አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 02 April 2018

 

አዲስ አበባ መጋቢት 24/2010 በዘንድሮው የመስኖ ልማት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር  በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ብርሃኑ ወቅታዊውን የግብርና ስራ አስመልክተው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በመላው አገሪቷ በዘንድሮ ዓመት በመስኖ ለማልማት ከተያዘው መሬት አብዛኛውን በዘር ተሸፍኗል።

ሚኒስቴሩ አርሶ አደሩን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅና ከተለመደው የአመራረት ስራ እንዲላቀቅ ቀደም ብሎ በቂ ዝግጅት ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ማከናወኑን ገልጿል። 

በግብርና ልማት ጣቢያ ሥር ለሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች ውሃን መሰረት ባደረገ የግብርናና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ትኩረት እንዲያደርጉም ሥልጠና መሰጠቱን ጠቅሰዋል።  

በተሰራው የዝግጅት ስራም ካለው 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ መሬት ውስጥ አብዛኛው በዘር መሸፈኑን አስረድተው፤ በመጀመሪያው ዙር የመስኖ ልማት ስራም 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።

አርሶ አደሩ የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ሰብሎችን፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችንና በገበያ ተፈላጊና የተሻለ ገቢ የሚያስገኙ ምርቶችን በማምረት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የመስኖ ልማትን በስፋት በመጠቀሙ ላይ ከሚታዩት ተግዳሮቶች ውስጥ የአርሶ አደሩ ከልማዳዊ አሰራር አለመውጣት፣ የሚገኙ የውሃ አማራጮችን በአግባቡ አለመጠቀምና የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን አለመዳበር መሆኑን አስረድተዋል።

ችግሩን ለመፍታትም በተጀመረው የገንዛቤ ማስጨበጫ ስራና የቴክኖሎጂ አቅርቦት የመስኖ ስራ መሻሻል ማሳየቱንና፤ በዘንድሮ ዓመትም ከመስኖ ልማት 469 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ከመስኖ ልማት በተጨማሪ በዋና ዋና የበልግ አብቃይ አካባቢዎች ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት የታረሰ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ከ400 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈን አቶ አለማየሁ ተናግረዋል።

በያዝነው ዓመት በአብዛኛው የበልግ አብቃይ አካባቢዎች ለግብርና ሥራዎች ምቹ የአየር ሁኔታ መኖሩን ሚኒስቴሩ ከሚቴዎሮሎጂ ኤጀንሲ መረጃ መግኘቱን ገልጸዋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 24/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያዊነት ላይ ያላቸው አመለካከት አገራዊ መግባባትን እንደሚያመጣ አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ።

ለአገራችን ለውጥም ህብረተሰቡና ከላይ እስከ ታች ያለው አመራር ከሳቸው ጎን ሊቆም እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሰየም ተከትሎ ኢዜአ በአዲስ አበባ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ንግግር ሰላምና አንድነትን የሚሰብክ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ካለው አለመረጋጋትና ግጭት አኳያም ያደረጉት ንግግር ለአንድነቱ ጠቃሚ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የከተማው ነዋሪ አቶ በቀለ ባልቻ በሰጡት አስተያየት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ያሰፈሩት አዲስና በጣም የሚደነቅ ሀሳብ ነው፤ በሳል የሆነ አካሄድና ንግግር ነው የታየባቸው። ግጭቶችና ሰላም መደፍረስን  የሚያስታርቁ ነገሮችን ነው የተናገሩት፤ የኢትዮጵያ እዚህ መድረስ  አባቶች የከፈሉት መስዋዕትነት እንደሆነና ይሄ መቀጠል እንዳለበት የተናገሩት ንግግር በጣም የሚደነቅ ነው  ያሉት፡፡ 

የአምስተኛ አመት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ኢንጂነሪንግ ተማሪው ብሩህይሁን ኪዳኔ

በበኩሉ ''በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካጋጠመው  ችግር አንጻር የተናገሩት ኢትዮጵያዊነት የሚባለው ነገር በጣም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፤ እዚያ ላይ በደንብ አትኩሮት ሰጥተው መናገራቸው ደስ ይላል''  ብሏል፡፡

ያስተላለፉት መልዕክት ወደ ተግባር ከተቀየረ በአገሪቷ የተሻለ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተግባር እንሰራዋለን ያሉትን ፍሬያማ ለማድረግ ህብረተሰቡና በየደረጃው ያሉ አመራሮች ተሳትፎና ድጋፍ ወሳኝ እንደሆነም በአስተያየታቸው አስፍረዋል። 

''እኛ ደግሞ ያንን ሰው ሲመረጥ ሊሰራ ያቀደውን እቅድ አብረን ከሰራን ያ ሰው ውጤታማ የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም፤ ህብረተሰቡም ከሳቸውም በታች ያሉ አመራሮች የሳቸውን ራዕይ ይዘው ከሰሩ ለውጥ የማይመጣበት ምንም ምክንያት አይኖርም።" ነው የምትለው  ወይዘሪት ኤልሳ ስዩም

ከዚሁ ጋር ተያይዞም ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በኢትዮጵያ መታየቱና በፍቅር መፈጸሙ በዲሞክራሲው ላይ መሻሻል መኖሩን የሚያሳይ ነው ሲሉ አስረድተዋል ነዋሪዎቹ።

በመጨረሻም አስተያየት ሰጪዎቹ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት ደስ መሰኘታቸውን ገልጸው መልካም የስራ ዘመን እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።  

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 24/2010 አፍሮ ፅዮን ኮንስትራክሽን ድርጅት የቦሌ አጠቃላይ ሆስፒታልን ለመገንባት ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር ስምምነት ተፈራረመ።

የከተማዋ አስተዳደር በ2007 ዓ.ም በቦሌ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች ሦሰት ሆስፒታሎችን ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጡ ይታወሳል።

አስተዳደሩ እንደገለጸው፤ በሦስቱ ክፍለ ከተሞች ላይ ከፍተኛ የሕዝብ ቁርጥና ከዚህ ቀደምም ሆስፒታል የሌላቸው በመሆናቸው ግንባታ እንዲካሄድ ተወስኗል። 

ይሁን እንጂ የሦስቱም ሆስፒታሎች ግንባታ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አለመጀመሩን የኢዜአ ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ ባደረገው ቅኝት ማረጋገጡን ከዚህ በፊት በሰራው ዘገባ መሸፈናችን ይታወቃል።

ለዚህም ደግሞ የመዲናው ጤና ቢሮ ግንባታው የዘገየው በዲዛይን ማሻሻያና ግንባታውን የሚያካሂዱ ተጫራጮች ባለመኖራቸው መሆኑን በምክንያት አስቀምጧል።

በዛሬው ዕለት ቢሮው ከሦስቱ ሆስፒታሎች አንዱ የሆነውን የቦሌ አጠቃላይ ሆስፒታልን ግንባታ ለማስጀመር ከአፍሮ ፅዮን ኮንስትራክሽን ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።

ሆስፒታሉ በመጀመሪያ ዲዛይኑ ላይ ማሻሻያ ሲደረግበት በተያዘለት የጊዜ ገደብ አለመጀመሩን የቢሮው ሀላፊ ዶክተር ጀማል አደም ተናግረዋል።

የቀድሞ ዲዛይን የከተማዋን ሕዝብ ብዛትና የወደፊት እድገት የማይመጥን ነበር ያሉት ኃላፊው  በአዲሱ ዲዛይን ላይ የዘርፉ ባለሙያዎች በስፋት መክረውበት መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በዚህም መጀመሪያ ከቀረበው ዲዛይን 98 በመቶ ማሻሻያ መደረጉን ጠቁመዋል።

በሰሚት አካባቢ በ30 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፈው ይኸው ሆስፒታል ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚገነባ ሲሆን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።

ሆስፒታሉ ባለ ስምንት ወለል ህንፃና አጠቃላይ 740 የመኝታ ክፍሎች ይኖሩታል።

ዘመናዊ የታካሚዎችን መረጃ የሚይዝ ቴክኖሎጂ፣ ለድንገተኛ ህክምና የሚሆን የሄሊኮፕተር ማረፊያን ጨምሮ ከ1 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች ማቆሚያ ስፋራ ይዟል።

በሌሎች ሆስፒታሎች የሌሉ ለአስታማሚዎች ማረፊያ፣ መመገቢያና ማብሰያ ሥፍራም በዲዛይኑ ተካቷል።

ተቋራጩ ከሁለት ወር በኋላ ግንባታውን እንደሚጀምርና ግንባታው በሦስት ዓመት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ኃላፊው ጠቁመዋል።

የተቋራጩ የአፍሮ ፅዮን ኮንሰትራክሽን ባለቤት አቶ ሲሳይ ደስታ በበኩላቸው ለግንባታ መጓተት ምክንያት የሚሆነውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመግታት ከመንግሥት የድጋፍ ይሁንታ መገኘቱን ገልጸዋል።

በመጀመሪያው ጨረታ ተጫራች ያልተገኘላቸው በንፋስ ስልክና በኮልፌ ቀራንዮ ለሚገነቡት ሁለቱ ሆስፒታሎች ሁለተኛ ጨረታ ወጥቶ ከአራት ወር በኋላ አሸናፊው እንደሚታወቅ ዶክተር ጀማል ተናግረዋል።

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 24/2010 አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በሥራ ዘመናቸው ለኢትዮጵያ ስኬታማ ተግባራትን እንዲያከናውን ኅብረተሰቡ በቂ ጊዜና ድጋፍ ሊሰጣቸው እንደሚገባ የአገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ተናገሩ።

ዛሬ የተካሄደው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለአገር ሰላም የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑንም የኃይማኖት አባቶቹ ተናግረዋል።

ዶክተር አቢይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውን የተሰማቸውን ደስታ የገለጹት  የኃይማኖት አባቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ አዎንታዊ ለውጥ ያመጣሉ የሚል ተስፋ መሰነቃቸውን ገልጸዋል።

አስተያየት የሰጡት የእስልምና እና የክርስትና ኃይማኖት አባቶች እንደተናገሩት፤ የሥልጣን ሽግግሩ በሠላማዊ መንገድ መካሔዱ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የሚኖረው እንደምታ የጎላ ነው።

ኩነቱ ለቀጣዩ ትውልድ ትምህርት ሰጪ እንደሆነም የኃይማኖት አባቶቹ አብራርተዋል።

በመሆኑም ሁሉም ባለበት አካባቢ ለሰላምና ልማት እየተረጋጋ ነገሮች ወደ ቀድሞ ጤናማ ጉዟቸው እንዲመለሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሊያግዟቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሼህ ኡመር ይማም እንደተናገሩት ኢትዮጵያችን በለፉት ሁለት ሶስት አመታት የሰላም እጦት አጋጥሟታል  የዛሬው ቀን ግን ትልቅ ሰላም በአገሪቱ እንደሚያመጣ እምነታቸውን ተናግረዋል፡፡

ስልጣን ማለት ለህዝብ ማገልገል እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ይህ ትምህርት ሰጪ መሆኑን የጠቆሙት ሼህ ኡመር ጥሩ ካለፉት ሁለት ሶስት አመታት የተሻለ ሰላም ብሩህ ተስፋ የሚታይበት  አመት ይሆናል ብለዋል

ቀሲስ በላይ መኮንን በበኩላቸው እንደተናገሩት ከህዝብ የሚጠበቀው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስተርን መስማት ማዳመጥ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የቦረና አባ ገዳ ኩራ ጃርሶ ኩራ በበኩላቸው ክስተቱን ካደነቁ በኋላ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲሰፍን ጠቁመው ይሕ ሒደት ለአገር ሰላም ያመጣል ብሎ ስለሚጠብቁ የተሰማቸውን የደስታና የተስፋ ስሜት ገልጸዋል።

አዲሱ አመራር ለአገሪቱ ስላም ብልጽግና በላቀ የኃላፊነት ስሜት መሥራት እንደሚገባው የተናገሩት አባ ገዳው ወጣቱም ለውጥ ለማምጣት ሲያስብ ከአመጽ ነጻ የሆነ መንገድ መምረጥ አለብት ብለዋል።

ዛሬም ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ድጋፍ ማድረግና የአካባቢውን አመራር ማዳመጥ አለበት ሲሉም አመልክተዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 24/2010 ኢትዮጵያዊያን ከታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚጠብቁትን  ጥቅም እንዲያገኙ ለሰላም ዘብ መቆም እንደሚገባ የፌደሬሽን  ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ያለው አባተ ተናገሩ።       

የግድቡ  ግንባታ የተጀመረበት ሰባተኛ ዓመት በዓል በቤንሻንጉል ጉሙዝ  ክልል ጉባ ወረዳ እየተከበረ ነው።  

"የታላቁ ህዳሴ ግድባችን የአገራችን ሕብረ ዜማ የህዳሴያችን ማማ'' በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ በሚገኘው በዓል ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ዲፕሎማቶች፣ የኃይማኖት አባቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ነው። 

አፈ ጉባዔ ያለው አባተ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ "ግድቡ ኢትዮጵያውያን በጋራ እየተረባረቡበት ያለ የአንድነታችን ነጸብራቅ ፕሮጀክት ነው።"

''ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ አህጉራዊ ፕሮጀክት ነው'' ያሉት አፈጉባዔው ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኃይል ለማስተሳሰር የጀመረችውን ጉዞ እውን በማድረግ በኩል የላቀ ሚና እንደሚኖረውም አንስተዋል። 

በግድቡ ላይ የታየውን ብሄራዊ መግባባት በማስቀጠል እጅ ለእጅ ተያይዞ ለአንድ አገራዊ ዓላማ ወደፊት መራመድ ይገባል ያሉት አቶ ያለው  ግድቡን ከዳር ለማድረስ ኀብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

''በዚህ ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ታሪክ እየሰራ በመሆኑ አንዱ ነጋሪ አንዱ አድማጭ ሊሆን አይችልም'' ሲሉም ተደምጠዋል።   

ዜጎች እስካሁን ባደረጉት ድጋፍ ግድቡ የሚያጓጓ  ደረጃ ላይ መድረሱን የተናገሩት አፈጉባዔው ''ይህ የማይዋጥላቸው አካላት ሠላምን ለማደፍረስ መንቀሳቀሳቸው አይቀርም '' ብለዋል። 

በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን ግድቡ የሰላም ምንጭ መሆኑን በመተማመንና በማሳመን ሰላምን መጠበቅና የህዳሴውን ዘመን ከፍታ ሊያረጋግጥ ይገባል ብለዋል።  

የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያ በበኩላቸው፤ ግድቡ ኃይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ መግባባትን የፈጠረና የፀረ ድህነት ትግሉን ያጠናከረ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል። 

መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው የላቀ ትኩረት በርካታ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው መጠነ ሰፊ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለፁት ወይዘሮ ፍሬነሽ ግድቡ በአገሪቷ እየጨመረ የመጣውን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን የኃይል ፍላጎት ጥያቄን ከመመለስ ባሻገር የምስራቅ አፍሪካ አገራትን የኃይል ፍላጎትን ማሟላትና የአካባቢውን ስነ ምህዳር ለመጠበቅ ጉልህ ሚና ያለው አህጉራዊ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።  

ግድቡ ጥራቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ሙቀቱ ሳይበግራቸው ሌት ተቀን እየተጉ ላሉት የፕሮጀክቱ አመራርና ሰራተኞችም አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር አዜብ አስናቀ በበኩላቸው የግድቡ ግንባታ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ረገድ የማይተካ ጠቀሜታ አስገኝቷል። 

የግንባታውን ፍፃሜ እውን ለማድረግ እጅግ በሚያኮራና በጠለቀ አገራዊ ፍቅርና ስሜት ቀንና ሌሊት ርብርብ እያደረጉ ላሉት የፕሮጀክቱ አመራሮች፣ ሰራተኞች እና ለፀጥታ አካላት ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል።

መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሃይል የማመንጨት አቅሙ ከ6 ሺህ ሜጋ ዋት  በላይ ነው፡፡

የግድቡን ግንባታ የሲቪል ስራዎቹን የሚያካሄደው ተቋራጭ ሳሊኒ ኢምፐርጂሎ የተሰኝ የጣሊያን ኩባንያ ሲሆን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች ደግሞ የኢፌዴሪ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ነው፡፡   

ግድቡን የማማከር ስራም የፈረንሳዩ ትሬክቶቤል ኢንጂነሪንግና የጣሊያኑ ኤሌክትሮ ኮንሰልት በጋራ እያከናወኑት ነው፡፡፡

አሁን ላይ በግድቡ ግንባታ እየተሳተፉ ያሉ ኢትዮጰያውያን ቁጥር 10 ሺህ 672 ሲሆን ከ30 አገራት የተውጣጡ 317 የውጭ ዜጎችና

በአሁኑ ሰዓት ከ9 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያንና 260 የውጭ ሃገር ዜጎች በተለያየ የሙያ ደረጃ ተሰማርተዋል፣ 2 ሺህ 300 የግንባታ ማሽኖችም በግንባታው ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ አፈጻጸም ከ 65 በመቶ በላይ መድረሱ በዚሁ ጊዜ ተገልጿል።  

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 24/2010 የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት (ጨፌ) መደበኛ ጉባዔ ሚያዝያ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ይካሄዳል።

የምክር ቤቱ 3ኛ ዓመት፣ 5ኛ የጨፌ የስራ ዘመንና 7ኛ መደበኛ ጉባዔ  ከየካቲት 30 እስከ መጋቢት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ሊካሄድ የታሰበው ላልተወሰነ ጊዜ መተላለፉ ይታወቃል።

በመሆኑም "መደበኛ ጉባዔው ከሚያዝያ 4 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በአዳማ ገልማ ጨፌ/አባ ገዳ አዳራሽ ይካሄዳል" ሲል የኦሮሚያ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ የጨፌ ጽህፈት ቤትን ዋቢ በማድረግ ገልጿል።

በዚህም መሰረት የጨፌው አባላት ሚያዝያ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ከ8:30 ጀምሮ ሪፖርት ማድርግ ይጠበቅባቸዋል በማለት ጥሪ አቅርቧል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 24/2010 በዘንድሮው የመስኖ ልማት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር  በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ብርሃኑ ወቅታዊውን የግብርና ስራ አስመልክተው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በመላው አገሪቷ በዘንድሮ ዓመት በመስኖ ለማልማት ከተያዘው መሬት አብዛኛውን በዘር ተሸፍኗል።

ሚኒስቴሩ አርሶ አደሩን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅና ከተለመደው የአመራረት ስራ እንዲላቀቅ ቀደም ብሎ በቂ ዝግጅት ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ማከናወኑን ገልጿል። 

በግብርና ልማት ጣቢያ ሥር ለሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች ውሃን መሰረት ባደረገ የግብርናና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ትኩረት እንዲያደርጉም ሥልጠና መሰጠቱን ጠቅሰዋል።  

በተሰራው የዝግጅት ስራም ካለው 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ መሬት ውስጥ አብዛኛው በዘር መሸፈኑን አስረድተው፤ በመጀመሪያው ዙር የመስኖ ልማት ስራም 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።

አርሶ አደሩ የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ሰብሎችን፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችንና በገበያ ተፈላጊና የተሻለ ገቢ የሚያስገኙ ምርቶችን በማምረት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የመስኖ ልማትን በስፋት በመጠቀሙ ላይ ከሚታዩት ተግዳሮቶች ውስጥ የአርሶ አደሩ ከልማዳዊ አሰራር አለመውጣት፣ የሚገኙ የውሃ አማራጮችን በአግባቡ አለመጠቀምና የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን አለመዳበር መሆኑን አስረድተዋል።

ችግሩን ለመፍታትም በተጀመረው የገንዛቤ ማስጨበጫ ስራና የቴክኖሎጂ አቅርቦት የመስኖ ስራ መሻሻል ማሳየቱንና፤ በዘንድሮ ዓመትም ከመስኖ ልማት 469 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ከመስኖ ልማት በተጨማሪ በዋና ዋና የበልግ አብቃይ አካባቢዎች ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት የታረሰ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ከ400 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈን አቶ አለማየሁ ተናግረዋል።

በያዝነው ዓመት በአብዛኛው የበልግ አብቃይ አካባቢዎች ለግብርና ሥራዎች ምቹ የአየር ሁኔታ መኖሩን ሚኒስቴሩ ከሚቴዎሮሎጂ ኤጀንሲ መረጃ መግኘቱን ገልጸዋል።

Published in ኢኮኖሚ
Published in ቪዲዮ

ጅማ መጋቢት 24/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሀገራቸውን ለማልማትና  ህዝባቸውን ለመጥቀም በትጋት ያገለግላሉ ብለው እንደሚያምኑ  ወላጅ አባት ፣ ወንድማቸውና  የቅርብ ጓደኛቸው ተናገሩ።

ዶክተር አብይ ዛሬ  በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጰያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመሰየማቸው ዘመዶቻቸውና የቅርብ ጓደኞቻቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወላጅ አባት የሆኑት የ94 ዓመቱ የእድሜ ባለፀጋ አቶ አህመድ አሊ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት "ማንኛውም ወላጅ ልጁ ትልቅ ደረጃ ሲደርስለት እንደሚደሰተው ሁሉ እኔም ተደስቻለሁ" ብለዋል ።

አቶ አህመድ በማያያዝ "እናቱ በህይወት በነበረችበት ወቅት ይህ ልጅ ትልቅ ደረጃ ይደርሳል ስትለኝ  ፈጣሪ ያውቃል ብዬ ምላሽ ሰጥቼያት ነበር " ሲሉም አስታውሰዋል፡፡

ትልቅ አደራን የተረከቡት ልጃቸው ዶክተር አብይ  ሀገራቸውንና ህዝቡን በቅንነት በማገልገል ውጤታማ እንዲሆኑ ፈጣሪ እንዲረዳቸውም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

"ዶክተር አብይ ቤተሰቡን፣ ህዝቡንና ሀገሩን የሚወድ ሰው ነው" ያሉት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ታላቅ ወንድም አቶ ዳፊስ  አህመድ ናቸው፡፡

ዶክተር አብይ በልጅነታቸው  ከእድሜ እኩያቸው ይልቅ ከታላላቆቻቸው ጋር መዋል ያዘወትሩ እንደነበር አስታውሰው  ሀገርቸውንና ህዝባቸውን በትጋት በማገልገል በስራቸውም ስኬታማ እንዲሆኑ  ምኞታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

የአጋሮ ከተማ ነዋሪና የዶክተር አብይ የቅርብ ጓደኛ አቶ ቲጃኔ አባዲጋ በበኩላቸው ዶክተር አብይ ለሀገር ዴሞክራሲያዊ አንድነት፣እድገትና ብልጽግና የሚበጁ ትክክለኛ ሰው መሆናቸውን ገልጸዋል።

አዲሱ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ  ለትምህርት በነበራቸው ትጋት አርአያ እንደነበሩም አስታውሰዋል ።

አስተያየት ሰጪዎቹ ዶክተር አብይ የኢትዮጰያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመሰየማቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው  ሀገራቸውን ለማልማትና  ህዝባቸውን ለመጥቀም በትጋት ያገለግላሉ ብለው  እንደሚያምኑ  ተናግረዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ጎንደር መጋቢት24/2010 አዲሱ የኢትዮጰያ ጠቅላይ ሚኒስትር በህዝቦችዋ ተጋድሎ ተከብራ የኖረች ኢትዮጵያ  አንድነቷ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለሚያደርጉት ጥረት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ በጎንደር ከተማ የስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስተሩ በድርጅታቸውና በመላው ህዝብ ያገኙትን ድጋፍና ተቀባይነት ወደ መልካም እድል በመቀየር ታሪክና ህዝብ የጣለባቸውን የመሪነት ሚና በብቃት ይወጣሉ ብለው እንደሚጠብቁ ነዋሪዎቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል ።

የጎንደር ከተማ የጀግኖች አርበኞች ማህበር አባል አባት አርበኛ ዋኘው ተበጀ ጀግኖች አባት አርበኞች ለሀገሪቱ የከፈሉትን መስዋእትነት በማስታወስ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለታሪክ የሰጡት ግምት የሚያኮራ መሆኑን ተናግረዋል ።

"ኢትዮጵያውያን በአድዋ፣ በመተማ፣ በካራማራ ብሎም በባድመ ለነጻነታቸውና ለአንድነታቸው የከፈሉት መስዋእትነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቅ ትርጉም መሰጠቱ ለጀግኖች አርበኞች ትልቅ ኩራት ነው " ብለዋል ።

በትውልድ ቅብብሎሽ ታፍራና ተከብራ ለዘመናት የኖረች ሀገር የመምራት ኃላፊነትን በሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የተረከቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ  የሀገራቸውን አንድነት አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ እምነታቸው መሆኑን ነዋሪዎቹ ገለፀዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱን አንድነት ለማጠናከር በሚያደርጉት ጥረትም የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ነዋሪ ወጣት ክብረት ተቀባ በበኩሉ "አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የወጣቱ ሰርቶ የመለወጥ ራእይ እንዲሳካ  ቀዳሚ ተግባራቸው አድረገው ሊሰሩ ይገባል " ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህቺ ሀገር "ለወጣቶቹዋ ተስፋ የምትሰጥ እንጂ ተስፋ የምታስቆርጥ አይደለችም’’ በማለት የተናገሩትን ንግግር ወደ ተግባር ሊቀይሩ እንደሚገባ ተናግሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዛሬው ታሪካዊ የህዝብ ኃላፊነት ለመብቃታቸው መሰረት ከሆኗቸው ምከንያቶች መካከል የወላጅ እናታቸውንና የባለቤታቸውን መልካም ምሳሌ መግለፃቸው ለሴት ልጅ ያላቸውን ክብር ያመለካተ ነው " ያሉት ደገሞ ወይዘሪት ሙሉዬ ድረስ ናቸው፡፡

"ባለፉት አመታት የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል በጎ ጅምሮች ተከናውነዋል"ያሉት  ወይዘሪት ሙሉዬ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ለዚህ ታላቅ ኃላፊነት ያበቁዋቸው ሴቶች መሆናቸውን የሰጡት ምስክርነት ለሴቶች የበለጠ ትኩረት በመስጠት ጅምሩን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ አመላካች መሆኑን ተናግረዋል ።

"የጠቅላይ ሚኒስትሩን ታሪካዊ ንግግር የሞራል ስንቅ በማድረግ በተሰለፍኩበት የስራ መስክ ውጤት ለማስመዘግብ ጠንክሬ ለመስራት ዝግጁ ነኝ" ሲሉም ወይዘሮ ሙሉዬ ተናግረዋል፡፡

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አድማስ ደሞዜ በበኩላቸው ''አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቃልን ወደ ተግባር በማሸጋገር ህዝቡን ለአመጽና ለብጥብጥ የሚዳረጉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት መፍትሄ እነዲሰጣቸው ሊያደርጉ  ይገባል'' ብለዋል።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን