ መምጣቱን አመልክተዋል።

 ችግሩን ለማቃለል የፐፕሊክ ሰርቪስ ተቋማት ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ፣ ልማታዊ መንግስት ባህርያትን የተላበሰና ሳይንሳዊና ዘመናዊ አካሄድን መከተል እንዳለባቸውም በጥናቱ አቅጣጫ ተመላክቷል።

 በሌሎች አገሮች ተሞክሮ ስብሰባዎች ሲደረጉ ደንብና መመሪያ እንዳላቸው ገልጸው፤ ይህም በጥናቱ ተለይቶ በኢንስቲትዩቱ አዘጋጅነት በፐፕሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ጸድቆ ለተቋማት የተበተነ የስብሰባ መመሪያ መኖሩን ገለጸዋል።

 ይሁንና ተቋማቱ አሁንም ቢሆን የሚካሂዱት ስብሰባ በመመሪያው መሰረት የማይደረግና ለመመሪያውም ያላቸው አመለካከት የተዛባ መሆኑን ጠቅሰዋል።

 ኢንስቲትዩቱ በመመሪያው ላይ ግልጽነት ለመፍጠር የሚያስችል ስልጠና ለየተቋማት አመራር ማዘጋጀቱን አስታውሰዋል።

 ጥናቱ የተካሄደው በስምንት የክልል፣ በሁለት አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በሁለት የፌዴራል በድምሩ በ12 የፐፕሊክ ሰርቪስ ተቋማት ላይ ነው።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Published in ማህበራዊ

መቀሌ መጋቢት 25/2010 አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስተር በአገር ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ ግንባታ ላስተላለፉት መልእክት ተግራዊነት በትጋት እንደሚሰሩ በትግራይ ክልል አስተያየታቸውን የሰጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለፁ ።

 የስልጣን ሽግግሩ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መንገድ የተከተለ በመሆኑ ወጣቱ ትውልድ ሊማርበት እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል ።

 የመቀሌ ከተማ ነዋሪና በዓዲግራት ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር ገብሩ ካህሳይ እንዳሉት፣ለሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት  ወጣት መሪ መሰየሙ ተደስተዋል።

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብና በአገር ሰላም፣ ልማትና  ዴሞክራሲ ግንባታ አስመልክተው ያቀረቡትን ጥሪ በመቀበል ለተግባራዊነቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል ።

 "ለሀገሪቱ የሚያስፈልገው ዘርና ብሄር የማይለይ፣ በኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ የታነፀና ለኢትዮጵያ ህዝብ ብልፅግና የሚሰራ መሪ ነው" ያሉት መምህር ገብሩአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስተሩ በዚህ አስተሳሰብ የተቃኙ መሆናቸውን ካስተላለፉት መልእክት መገንዘባቸውን ገልፀዋል ።

 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በሃገራቸው ጉዳይ ላይ እንዲመክሩና የድርሻቸውን እንዲወጡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው ጥሪም የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዲጎለብት ትኩረት የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል ።

 "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነታቸው እንዲወጡ ነባር አመራሮችና ምሁራን በቀናነት ሊያግዟቸው ይገባል " ብለዋል ።

 በትግራይ ማእከላዊ ዞን የጣንቋ አበርገለ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ መዓሾ ልጃለም በበኩላቸው "የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር  ዜጎች ወቅታዊ ችግሮችን እየፈታን ለጋራ ለእድገትና ብልፅግና የበኩላችንን እንድንወጣ መነቃቃት የፈጠረ ነው" ብለዋል።

 በተለይ ሴቶችን አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክትና ያቀረቡት ጥሪ በመልካም ስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለማፍራት ላፍነታቸውን ያነሳሳቸው መሆኑን ገልፀዋል ።

 በዓብይ ዓዲ ከተማ ነዋሪ መምህር መስፍን ወልደገብሪኤል በበኩላቸው "የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሰየም ለአሁኑ ትውልድ አዲስ የፖሊቲካ ምዕራፍ የከፈተ ታሪካዊ ክስተት ነው" ብለዋል።

 የሀገርና ህዝብ ሰላምና ብልፅግና መረጋገጥ የሚቻለው በአንድ መሪ ወይ መንግስት ብቻ ሳይሆን በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተቀናጀ ትግልና ጥረት ነው" ያሉት መምህር መስፍን ሁሉም ዜጋ በአንድነት ሊሰራ እንደሚገባ መክረዋል ።

 በጠቅላይ ሚኒስተሩ የተላለፈውን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትግበራ ስኬታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

 የህወሓት ነባር ታጋይ ገብረአሳይ አምባዬ እንዳሉት የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሰየም የአዲሱን ትውልድ የስልጣን መተካካት ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል ።

 "ወጣት ጠቅላይ ሚኒስትር በመሰየሙ ደስ ብሎኛል "ያሉት ታጋይ ገብረአሳይ የአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ስያሜ በስነ ምግባርና ግብረ ገብነት ያደገና የተማረ አገር መምራትና መመራመር እንደሚችል ያስተማረ ክሰተተ መሆኑን ተናግረዋል ።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2010 የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የማስፈፀም አቅሙን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

ሚኒስቴሩ ያለፉት ስምንት ወራት እቅድ አፈፃፀሙን ለሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት አቅርቧል።

የምክር ቤቱ የግብርና ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አልማዝ መሰለ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፤ በተፋሰስ ልማት፣ የመሬት አጠቃቀምን በማሻሻልና የአፈር ጤንነትን በመጠበቅ  የጀመራቸውን ተግባራት ይበልጥ ሊያጎለብት ይገባዋል።

በተጨማሪም ምርጥ ዘርና ማዳበሪያን የመሳሰሉ ግብአቶች በወቅቱ እንዲቀርቡና ማቀነባበሪያዎች አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ በኩል የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲስተካከሉም የቋሚ ኮሚቴው አባላት ጠይቀዋል።

ስር የሰደደ የምግብ እጥረት ያለባቸው አካባቢዎችን በመለየት ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ በማድረግ ድርቅ የሚያጠቃቸውን ደግሞ በቋሚነት ከችግሩ ለማውጣትና ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግም መስራት እንደሚገባው ተጠቁሟል።

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ ዶክተር እያሱ አብርሀም በበኩላቸው፤ ሚኒስቴሩ በግብርና ኤክስቴንሽን፣ በበልግ ስራ እንቅስቃሴ፣ በሞዴል አርሶ አደሮችን ቁጥር በማሳደግና የእርሻ ግብአቶች ላይ ጥናት በማድረግ ስኬታማ ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል።

"የሰው ሀይልና የሎጂስቲክ እጥረት፣ በፌዴራልና በክልል ያለው የአደረጃጀት አለመጠናከር፣ የእጽዋት ቁጥጥርና ጥበቃን ጨምሮ በአፈር ለምነት ማሻሻያ መስኮች የተቋሙን የማስፈፀም አቅም እየተፈታተኑ ያሉ ችግሮች ናቸው" ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከባ ኡርጌሳ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት ድርቅ አዘውትሮ የሚታይባቸው የአገሪቷ አካባቢዎችን ከችግር የሚያወጣ ምርምር እየተካሔደ መሆኑን ገልጸዋል።

ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ የመሳሰሉ የእርሻ ግብአቶችን ለአካባቢ ተስማሚነት በሚመለከትም በተመሳሳይ ምርምር መደረጉንና ማዳበሪያና ምርጥ ዘርን ቀድሞ ለአርሶ አደሮች ለማድረስ የሚቻልበት አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።

ለአብነትም በዚህ ዓመት ካለፈው በጀት ዓመት የከረሙትን ሳይጨምር አራት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ የተፈፀመ ሲሆን፤ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል የምርጥ ዘር ክምችትም እንዳለ አስታውቀዋል።

እስከ ቀጣዩ ግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ማዳበሪያውን ሙሉ በሙሉ ለአርሶ አደር የማድረስ ስራው እንደሚጠናቀቅም ጨምረው ገልፀዋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2010 ሴቶች በዜና፣ በፕሮግራም፣ በመዝናኛና ማስታወቂያዎች ላይ ያላቸው ውክልና ምን እንደሚመስል የሚያሳይ አገር አቀፍ ጥልቅ ጥናት ሊካሄድ ነው።

 ጥናቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ክፍል ከሴቶች ስትራቴጂያዊ ልማት ማዕከል ጋር በመተባበር እንደሚያካሄደው ታውቋል።      

 ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እሸቱ ጮሌ አዳራሽ በተካሄደው አውደ ጥናት ሴቶች በዜናና ፕሮግራሞች ያላቸው ውክልና እንዲሁም በመዝናኛና ማስታወቂያዎች ላይ ያላቸውን ገጽታ የሚያሳይ የውይይት መነሻ ሀሳብ ቀርቦ የሀሳብ ልውውጥ ተደርጎበታል።

 በውይይቱም የዩኒቨርስቲ መምህራን፣ ተማሪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊዎች ነበሩ። 

 የኢትዮጵያ ቋንቋና ባህል ጥናት አካዳሚ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር አበባ አማረ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ፊልሞችና ድራማዎች ላይ ሴቶች አብዛኛውን ጊዜ የበታች፣ ጥገኛ፣ ስሜታዊና ምክንያታዊ ያልሆኑ ተደርገው ይሳላሉ።

 "ይህም ህጻናትና ወጣቶች ስለሴቶች አሉታዊ አስተሳሰብ እንዲያዳብሩ ያደርጋል" ብለዋል።

 ጥናቱን ለማካሄድ የሚያስችሉ ተከታታይ አገረኛ ድራማዎችና ፊልሞች መመረጣቸውን ገልጸው፤ በአዲስ አበባ፣ መቀሌ፣ ባህርዳር፣ ድሬዳዋ እና ሀዋሳ ከተሞች በሚገኙ ተመልካቾች ላይ ለጥናቱ ግብዓት እንደሚሰበሰብ ጠቁመዋል።

 ጥናቱ "ፊልሞችና ድራማዎች ምን አይነት ይዘት አላቸው? የሴቶች ውክልና ከወንዶች ጋር ሲነጻጸር ምን ይመስላል? እንዲሁም ድራማዎቹ የሚተላለፍባቸው መገናኛ ብዙሃን ምን አይነት መስፈርት አላቸው?" የሚሉ ጥያቄዎችን እንደሚመልስም ተናግረዋል።  

 ጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር አጋረደች ጀማነህ እንደተናገሩት፤ ሴቶችን የተመጣጠነ ውክልና እንዲኖራቸው ማስቻልና በመዝናኛው ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት ከጥናቱ የሚጠበቁ ውጤቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

 የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን መምህርት ወይዘሮ አስመረት ኃይለሥላሴ በበኩላቸው፤ ሴቶች ካላቸው የተዛባ ውክልና አኳያ በራስ የመተማመናቸው እንዲቀንስ፤ ጾታዊ ትንኮሳና አስገድዶ መድፈር እንዲጨምር ማድረጉን የተለያዩ ዓለማቀፋዊ ጥናቶች ማመላከታቸውን ተናግረዋል።    

 ''ሴቶች ለአገር እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ቢሆንም እነርሱን የሚመለከቱ ጉዳዮች በዋና ዋና ዜናዎች ሲዘገቡ አይታይም '' ያሉት ደግሞ የሴቶች ስትራቴጂያዊ ልማት ማዕከል ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ዶክተር ገነት ዘውዴ ናቸው።

 በርካታ አገረኛ ፊልሞች ለመብታቸው የሚታገሉ ሴቶችን ገጸ ባህሪያት ላይ ከማተኮር ይልቅ በወንዶች ሲጉላሉ፣ ሲያለቅሱ፣ ሲታለሉ ወይም ሲያታልሉ መሆኑ በኅብረተሰቡ ላይ የከፋ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አብራርተዋል።

 ጥናቱም እነዚህ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ  አቅጣጫ በመጠቆም ረገድ ሚናው የጎላ በመሆኑ ለጥናቱ እውን መሆን ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2010 ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሶስት ሺህ አምቡላንሶችን ለጤና ጣቢያዎች ሊያከፋፍል መሆኑን ገለጸ።

አምቡላንሶቹ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በሁሉም የጤና ተቋማት እንድ አንቡላንስ እንዲኖር የተያዘው እቅድ አካል ናቸው።

 ይህም በአገር አቀፍ ደረጃ በጤና ጣቢያዎች ያለውን 1500 የመንግስት አምቡላንስ ቁጥር ወደ 4500 ያሳድገዋል ተብሏል።

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶች፤ ወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ጤና ቡድን አስተባባሪ አቶ ዘነበ አካለ ለኢዜአ እንዳሉት ኢትዮጵያ በሚሊኒያም የልማት ግቦች እቅድ መሰረት በአንድ ወረዳ አንድ አምቡላንስ ለማዳረስ የተያዘውን እቅድ ማሳካት ችላለች።

 ያም ሆኖ አገሪቷ የእናቶች ሞት ቅነሳን ጨምሮ በሌሎች ጤና ዘርፍ ከያዘቻቸው እቅዶች ረገድ በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን 2012 ዓ.ም መጨረሻ በጤና ጣቢያ ደረጃ ቢያንስ አንድ አንቡላንስ እንዲኖር እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።

 ግዥያቸው እየተከናወነ የሚገኘውና እስከ ሰኔ 2010 ዓ.ም ለጤና ተቋማት የሚተላለፉት ሶስት ሺህ አምቡላንሶች ይህን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ይናገራሉ።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ አምቡላንሶቹ ስራ ሲጀምሩ ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የእናቶችን ሞት በመቀነሱ ረገድ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል።

ከሚገዙት ሶስት ሺህ አምቡላንሶች ውስጥም 1 ሺህ 500 ህዝቡ ባዋጣው ሲሆን ቀሪዎቹ በመንግስት የተገዙ ናቸው።

መንግስት በአገር አቀፍ ደረጃ የአምቡላንስ ቁጥር እንዲጨምር ከሚሰራው ተግባር በተጨማሪ የህብረተሰቡ ተሳትፎም ትልቅ መሆኑን በመግለጽ ግዢውና ክፍፍሉም የህብረተሰቡን ተሳትፎ ታሳቢ ያደረገ እንደሚሆን ተገልጿል።

 በየክልሉ ከሚገኙ ጤና ተቋማት ጋር በመሆን የአምቡላንሶችን ቁጥር ለመጨመር በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ እያሳየ ያለውን ተነሳሽነትንም አድንቀዋል።

 በቀሪው ሁለት አመት ተኩልም በሁሉም የአገሪቷ ጤና ተቋማት አንድ አምቡላንስ እንዲኖር መንግስት ለያዘው እቅድ ስኬት ህብረተሰቡ እንዲያግዝ መልዕክት አስተላልፈዋል።

 በኢትዮጵያ ከአራት ሺህ በላይ ጤና ጣቢያዎችና ከ300 በላይ ሆስፒታሎች እንደሚገኙ የጤና ጥበቃ መረጃ ያሳያል።

 

 

 

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2010 አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት በትምህርት ዘርፍ ለሚያከናውነው ተግባር የትምህርቱ ማህበረሰብ ትብብር እንዲያደርግ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ጥሪ አቀረበ።

 ማህበሩ ለኢዜአ በላከው የመልካም ምኞት መግለጫ እንዳመለከተው፤ በአሁኑ ወቅት ከአገሪቷ ህዝብ አንድ ሶስተኛው ወጣት በትምህርት ተቋማት ይገኛል።

 ይህ ወጣት አገሩን የሚያገለግል በህግና በስርዓት የሚመራ እንዲሁም በእውቀት የታነጸ መሆን እንዳለበት በመግለጫው ሰፍሯል።

 በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንደ ሌላው ዘርፍ ሁሉ ለትምህርት ዘርፍም ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡት እምነቱን ገልጿል።

 በተመሳሳይም መምህራን ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች የተጀመሩ ምላሾችን እንደሚያስቀጥሉም እንዲሁ።

 በመሆኑም መምህራን፣ ርዕሰ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮችና አጠቃላይ የትምህርቱ ማህበረሰብ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለሚያከናውኗቸው ተግባራት ትብብር እንዲያደርጉ ማህበሩ ጥሪ አቅርቧል።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን