አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 17 April 2018

ሚያዝያ 9/2010 በባህር ዳር ከተማ የሚካሄደውን ሰባተኛውን የጣና ከፍተኛ የደህንነት ፎረም ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅት መጠናቀቁን የፎረሙ አዘጋጅ ኮሚቴ አስታወቀ።

የአማራ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤት የዲያስፖራ፣ ህዝብ ግንኙነት፣ ፕሮቶኮል ዳይሬክተርና የአዘጋጅ ኮሚቴው ፀሐፊ አቶ አውላቸው ማስሬ እንደገለጹት ፎረሙ ከሚያዝያ 13 እስከ 14 ቀን 2010 ዓ.ም ይካሄዳል።

"በአፍሪካ ሃገራት ሰላምና ደህንነት ዙሪያ የሚመክረው የጣና ፎረም ተጀምሮ በስኬት  እንዲጠናቀቅ ከወዲሁ ተገቢው ዝግጅት ተጠናቋል" ብለዋል።

እንግዶች ተቀብለው የሚያስተናግዱ አስር ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ተለይተው እንዲሰናዱ መደረጉን ያመለከቱት  አቶ አውላቸው

በፎረሙ እስከ 250 የሚደርሱ የተለያዩ ሃገራት መሪዎች፣ ምሁራንና ተመራማሪዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

እንግዶቹ ከአርብ ጀምሮ ባህር ዳር እንደሚገቡና ከፍተኛ የክልሉ የስራ ኃላፊዎች ከግንቦት 20 ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጀምሮ አቀባበል ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የመስተንግዶ፣ የፀጥታ፣ የትራንስፖርትና ሌሎችንም ስራዎች የሚያስተባበሩ አብይና ንፁሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመው እየሰሩ መሆናቸውን አመለክተዋል።

"በአፍሪካ ሀገራት ሰላምና ደህንነት የሚመክረው ፎረም በባህር ዳር መካሄዱ በአካባቢው ያለውን አስተማማኝ ሰላምና ከተማዋ ለቱሪዝም ያላትን ምቹነት ለተሳታፊዎች ለማሳየት ሰፊ እድል ይፈጥራልም" ብለዋል ጸሐፊው።

ለእንግዶች ማረፊያ ከተመረጡት ሆቴሎች መካከል የብሉ ናይል ሪዞርት ሆቴሎች ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ዘውዱ እንዳሉት  እንግዶች የሚስትናገዱባቸውን ቦታዎችን ደረጃቸውን ባሟላ መልኩ በማመቻቸት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።

ደረጃውን የጠበቀ የመስተንግዶ ስፍራዎችንና መገልገያዎችን  አዘጋጅተው ለእንግዶች ምቹ ማድረጋቸውን የገለጹት ደግሞ የግራንድ ሪዞርትና ስፓ ባህር ዳር ዋና ስራስኪያጅ አቶ ብዙአየሁ ተመስጌን ናቸው።

በሰባተኛው የጣና ፎረም አፍሪካውያን የአህጉሪቱን  ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ የአፍሪካን ህብረት የፋይናንስ አቅም ማጎልበት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግ

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 9/2010 የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የአረጋውያንን የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራቱን ገለጸ።

 በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ27ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ 26ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘው የአረጋዊያን ቀን የፊታችን ሐሙስ ይጠናቀቃል።

 የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮው ከኢትዮጵያ አረጋውያን ማህበር ጋር በመሆን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አረጋውያንን በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳዮች ተጠቃሚ ለማድረግ በልማታዊ ሴፍቲኔት፣ በማህበራዊ ጥበቃ ፈንድ እና በስራ ዕድል ፈጠራ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

 በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የቢሮው ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ግዛው እንዳሉት፤ የአረጋዊያንን የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

 የአረጋዊያን የማህበራዊ ጥበቃ፣ የተለያዩ ድጋፎች ተጠቃሚ እንዲሆኑና የበኩላቸውን ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲወጡ ፓኬጅ ተቀርጾ እየተተገበረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

 በከተማዋ በልማታዊ ሴፍቲኔትና በሌሎች የድጋፍ ዘርፎች ተጠቃሚ ከሆኑ 34 ሺህ ሰዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት አረጋዊያን መሆናቸውን ተናግረዋል።

 አረጋዊያን የማህበራዊ ጥበቃ ፈንድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በአደረጃጀት ተቀርጾ እየተተገበር ይገኛል ያሉት አቶ ኤፍሬም ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም በከተማዋ ያሉ አረጋዊያን የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።

 ቢሮው ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆኑን በከተማዋ የአረጋዊያን ቁጥር ና ያለባቸውን ችግሮች ለመለየት የሚያስችል ጥናት ከሁለት  ወራት በኋላ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

 በከተማዋ አረጋውያንን ተጠቃሚ ለማድረግ ህብረተሰቡ በቂ ዕውቀት ኖሮት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ለማስቻል በተለያዩ መድረኮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

 የአረጋውያን ቀን ሲጠቃለል አረጋዊያን፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ የፌዴራልና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሚሌኒዬም አዳራሽ ይከበራል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 9/2010 በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ሕዝቦችን የማስተሳሰር ስራ በበቂ መጠን አለመሰራቱ ተገለጸ።

የአማራ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ከፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።  

ውይይቱ 'የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝምና ዲሞክራሲያዊ አንድነት ግንባታ ዕድሎችና ፈተናዎች' በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደ ሲሆን ምሁራን፣ የኃይማኖት ተቋማት ተወካዮች፣ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችና ተማሪዎች ተሳትፈዋል።  

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር አሰፋ ፍሰሃ በፈዴራል ስርዓቱ የተገኙ ስኬቶችና ያጋጣሙ ችግሮች ላይ የውይይት መነሻ ጸሁፍ አቅርበዋል።      

ዶክተር አሰፋ በጹሁፋቸው እንደገለጹት፣ የፌደራል ስርዓት ለአገር ግንባታ ያለው ሚና ከፍተኛ ቢሆንም ባለፉት ዓመታት ሕዝቦችን በማስተሳሰር በኩል የተሰሩ ሥራዎች በቂ አይደሉም።

''ስርዓቱ በአግባቡ ካልተተገበረ አደጋም ሊሆን ይችላል'' ያሉት መምህሩ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የታዩ አለመረጋጋቶች የዚህ ማሳያ መሆናቸውን አክለዋል።     

የክልልና የፌዴራል መንግስት በጋራ ጉዳዮች ላይ አብሮ የመወሰን ክፍተት እንደነበር ጠቁመው የክልሎች የተመጣጠነ ውክልና ጉዳይ ትኩረት እንደሚያሻ ጠቁመዋል።  

ኢትዮጵያዊነት ላይ የጋራ ስምምነት እንደሚያስፈልግ ያነሱት ዶክተር አሰፋ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበረሰብና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።         

ፌዴራሉም ሆነ ክልሎች ከሁለቱም ወገኖች የሚወጡ ህጎችን ማክበር እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በሰጡት አስተያየት 'የምንከተለው የፌዴራሊዝም ስርዓት አንድነት የሚያመጣ ሊሆን ይገባል' ብለዋል።

''በፌዴራል ደረጃ የአንድነት እሴቶች ላይ የሚጠበቀውን ያህል አልተሰራም'' ያሉት ዲያቆን ዳንኤል የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር መልካም እሴቶች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚያሻ አጽንኦት ሰጥተዋል።    

ጠንካራ የፍትህ ተቋማት፣ ርዕዮተ ዓለም ላይ የሚያተኮሩ ፓርቲዎች ምስረታ፣ በነጻነት ሀሳብን የሚያስተናግዱ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም አገራዊ እሴቶች ላይ የሚሰሩ የትምህርት ተቋማት መፍጠር ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።     

ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ የምርጫ ጉዳይ አይደለም በማለት የስርዓቱን አስፈላጊነት ያነሱት ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ሰይፉ ክንፉ ናቸው። 

'እኔ ብቻ ነኝ ትክክል' የሚል አስተሳሰብ ስርዓቱ በአግባቡ እንዳይተገበር እንደሚያደርግ ገልጸው የተለያየ የሀሳብ ፍጭት ለአገር ግንባታ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልጸዋል።      

ከዚህ ጋር በተያያዘ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መብትና ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲያውቁ በማድረግ ትውልድን የማነጽ ሥራዎችን በኃላፊነት መወጣት አለባቸው ብለዋል።  

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ተወካይ አቶ አዳነ ጥላሁን በበኩላቸው ''የሕዝቦች አንድነት የሚረጋገጠው የዘረኝነት አስተሳሰብ ሲወገድ ነው'' ብለዋል።     

የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ውለታው በሰጡት ምላሽ በኢትዮጵያ ያለው ማንነት በራሱ ችግር አያመጣም ችግር የሚሆን አያያዝ ላይ በሚፈጠር ክፍተት ነው የሚል ሀሳብ አንጸባርቀዋል።      

በተለይ ክልሎች የማንነት፣ የኃይማኖት፣ የመሳሰሉ ጉዳዮች በአግባቡ መያዛቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ጠቁመው የብሄር ብሄረሰቦች ጥያቄዎችን ለመመለስ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።    

 

Published in ፖለቲካ

መቀሌ ሚያዝያ 9/2010 መንግስት ድህነትን ለማስወገድ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የምሁራን አቅም በአግባቡ እንዳልተጠቀመበት የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል አስታወቁ።

"ምሁርነታችን ለህዝባዊ ለውጥ" በሚል መሪ ቃል ለሶስት ቀናት የሚቆይ የምሁራን ኮንፈረንስ በመቀሌ ከተማ ተጀምሯል።

በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ ዶክተር ደብረጽዮን እንደተናገሩት ባለፉት ጊዜያት መንግስት የምሁራንን አቅም በሚገባ ባለመጠቀሙ በክልሉ የተጀመረውን የጸረ-ድህነት ትግል የሚፈለገውን ያክል ውጤት አላመጣም።

ክልሉን የሚመራው ህወሃት በቅርቡ ያካሔደው ግምገማም ይሔንኑ ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸው "የምሁሩን አቅም በሚፈለገው መንገድ አለመጠቀማችን ብቻ ሳይሆን ከምሁሩ ተራርቀን ቆይተናል"ብለዋል።

ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ደረጀ አሰፋ እንደገለጹት መንግስት የምሁራንን አቅም በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል መድረኩን ማመቻቸቱ ቀጣይ ስራዎችን በቅንጅት ለማከናወን ያስችላል።

ከክልሉ ግብርና ምርምር ማዕከል የመጡት ሌላው ተሳታፊ ወይዘሮ ሉቺያ ተኹሉ  እንደገለጹት መድረኩ ከአርሶ አደሩ ጋር በመተባበር የሚያደርጉትን የምርምር ስራ በምን አግባብ ሊያከናውኑት እንደሚገባ አቅጣጫ ሰጥቷቸዋል።

"ምሁራን ሲሰባሰቡ በማህበረሰቡ ያሉትን ችግሮች በጥልቀት እንዲመለከቷቸውና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን እንዲያስቀምጡ ያግዛሉ" ያሉት ደግሞ በመዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህር  ናይዝጊ አባይ ናቸው።

ለሶት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ኮንፈረንስ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ በትግራይና በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የክልሉ ተወላጅ ምሁራን ተሳታፊ ሆነዋል።

 

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 9/2010 በኢትዮጵያ የሚገነቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከኢኮኖሚ ዕድገት ባሻገር አገራዊ አንድነትን እያጠናከሩ መሆኑ ተገለጸ።

 ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እየተመዘገበ ቢሆንም ከድህነት ለመውጣት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መድፈር አስፈላጊ ነበር።

 በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የባቡር ትራንስፖርት፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ሌሎችም ታላላቅ ፕሮጀክቶች በክንውን ላይ ይገኛሉ።

 በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሃብት መምህሩ አቶ ፋሲል ጣሰው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ሃብትና የሰው ኃይል ተቀናብሮ የሚሰሩና ዜጎችን ከድህነት ለማውጣት የሚጀመሩ መሆናቸውን ያነሳሉ።

 እነዚህ ፕሮጀክቶች በሚሰሩበት ወቅት የሚፈጥሩት የስራ ዕድል እንዳለ ሆኖ ስራው ካለቀ በኋላ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር ወሳኝ ናቸው ይላሉ።

 በኢትዮጵያ የሚገነቡት  ግዙፍ ፕሮጀክቶች ትውልድን በማስተሳሰር የስልጣኔ ማቀላጠፊያ መሰረቶች ናቸው ሲሉ ይደመጣሉ ባለሙያው።

 በአገሪቱ እየተገነቡ ካሉት ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ አንድ ያደረገውና የይቻላል መንፈስን ያጠናከረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አንዱ ነው።

 ግንባታው ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ ሲጠይቅ መንግስትና ህዝብ በአንድነት ግድቡን ለመስራት በመነሳታቸው ስራው 65 በመቶ ደርሷል ።

 የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም እንደሚሉት የግድቡ የመጀመሪያ ጠቀሜታ የይቻላልና አንድነት መንፈስ መፍጠሩ ነው።

 በኢኮኖሚ ተጠቃሚነትም ከ11 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ግድቡን ከሚጎበኙ ዜጎች የሚገኘው ገቢ ለከተሞች መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡

 ግድቡ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ ለሀገሪቱና ለጎረቤት አገራት ኃይል በማቅረብ ተጨማሪ ገቢም ያስገኛል።

 ግድቡ ከጎረቤትና ከተፋሰሱ አገራት ጋርም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በመፍጠርና ልዩነትን ለማጥበብ  እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

 የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ተፈራ የባቡር መሰረተ ልማት ለመገንባት ከፍተኛ መዋዕለ-ነዋይ የሚጠይቅ ቢሆንም ከተገነባ በኋላ በቀላል ጥገና ከመቶ ዓመት በላይ ማገልገል እንደሚችል ይናገራሉ።

 በቅርቡ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር የንግድ እንቅስቃሴውን ከማሳለጥ አኳያ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

 የአገሪቱ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የወጪና ገቢ ንግድ የሚካሄደው በጅቡቲ በኩል በመሆኑ ይህንን በማቀላጠፍ በኩል ከአምስት በላይ የተለያዩ ጭነቶችን የሚያመላልሱ አንድ ሺህ  አንድ መቶ ተጎታች ባቡሮች አሉ።

 ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ 30 ባቡሮችም የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን ይህ የባቡር መስመር ቀጣዩን የኢኮኖሚ ዕድገት ታሳቢ ያደረገ ነው ይላሉ።

 ፕሮጀክቱ የበርካታ አርሶ አደሮችን መሬትና የከተማ ነዋሪውን ቤት የሚነካ ቢሆንም ህብረተሰቡ የወደፊት ጥቅሙን በማየት በመግባባት እየተሰራ ነው ብለዋል።

 የባቡር መሰረተ ልማት በአገር ውስጥ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን ብቻ ሳይሁን ሀገሪቱ ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር አፍሪካን በባቡር መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር ቀድማ እየተንቀሳቀሰች መሆኑንም ነው ያመለከቱት።

 እነዚህን መሰረተ ልማቶች ለማከናወን የሚጠይቁት ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ የግብር አሰባሰብ ስርዓቱ ላይ ጠንክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ የምጣኔ ኃብት መምህሩ መክረዋል።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ ሚያዝያ 9/2010 በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዘርፎች የተደራጁ ወጣቶች ከ 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን የክልሉ የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በአዳማ ከተማ በተካሄደበት ወቅት የኤጀንሲው ኃላፊ አቶ አወል አብዲ እንደገለጹት ገቢውን ያገኙት ከ904 ሺህ የሚበልጡ የገጠርና የከተማ ወጣቶች ናቸው።

ከሥራ ዕድል ተጠቃሚዎች መካከል ከ34 ሺህ የሚበልጡት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቋን መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በክልሉ በሚገኙ 20 ዞኖችና 19 ዋና ዋና ከተሞች የሚገኙ እነዚሁ ወጣቶች ገቢውን ያገኙት በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በግብርና፣ በአገልግሎት፣ በእንስሳት እርባታና በማዕድን ልማት በመሳተፍ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደአቶ አወል ገለጻ ወጣቶቹ ካገኙት ገቢ ውስጥ 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚሆነው በመንግስትና በባለሀብቶች በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስር የተገኘ ነው።

እስከ ሦስተኛው ሩብ በጀት ዓመት ድረስ ከ63 ሺህ የሚበልጡ ኢንተርፕራይዞችን ወደሥራ ማስገባት መቻሉን ጠቅሰው፣ ኢንተርፕራይዞቹ ውጤታማ እንዲሆኑም ከስልጠና በተጨማሪ 23 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ የእርሻና የመስሪያ ቦታ እንደተመቻቸላቸው ተናግረዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ 929 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድና 458 ሚሊዮን ብር መደበኛ ብድር ለወጣቶቹ መሰራጨቱን ተናግረዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል ሰበታ፣ አዳማ፣ ቢሻንጉራቻ፣ ጅማና ሻሸመኔ ከተማ አስተዳደሮች ከፍተኛ አፈጻጸም ሲያስመዘግቡ አብዛኞቹ የክልሉ ዞኖችም አፈጻጸማቸው በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ የማሽነሪ ሊዝ ክፍያን ፣ ብድር በወቅቱ ከማስፈጸም እንዲሁም የወጣቶችን አመለካከት ከመቀየር፣ ከመደገፍና  ትክክለኛ ሪፖርት ከማቅረብ አኳያ ክፍተት ታይቷል።

በጉባኤው ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኡመር ሁሴን በበኩላቸው "በክልሉ አጋጥሞ ከነበረው የጸጥታ ችግር አንጻር በሥራ ዕድል ፈጠራ የተከናወነው ሥራ አበረታች ነው"ብለዋል።

የስራ እድል ለተፈጠረላቸው አካላት የማምረቻና የመሸጫ ቦታ ችግርን ከማቃለል፣ በስልጠና ከማብቃት፣ ከሙስና የፀዳ አገልግሎት ከመስጠት አንጻር አሁንም የሚታዩ ማነቆዎችን ፈጥኖ ማሻሻል እንደሚገባ አሳስበዋል።

አነዚህንና ሌሎች መሰናክሎችን ለማስወገድ የምክር ቤቱ አባላት በቀሪዎቹ ወራት በባለቤትነትና በቁርጠኝነት እንዲንቀሳቀሱም አሳስበዋል።

መንግስት በቀሪዎቹ ሁለት ወራት ለሥራ ዕድል ፈጠራ መርሃ ግብሩ አንድ ቢሊዮን ብር በማሰራጨት የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ለማሳካት ርብርብ እንደሚያደርግም ነው ፕሬዚዳንቱ ያመለከቱት።

በመድረኩ ላይ ከክልሉ፣ ከዞንና ከከተማ መስተዳድር የተውጣጡ ከንቲባዎችና አስተዳደሮች እንዲሁም የድርጅትና የሴክተር ቢሮ ኃላፊዎች የተሳተፉ ሲሆኑ በቀረበው ሪፖርት ላይ በመወያየት የወደፊት አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 9/2010 መቀሌ ከተማና ወልዲያ ከተማ በ20ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ያደረጉት ጨዋታ ዜሮ ለዜሮ ተጠናቀቀ።

 በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 8፡00 ሠዓት ጀምሮ በተደረገው ጨዋታ መቀሌ ከተማ በኳስ ቁጥጥርና በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ ተጋጣሚው ቡድን የግብ ክልል ደርሶ የግብ እድል በመፍጠር የተሻለ ነበር።

 በአንጻሩ ወልዲያ ከተማ መከላከል ላይ በማመዘን በመልሶ ማጥቃት ወደፊት በመሄድ የግብ እድሎችን ለመፍጠር የሞከረ ሲሆን በተለይም ለክለቡ የፊት መስመር ተጫዋች ለሆነው አንዱአለም ንጉሴ ረጃጃም ኳሶችን በመጣል ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርጓል

 ጋናዊው የመቀሌ ከተማ የክንፍ መስመር ተጫዋች ቢስማርክ ጋይስ መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ በተጨማሪ ሠዓት ከወልዲያው በረኛ ቤሊንጋ አኖህ ጋር ተገናኝቶ ያመከነው ኳስ መቀሌን ሶስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ ነበር።

 የመቀሌ ከተማው አንተነህ ገብረክርስቶስና የወልዲያ ከተማ አምበል አንዱአለም ንጉሴ በጨዋታው ቢጫ ካርድ አይተዋል።

 የመቀሌ ከተማ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በጨዋታው የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ቡድናቸው የተሻለ ቢሆንም ወልድያ ይዞት የገባው የመከላከል ስልት ግብ ለማስቆጠር እንዳላስቻላቸው ተናግረዋል።

 በቀጣይ ቡድናቸው በማጥቃት ክፍሉ ላይ በተለይም የግብ እድሎችን መጠቀም ላይ ያለበትን ድክመት አስተካክሎ በመቅረብ ወደ አሸናፊነት እንደሚመለስ ገልጸዋል።

 የወልድያ ከተማ ግብ ጠባቂ አሰልጣኝ አንተነህ አሳዬ በበኩሉ ያለ አሰልጣኝ እንደመጫወታችን ያገኘነው ውጤት አስደሳች ነው ብሏል።

 ቡድኑ በመልሶ ማጥቃት የግብ እድሎች መፍጠር የሚያስችል የጨዋታ ስልት ይዞ እንደገባና የግብ እድል ለመፍጠርም እንደጣረ ገልጿል።

 ወልድያ በቀጣይ የሊጉን ጨዋታዎች በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና ስጋት ይወጣል ሲልም አንተነህ ተናግሯል።

 በተመሳሳይ በጎንደር አጼ ፋሲለደስ ስታዲየም ፋሲል ከተማ በናይጄሪያዊው አጥቂ ፍሊፕ ዳውስ ጎል ደደቢትን አንድ ለዜሮ አሸንፏል።

 በሃዋሳ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ በዳዊት ፍቃዱና አዲስዓለም ተስፋዬ ግቦች አዳማ ከተማን 2 ለ 1 ማሸነፍ ችሏል። ከነዓን ማርክነህ ለአዳማ ከተማ ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል።

 በይርጋለም ስታዲየምም ጅማ አባ ጅፋር በሄኖክ ኢሳያስ፣ በናይጄሪያዊው ኦኪኪ አፎላቢና በማሊያዊው አዳማ ሲሶኮ ጎሎች ከሜዳው ውጪ ሲዳማ ቡናን ሶስት ለአንድ አሸንፏል። ይገዙ ቦጋለ የሲዳማ ቡናን ብቸኛ ጎል ከመረብ አሳርፏል።

 የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ጅማ አባ ጅፋር በ35 ነጥብ ሲመራ፣ ደደቢት በ33 ነጥብ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና በ32 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

 

 

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ  ሚዚያ 9/2010  የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የዓለም ዓቀፉ ዓመታዊ የኢንቨስትመንት ጉባኤ የ2018 የምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ተቋም ተሸላሚ ሆነ።

 የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የሩዋንዳ አቻው ከምስራቅ አፍሪካ ለሽልማቱ ታጭተው የነበረ ሲሆን ኮሚሽኑ በቀዳሚነት የምስራቅ አፍሪካ ውጤታማ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ተቋም ሆኖ ተመርጧል።

 ዓለም ዓቀፉ ዓመታዊ የኢንቨስትመንት ጉባኤ ኢንቨስትመንት በመሳብ ውጤታማ አፈፃፀም ያሳዩ አገራትን በየዓመቱ በማወዳደር ይሸልማል።

 ይህ ጉባኤ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ ምሁራንና ሙያተኞች የሚሳተፉበትና በዘርፉ ከፍተኛ ዕውቅና ያተረፈ ነው።

 ሽልማቱ በተመረጡ ዘርፎች የውጭ ባለሃብቶችን በመመልመልና ቀጥተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው የላቀ ኢንቨስትመንቶችን በማስፋፋት አመርቂ ውጤት ላስመዘገቡ አገራትና የኢንቨስትመንት ተቋማት የሚበረከት ነው።

 በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ቆንስል ጀኔራል ወይዘሮ እየሩሳሌም ዓምደማርያም ዱባይ ላይ ከሚያዝያ 1- 4 ቀን 2010 ዓ.ም በተካሄደው ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ የተበረከተውን ሽልማት ኮሚሽኑን በመወከል ተቀብለዋል።

 መንግስት የውጭ ኢንቨስትመንቱ የአካባቢ ጥበቃን ባማከለ፣ ኤክስፓርትን በሚያበረታታ፣ ከአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በሚያፋጥን መልኩ በማሳለጥ ባሳየው ከፍተኛ አፈፃፀም ለሽልማት እንደበቃም ተናግረዋል።

 እነዚህ ኢንቨስትመንቶች አገሪቱ ያስቀመጠቻቸውን የኢኮኖሚ ዕድገት ዕቅዶችና ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ ቁልፍ መሳሪያዎች መሆናቸውንም ነው የገለጹት።

 የጉባዔው ፕሬዚዳንት ዳውድ አል ሼዛዊ “ሽልማቱ ተቋማቱ አገራቸውን በማስተዋወቅና መልካም ስም በመፍጠር ኢንቨስትመንት በመሳብ የአገራቸውን ኢኮኖሚ በማሳደግና ስራ ፈጠራን በማስፋፋት ላደረጉት ውጤታማ እንቅስቃሴ ማሳያ ነው” ብለዋል።

 የተሸላሚዎቹ አገራት አመርቂ ውጤት ለሌሎች ምሳሌ እንደሚሆንም እምነታቸውን ገልፀዋል ሲል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታውቋል።

 ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በጉባኤው የቤልጂየም፣ ህንድ፣ ሰርቢያ፣ ግብፅ፣ የጋናና ስዋዚላንድ ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ተቋማት ከየክፍለ አህጉራቸው ቀዳሚ በመሆን እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 9/2010 በአገር አቀፍ ደረጃ ለማከናወን የታቀደው የስራ እድል ፈጠራ በሚፈለገው ደረጃ እየተተገበረ አይደለም ተባለ።

የፌዴራል የከተሞች ስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ እንደገለጸው ባለፉት ስምንት ወራት በአገር አቀፍ ደረጃ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የስራ ዕድል ለመፍጠር ቢታቀድም የተከናወነው 889 ሺህ ነው።

ወጣቶች ከተደራጁ በኋላ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ አለማግኘታቸው ለዕቅዱ አለመሳካት ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞ ተናግረዋል።

ወጣቶች ለስራዎቹ የሚሰጡት ትኩረት አናሳ መሆን፣ የአበዳሪ ተቋማት መስፈርቶች መብዛትና የገበያ ትስስር ዝቅተኛ መሆንም ተጨማሪ ምክንያቶች እንደሆነ አብራርተዋል።

በተጨማሪም በአገሪቱ ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት የስራ እድሉ ተጠቃሚ ዜጎች ቁጥር እንዲቀንስ ማድረጉን አቶ ዘነበ ጠቅሰዋል።

ከመስሪያና መሸጫ ቦታዎች ዝግጅት ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች ለማቃለል በየደረጃው ካሉ አመራሮች ጋር በቅንጅት መስራት መጀመሩንም ገልፀዋል።

ከአበዳሪ ተቋማትና ከገበያ ትስስር ጋር የተያያዙ እክሎችን ከሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች ጋር በመወያየት ችግሮቹን ለመፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መግባባት ተደርሷልም ነው ያሉት።

በበጀት ዓመቱ ሁለት ሚሊዮን ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ስራ መግባቱን የገለጹት አቶ ዘነበ በቀሪዎቹ ወራት እቅዱን ለማሳካት 'በትኩረት ይሰራል' ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም ለ200 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር በሂደት ላይ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።

ባለፉት ስምንት ወራት የስራ እድል ከተፈጠረላቸው 889 ሺህ ዜጎች መካከል 200 ሺህ ያህሉ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የተመረቁ እንደሆኑ ተገልጿል።

መንግስት ለነዚህ የስራ እድል ተጠቃሚዎች 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱንም አቶ ዘነበ ተናግረዋል።

ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ ንግድ፣ የከተማ ግብርና አገልግሎት ዘርፎች የስራ እድል ፈጠራው ተግባራዊ የሚደረግባቸው መስኮች መሆናቸው ታውቋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 9/2010 መንግስት ከፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት ጥሪ ማድረጉን በአዎንታ እንደሚመለከቱት የአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

ኢህአዴግን ጨምሮ 13 ተደራዳሪ አገር አቀፍ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ያቀፈው ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ አካሂዷል።

ምክር ቤቱ በሶስት አጀንዳዎች ላይ ለመወያየት ተስማምቶ ''የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፓርቲዎች ጋር በጋራ የእንስራ ጥሪ እና በሥነ-ምግባር መተዳደርያ ደንብ ማክበር'' ተወያተዋል፡፡

''የአሜሪካ ኮንግረስ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ባሳለፈው ኤች አር 128 የውሳኔ ሀሳብ'' ላይ በጊዜ እጥረት ምክንያት ሳይወያዩም ቀርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ የአገሪቱን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ለማጠናከርና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን ለማጎልበት በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጥላቻ በመውጣት በጋራ እንስራ ሲሉ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል።

እንዲሁም አማራጭ ሃሳብ ይዘው በሰላማዊ መንገድ ለሚፎካከሩ ፓርቲዎች መንግስት ነፃ፣ ፍትሃዊና ገለልተኛ ምርጫ እንዲካሄድ ዝግጁ ነው ማለታቸው ይታወቃል።

ይህን ተከትሎ አገር አቀፍ ፓርቲዎቹ ወቅታዊ የአገሪቱ የፖለቲካ ጉዳይ እኛንም ይመለከተናል ፤ ግብረ-መልስም መስጠት ይገባናል በሚል ተወያይተውበታል።

በውይይቱ ዶክተር አብይ አህመድ ለሰላምና መረጋጋት መስፈን ተስፋ ሰጪ ንግግሮች እያደረጉ በመሆኑ ምስጋና ይገባቸዋል የሚል ሃሳብ ቀርቧል።

በሌላ በኩል አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት አመራሮች ከዚህ በፊት ከተናገሯቸው ንግግሮች የተለየ ነገር አላቀረቡም፤ ከቃል ባለፈ በውጤት የተገለጠ አይደለም ለድጋፍ ምስጋና ቸኩለናል የሚል ሃሳብም ተንሸራሽሯል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ሊያሰራ የሚችል የፖለቲካ ሥነ-ምህዳር ለማስፋት ቃል ከመግባት ባሻገር ሊተገበር ይገባልም ብለዋል።

መንግስት በአገሪቱ የተከሰቱ ችግሮችን መንስኤ ለይቶ የመፍትሄ እርምጃ በመውሰዱና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት መጀመራቸው መልካም ነው በማለት በፓርቲዎቹ መግባባት ላይ ተደርሷል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ለፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የእንስራ ጥሪ በአዎንታ እንደሚመለከቱት ገልጸው ከፓርቲዎች ጋር በመወያየት ቃላችንን መስማት አለባቸው ብለዋል።

የአገሪቱን ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በተሻለ ለማስቀጠል የገቡትን ቃል ወደ ተግባር በመለወጥ የፖለቲካ ሥነ-ምህዳሩን የሚያሰፉ እርምጃዎችን እንዲወስዱም ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን