አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Saturday, 14 April 2018

አዲስ አበባ ሚያዚያ 6/2010 አዱሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከውጭ ምንዛሬ ጋር በተያያዘ እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ መሰረታዊ እርምጃዎች እንደሚወስዱ እምነታቸው መሆኑን የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽንና በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለባለሀብቱም ሆነ ለሕዝቡ መሰረታዊ ጉዳይ ለሆነው ሰላምና መረጋጋት የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡም ጠይቀዋል።

ኢዜአ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በጤና፣ ትምህርት ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶችንና የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በሚያደርጉት ውይይት ምን እንደሚጠብቁ አነጋግሯል።

የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመር እንደተናገሩት፤ ለባለሃብቱ የሚያስፈልገው ዋነኛ ጉዳይ ሰላምና መረጋጋት ነው።

ኢንዱስትሪው ሰላማዊ እንዲሆን፣ የሰራተኛውና የአሰሪዎች መብትና ጥቅም እንዲጠበቅ፣ ከሙስና የጸዳ አሰሪ እንዲፈጠር፣ ሙስናን የሚሞግት ትውልድ ለመፍጠርና የአገር ኢኮኖሚ ለማሳደግ ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሰላም ጥያቄውን ለመፍታት የሚያስችል አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ ፍላጎታቸው እንደሆነ የተናገሩት አቶ ታደለ፤ በአገሪቷ አሁን የሚታየውን ሰላምና መረጋጋት ማስጠበቅና የባለሃብቱ ቁልፍ ጥያቄ የሆነውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመፍታት እንደሚሰሩ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ ለባለሃብቱ መሰረታዊ የሆኑት የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የሰላም ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጡ እምነታቸው መሆኑን በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶች ተናገሩ።

በሆቴልና ቱሪዝም ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ታደሰ እያሱ እንዳሉት፤ የተሰማሩበት ዘርፍ በአገሪቷ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትና ከፍተኛ የሰው ሃይል በመቅጠር ቢታወቅም የውጭ ምንዛሬ በማጣት የሚፈለገውን አስተዋጽኦ እያበረከተ አይደለም።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ እንደሚሰጡ እምነታቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

በምግብና መጠጥ ላይ የተጣለው የ15 በመቶ እሴት ታክስ ተገልጋዩ ላይ ቅሬታ እያስነሳ መሆኑን ጠቁመው፤ መፍትሄ እንዲሰጠው የቀረበው ተደጋጋሚ ጥያቄ ምላሽ እንደሚያገኝ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

በጤናው ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ዳዊት ሞገስ እንዳሉት፤ ዘርፉ ለትርፍ ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡን ለመርዳት የተቋቋመ እንደመሆኑ እንደሌሎች ድጋፍ እየተደረገለት አይደለም።

በትምህርት ዘርፍ  የተሰማሩት አብዱህማን ቁብሳ በበኩላቸው፤ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና የትምህርት ፖሊሲው የሚጠይቃቸውን መስፈርቶች ለሟሟላት ባለሃብቱ ችግር እየገጠመው እንደሆነ ገልጸዋል።

በተለይ በሰው ሃይል ብቁ መምህራንን የሚያፈሩ ተቋማት እጥረት በትምህርት ጥራቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን ጠቁመዋል።

አሁን የሚደረገው ከዩንቨርስቲ የሚመረቁ ልጆች እንደገና  ለአንድ ዓመት እንዲሰለጥኑ ይደረጋል ይህ ደግሞ የጊዜና የገንዘብ ብክነት አለው፡፡

ባለሃብቶቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚች አገር ዕድገትና ለውጥ በሚያደርጉት መልካም ስራ ሁሉ  ከጎናቸው በመሆን እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሚያዚያ 8 ቀን 2010 ዓ.ም ከባለሃብቶች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ድሬዳዋ ሚያዚያ 6/2010 የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለሁለተኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 16 ኃኪሞች ዛሬ በዶክትሬት ዲግሪ አስመረቀ።

 ምሩቃን በበኩላቸው በየትኛውም ጊዜና ቦታ ህብረተሰቡን በቅንነት፣ በታማኝነትና በርህራሄ ለማገልገል ቃል ገብተዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቁት ኃኪሞች ላለፉት 6 ዓመታት በኮሌጁ በንድፍ ሃሳብና በተግባር የተሰጠውን ትምህርት ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው።

በምርቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ያሬድ ማሞ ሕክምና ከፍተኛ ማህበራዊ ኃላፊነት ያለበት ትልቅ ሙያ መሆኑን አስታውሰው፣ ምሩቃን በኮሌጁ ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ሕብረተሰቡን ሳይሰለቹ ማገልገል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

"ሙያው በየጊዜው ራስን ማሳደግና መማርን የሚጠይቅ ነው፤ በመሆኑም ይህን በመገንዘብ ሁልጊዜም ራስን በማብቃት የተሻለ ውጤታማ ሥራ ለመስራት መታጋት አለባቸሁ" ብለዋል፡፡

ለተመራቂ  ኃኪሞች ዲግሪና ክፍተኛ ውጤት ላመጡት የተዘጋጀውን ሽልማት የሰጡት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል አቶ ኢብራሂም ዑስማን ናቸው፡፡

ከንቲባ ኢብራሂም በእዚህ ወቅት እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ያስመረቃቸው እጩ ኃኪሞች መንግስት በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የሕክምና ዶክትሮች እጥረት ለመፍታት እያደረጋቸው ላሉ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች አንድ ማሳያ ነው፡፡

የዕለቱ ምሩቃን ኃኪሞች ሕብረተሰቡን በታላቅ ሀገራዊና ሙያዊ ኃላፊነት በማገልገል በሀገር ደረጃ በጤናው ሴክተር እየተመዘገበ ያለውን ውጤት ማስቀጠል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

የዕለቱ ምሩቃን በበኩላቸው ህብረተሰቡን በየትኛውም ጊዜና ቦታ ያለምንም አድልኦ በቅንነት፣ በታማኝነትና በርህራሄ ቀን ከሌት ለማገልገል ቃል ገብተዋል፡፡

ከምሩቃን መካከል በትምህርቱ 3 ነጥብ 6 በማምጣት ልዩ ተሸላሚ የሆነው ተመራቂ ዶክተር ራህመት በድሩ በበኩሉ "መነሻችንም መድረሻችንም ህብረተሰቡን በርህራሄና በቅንነት ማገልገል ነው፤ ይህን ትልዕኮ በየትኛው ጊዜና ቦታ ለመፈፀም ዝግጁ ነኝ" ብሏል፡፡

በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀችው ዶክተር አለምፀሐይ ተሸመ በበኩሏ በቀጣይ በምትመደብበት ሥፍራ ሁሉ ጤናማና አምራች ሕብረተሰብ ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደምተሰራ ተናግራለች፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የዛሬዎቹን ጨምሮ 60 ኃኪሞችን ማስመረቁ ታውቋል ፡፡

Published in ማህበራዊ

ባህርዳር ሚያዚያ 6/2010 የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን /  ለጣና ሃይቅ ስጋት የሆነውን የእምቦጭ አረም ለመከላከል የሚረዳ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

የክልሉ አካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን በበኩሉ የገንዘብ ድጋፉ እስከ ዛሬ እየተደረገ ያለውን የመከላከል ስራ ይበልጥ እንደሚያፋጥነው አስታውቋል።

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ አለምነው መኮነን በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት ብአዴን የሚመራው የክልሉ መንግስት ህዝቡ በገንዘቡ በጉልበቱና በእውቀቱ አረሙን በማጥፋት ስራ ላይ እንዲረባረብ ሲያስተባብር ቆይቷል።

የጣና  ሃይቅ ላይ የተከሰተው የእምቦጭ አረም የሃይቁን ህልውና ስጋት ላይ በመጣሉ አርሶ አደሩና ህብረተሰቡ በዘመቻ መልክ ሲያደርጉት የቆየውን የመከላከል ስራ እንደሚያደንቁም ተናግረዋል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው ያደረገው ድጋፍም ቀደም ሲል አርሶ አደሩና ባለሃብቶች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የሚያግዝ የአረም ማስወገጃ ማሽን ለመግዛት እንደሚውልም ገልጸዋል።

የክልሉ አካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳያሬክተር አቶ በልስቲ ፈጠነ ድጋፉን ሲረከቡ እንደገጹት አረሙ በተለይ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በሃይቁ ዙሪያ ሲከሰት በዚህ ደረጃ ለሃይቁ ደህንነት ስጋት ይሆናል ተብሎ አልታሰበም።

ችግሩን ለማቃለልም በተለይ ከ2008 ጀምሮ በተከታታይ ሲከናኑ ቆዩት የዘመቻ ስራዎች ገልጸው የተገኘው ውጤትም አበረታች እንደሆነ አስረድተዋል።

ስራው ከዘመቻም ባለፈ በመደበኛነት እንዲቀጥል እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ዳያሬክተሩ ብአዴን የክልሉ ብሎም የሃገሪቱ ሃብት የሆነው የጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተውን ስጋት ለመታደግ ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

የጣና ሃይቅና አካባቢው 130 ቀበሌዎችን ያቀፈ ሲሆን እምቦጭ አረምን ለመከላከል በተካሔደው ስራም እስከ ታህሳስ 2010  87 በመቶ ያክሉን ማስወገድ እንደተቻለ  ከባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ 6/2010 በተያዘው በጀት ዓመት መንግሥት ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር የለቀቀውን የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ አፋርና ጋምቤላ ክልሎች አለመውሰዳቸው ተገለጸ።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው መግለጫ፤ በተያዘው በጀት ዓመት የታየውን 52 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ለመሙላት በቀሪዎቹ ወራት ትኩረት ይደረጋል ብሏል።

መንግሥት ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ 10 ቢሊዮን ብር ለወጣቶች ተዘዋወሪ ፈንድ መመደቡ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ መግለጻቸው ይታወሳል።

ያም ሆኖ ገንዘቡ ለወጣቶች በምን መልኩ መድረስ አለበት በሚለው አሰራር ማሻሻያ ተደርጎበት በታየዘው ባጀት ዓመት መግቢያ ጀምሮ ፈንዱ ወደ ወጣቶች እጅ እንዲደርስ አዲስ አቅጣጫ ተቀምጧል።

ይሁንና በእስካሁኑ ሂደት የአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም የአፋርና የጋምቤላ ክልሎች የተመደበውን የወጣቶች ፈንድ ወስደው እስካሁን አለመጠቀማቸውን የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሐጂ ኢብሳ ገልፀዋል።

ይሁንና ከእነዚሁ ክልሎችና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በጉዳዩ ዙሪያ በጋራ መምከራቸውን ጠቁመው በቅርቡ ገንዘቡን ወስደው ሥራ ይጀምራሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል። 

በአንጻሩ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣  አማራና ደቡብ ክልሎች የተመደበውን የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ በመጠቀምና በአግባቡ ለታለመት ዓለማ በማዋል አፈጻጸመቸውን አድንቀዋል።

በሌላ በኩል በተያዘው ባጀት ዓመት 52 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት መኖሩን ጠቁመው ይህም ከአገር ውስጥ ግብርና ከውጭ ብድርና እርዳታ ለመሙላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

ለበጀት መጓደሉም የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱ መዳከም መሆኑን ገልጸው በዓመቱ ሊሰበሰብ ከታቀደው 244 ቢሊዮን ብር እስካሁን ከ60 በመቶ እስከ 70 በመቶ መሰብሰቡን አቶ ሐጂ ለአብነት ጠቁመዋል።

ጎነ ለጎን ከውጭ የሚገኘውን የብድር ፍሰቱም ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ20 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ነው ያረጋገጡት።  

በሌላ በኩል በውጭ ምንዛሪ ተመን የተወሰደው ማሻሻያ በተለይም በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በውጭ ንግድ አፈጻጸም ላይ እስከ 6 በመቶ የሚሆን አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።

በትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ የፋይናንስ እጥረት አለ ወይ? ተብለው ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም እስካሁን ድረስ በገንዘብ አጥረት ምክንያት የተቋረጠ ፕርጀክት አለመኖሩን ኃላፊው ተናግረዋል።   

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ ሚያዝያ  6/2010 በትግራይ ክልል የቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ፖሊሲውን መሰረት ያለደረገ ስልጠና ሲሰጡና ከህግ ወጭ ሲሰሩ የተገኙ አስር የግል ኮሌጆች ከሥራቸው ታገዱ።

የትግራይ ክልል ቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ በዘርፉ የተስተዋሉ ችግሮችን በጋራ ለማስተካከል በመቀሌ ከተማ ለሦስት ቀናት ያካሄደው የምክክር መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሙሉጌታ ሀዱሽ የምክክር መድረኩን ሲከፍቱ እንዳሉት ኮሌጆቹ የትምህርት ሚኒስቴር መስፈርትን ሳያሟሉ ተማሪዎች ተቀብለው ማስተማራቸውና ብቃት የሌላቸው ሰልጣኞችን እያስመረቁ መሆናቸው ተደርሶበታል፡፡

"አንዳንድ የግል ኮሌጆችም ከእውቅና ውጪ ለተቀበሏቸው ተማሪዎች ሙያና ክህሎት ይዘው እንዲወጡ ከማድርግ ይልቅ የምስክር ወረቀት በገንዘብ በመሸጥ አካዳሚክ ሙስና እየፈፀሙ ናቸው" ብለዋል።

ሀሰተኛ የስልጠና ሪፖርት ማቅረብን እንደባህል የያዙት ኮሌጆች መኖራቸውንም ዶክተር ሙሉጌታ ጠቁመዋል፡፡

ኮሌጁ ከሥራቸው የታገዱት በተያዘው ዓመት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የቢሮው የህዝብ ግኑኝነት ባለሙያ አቶ አብርሃም ብርሃነ ናቸው፡፡

ኮሌጆቹ ትምህርት ሚኒስቴር ካወጣው የስልጠናና ትምህርት ፖሊሲ ውጭ ሲሰሩና ብቃት የሌላቸውን ተማሪዎች ተቀብለው በማስተማራቸው እገዳ የተጣለባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኮሌጆቹ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች እገዳው እስከተላለፈበት ድረስ የተማሩበትን የትምህርት ማስረጃ በመያዝ  ወደ ሌላ ኮሌጅ እንዲዛወሩ መደረጉን አመልክተዋል።

በቢሮው የግል ኮሌጆች ብቃት ማረጋገጥና ማስፋፋት ባለሙያ አቶ ገብረጨርቆስ ዮሐንስ በበኩላቸው በስርዓተ ትምህርቱ መሰረት ተግባራዊ ስልጠና ሳይሰጡና ሙያ ሳያስጨብጡ ምስክር ወረቀት የሚሰጡ የግል ኮሌጆች በርካታ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

" ኮሌጆቹ አስፈላጊ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችንና ብቃት ያለው ስልጠና የሚሰጡ ባለሙያዎች በማሟላት ከማስተማር ይልቅ ተጠያቂነት የጎደለው ሥራ እየፈጸሙ መሆናቸው ተደርሶባቸዋል" ብለዋል፡፡

በክልሉ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የግል ኮሌጆች ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀሐየ ገብረ ስለጉዳዩ ተጠይቀው ሲመልሱ መመሪያና ህግ ተከትለውና መስፈርት አሟልተው የማይሰሩ ኮሌጆች መኖራቸውን አምነዋል፡፡

ማህበሩ ህግና መመሪያን ተከትለው በአግባቡ የሚሰሩ ኮሌጆችን እንደሚደግፍ ሁሉ ከህግ ውጭ የሚሰሩ የግል ኮሌጆችን እንደሚቃወም ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ኮሌጆቹ ከጥፋታቸው የሚስተካከሉበት መንገድ ካለ ሥራቸውን እንዲጀምሩ ማህበሩ ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ጋር በጋራ የሚመካከርበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም አመልክተዋል።

"ብቃት ላለው የሰው ኃይል ስልጠና የሚሰጡ ኮሌጆችም በጋራ ሆነውና ተቀናጅተው የሚሰሩበት መንገድ እንዲመቻች በማህበሩ በኩል ጥረት ይደረጋል" ብለዋል፡፡

በክልሉ በቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና የተሰማሩ 64 የግል ኮሌጆች የሚገኙ ሲሆን ኮሌጆችም ከደረጃ 1 እስከ 4 የሚሰለጥኑ ከ31 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብለው በማስተማር ላይ እንደሚገኙ የቢሮው መረጃ ያመለክታል፡፡

እገዳ የተጣለባቸውን ኮሌጆች ኢዜአ ለማነጋገር ጥረት ቢያደርግም የኮሌጆቹ ሥራ ኃላፊዎች ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሳይሳካ ቀርቷል።

በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት በትምህርት ሚኒስቴር መስፈረት መሰረት መመሪያና ደንብ ሳያሟሉ ሲሰሩ የነበሩ ሰባት የግል ኮሌጆች እንዲዘጉ መደረጉ ይታወሳል።

Published in ማህበራዊ

ሀዋሳ ሚያዚያ 6/2010 ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ያለበትን የአደረጃጀት፣ የአሰራርና ከብድር ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን የቦርዱ ሰብሳቢ ገለጹ፡፡

የተቋሙ ሰራተኞች በአዲሱ አሰራር ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ለማጎልበት የ15 ቀን ስልጠና ትናንት በሀዋሳ ተጀምሯል፡፡

ሰብሳቢው አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ ለኢዜአ እንደገለጹት የተቋሙን ያለፉት ሀያ ዓመታት አሰራር በመፈተሽ ከሰው ሀይል ስምሪት፣ ከተደራሽነት፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከቁጠባና ከብድር አመላለስ ጋር ተያይዞ የተስተዋሉ ችግሮችን በመለየት የማስተካከል ስራ ተሰርቷል፡፡

በአዲስ መልክ የተዋቀረው አደረጃጀት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ኢኮኖሚያዊ አቅም የበለጠ ለማጎልበት  እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡

''ስለዚህ ከባንኩ አላማና ተልዕኮ ጋር ሊሄዱ የሚችሉ ወጣት  ባለሙያዎችን መመደብ አንዱ ስራ አድርገን እየሰራን ነው'' ብለዋል፡፡

በተጨማሪ ክልሉ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውና ለውጪ ገበያ መቅረብ የሚችሉ ምርቶች የሚገኝበትና የአርሶ አደሩ የገቢ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመምጣቱን ያህል የሚሰበሰበው  ቁጠባ የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ  ተናግረዋል፡፡

ከብድር አመላለስ ጋር የሚታዩ ውስንነቶች ተቋሙ በክልሉ ልማት ላይ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ እያሳሳው በመሆኑ ውዝፍ ብድርን የማስመለስና ቁጠባን የማሰባሰብ ስራ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡፡

በተጨማሪ ከፍተኛ ቁጥር ያለውንና አምራች የሆነውን ወጣት ተጠቃሚ ለማድረግና በክልሉ በገጠርና በከተማ የተጀመሩ ምርታማነትን የማሳደግ ስራ ላይ ተቋሙ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት በከተማ ተወስኖ የነበረውን ተደራሽነት እስከ ቀበሌ ማውረድ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡

የተቋሙ ተወካይ ስራ አስፈጻሚ አቶ የሸዋስ አለሙ በበኩላቸው እንዳሉት ተቋሙ ባለፉት ሀያ አመታት የነበሩ ጠንካራና ደካማ ጎኖቹን ገምግሞ በተያዘው ዓመት የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎች ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ማሻሻያም የወለድ መጠንና የቅድመ ብድር ቁጠባ መጠን በማስተካከል ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱን አስታውቀዋል፡፡

ተቋሙ በክልሉ በአዲስ መልክ በዘረጋው አሰራር መሰረት ከ3 ሺህ 700 በላይ በሚሆኑ ቀበሌዎች ቅርንጫፍ በመክፈት ተደራሽነቱን ማሳደጉን ገልፀዋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሰራተኞቹ በአዲሱ አሰራር ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ለማጎልበት የ15 ቀን ስልጠና ከትናንት ጀምሮ በሀዋሳ በመስጠት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም  4 ነጥብ 8 ሚሊዮን የቁጠባና ብድር ደንበኞች ያሉት ሲሆን 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ በቁጠባ ሰብስቧል፡፡

ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ደግሞ በብድር ማሰራጨቱን ጠቁመዋል፡፡

ተቋሙ አዲስ በዘረጋው አሰራር በመታገዝ የደንበኞቹን ቁጥር ለማሳደግና አጠቃላይ ሀብቱ ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 6/2010 መንግስት የወጣቱን የተጠቃሚነት ጥያቄ ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት እንዲሳካ ወጣቱም  የሚጠበቅበትን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በነገው እለት እስከ 15ሺህ ወጣትና 10ሺህ ከሚደርሱ የተለያዩ የሰራተኛ ተወካዮች የሚሳተፉበት የትውውቅ መድረክ በሚሊኒዬም አዳራሽ ይካሄዳል።

የፌድሬሽኑ ፕሬዚዳንት ወጣት ታረቀኝ አብዱልጀባር መድረኩን አስመልክቶ ለኢዜአ እንዳስታወቀው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣቱን ጥያቄ ለመመለስ የተቀመጡ የመንግስት አቅጣጫዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ይሰጣሉ ብሎ ይጠብቃል።

ወጣቱ ከፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ እንዲሁም ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች እንዳሉት የሚገልጸው ወጣት ታረቀኝ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው ተናግሯል።

መንግስት የወጣቱንና የህዝቡን አጠቃላይ ጥያቄዎች ለመፍታት እራሱን ገምግሞ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስቴር እስከ መሰየም መድረሱ ትልቅ ለውጥ ቢሆንም የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሁሉም ቅንጅት እንደሚያስፈልግ ገልጿል።

ለወጣቱ ስራ ከመፍጠር አኳያ እስካሁን የተሄደው ርቀት ጥሩ ቢሆንም ያሉት የአፈፃፀም ችግሮች እንዲፈቱና የወጣቱን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝቧል።

'መንግስት የሚፈጥረውን የስራ እድል ብቻ ከመጠበቅ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን በመደገፍ፣ በማስተባበርና ስራ በመፍጠርም ጭምር ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ከወጣቱ ይጠበቃል' ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በነገው እለት በሚሌኒየም አዳራሽ እስከ 25 ሺህ ከሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር በሚኖራቸው የትውውቅ መድረክ በአገሪቱ መፃኢ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Published in ፖለቲካ

መቀሌ ሚያዚያ 6/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በመቀሌው የህዝብ ውይይት መድረክ ላይ በመንግስት ሊመለሱ በሚገቡ የህዝብ ጥያቄዎች ላይ በቂ ማብራሪያ መስጠታቸውን አስተያየታቸውን የሰጡ ተሳታፊዎች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመቀሌ ከተማ በነበራቸው ቆይታ ከትግራይ ክልል የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ተሳታፊዎቹ እንዳሉትም ጠቅላይ ሚንስትሩ በውይይቱ ወቅት ለተነሱ ጥያቄዎችና ሊፈቱ በሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ በቂ ማብራሪያ እንዳገኙ ተናግረዋል።

በመድረኩ የተሳተፉት አቶ ኃይለ ሓጎስ እንዳሉት

˝እሳቸው ወደ ስልጣን ከመጡበት ጀምረው የተከሰቱ ችግሮችን ሊፈቱ በሚቻልበት መልኩ  ከሕብረተሰቡ ጋር ጥሩ ውይይት እያደረጉ ናቸው፤ ከትግራይ ክልል ህዝብ ጋር መወያየታቸውና በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ከመፍጠር ባለፈ ጥሩ የልማት ዕድገት እንደሚመዘገብ ነው  የተረዳሁት ˝ ብለዋል፡፡   

የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ይሁን የልማት ጥያቄዎች በቀጥታ ከህዝቡ ለመስማትና ለመወያየት መምጣታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል ደግሞ ሰላም ገብሩ ናቸው።

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝቦች የእኩልነት፣ የፍትህና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ስራዎችን ለማጠናከር ቃል መግባታቸው የትልቅነታቸው ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላው  ተሳታፊ ወጣት ዕበ ለገሰ  እንዲሁም ወጣቱ ትውልድ ስራ ወዳድ እንዲሆን፣ ማህበራዊ  ኃላፊነቱን እንዲወጣና ለአገራዊ አንድነት ተሳትፎውን እንዲያሳድግ ጥሪ ማድረጋቸው ተገቢና ትክክል ነው ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየት ላይ ሲሆኑ በቀጣዮቹ ቀናትም ከንግዱ ማህበረሰብና ሌሎች አካላት ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።  

Published in ፖለቲካ

ወልዲያ ሚያዝያ 6/2010 በሰሜን ወሎ ዞን በጤና ተቋም መውለድ ስላለው ጠቀሜታ በተፈጠረው ግንዛቤ 23ሺህ ነፍሰ ጡር እናቶች በጤና ባለሙያ ታግዘው እንዲወልዱ መደረጉን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ። 

በመምሪያው የእናቶችና ህጻናት ጤና ባለሙያ አቶ ጀማል መሀመድ ለኢዜአ እንደገለጹት ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ ለነፍሰ ጡሮች  በሚደረግ ክብካቤ በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል።

በዚህ ዓመት በዞኑ 56ሺህ ነፍሰጡር እናቶች ይኖራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና እስካሁን 29 ሺህ ከሚሆኑ ነፍሰጡር እናቶች ጋር በተዘጋጁላቸው መድረኮች ውይይት ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

ነፍሰጡሮች በእርግዝና ወቅት ቢያንስ ለአራት ጊዜ ያህል ምርመራና ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው በተደረሰው መግባባት መሰረት 25 ሺህ ነፍሰጡሮች ከመውለዳቸው በፊት በባለሙያ እገዛ እንደተደረገላቸው አመልክተዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራትም 23ሺህ ወላድ እናቶች በጤና ተቋም በጤና ባለሙያ ታግዘው እንዲወልዱ መደረጉን አመልክተዋል። 

እንደአቶ ጀማል ገለጻ፣ እናቶች የመውለጃ ጊዜያቸው ሲደርስ ከቤታቸው ወደ ጤና ተቋማት በአምቡላንስ የሚወሰዱ ሲሆን በጤና ተቋማት የሚሰጣቸውን አገልግሎትም ለማሻሻል እየተሰራ ነው።

ከጤና ተቋማት ርቀው የሚገኙ ነፍሰጡሮችም ለመውለድ የሳምንት ጊዜ ሲቀራቸው ወደሚቀርባቸው ጤና ተቋም ሄደው በተዘጋጁላቸው ጊዜያዊ ማረፊያዎች እንዲቆዩ ይደረጋል።

ሕብረተሰቡ በጊዜያዊ ማረፊያ ለሚቆዩ ወላድ እናቶች ድጋፍ የሚውል 205 ሺህ ብር እና 347 ኩንታል ጥራጥሬ አዋጥቶ መስጠቱንም አቶ ጀማል አስታውቀዋል።

በራያ ቆቦ ወረዳ የሮቢት ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ በላይሁን አባተ በበኩላቸው እንዳሉት ተቋሙ አገልግሎት በሚሰጣቸው ሦስት ቀበሌዎች ዘንድሮ 860 ነፍሰጡር እናቶች ይኖራሉ ተብሎ ታቅዶ አስካሁን 250 እናቶች በጤና ተቋም እንዲወለዱ ተደርጓል፡፡

" በወረዳው ሁለት የመንግስት አምቡላንሶች ወላዶችን ከገጠር ቀበሌ የሚያመጡ ቢሆንም ለ45 ቀበሌ አገልግሎት የሚሰጡ በመሆናቸው አልፎ አልፎ የመዘግየት ችግር ይስተዋላል" ብለዋል። 

በቅርብ ጊዜ በወልድያ ሆስፒታል መንታ ልጆችን በቀዶ ሕክምና በሰላም መገላገላቸውን የገለጹት ደግሞ በወልድያ ከተማ የቀበሌ 05 ነዋሪ ወይዘሮ ተዋበች መኮንን ናቸው፡፡

"ፈጥነው ወደ ጤና ተቋም መሄድ ባይችሉ በሕይወታቸው ላይ አደጋ ይፈጠር እንደነበር አስታውሰው፣ በቀጣይ ሌሎች ወላድ እናቶችን በመምከር በጤና ተቋም እንዲወልዱ ለማድረግ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ዓለምነሽ ብሩ በበኩላቸው አምና የመጀመሪያ ልጃቸውን ሲወልዱ ለስምነት ሰዓት ያህል ምጥ ጠንቶባቸው አምጦ መውለድ ባለመቻላቸው በቀዶ ሕክምና ጤነኛ ልጅ በሰላም መገላገላቸውን ገልፀዋል።

በዞኑ ባለፈው በጀት ዓመት ከ39 ሺህ በላይ ነፍሰጡር እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ የተደረገ ሲሆን በዚህ ዓመትም 56 ሺህ እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ነው።

በሰሜን ወሎ ዞን የማዋለድ አገልግሎት የሚሰጡ አምስት ሆስፒታሎችና 65 ጤና ጣቢያዎች ይገኛሉ ።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ  ሚያዚያ 6/2010  የዘመናዊ ዲፕሎማሲ አንድ አካል የሆነው ስፖርት ለሰዎች አንድነት ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ገለጹ። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዝነኛውን የብራዚል እግር ኳስ ተጫዋች ሮናልዶ ዲ አሲስ ሞሬራን (ሮናልዲኒሆ ጎቾ) ዛሬ ከሰዓት በኋላ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ዶክተር ወርቅነህ እንደገለጹት ስፖርት ዘርና ሀይማኖትን ሳይለይ በሰዎች መካከል አንድነት ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት የዘመናዊ ዲፕሎማሲ አካል ነው።

ስፖርት በተለይ የእግር ኳስ ዓለምን ማህበረሰብ አንድ ያደረገ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ወርቅነህ ዝነኛውን ተጫዋች ሮናልዲንሆ ጎቾን 'የሰው ልጅ መገኛ  ወደ ሆነችዉ ኢትዮጵያ እንኳን ደህና መጣህ' በማለት የሮናልዲኒሆ አድናቂ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የጠንካራ አትሌቶች አገር የመሆኗን ያህል ብራዚልም የታዋቂ እግር ኳስ ተጫዋቾች አገር በመሆኗ ተመሳሳይነት አላቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ አበበ ቢቂላ፣ ማሞ ወልዴ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ ሀይሌ ገብረስለሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ የዲባባ ቤተሰቦች እና ሌሎች ታዋቂ አትሌቶችን  ያፈራች አገር ስትሆን፤ ብራዚልም ፔሌ፣ ሶቆራትስ፣ ዱንጋ፣ ቤቤቶ፣ ሮማሪዮ፣ ሮናልዶ፣ ኔማር በማለት በርካታ ታዋቂ እግር ኳስ ተጫዋቾችን መጥቀስ የምትችል አገር መሆኗን አውስተዋል።

ሮናልዲኒሆ ጎቾ በበኩሉ  ወደ  ኢትዮጵያ ሲመጣ  ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ጠቅሶ  ስለ አገሪቷ የበለጠ ለማወቅ እንደሚፈልግ ተናግሯል።

ኢትዮጵያውያን እግር ኳስ ተጫዋቾች በዓለም አቀፍ መድረክ እንዲታዩ ጠንክረው መስራት እንደሚገባም ገልጿል።

Published in ስፖርት
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን