አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Sunday, 15 April 2018

ሽሬ ሚያዝያ 7/2010 ሽሬ እንደሰላሴ ከተማ  "ዞአ" በተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ድጋፍ ስራ ያልነበራቸው 74 ወጣቶች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን የከተማው የስፖርትና የወጣቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ወጣቶቹ ወደ ስራ እንዲገቡ የተደረገው ድርጅቱ ባደረገው የ5ሚሊዮን ብር ድጋፍ ወጣቶቹ ስልጠናና ቁሳቁስ ተመቻችቶላቸው ባለፈው ሳምንት ነው፡፡

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ጎይቶም ይሰማ ለኢዜአ  እንዳሉት ወጣቶቹ የተሰማሩባቸው መስኮች መካከል የምግብ ዝግጅት፣የባንቧ መስመር ዝርጋታና ጥገና እንዲሁም የሴቶች ፀጉር ስራዎች ነው።

በማህበር ተደራጅተው በምግብ ዝግጅት የተሰማራችው ወጣት ማሾ አብራሃ  በሰጠችው አሰተያየት ከዚህ ቀደም ስራ እንዳልነበራት ገልጻ ከጓደኞቿ ጋር በመሆን በተሰጣቸው ስልጠናና ቁሳቁስ በመታገዝ ስራ መጀመራቸውን ተናግራለች።

ከስልጠናና ቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ  የአራት ወር ቤት ኪራይ ወጪ ተከፍሎላት በግሏ በምግብ ዝግጅት ሰራ መሰማራቷን የገለፀችው ደግሞ ወጣት ሰማእት ታደሰ ናት፡፡  

ራስዋን ችላ ቤተሰቦችዋን ለመርዳት  ጠንክራ እንደምትሰራ ጠቅሳ "ስራውን ከጀመርኩ ሳምንት ቢሆነኝም ውጤታማ እንደምሆን ተስፋ አለኝ " ብላለች ።

ወጣት ብርሀን አለም  በበኩሏ "በተደረገልን ድጋፍ በመታገዝ " ወይኒ" ብለን በሰየሙት ማህበራቸው  ምግብ ቤት ከፍተው መንቀሳቀስ ከጀመሩ አምስት ቀናት እንደሆናቸው ተናግራለች፡፡

በተሰጣቸው ስልጠናና ቁሳቁስ ድጋፍ በመታገዝ ከአምስት ጓደኞቹ ጋር ተደራጅቶ በቧንቧ  መስመር ዝርጋታና ጥገና ሥራ መሰማራቱን የገለፀው ደግሞ ወጣት ፍሰሀ አባዲ ነው፡፡

ድርጅቱ ካደረገላቸው የሙያ ስልጠና የቁሳቁስ ደጋፍ ሌላ የአራት ወራት  የቤት ኪራይ  የከፈለላቸው መሆኑንም ያመለከተው ወጣት ፍሰሀ  ስራውን  ከጀመሩ አምስት ቀናት ቢሆናቸውም ውጤታማ ለመሆን ተግተው እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጿል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ደሴ ሚያዝያ 7/2010 ታሪካዊው መቅደላ አምባን ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የተጠናከረ አካባቢ ጥበቃና መልሶ ግንባታ እንደሚያስፈልገው ተጠቆመ፡፡

 የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ 150ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓልን አስመልክቶ ህይወታቸው ያለፈበት የመቅደላ አምባ ተራራን የአውሮፓ  ምሁራን ትናንት ጎብኝተዋል፡፡

 ከምሁራኑ መካከል የህጻናት መጽሐፍ ደራሲ ዌልሳዊቷ ሄለን ፓፕወርዝ ጉብኝቱን  አስመልክታ እንደተናገረችው በ1868 እንደ ኤሮፓ አቆጣጠር  ከኒዮርክ ሄራልድ ጋዜጣ ጦርነቱን ለመዘገብ ከዌልስ ወደ መቅደላ ተጉዞ የነበረውን ሄንሪ ሞርተን ስታንሌይ አስታውሰዋል፡፡

 ዘጋቢው " ኮማሲ ኤንድ መቅደላ" በሚል ባዘጋጀው መጽሐፉ  ጦርነቱንና የአጼ ቴዎድሮስን አሳዛኝ ፍጻሜ ለማወቅ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

 በአውሮፓ  አጼ ቴዎድሮስም ሆኑ መቅደላ አምባ የገዘፈ ስም እንዳላቸው ያወሱት ምሁሩ ይህ ታሪካዊ ጀግና የተዋጉበትና ያረፉበት ቦታ በሚጠበቀው ደረጃ የቱሪስት መዳረሻ ሳይሆኑ እንደቆየ መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡

 መቅደላ አምባ ታሪካዊነቱን ሳይለቅ በኤኮ ቱሪዝም መጠናከር እንዳለበት የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዋ  ወደ ታሪካዊው ስፍራ መዳረሻ ሆቴሎችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መገንባት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

 "በጦርነቱ ወደ እንግሊዝ ተሰርቀው የተወሰዱ ታሪካዊ ቅርሶች እንዲመለሱ በማድረግ የአካባቢውን ታሪካዊነት ማስቀጠል ይገባል" ብለዋል፡፡

 በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ስፔናዊው እንድሪያስ ማርቲኔዝ በበኩላቸው በአውሮፓ ውስጥ በገናናነታቸው በስፋት የሚታወቁት አጼ ቴዎድሮስ ከእንግሊዞች ጋር ተዋግተው ራሳቸውን የሰውበትን  ቦታ ፣ ቤተመንግስታቸውንና ሌሎች ታሪካዊ ቤቶች ፍርስራሽ ምልከታቸው  "የአካባቢውን ውበትና ስትራቴጂክ አቀማመጥ ለማድነቅ ቃላት ያጥረኛል" ብለዋል፡፡

 የንጉሱን መቃብር ጨምሮ በአካባቢው በርካታ ታሪካዊ ቦታዎች ቢኖሩም በሚፈለገው ደረጃ እንክብካቤ እንዳለገኙ መመልከታቸውን አውስተዋል፡፡

 በወቅቱ በአካባቢው የነበሩትንና አሁን ፍርስረሳሻቸው የሚታዩ ቤቶችን እንደ አዲስ በመገንባት ታሪካዊነቱን ማጠናከር እንደሚገባ  ጠቁመዋል፡፡

 የደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ኢያሱ ዮኃንስ መቅደላ አምባን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በአምባው የሚገኙ ስምንት ታሪካዊ ቦታዎች ከሶስተኛ ወገን በማጽዳት የይዞታ ማረጋጋጫ ማግኘቸውን ገልጸዋል፡፡

 አቶ ኢያሱ እንዳመለከቱት በተጨማሪም  አምባው ላይ 9 ሚሊዮን ብር የሚወስድ የሙዚየም ግንባታ ለማከናወን የዲዛይን ስራ ተከናውኗል፡፡

 እስካሁን ለስራው ከአካባቢው ኅብረተሰብና ከመንግስት ከ600 ሺህ ብር በላይ መገኘቱን ጠቁመው፤በተለይ ባለሀብቶችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የተጀመረውን እንቅስቃሴ ዳር ለማድረስ ድጋፍ እንዲያደርጉ  መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን ታሪካዊውን ቦታ ከ150 ዓመት በላይ በማስከበርና በመጠበቅ የአካባቢው ኅብረተሰብ ላደረገው የላቀ አስተዋጽኦ አድናቆታቸውን ገልጸጸዋል፡፡

 ዩኒቨርሲቲው ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ  ጋር በመተባባር አካባቢውን የማልማትና ቅርሶቹን የመንከባከብ ስራ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

 ከገብኝቱ በኋላ በመቅደላ አምባ አካባቢ ዘጠኝ  የሚደርሱ ጥናታዊ ጽሑፎች በተጋባዥ እንግዶች የቀረቡበት ስብሰባ ተካሄዷል፡፡

 በስብሰባው የጎንደርና ሌሎችም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ አርቲስቶችና ጥሪ የተደረጋላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

Published in ማህበራዊ

 አዲስ አበባ  መጋቢት 7/2010 ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ከአትሌቲክ ሬኔሳንስ አይግሎን ጋር ላለበት የመልስ ጨዋታ ኮንጎ ብራዛቪል ገባ።

 ቅዱስ ጊዮርጊስና አትሌቲክ ሬኔሳንስ አይግሎን የፊታችን ረቡዕ 33 ሺህ ደጋፊ በሚያስተናግደው በስታድ አልፖንስ ማሴምባ-ዴባት ስታዲየም ከቀኑ በ10 ሠዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

 የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ምኒልክ ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት 18 ተጫዋቾችና ዘጠኝ የልዑካን ቡድን አባላትን ይዞ ዛሬ ማለዳ የተጓዘው ክለቡ ኮንጎ ብራዛቪል ገብቷል።

 ቡድኑ ብራዛቪል አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የአገሪቷ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተወካዮች አቀባበል ያደረጉለት ሲሆን የመገናኛ ብዙሃንም የልዑካን ቡድኑን መድረስ ለመዘገብ ተገኝተዋል።

 የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች የመጀመሪያውን ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ካደረጉበት ጊዜ ጀምሮ ለመልሱ ጨዋታ ልምምድ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አቶ ምኒልክ ገልጸዋል።

 የመጨረሻ ልምምዳቸውን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቃቸውንም አክለዋል።

 በመጀመሪያው ጨዋታ በጉዳት ያልተሰለፈው የመሐል ተከላካዩ አስቻለው ታመነ በቡድኑ ተካቶ ወደ ብራዛቪል አቅንቷል።

 ከሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዳነ ግርማ ጎል አንድ ለዜሮ ማሸነፉ የሚታወስ ሲሆን በአጠቃላይ በደርሶ መልስ የሚያሸንፈው ቡድን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ወደ ምድብ ድልድሉ ይገባል።

 በተመሳሳይ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው ወላይታ ድቻ የፊታችን ረቡዕ ከታንዛኒያው ያንግ አፍሪካንስ ጋር በሃዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ በአስር ሠዓት ይጫወታል።

 የክለቡ ቡድን መሪ አቶ አሰፋ ሆሲሶ ከወላይታ ድቻ ጋር ጨዋታውን የሚያደርገው ያንግ አፍሪካንስ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ መግባቱንና ከሠዓታት በኋላም ሃዋሳ እንደሚደርስ ገልጸዋል።

 ጨዋታውን የሚመሩት የኡጋንዳ ዳኞች እንዲሁም ጅቡቲያዊው የጨዋታው ኮሚሽነር ነገ አዲስ አበባ ገብተው ቀጥታ ወደ ሃዋሳ እንደሚጓዙ ጠቁመዋል።

 ወላይታ ድቻ ያለፈውን ጨዋታ በታንዛኒያ ዳሬሰላም ካደረገ በኋላ ለመልሱ ጨዋታ ልምምድ ሲያደርግ ቆይቷል።

 ቡድኑ በጥሩ መንፈስ ላይ እንደሚገኝና የመጀመሪያውን ጨዋታ ውጤት በመቀልበስ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ለመሸጋገር ዝግጁ መሆኑንም አክለዋል።

 ከሳምንት በፊት በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ያንግ አፍሪካንስ ሁለት ለዜሮ ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

 ወላይታ ድቻ የግብጹን ዛማሌክን በሜዳው አሸንፎ ወደ 32 ውስጥ በመግባት በኢትዮጵያ እግር ኳስ አዲስ ታሪክ ማስመዝገቡ አይዘነጋም።

Published in ስፖርት

 አዲስ አበባ ሚያዝያ 7/2010 በአንድነትና በመተሳሰብ ስሜት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ድጋፍ እንደሚያደርጉ በሚሊኒየም አዳራሽ የተገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ማምሻውን 25 ሺህ ከሚሆኑ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ጋር በሚሊኒየም አዳራሽ ይወያያሉ።

በአዳራሹ የተገኙት የውይይቱ ተሳታፊዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን መምጣት በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የስራ ዘመን ስኬታማ እንዲሆን በሙሉ አቅማቸው እንደሚደግፏቸው ነው የገለጹት።

የመዲናዋ ነዋሪ አቶ አማኑኤል ሙላቱ ባለፉት ጊዜያት አገሪቷ ሁከትና አለመረጋጋት ውስጥ ገብታ እንደነበረ አስታውሰው በተደረገው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ወደ ቀድሞ ሰላሟ እየተመለሰች ነው ብለዋል።

አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትርም የገቡትን ቃል ለመፈጸም በጊዜ የለኝም መንፈስ መስራት ይጠበቅባቸዋል ካሉ በኋላ እርሳቸውም በሚችሉት አቅም የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንደሚወጡና ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ወይዘሮ ዘነበች ወልደሰማያት የጠቅላይ ሚኒስትሩን መምጣት በጉጉት እየተጠባበቁ መሆናቸውንና በአዳራሹ ውስጥ ያለውም ድባብ ይህንኑ እንደሚያንፀባርቅ ነው የተናገሩት።

ህብረተሰቡ በፍቅር፣ በመተሳሰብና በአንድነት በመቆም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ያሉት ወይዘሮዋ እርሳቸውም ለዚህ ዝግጁ መሆናቸውን አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህብረተሰቡ ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች የሚሰጡትን ምላሽ ለማድመጥ መጓጓታቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ ለታ ተመስገን ናቸው።

እርሳቸውም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስራ ዘመን ስኬታማ እንዲሆን እንደ ዜጋ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህብረተሰቡ ተወካዮች ጋር የሚያደርጉት ወይይት “የፍቅርና የአንድነት ኪዳን” የሚል መሪ ሃሳብ የተሰጠው ሲሆን፤ አንድነትና የዴሞክራሲ ስርዓትን ለማጎልበት ከህዝብ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት እንደሚያግዝ ታምኖበታል።

በመድረኩ የፌዴራል፣ የክልልና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራንና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ተወካዮች እንደሚታደሙ እየተጠበቀ ነው።

Published in ፖለቲካ

አሶሳ ሚያዝያ 7/2010 የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ፖሊስ ማሰልጠኛ ኮሌጅ 343 የሚሊሻ አባላትን ትላንት አስመረቀ ።

ከተመራቂዎች መካከል 43 ቱ ሴቶች ናቸው።

በክልሉ ፖሊስ ኮሌጅ የአካዳሚክ ጉዳዬች ምክትል ዲን ምክትል ኢንስፔክተር ምስጋና እንጅፋታ እንደገለፁት ኮሌጁ የሚሊሻ አባላቱን አሰልጥኖ ያስመረቀው የክልሉን የፀጥታ መዋቅር ለማጠናከር ነው።

ተመራቂዎቹ በቆይታቸው በወንጀል መከላከል ከተሰጣቸው ተግባር ተኮር ስልጠና በተጨማሪ በህገ መንግስት ዙሪያ ግንዛቤ እንዲጨብጡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የክልሉ አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዬች ማስተባበሪያ  ቢሮ  ምክትልኃላፊ ኮማንደር አብዱላዚም መሃመድ "የሚሊሻ አባላቱ ለህብረተሰቡ ቅርብ እንደመሆናቸው የየአካባቢያቸውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ተግተው ሊሰሩ ይገባል" ብለዋል፡፡

ከተመራቂ ሚሊሺያዎች መካከል  ወይዘሮ ትዕግስት ደጀኔ በሰጡት አስተያየት ስለወንጀል አስከፊነት ግንዛቤ በመፍጠር ድርጊቱን ለመቀነስ  እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

አቶ ኦላና ሃብቴ እንዳሉት የወንጀል መነሻ የሚሆኑ ጉዳዬች በመለየት ከአካባቢያቸው ነዋሪዎችና የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ለመስራት ተዘጋጅተዋል፡፡

የቤንሻንጉል ክልል ፖሊስ ማሰልጠኛ ኮሌጅ የአሁኖቹን ጨምሮ በሶስት ዙር ከ900 በላይ የሚሊሻ አባላት ማስመረቁ ተመልክቷል፡፡

 

 

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አርባምንጭ ሚያዝያ 7/2010 በማህበር ተደራጅተው በተሰማሩበት የሰራ መስክ ውጤታማ መሆናቸውን በጋሞጎፋ ዞን በዲታና ካምባ ወረዳዎች አስተያየታቸውን የሰጡ  ሴቶች ገለፁ።

በዲታ ወረዳ የሌሻ ቀበሌ ሴቶች ማህበር  ሰብሳቢ ወይዘሮ ኦቢቴ ኦኖ ለኢዜአ እንዳሉት  191 የማህበሩ አባላት 2008 ዓ.ም ተደራጅተው በግብርና ስራ ተሰማርተዋል ።

"በተሰጠን ሶስት ሄክታር መሬት ላይ ድንች፣ አተር፣ ባቄላና የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማምረት ከምናገኘው ገቢ በማህበሩ ስም 100 ሺህ ብር ቆጥበናል " ብለዋል ።

አባላቱ በተያዘው ዓመት ከምርት ሽያጭ ከ10 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ከማህበሩ በብድር  ባገኙት ገንዘብ የሳር ክዳን ቤታቸውን በቆርቆሮ መቀየራቸውን የገለፁት ወይዘሮ ኦቢቴ ከጠባቂነት ተላቀው ባለቤታቸውን በወጪ እያገዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በካምባ ወረዳ ኡጹማ ቀበሌ ዕድገት በህብረት ሴቶች ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ አስቴር ያቻ በበኩላቸው 135 የማህበሩ አባላት  በ2009 ዓ.ም ተደራጅተው በዶሮ እርባታና የጓሮ አትክልት ልማት  ተሰማርተው ሲሰሩ መቆየታቸውን አመልክተዋል።

"አባላቱ በተሰማራንበት መስክ ውጤታማ በመሆን ከምርት ሽያጭ ካገኘነው ገቢ ከ160 ሺህ ብር በላይ ቆጥበናል" ብለዋል ።

በግላቸው ሚያገኙት ገቢና ከማህበሩ የቁጠባ ብድር በመታገዝ ሁለት  ልጆቻቸውን በከፍተኛ ትምህርት ተቋም እያስተማሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ያልተማሩ የማህበሩ አባላት የመፃፍና የማንበብ ክህሎት እንዲያዳብሩ  ዘንድሮ የተግባር ተኮር ትምህርት እየተከታተሉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በዞኑ የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ የሴቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ ወይዘሮ በላይነሽ በቀለ ከ2008 ዓ.ም ወዲህ ሴቶች ተደራጅተው በብድርና ቁጠባ አገልግሎት  ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መምጣቱን ተናግረዋል።

"በማህበር የተደራጁ ሴቶች 12 ሚሊዮን ብር ብድር ተሰጥታቸው የተሰማሩባቸውን የግብርና ስራዎች እያሰፋፉና እያጠናከሩ ናቸው " ብለዋል ።

በዞኑ 15 ወረዳዎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ከ12 ሺህ  በላይ ሴቶች 265 የብድርና ቁጠባ ማህበራት አቋቁመው ከ4 ሚሊዮን ብር ካፒታል ማፍራታቸውን ጠቅሰዋል ።

ሴቶቹ የቆጠቡትን ሶስት እጥፍ የብድር አገልግሎት በማግኘት በተለያዩ የግብርና ሥራዎች ተሰማርተዋል፡፡

በዞኑ ተጨማሪ 255 የሴቶች ማህበራትን ለማቋቋም  ታቅዶ እየተሰራ ነው ።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 7/2010 የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ከአራዳ ኬር ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በመዲናዋ ለሚገኙ 150 የጎዳና ተዳዳሪዎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት ሰጠ።

 ሆስፒታሉ ለጎዳና ተዳዳሪዎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ የዛሬው ለሶስተኛ ጊዜ ነው።

 የህክምና አገልግሎቱን ሲሰጡ ያገኘናቸው ዶክተር ሰለሞን ደሳለኝ ለኢዜአ እንደገለጹት የጎዳና ተዳዳሪዎች ባሉባቸው የኢኮኖሚና ሌሎች ተደራራቢ ችግሮች ሳቢያ ሕክምና አያገኙም።

 በመሆኑም ካሉባቸው የጤና ችግሮች እንዲፈወሱ ሆስፒታሉ ተከታታይ ህክምና ማግኘት የሚያስችላቸውን ስርዓት በመዘርጋት ሙሉ የህክምና አገልግሎት እየሰጣቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

 አራዳ ኬር ፋውንዴሽን የምገባና የአልባሳት ድጋፍ ሲያደርግላቸው ቆይቷል ያሉት ዶክተር ሰለሞን ሆስፒታሉ ደግሞ ለምን ነጻ ሕክምና አያደርግም በሚል ተነሳሽነት አገልግሎቱን መጀመሩን ተናግረዋል።

 የአራዳ ኬር ፋውንዴሽን መስራች አቶ ሄኖክ ዓብይ ነጻ ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን በርካታ የጎዳና ተዳዳሪዎች ለመደገፍ በማሰብ ከአራት ዓመታት በፊት ማሕበሩን መመስረታቸውን ገልፀዋል።

 ፋውንዴሽኑ ከሆስፒታሉ ጋር በመተባበር ሕክምና እንዲያገኙ ሲያደርግ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑንና ከዚህ ቀደም የመመገብና ልብስ የማልበስ ተግባራትን ያከናውን እንደነበር ጠቅሰዋል።

 በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የሕክምና ፕሮግራሙ አስተባባሪ ወይዘሮ ቅድስት ተስፋዬ ለጎዳና ልጆች ምግብና አልባሳት ከመስጠት ባለፈ ጤንነታቸውን መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

 በእስካሁን ሂደት የቆዳና የጉበት በሽታዎች በአብዛኞቹ የጎዳና ተዳዳሪዎች ላይ የሚስተዋሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

 በቀጣይም ከመንግስት ጋር በመስራት መማር የሚፈልጉ እንዲማሩ፤መስራት የሚሹም እንዲሰሩ ይደረጋል ብለዋል።

 የጎዳና ተዳዳሪዎችም የተደረገላቸው ሕክምና በቀጣይ የተስተካከለ ሕይወት እንዲኖሩ ተስፋ እንደሰጣቸው ገልጸው ዕድሉን ያላገኙትም ህክምና የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ሶዶ ሚያዝያ 7/2010 ማህበረሰብ አቀፍ የትምህርት ልማት ሠራዊት ግንባታ በዘርፉ የተሻለ ለውጥ  እንዲመጣ ማገዙን የወላይታ ሶዶ ከተማ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የአስተዳደሩ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ባዳቾ በትምህርት አስተዳደር ጉባኤ  በገመገመበት  ወቅት እንዳሉት የተማሪዎች የተነሳሽነት ጉድለት የስነ ምግባር ችግርና ለኩረጃ ያላቸው የተሳሳተ አተያይ ባለፈው ዓመት ውጤት እንዲቀንስ አድርጓል፡፡

የግብአት ፣የመምህራን አቅም ማነስና ከስነ ምግባር ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲሁም የውሸት ሪፖርትና ጊዜውን የጠበቀ ድጋፍና ክትትል ማነስ አምና የተለዩ ችግሮች እንደነበሩ አስታወሰዋል፡፡

ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት ማህበረሰብ አቀፍ የትምህርት ልማት ሠራዊት መገንባት በማስፈለጉ በበጀት ዓመቱ በተቀመጠው አቅጣጫ ስራው መጀመሩንና ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

የተማሪዎችን ማርፈድ በማስቀረት የትምህርት ብክነትን መቀነስ፣ የጥናት ባህሉን ማሳደግ የሚያስችሉ ቤተ መጽሃፍትን መስራትና የፕላዝማ ትምህርት እንዳይቋረጥ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

"የመምህራንን አቅም ለማሳደግ በተለያዩ ስልጠናዎችና ማትጊያዎች በማመቻቸት  ቁጭት እንዲያድርባቸው በመደረጉ በዞን ደረጃ በተሰጠው ው ፈተና የተሻለ ውጤት ሊመዘገብ ችሏል "ብለዋል፡፡

የግብአት እጥረትን ለማስተካከል ማህበረሰቡ የተሳተፈበት ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ መጪ መጪ በማድረግ  የማጣቀሻ መጻሐፍት መገዛቱንና  ከ18 በላይ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸውም ተመልክቷል፡፡

የከተማው አስተዳደር  ከንቲባ አቶ ጸጋዬ ኤካ ለውጥ ለማምጣት  የዓመቱ ስራ ሲጀመር ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ንቅናቄ ህዝባዊ መሰረት መያዝ በመቻሉ በተማሪዎች ውጤት አመላካች ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ማህበረሰቡን በማሳተፍ በጋራ በመሰራቱ በተማሪዎች ስነ ምግባር እየተሻሻለ  መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ የትግል ፍሬ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህርት አስራት ከበደ ናቸው፡፡

በሶዶ ከተማ የዋጃ ቀሮ ትምህርት ቤት የወላጅ ተማሪ መምህራን ህብረት ሰብሳቢ አቶ ታምራት ዮሃንስ  "ባለፈው ዓመት የነበረው የውጤት ማሽቆልቆል አስደንጋጭ ነበር "ብለዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዳማ ሚያዝያ 7/2010 የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የክልልና የፌዴራል ምክር ቤቶች ጠንካራ ድጋፍ  እንደሚያስፈልግ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

 የሴቶችን ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገር በሚቻልበት ላይ የክልልና የፌዴራል ምክር ቤቶች የዘርፉ ቋሚ ኮሚቴ ድጋፍና ክትትል ለማጠናከር የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሄዷል።

 በመድረኩ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስትሩ ወይዘሮ ደሚቱ ሀምቢሳ እንዳሉት  ባለፉት ዓመታት የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተደረጉ ጥረት አበረታች ውጤቶች ተመዘግበዋል።

 የውሳኔ ሰጪነት ሚናን ከማሳደግ አኳያ በፌዴራልና በክልል ምክር ቤቶች የሴቶች ተሳትፎ 38 በመቶ መድረሱን ጠቅሰዋል።

 ሴቶች ከወንዶች የኢኮኖሚ ጥገኝነት እንዲላቀቁ በተፈጠረው ንቅናቄ በብድርና ቁጠባ፣በህብረት ሥራ ማህበራት፣ጥቃቅንና አነስተኛ ፣በግብርናና አግሮ ፕሮሰስንግ እንዲሰማሩ መደረጉን ተናግረዋል።

 "የሴቶችን የቁጠባ ባህል ለማሳደግ በተደረገው ጥረት ከዘጠኝ ቢሊዮን ሁለት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ቁጠባ መሰብሰብ ችለናል "ያሉት ሚንስትሯ በዚህም በ942 መሰረታዊ ማህበራት የተደራጁ ከ1 ሚሊዮን 400ሺህ በላይ ሴቶች በተለያዩ የሥራ መስኮች እንዲገቡ መደረጉን አመልክተዋል።

የእናቶችና የህጻናትን ሞት ለመቀነስ በተደረገው ጥረትም  አበረታች ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

 የሴቶች  በመጀመሪያ ደረጃ የትምህርት እርከን ተሳትፎ የተሻለ ሲሆን  በሁለተኛና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተፈለገውን  ውጤት ባለመታየቱ  ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡

 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እሚዬ ብተው በበኩላቸው  ምክር ቤቱ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አስፈፃሚውን አካል የሥራ ክንውን የመከታተልና የመቆጣጠር ተግባር እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

 በዚህም " በሴቶች ዙሪያ በየተቋማቱ የተከናወኑ ሥራዎች በመስክ ምልከታ በመገምገምና ለፈጻሚው አካል ግብረ መልስ በመስጠት የሚገኙበትን ሁኔታና ሊደረጉበት ሰለሚገባው መሻሻያዎች ሃሳብ እየሰጠን ክትትል እናደርጋለን "ብለዋል።

 ምክር ቤቱ የሴቶችን ደህንነት፣መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚወጡ አዋጆችን በትክክል በመፈተሽ ማስተካካያ እንዲደረግባቸው መደረጉን ገልጸዋል፡፡

 ለዚህም የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ፣የጋብቻ ፣ ሌሎች ህጎችና አዋጆች ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ማድረጉን ጠቅሰዋል።

 በክልላቸው የሴቶች የህዝብ ምክር ቤቶች ተሳትፎ 47 በመቶ መድረሱን የተናገሩት ደግሞ በሐረር ክልል ምክር ቤት የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳብ ወይዘሮ አዲስዓለም በዛብህ ናቸው።

 በክልሉ ሴቶች በሥራ እድል ፈጠራ፣በጤና፣ትምህርትና ተጓዳኝ አገልግሎቶች  ተሳትፏቸውና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋጋጥ  ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።

 ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ከፌዴራል፣ ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የምክር ቤቶች የቋሚ ኮሚቴ አመራሮች ተሳትፈዋል።

 

 

Published in ማህበራዊ

ጅጅጋ ሚያዝያ 7/2010 በጎሳዎች መካከል የሚታየውን የጋብቻ መገለልን በማስቀረት ትስስራቸውን ለማጠናከር የ29 ጥንዶች የጋብቻ ስነ- ስርዓት ትላንት በጅግጅጋ ከተማ ተፈጸመ፡፡

የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ባደረገው ድጋፍ  በአንድ አዳራሽ ጋብቻቸውን የፈፀሙት ጥንዶች ከተለያዩ የሶማሌ ጎሳዎች የተውጣጡ ናቸው ።

የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሐሙድ በስነ ስርዓቱ ላይ እንደገለፁት  በገቦዩ ጎሳ ስር ያሉ ሚድጋን፣ ቱማልና ዓደልቃተ የተሰኙ ጎሳዎች እርስ በርሳቸው ካልሆነ ከሌሎች ጎሳዎች ጋር በጋብቻ እንዳይተሳሰሩ ተደርገው ለዓመታት ተገለው ቆይተዋል።

በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ላለፉት ስድስት ወራት በድርጊቱ ጎጂነት ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠቱን ተከትሎ ጥንዶቹ በፍላጎታቸው ባቀረቡጥ ጥያቄ መሰረት የክልሉ መንግስት አስተማሪነቱን በመገንዘብ የጋብቻ ስነ- ስርዓቱን ማዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ጎሳዎች እኩል በመሆናቸው  ኋላቀር አመለካከት የፈጠረውን ልዩነት በማስቀረት ትስስራቸውን ለማጠናከር  በጎሳዎች መካከል ጋብቻ እንዲፈፀም መደረጉን አመልክተዋል፡፡

"አንዱ ጎሳ ከሌላው ጎሳ እኩል ነው" ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ አንድነታቸውን በማጠናከር  በጋብቻ እንዳይተሳሰሩ የመከልከል ጉዳይ ተገቢነት እንደሌለው ተናግረዋል ።

ሁሉም የክልሉ ህብረተሰብ ይህንን መሰል ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለማስወገድ መተባበር እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በባህል ስም የሚፈፀመውን በደል ለማስቆምና የህዝቡን  አንድነት የሚሸረሽሩ አላስፈላጊ ተግባራት ለመከላከል መንግስት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የጋብቻ ስነ- ስርዓታቸውን ከፈፀሙ ሙሽሮች መካከል የሀዊያ ጎሳ ተወላጅ የሆነው ወጣት መሀመድ አብዱረህማን  የገቡዩ ጎሳ ተወላጅ የሆነች ፍቅረኛውን ለማግባት ቢፈልግም የማህበረሰቡን ተፅዕኖ በመፍራት ተግባራዊ ሳያደርገው መቆየቱን  አስታውሷል ።

"አሁን ላይ ከፍቅረኛዬ ጋር በጋብቻ የተሳሰርንበት አጋጣሚ በመፈጠሩ ተደስቻለሁ" ብሏል።

በስነ -ስርዓቱ ላይ ከተገኙ የኃይማኖት አባቶች መካከል ሼህ አብዱራህማን ዑመር በበኩላቸው  የገቦዩ ጎሳ ተወላጆች  እርስ በእርሳቸው ካልሆነ ከሌሎች የጎሳ ተወላጆች ጋር በጋብቻ መተሳሰር እንዳይችሉ ለዘመናት የቆየው ባህላዊ ጭቆና  ኃይማኖታዊ መሰረት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

ወጣት አህመድኑር ኢብራሂም በሰጠው አስተያየት "በክልሉ ጎሳዎች መካከል የሚደረገው ልዩነቶች መሰረታቸው ኋላ ቀር አመለካከት እንደሆነ እገነዘባለሁ" ብሏል፡፡

በሶማሌ ክልል 38 ጎሳዎች ሲኖሩ የጋብቻ ስነ- ስርዓታቸውን ከፈፀሙ መካከል 29 ወጣት ወንድና ሴት ሙሽሮች የገቦዩ ጎሳ ተወላጅ ሲሆኑ 29ኙ ደግሞ ከተለያዩ ጎሳዎች የተውጣጡ ናቸው።

የክልሉ መንግስት  ለ29 ጥንዶች ያሰራውን የመኖሪያ ቤት ቁልፍና ለስራ መነሻ የሚሆን ገንዘብ በስጦታ አበርክቶላቸዋል ።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን