አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 16 April 2018

አዲስ አበባ ሚያዚያ 8/2010 በተሰማራንበት መስክ የሚጠበቅብንን በመፈጸም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለገቡት ቃል ስኬት ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት ማምሻውን በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ ባደረጉት ንግግር የበርካቶችን ቀልብ ስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የአዲስ አበባን ነዋሪ ባገኙበት በዚሁ መድረክ ከህዝቡ አድናቆትና ፍቅር ተችሯቸዋል።

የመጀመሪያ የስራ ጉብኝታቸውን በሶማሌ ክልል፣ ቀጥሎም በኦሮሚያ ክልል አምቦ፤ ከቀናት በፊት ደግሞ በመቀሌ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

"የፍቅርና የአንድነት ኪዳን" በሚል መሪ ሐሳብ በተካሄደው የአዲስ አበባው መድረክ በወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የመንግስትን የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ፣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ እና የፍትህ ሥርዓቱን ለማጎልበት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡትን ቃል እንዲፈጽሙ ከእያንዳንዱ ዜጋ ምን ይጠበቃል ሲል ኢዜአ ያነጋገራቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጤታማነት የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ነው የገለፁት።

ከሐረርጌ አቶ ዩሱፍ አብዱረህማን በሰጡት አስተያየት “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻቸውን ሳይሆን  ኢትዮጵያውያን በሙሉ ትንሽ ትልቅ ሳይል መደገፍና አብረን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ከአዲስ አበባ አቶ ሚሊዮን ሻምበል በበኩላቸው “መላ ኢትዮጵያዊያን ሲሰማን የነበረው ስጋትና ሰላም ማጣት ተወግዶልን ሰላም ወጥተን መግባት የምንችልበትን ሁኔታ የፈጠሩልን መሪ ናቸው። ሙያችንን እውቀታችንን ተጠቅመን አገራችንን ልዩ ለማድረግ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን።"

"ያደረጓቸው ንግግሮች እጅግ በጣም ማርከውኛል ከልብ ተግባራዊ ሆነው ማየትም እፈልጋለሁ። ለተግባራዊነታቸውም የበኩሌን አስተዋፅኦ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ።" ያሉት ደግሞ ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኮማንደር ካሳሁን ገብረዮሐንስ ናቸው፡፡

ከጎንደር የመጣው ወጣት ቶፊቅ እስማኤል ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኬት ከጎናቸው እንደሚቆም ነው የገለፀው፤“ለእኛ ለወጣቶች የምንፈልገውን ነገር ነው የተናገሩት ስሜታችንን የሚያነሳሳ ወደ ለውጥ የሚመራን ነገር ነው ፣ ስናግዛቸው ደግሞ ለውጥ ማምጣት ይችላሉ የእኛ ተግባር ከእሳቸው ጎን መቆም ነው"

የኢትዮጵያ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ ሰዒድ ዑመር አሊ በበኩላቸው ህብረተሰቡ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጎን በመሰለፍ ለሰላም መስፈን ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ቃለ መሃላ በፈፀሙበት ወቅት ከሁሉም ወገን ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ ነኝ ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል።

በትናንት ምሽቱ መድረክም የተጀመሩ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ስራዎችን ለማስቀጠል ህዝብና መንግስት ተቀራርበው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

 

Published in ፖለቲካ

ባህር ዳር ሚያዚያ 8/2010 የደብረታቦር - ጃራገንዶ በአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባው 88 ኪሎ ሜትር አዲስ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

የመንገዱ መሰራት በእግር ጉዞ ከስድስት ሰዓት በላይ ያደርጉት የነበረውን አድካሚ ጉዞ በተሽከርካሪ ወደ አንድ ሰዓት ዝቅ በማድረግ ከእንግልት እንደታደጋቸው ነዋሪዎች ገልፀዋል።

በባለስልጣኑ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ መንገዱ ትናንት በባለሙያዎች በተጎበኘበት ወቅት እንደገለፁት በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ማጠናቀቂያ ላይ አጠቃላይ የሃገሪቱ  የመንገድ አውታር 110 ሺህ ኪሎ ሜትር ነበር፡፡

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የመንገድ አውታሩን 210 ሺህ ኪሎ ሜትር ለማድረስ ታስቦ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ግቡን ለማሳካትም መንግስት በርካታ የአዳዲስ መንገዶች ግንባታና የደረጃ ማሻሻል ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የዚህ መንገድ ግንባታም የእቅዱ አካል መሆኑን አመልክተው፤ ይህም የህዝቡን የዘመናት የመንገድ ጥያቄ የመለሰ መሆኑን አቶ ሳምሶን አስታውቀዋል።

መንገዱ የንኮማንድ በተባለ ሃገር አቀፍ ተቋራጭ እንደተሰራና ሙሉ ወጭው በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ መሆኑንም አብራርተዋል።

የሃገር ውስጥ ተቋራጮች አቅማቸው እያደገ መምጣቱንና በአሁኑ ወቅትም በፌደራል መንገዶች ግንባታ የተሰማሩ 100 የሚሆኑ ተቋራጮች አሉ ብለዋል።

ከዚህ በላይ አቅማቸው እንዲያድግም መንግስት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

መንገዱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ምን ሲሰራ ነበር?

የንኮማንድ ኩባንያ ባለቤትና የመንገዱ ተቋራጭ አቶ የምሩ ነጋ በበኩላቸው የአካባቢው መልካምድራዊ አቀማመጥ አስቸጋሪነትና መሬቱ ዋልካ አፈር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ግንባታውን አስቸጋሪ አድርጎት ነበር።

በተለይም ከዲዛይን አለመስተካከል ጋር በተያያዘ ችግር የገጠመ ቢሆንም ችግሩን በመቋቋምና ዲዛይኑን በማስተካከል “መንገዱን ገንብቶ ማጠናቀቅ ተችሏል” ብለዋል።

የመንገዱን ደረጃና ጥራቱን ጠብቆ እንዲሰራ እንደተቋራጭ ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ ዜጋ በባለቤትነት ለመስራት ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

በመንገድ ግንባታም ከ5 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን በቀጣይም የመንገዱ ሙሉ ርክክብ እስኪካሄድ በውላቸው መሰረት ችግር ቢኖር ተገቢን ማስተካከያ እንደሚያደርጉ አብራርተዋል።

የመንገዱ ተቆጣጣሪ መሃንዲስ አቶ ሲሳይ ጫላ በበኩላቸው መንገዱ ጥራቱን ጠብቆ እንዲከናወን ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር መደረጉን አመልክተው። 

በዲዛይን መቀየርና በአካባቢው መልካ ምድራዊ አቀማመጥ ችግር ምክንያት የመንገዱ የግንባታ ውል ጊዜ ሦስት ዓመት ቢሆንም ከአንድ ዓመት መዘግየት በኋላ በአራተኛ ዓመቱ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

የመንገዱ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ምንአሉ?

በእስቴ ወረዳ ጎሽ በረት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሹመት ምትኩ በበኩላቸው በአካባቢያቸው ቀደም ሲል የከፋ የመንገድ ችግር እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን የመንገዱ መሰራት “ካለመኖር ወደ መኖር የመለሰን ነው ማለት ይቻላል” ብለዋል።

በዚህም ህመምተኞችን ያለምንም ችግር አጓጉዞ በማሳከም ጤንነታቸውን መመለስ እንደተቻለ፣ ዘመድ ከዘመዱ በቀላሉ ሊገናኝ እንደቻለም ተናግረዋል።

መንገዱን ተከትሎም አዳዲስ ከተሞችን መመስረት እንደተቻለ ጠቁመው፤ በዚህም ከገጠር ወደ ከተማ መሸጋገር እንደቻሉና ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በመንገዱ መሰራትም ቀደም ሲል ደብረታቦር ከተማ ለመሄድ በእግር ከስድስት ሰዓት በላይ ይጓዙ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን በመኪና በአንድ ሰዓት መድረስ እንደቻሉ ተናግረዋል።

የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ላቀው አልታሰብ በበኩላቸው ቀደም ሲል ወደ ከተማ ሲጓዙ በወንዝ ሙላት ይወሰዱ እንደነበርና ገንዘባቸውን በሽፍታ ይቀሙ እንደነበር አመልክተዋል።

አሁን ላይ በመስኖ ያመረቱትን ድንችም ሆነ ሽንኩርት በመኪና በማጓጓዝ በቀላሉ መሸጥ እንደቻሉና የመስኖ ልማታቸውንም ለማስፋፋት እድል እንደፈጠረላቸው ጠቁመው፤ የተሻለ መኪና እንዲመደብላቸውም ጠይቀዋል።

ከደብረታቦር፣ ጅብ አስራ ማርያም ጃራገንዶ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት የማጠናቀቂያ ስራ ትናንት በባለሙያዎች ተጎብኝቷል።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

 አዲስ አበባ ሚያዝያ 8/2010 የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለስልጣን በአገሪቱ ያለውን የሃይል ብክነት ለማስቀረት እየሰራ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል ውጤት አለማምጣቱን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።

የምክር ቤቱ የተፈጥሮ ሃብት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባለስልጣኑን የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸም ዛሬ ገምግሟል።

በአገሪቱ ካለው ሃይል በአጠቃቀም ሂደት 26 በመቶ እንደሚባክንና ተቋሙ ይህንን የሃይል ብክነት ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በመተባበር ለማዳን እንዲሰራ ተቋቁሟል።

ነገር ግን ተቋሙ የተሰጠውን ዋና ተልዕኮ ለማስፈጸም የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግና የተለያዩ የማስፈጸሚያ ጥናቶችን ቢያካሂድም  የሃይል ብክነቱን ለመቀነስ በተሰራው ስራ ተጨባጭ ውጤት አልታየም።

በአገሪቱ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ መሆኑን የተናገሩት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አስቴር አማረ የሚባክነውን ሃብት ወደ ልማት ቀይሮ የህብረተሰቡን ጥያቄ የመመለስ ስራ ጊዜ የሚሰጠው እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።

የኢነርጂ አዋጅ ወጥቶ የማስፈጸሚያ ደንብ ለማዘጋጀት ብቻ አራት አመታትን በማስቆጠሩ ባለስልጣኑ አስገዳጅ እርምጃዎች መውሰድ እንዳይችል ማድረጉ ተጠቁሟል።

በዚህም ምክንያት በተለይ ትልልቅ ሃይል የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች፣ ሆቴሎች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ተቋማት የሚያባክኑትን ሃይል

መቆጣጣር አልተቻለም ብለዋል።

መንግስት የተቋሙን አቅም ከኤጀንሲ ወደ ባለስልጣን ቢያሳድገውም እስካሁን አላስፈላጊ ሃይል በሚጠቀሙና ህገ-ወጥ ተግባር በሚፈጽሙ አካላት ላይ እርምጃ አልወሰደም ተብሎል ።

ባለስልጣኑ የሃይል ብክነቱን ለመከላከል በርካታ ተግባራትን አከናውኛለሁ ቢልም ተጨባጭ አድርጎ መረጃውን አለማቅረቡን ገልጸዋል።

በቀጣይ ተቋሙ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን የቅንጅት ስራ እንዲያጠናከር፣ የኢነርጂ ብቃትና ቁጠባ ደንብን እንዲያፋጠን፣ የተሰጠውን የስልጣን ሃላፊነት በመወጣትና ምክር ቤቱ የሰጠውን ግብረ መልስ መተግበር እንዳለበት አሳስቧል።

ባለስልጣኑ ክልሎችን የማሰልጠን፣  ሪፖርት በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ለምክር ቤቱ በመላክና የተጀመሩ የፋይናንስና ኦዲት ግኝቶችን በአፋጣኝ ምላሽ የመስጠት ተግባርን አጠናክሮ እንዲቀጥልም  ተጠይቋል።

ምክር ቤቱም ከተቋሙ አቅም በላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል። 

Published in ኢኮኖሚ

ድሬደዋ ሚያዝያ  8/2010 ላለፉት አምስት ወራት በድሬዳዋ ሲካሄድ የቆየው የጤና ቡድኖች እግር ኳስ ውድድር በድሬ ፍቅርና በአፍካት አሸናፊነት ትናንት ተጠናቀቀ፡፡

በድሬዳዋ የሚገኙ 19 የጤና ቡድኖች በሁለት የዕድሜ ጎራ ተከፍለው ውድድራቸውን አድርገዋል፡፡

ትላንት በድሬዳዋ ስታዲዮም በተካሄደው ከ40 ዓመት በላይ የፍጻሜ ውድድር ድሬ ፍቅር ሣብያን ህብረትን ሁለት ለአንድ  በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት ሆነዋል፡፡

በተመልካቾችና በደጋፊዎች የደመቀ ህብረት ታጅቦ የተካሄደው ከ40 ዓመት በታች የፍጻሜ ውድድር ደግሞ አፋካት ከድሬ ኮተን ዘጠና ደቂቃውን አንድ ለአንድ ጨዋታቸውን በማጠናቀቃቸው  በተሰጠው የመለያ ምት አፋካት አራት ለሶስት በመርታት ዋንጫ ተሸልሟል፡፡

የድሬዳዋ የስፖርት ለሁሉም ፕሬዘዳንት አቶ ፋታሁን ታደሰ እንደተናገሩት ለአራተኛ ጊዜ የተካሄደው ዓመታዊ የጤና ቡድኖች ውድድር   ጤናማ ህብረተሰብን የማፍራት ዓላማን መሰረት በማድረግ ነው፡፡

የድሬዳዋ ስፖርት ኮሚሽን ለውድድሩ መሳካት ከ66 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው የውድድሩ አሸናፊዎች በዚህ ወር መጨረሻ አዳማ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ የጤና ስፖርት ውድድር ላይ ድሬዳዋን በመወከል እንደሚሳተፉ ገልጸዋል፡፡

የድሬ ኮተን ተጫዋቾች ኤፍሬም ፀጋዬ ውድድሩ " ጤናችንን ለመጠበቅ ፣ በድሬዳዋ ለዘመናት ዜጎች የገነቡትን የእርስ በርስ ፍቅርና አንድነት እንዲጠናከር የሚበጅ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል  እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በውድድሩ አሸናፊና ተሳታፊ ለሆኑ ቡድኖች፤ ኮከብ ተጫዋቾችና ኮከብ ግብ አግቢዎች የተዘጋጀውን የዋንጫና ልዩ ልዩ ሽልማቶች ከዕለቱ ከድሬዳዋ ወጣቶችና የስፖርት ኮሚሽን አመራሮችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተበርክቶላቸዋል፡፡   

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ  ሚያዝያ 8/2010 ለአርሶ አደሮች መፈጸም ያለባቸው የመሬት ካሳ ክፍያና የምትክ ቦታ አሰጣጥ ችግሮች ለኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ የህንጻ ግንባታዎች መዘግየት ተግዳሮቶች መሆናቸው ተገለጸ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትምህርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዩኒቨርሲቲው የ2010 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ከስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል።

የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ በአራተኛው ዙር ከተቋቋሙ 11 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ጭሮ ይገኛል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙክታር መሃመድ እንደገለፁት በ2008 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲው ከ20 በላይ ህንጻዎች ግንባታ ለመጀመር እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል።

ሆኖም ግንባታዎቹ በሚከናወኑባቸው ቦታዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ከሚፈጸሙ የካሳ ክፍያዎችና ከሚሰጡ ምትክ ቦታዎች ጋር በተያያዘ የተነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ጊዜ በመውሰዱ ግንባታውነ በታቀደው ጊዜ ለመጀመር አልተቻለም ብለዋል።

እንደ ዶክተር ሙክታር ገለጻ በትምህርት ሚኒስቴር ለ200 ሄክታር መሬት ካሳ ክፍያ 20 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘ ሲሆን በምዕራብ ሀረርጌ ዞን አስተዳደር ደግሞ ለ164 ሄክታር ወደ 300 ሚሊዮን ብር ግምት ቀርቧል።

በመሬት ካሳ ክፍያ ግምቱ ከፍተኛ ልዩነት ሳቢያ ተጨማሪ በጀት በማስፈለጉ የካሳ ክፍያ ቅሬታዎችን ለመፍታት ጊዜ ፈጅቷል።

በአሁኑ ወቅት የሕብረተሰቡ ቅሬታዎች ሙሉ ለሙሉ ባይፈቱም ከታቀዱት ግንባታዎች የተወሰኑት ህንጻዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።

አብዛኞቹን ግንባታዎች በሚቀጥለው ዓመት ህዳር ላይ ለማጠናቀቅና ተማሪዎችን ለመቀበል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።

ይህን ለማሳካትም ጉዳዩ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን አስተዳደር፣ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማትና በትምህርት ሚኒስቴሮች ልዩ ትኩረት የሚያገኝበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከቋሚ ኮሚቴው እገዛ እንዲያደረግላቸው ዶክተሩ ጠይቀዋል።

በዩኒቨርሲቲው ውስጥና በአካባቢው ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት የትምህርት ጊዜ መስተጓጎሉ፣ ለግዢ የሚቀርቡ ዕቃዎች በወቅቱ ያለመቅረብ፣ የመማሪያ ክፍሎችና ቢሮዎች እጥረትና 3ኛ ዲግሪ ያላቸውን መምህራን በበቂ ሁኔታ ያለማግኘት ችግሮች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያጋጠሙ ችግሮች ሲሉም  ጠቅሰዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ተወካይ አቶ ዋቅጅራ ተርፋሳ ዩኒቨርሲቲው ከግንባታ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመፍታት ከስራ አመራር ቦርዱ ጋር በቅርበት መስራት እንደሚገባው ገልጸው ቋሚ ኮሚቴውም እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የተማሪዎችን አደረጃጀት በመጠቀም ሠላማዊ ግንኙነት እንዲፈጠር መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የመምህራን የትምህርት ደረጃ ወሳኝ በመሆኑ ሶስተኛ ዲግሪ ያላቸውን መምህራን ቁጥር ለማሳደግ ጥረት ማድረግም ይገባል ነው ያሉት።

የሴት መምህራንን ቁጥር ለማሳደግና ሴቶችን ወደ አመራር ለማምጣትም ዩኒቨርሲቲው በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 8/2010 ኢትዮጵያና ማልታ ያለተጨማሪ ቀረጥ ምርቶችን ወደ አገሮቻቸው ለማስገባት ተስማሙ።

የኢትዮጵያና ማልታ የቢዝነስ ሴሚናር በማልታ መዲና ቫሌታ ላይ የተካሄደ ሲሆን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል የተመራ የልዑካን ቡድን በሴሚናሩ ተሳትፏል።

ሴሚናሩ ሮም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዲሁም በማልታ የውጭ ጉዳይ እና ንግድ ሚኒስቴሮች በጋራ የተዘጋጀ ነው።

በሴሚናሩም ኢትዮጵያና ማልታ ያለተጨማሪ ቀረጥ ምርቶቻቻውን ለማስገባት መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው ማግለጫ አስታውቋል።

ስምምነቱ በሁለቱ አገራት መካካል ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ ያጠናክራል ተብሏል።

ሴሚናሩ ኢትዮጵያ ለማልታ ባለሃብቶች ምቹ መሆኗን ለማስገንዘብ የተዘጋጀ ሲሆን ሚኒስትር ዴኤታው በኢትዮጵያ ያሉትን የኢንቨስትመንት እድሎች ደንቦችና ሊያስገኙ በሚችሉ ጥቅሞች ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዶክተር አክሊሉ የተመራው ቡድን ከማልታ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካርኔሎ አቤላ ጋር በሁሉቱ አገሮች መካካል ያለውን የንግድና የኢኮኖሚ ግንኙነት ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

ቡድኑ ታላላቅ የግብርና እና የምግብ ማቀነባባሪያ ኩባንያዎችን እንዲሁም ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ የሆቴልና ቱሪዝም ዘረፍችን ጎብኝቷል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 8/2010 በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፈን ኢትዮጵያ የምታደርገው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፍላጎቱ መሆኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የሰላም ማስከበር ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ በተመድ የሰላም ማስከበር ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ጄአን ፕየር ጃክሮኤክሲ ጋር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር በምታደርገው ጥረት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

ምክትል ዋና ጸሐፊው ኢትዮጵያ ሰላም ለማስከበር እያደረገች ላለው ተሳትፎና እንቅስቃሴ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይሎች የተሰጣቸውን ሰላም የማስከበር ተልዕኮ በመወጣት በኩል ያላቸው ብቃትና ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር በኢትዮጵያ በኩል እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርጅቱ ፍላጎት መሆኑንም ገልጸዋል።

በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል ሰላማዊ ድርድርና እርቅ እንዲመጣና በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ አጠናክራ እንድትቀጥል ምክትል ዋና ጸሐፊው ጠይቀዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የጎረቤት አገሮችን ሰላምና መረጋጋት ከራሷ ጉዳይ ነጥላ እንደማታየው ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሂሩት ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላም የማስከበር ተልዕኮዋን ከመወጣት ባሻገር የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች በአገሪቱ እርቀ ሰላም እንዲያመጡ የጀመረችውን እንቅስቃሴ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ በሶማሊያ ሰላም ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ ሁለገብ ተሳትፎ የምታደርግ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የአካባቢው ሰላም እንዲረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት ተመድ የሚያደርገውን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥያቄ መቅረቡም ተገልጿል።

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 8/2010 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ 124ሺ የሚጠጉ ሰዎችን በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚ ማድረጉን  አስታወቀ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አሳመነ ጌራወርቅ እንደተናገሩት፤ በመጀመሪያው ዙር የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ትግበራ ለምግብ ዋስትና እጦት ተጋላጭ የሆኑ 123ሺህ918 ሰዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

በከተማዋ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ከተለዩ 35 ወረዳዎች የምግብ ዋስትናቸውን ያላረጋገጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በህዝብ ተለይተው በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት እንዲሁም በጽዳትና ውበት በመሳሰሉ የማህበረሰብ አቀፍ ስራዎች እንዲሰማሩ ተደርጎ በፕሮግራሙ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ ።

ፕሮግራሙን ከሚታቀፉት ውስጥ 86 በመቶ የሚሆኑት በልማት ስራ ተሳትፎ እያደረጉ የሚጠቀሙ ሲሆን በተለያየ ምክንያት መስራት የማይችሉና የምግብ ዋስትናቸውን ያለረጋገጡ ቀሪዎቹ 14 በመቶዎቹ የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ ናቸው  ብለዋል ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በበጀት ዓመቱ የዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸውን ተግባራት ካዳመጠ በኋላ በተመረጡ ቀጠናዎች የመስክ ምልከታ አድርጓል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በጉለሌ ክፍለ ከተማ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን ከጎበኙና በምግብ ዋስትና ልማት የማህበረሰብ አቀፍ ልማት ስራዎች ላይ የተሰማሩ ተጠቃሚዎችን ካነጋገሩ በኋላ ኤጀንሲው የተመደበለትን ገንዘብ በአግባቡ ተግባር ላይ ማዋሉን ተመልክተናል ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ነጋልኝ ዮሴፍ የምግብ ዋስትናቸውን ያላረጋገጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከመለየት ጀምሮ የተደረገውን ጥረትና የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሌላው የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ እባቡ ብርሌ 'ኤጀንሲው ከሰኔ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለምግብ ዋስትና ትግበራ የተመደበለትን ገንዘብ ለታለመለት ተግባር እያዋለው መሆኑን በመስክ ምልከታችን አረጋግጠናል' ብለዋል።

በምግብ ዋስትና ትግበራ ፕሮግራሙ ከተሰማሩት መካከል ወይዘሮ ቀለሟ  ግዛቸውና አቶ ቢሰጥ አለነ ባገኙት እድል ራሳቸውን በመቻላቸው ከምግብ ዋስትና እጦት ችግር መላቀቃቸውን ተናግረዋል።

በማህበረሰብ አቀፍ ልማት ስራው ደስተኛ ቢሆኑም ክፍያው ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል።

በ2ኛው ዙር የምግብ ዋስና ፕሮግራም 200ሺ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ ተይዞ ከታህሳስ 1 ቀን 2010 ዓ ም ጀምሮ በሁሉም ወረዳዎችና ቀጠናዎች በልየታ ኮሚቴዎች አማካኝነት ምዝገባ መካሄዱን ኤጀንሲው አስታውቋል።

በከተሞች እየተካሄደ ያለው የምግብ ዋስትና ፕሮግራም በመላ አገሪቱ አዲስ አበባን ጨምሮ በ11 ከተሞች እየተተገበረ ይገኛል።

ፕሮግራሙ የሚካሄደው ከዓለም ባንክ በተገኘ 300 ሚሊዮን ዶላር ብድር እና 150 ሚሊዮን ዶላር መንግስት በመደበው ገንዘብ ሲሆን ዜጎችን ከድህነት ያወጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

በአዲስ አበባ በሚካሄደው ፕሮግራም የክፍያ ማነስና የማህበረሰብ ዓቀፍ ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችል የመስሪያ መሳሪያ አቅርቦት ችግር እንዳለ በተደጋጋሚ ጥያቄ እየቀረበ ነው።

Published in ኢኮኖሚ

አዲሰ አበባ ሚያዝያ 8/2010 የወልዲያው የሼህ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታዲየም ለአንድ ዓመት ማንኛውንም ውድድሮች እንዳያካሂድ ታገደ።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የስነ ምግባር ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት በተደረገው የ19ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ወልዲያ ከተማ ፋሲል ከተማን ባስተናገደበት ጨዋታ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች መከሰታቸው ይታወቃል።

በእለቱ በ89ኛው ደቂቃ ፋሲል ከተማ የፍጻም ቅጣት ምት ማግኘቱን ተከትሎ የወልዲያ አሰልጣኝና የወልዲያው ተጫዋች ብሩክ ቃልቦሬ  ቅጣት ምቱ እንዳይመታ ለማድረግ በመሞከራቸውና አንዳንድ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ በመግባት ረብሻ እንዲፈጠርና ጨዋታው እንዲቋረጥ አድርገዋል በሚል ነው  ቅጣቱ የተላለፈው።

ይህን ተከትሎም ጨዋታ የተደረገበትን  የሼህ ሁሴን አላሙዲ ስታዲየም እስከ ሚያዚያ ወር 2011 ዓ.ም ድረስ ለአንድ ዓመት ያህል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚያካሂዳቸው ማንኛቸውንም ውድድሮች እንዳያስተናግድ ውሳኔ ተላልፎበታል።

የወልዲያ ከተማ እግር ኳስ ክለብም ቀሪ ጨዋታዎችን በሙሉ ከከተማዋ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ባለ ሜዳ ላይ እንዲያካሂድ ተወስኖበታል።

ከዚህ በተጨማሪ የወልዲያ እግር ኳስ ክለብ  የ250 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣትም እንዲከፍል ቅጣት ተላልፎበታል ።

ክለቡ በጨዋታው ወቅት በተፈጠረው ረብሻ ምክንያት የተጎዱትን የመሀል ዳኛና ረዳት ዳኛውን ሙሉ የህክምና ወጪ የሚሸፍን ይሆናል።

የወልዲያ  ከተማ አሰልጣኝ ዘማሪም ወልደጊዮርጊስ  የፍጹም ቅጣቱ እንዳይመታ ለማድረግ ወደ  ሜዳ በመግባት ለፈጠረው ችግር ለአንድ ዓመት ከአሰልጣኝነት እንዲታገድና 20 ሺህ ብር የገንዝብ ቅጣት ተላልፎበታል።

በተመሳሳይ የወልዲያ ተጫዋች የሆነው ብሩከ ቃልቦሬ ፍጹም ቅጣት ምቱ እንዳይመታና ዳኞችን ለመደብደብ ሙከራ በማድረጉ ለአንድ ዓመት ከጨዋታ የታገደ ሲሆን 10 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣትም ተላልፎበታል።

የእለቱ ውጤትም በፎርፌ ለፋሲል ከተማ እግር ኳስ ክለብ እንዲሰጥ በማድረግ ሶስት ነጥብና ሶስት ጎል እንዲያገኝ ተወስኗል።

ክለቡ ከላይ የተዘረዘሩትን ግዴታዎች ካልተወጣ  ከፕሪሚሪ ሊጉ ውድድር የሚታገድ መሆኑን ፌደሬሽኑ በጻፈው ደብዳቤ ገልጿል።

Published in ስፖርት

ሰመራ ሚያዝያ 8/2010 በክልሉ በሚከናወኑ የልማትና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሥራ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሱ የብዙሃንና ሙያ ማህበራት ገለጹ።

የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር በክልሉ ለሚገኙ የብዙሃንና ሙያ ማህበራት ለሁለት ቀን በሎግያ ከተማ የሰጠው የአቅም ግንባታ ስለጠና ተጠናቋል።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የአሌደአር ወረዳ መምህራን ማህበር ተወካይ መምህር አንዳለ በላይ እንዳለው የሙያ ማህበሩ የአባላቱን ጥቅምና መብት ከማስከበር ባለፈ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በትኩረት እየሰራ ይገኛል። 

በቀጣይም ማህበሩ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች ከማጠናከር ባለፈ አባላቱን በማነቃነቅ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የጎላ ሚና በመጫወት ሥራ ፈጣሪና በሥነምግባር የታነጸ ትውልድ ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ከኮሪ ወረዳ ወጣቶች ፌዴሬሽን የመጣው ወጣት ሲሌ ሃቢብ በበኩሉ በህገ መንግስቱ የተረጋገጠላቸውን የመደራጀት መብት ተጠቅመው በክልሉ ሰላምና ዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለመሆኑ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግሯል።

"በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ በሚካሄዱ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሥራዎች በያገባናል መንፈስ ለመንቀሳቀስ ከመቼውም ጊዜ በላይ የፌደሬሽኑን አባላት አንቀሳቅሰን እንሰራለን" ብሏል።

በተለይ ወጣቶች ከጥገኝነትና ጠባቂነት አመለካከት ተላቀው ወደሥራ በመሰማራት ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ፌደሬሽኑ እስከ ቀበሌና ጎጥ ድረስ ያሉ አባላቱን በማስተባበር እንደሚሰራ አመልክተዋል። 

በሰመራ ከተማ የሚገኘው "መኤ-አጎ የአካል ጉዳተኞች ማህብር" ምክትል ሊቀመንበር አቶ መሀመድ ዳርጌ በበኩላቸው በህብረተሰቡ ዘንድ ለአካል ጉዳተኞች ዝቅተኛ ግምት ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ይህን አመለካከት ተደራጅቶ ለመከላከልና የአካል ጉዳተኞችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለመረጋገጥ ማህበሩ ባለፉት 10 ዓመታት ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ተናገረዋል።

" ይሁንና ማህበሩ ባለበት የአቅም ውስንነትና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ድጋፍ ማነስ የዕድሜውን ያህል እድገት እያሳየ አይደለም " ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም አባላቱ ተደራጅተው ካለባቸው የባህል ጫናና ተረጂነት እንዲላቀቁና እራሳቸውን ችለው በመንቀሳቀስ በክልሉ ልማትና እድገት ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ማህበሩ በትኩረት እንደሚሰራ አመለክተዋል።

ከሃደለኤላ ወረዳ የመጣችው የወረዳው ሴቶች ፌደሬሽን ሊቀመንበር ወይዘሮ ብርቱካን እንድሪስ በበኩላቸው ሴቶች ካለባቸው የባህል ጫናና ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲላቀቁ ሲሰራ መቆየቱን አመልክተዋል።

ባለፉት ዓመታት በክልሉ የልማትና የሰላም እሴት ግንባታ ሴቶች ከወንዶች እኩል የድርሻቸውን ለመጣት ተደራጅተው የጀመሩትን ጥረት በቀጣይም የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል አንደሚሰራ ተናግረዋል።

በፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ልማት ሚኒስቴር የብዙሃንና ሙያ ማህራት ተሳትፎ ዳይሬክተር ጄኔራል ወይዘሮ ሂሩት ደሌቦ በበኩላቸው የብዙሃንና ሙያ ማህበራት ለህብረተሰቡ ያላቸውን ቀረቤታ በመጠቀም በሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ላይ ቁልፍ ሚና መጫወት እንደሚችሉ አመልክተዋል።

ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት ያለበትን የፖሊሲ ክፍተትና የአፈጻጸም ውስንነቶች ፈጥኖ ለማረም እንዲችል ከብዙሃንና ሙያ ማህብራት ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

 

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን