አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Friday, 13 April 2018

አዲስ አበባ ሚያዝያ 5/2010 የኢትዮዽያ ቀይ መስቀል ማህበር ባለፉት አራት ዓመታት ከ 1 ሚሊዮን በላይ ለአደጋ የተጋለጡ ዜጎች መደገፉን አስታወቀ።

በማህበሩ 18ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ፕሬዘዳነት ዶክተር ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ የቀይ መስቀል ማህበር አባላት፣ሰራተኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ አካሂዷል።

የማህበሩ የበላይ ጠባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ በዚህ ጊዜ እንዳሉት ማህበሩ አቅሙን ለማሳደግ ለሚያደርገው ጥረት መንግስት ድጋፍ ያደርጋል።

ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች እየተበራከቱ በመጡበትና እርዳታ አቅራቢዎች የሚሰጡት ድጋፍ እየቀነሰ በመጣበት በአሁኑ ወቅት ማህበሩ በለውጥ ሂደት ውስጥ መሆኑ የሚያበረታታ ነውም ብለዋል ።

ይህንኑ ለማገዝም መንግስት ድጋፍ እንደሚደርግም አስታውቀዋል።

የመሀበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር አህመድ ረጃ በበኩላቸው የሰብአዊ ስራን ውጤታማ ለማድረግ ወሳኝ የህግ ማዕቀፎች በመዘጋጀታቸው ባለፉት አራት ዓመታት ስኬታማ ተግባራት መከናወኑን ተናግረዋል።

በድርቅና ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ፣ በእሳት ቃጠሎ፣ በግጭት፣ በአተት ወረርሽኝና በመሬት መደርመስ አደጋ ለደረሰባቸው ከ 1 ሚሊዮን 332 ሺ በላይ ሰዎች ከምግብና አልባሳት በተጨማሪ የእርሻ መሳሪያዎች ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል።

በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ የተጋለጡ ወገኖችን አቅም ለማጎልበት፣የተጠፋፉ ወገኖችን ማገናኘት፣ የማህበረሰቡን አደጋ የመቋቋም አቅምን ማሳደግ የማህበሩ ዋነኛ የትኩረት ማዕከሎች መሆናቸውን ዶክተር አህመድ ገልጸዋል።

በዚህም  ማህበሩ ከ 1 ሚሊዮን 24 ሺ በላይ ለሆኑ ዜጎች ድጋፍ ማድረጉን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

በአምቡላንስ አገልግሎት ፣በኤች አይ ቪ መርሐ ግብርና አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከትን (አተት) ለመከላከል ማህበሩ ባደረገው ጥረትም ከ 1 ሚሊዮን 8 መቶ ሺ በላይ ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ ማግኘታቸውንም ፕሬዘዳንቱ ገልጸዋል።

በሀገሪቱ  በተደጋጋሚ በተከሰተው ድርቅና ግጭት የድጋፍ ፈላጊዎች መብዛት ፣ከአጋር አካላት የሚለቀቀው ገንዘብ መዘግየትና የውጭ ምንዛሬ  እጥረት ማህበሩ ለተጎጂዎች በቂ ድጋፍ እንዳያደርግ እንቅፋት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በኢትዮዽያ ተወካይ ሚስተር ጀምስ ሪኖልድስ የኢትዮዽያ ቀይ መስቀል ማህበር በተለይም ከ2007 ዓ.ም በኋላ ስኬታማ ተግባራትን አከናውኗል ብለዋል።

ከ47 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች ማህበሩን በመቀላቀላቸው በ2007 ዓ.ም 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን አባላት የነበረው የኢትዮዽያ ቀይ መስቀል ማህበር በ2009 ዓ.ም የአባላቱ ቁጥር 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን መድረሱና የሰብአዊ ድጋፍ አቅሙ መጨመሩ ለስኬቱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

የአለም አቀፉ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሚስተር ሮበርት ኩፍማን በበኩላቸው የኢትዮዽያ ቀይ መስቀል ማህበር ከአደጋ ስጋት ስራ አመራር በተጨማሪ ሀብት ማሰባሰብና ማልማት የሚል አዲስ የስራ ሂደት ማዋቀሩን አድንቀዋል።

ማህበሩ አዲስ ስትራቴጂካዊ እቅድና መዋቅር ማዘጋጀቱ የሰብአዊ እርዳታ አቅሙን አሳድጎታል ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ ለማህበሩ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በ1927 ዓ.ም ሁለተኛውን የጣልያን ወረራ ተከትሎ የተመሰረተ ሲሆን ከዓንድ ዓመት በኋላም የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማህበራት ፌዴሬሽን 48ኛ አባል ሆኗል

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 5/2010 ኢትዮጵያውያን የመተሳሰብና የመደጋገፍ ባህላቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ መንግስት ጥሪ አቀረበ።

የመንግስት ኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በሳምንታዊ የአቋም መግለጫው እንዳስታወቀው፤ ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁበትን የመደጋገፍ፣ የመተሳሰብና የመተባበር ባህል አጠናክረው መቀጠል አለባቸው።

የኢትዮጵያውያን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወሰነው በማንም ሳይሆን ዛሬ ላይ ዜጎች በሚያደርጉት አስተዋጽኦ ልክ ነው።

በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ መነሻና መድረሻው የኢትዮጵያን ህዝቦች ተጠቃሚነት ማረጋገጥ  መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

በመሆኑም ኢትዮጵያውያንን በመላው ዓለም ዘንድ ልዩ የሚያደርጋቸውን የመቻቻል የመተሳሰብ፣ የመተባበር፣ እሴቶቻቸውን ጠብቀው በአንድነትና በመፈቃቀድ እጅ ለእጅ በመያያዝ ልማቱን እንዲያፋጥኑ መንግስት ጥሪ አቅርቧል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል

አገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ውስጥ ትገኛለች ። በአገራችን አስተማማኝ ሰላም፣ ዘላቂ ልማት፣ መሰረተ ሰፊ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ከመቼውም በላቀ አፈጻጸም ተግባራዊ ለማድረግ በመንግስት የተጀመረው አገራዊ የለውጥ አንቅስቃሴ በላቀ የህዝብ ተሳትፎ ለድል እንደሚበቃም መንግስት በጽኑ ያምናል።

ሰላም በሌለበት ስለልማትና ዴሞክራሲ ማስብ ይቅርና በህይወት መኖርም አጠያያቂ ነው።በመሆኑም በአገራችን ተከስተው በነበሩ ግጭቶች ሳቢያ ተፈጥሮ የነበረውን መቃቃርና ጥርጣሬ ከመሰረቱ ለማስወገድና ሰላማችንን ወደ ቀድሞው ሁኔታ ለመመለስ ይቻል ዘንድ በህዝቦች መካከል አንድነትን የሚያጠናክሩ ስራዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

በሌላ በኩል በአገራችን አስተማማኝ ሰላም ሊረጋግጥ የሚችለው ህዝቡ የሚያነሳቸው ተገቢ ጥያቄዎች ምላሽ ሲያገኙና ፍትህ ሲሰፍን መሆኑን በመገንዘብ መንግስት ከመላው ህዝቦች ጋር በመሆን አስፈላጊውን ስራ በማከናወን ላይ ነው።

ልማታችን መላውን ህዝብ ለልማቱ ባበረከተው አስተዋጽኦ ልክ ተጠቃሚ የሚያደርግ ከድህነትና ኋላቀርነት ለመላቀቅ የተያያዝነውን አገራዊ ግብ በሚያሳካ መልኩ የሚፈጸምና በፍትሀዊ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባ መንግስት ይገነዘባል።

ዴሞክራሲያችን በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ ህዝብን ያሳተፈና ባለቤት ያደረገ መሰረት ሰፊና አሳታፊ እንዲሆን በአመለካካቱ የተስተካካለና በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ የሚሰጥ ህብረተሰብ የመገንባት ስራ ዴሞክራሲን ባህል ከማድረግና ተቋማትን ከማጠናከር ጋር ተያይዞ የሚፈጸም ይሆናል።

በአጠቃላይ ለአስተማማኝ ሰላም መሰረት የሆነና ሁሉንም በየደረጃው በፍትሃዊነት ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ልማት ማረጋገጥ፤ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን፣ የህግ የበላይነትን፣ የግልጸኝነትና የተጠያቂነት ስርዓትን ለማስፈን እና የሰብዓዊ መብቶችን ጥበቃ በሚፈለገው ደረጃ ለማረጋገጥ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ለማረጋገጥ ይወዳል።

ችግሮቻችን ሁሉ የሚፈቱት ግን በመንግስት ጥረት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ህዝብ ባሳተፈ ርብርብ መሆኑን በውል መረዳት ይገባል።

በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራትና ህዝባዊ ማህበራት፣ እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍልና ዜጎች በአጠቃላይ ምልአት ህዝቡ መንግስታችን እያካሄደው ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከዳር ለማድረስ እንዲረባረቡ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።

የኢትዮጵያውያን የወደፊት እጣ ፋንታ የሚወሰነው በማንም ሳይሆን ዛሬ የገዛ ልጆቿ  በሚያደርጉት አስተዋጽኦ ልክ ብቻ ነው። ዛሬ እያካሄድነው ያለው የለውጥ እንቅስቃሴም መነሻውም ይሁን መድረሻው የኢትዮጵያን ህዝቦች የአትዮጵያን ህዝቦች ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው። በመሆኑም መላው ኢትዮጵያውያን በመላው ዓላም ዘንድ ልዩ የሚያደርጉንን የመቻቻል የመተሳሰብ እና የመተባበር እጹብ ድንቅ እሴቶቻችንን ጠብቀን በአንድነትና በመፈቃቀር እጅ ለእጅ ተያይዘን ልማታችንን እንድናፋጥን መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።

 

Published in ፖለቲካ

መቀሌ ሚያዚያ 5/2010 የአዲስቷን ኢትዮጵያ ህዳሴ ቀጣይ ለማድረግ ወጣቶች   ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን እንደሚገባቸው  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመቀሌ የሰማእታት ሀውልት አደራሽ ከህዝብ ጋር እየተወያዩ ነው፡፡

በዚሁ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ወጣቶች እንደ አባቶቻቸው  ጽናትን በመውረስ ድህነትና ኋላቀርነትን ታሪክ ለማድርግ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጣቶች የአባቶቻቸውን ፅናትና ክብር ጠብቀው አንድነታቸውን በማጠናከር ከድህነት ለመውጣት ተግተው መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል። 

"ትግራይ በሀገራችን ለውጥ ለማምጣትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት በደርግ ወቅት ለበርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከለላና ማገር በመሆን አታግለዋል" ብለዋል፡፡

ይህንን ከፍ ያለ ታሪክ ወጣቱ ትውልድ በመውረስ  አንድነቱን ማጠናከር እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውስተው  በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ችግር ማዘናቸውን ገልጸዋል።

"መንግስት ከእንግዲህ በኋላ ጥፋት  እንዳይደገም ከህዝቡ ጋር ሆኖ አስፈላጊው ጥረት ያደርጋል "ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፡፡ 

" ትግራይ የውጭ ወራሪዎች ሃፍረትን ተከናንበው የተባረሩባት የኢትዮጵያ ክፍል ናት " ብለዋል፡፡

ዶክተር አብይ አህመድ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሰየሙ ወዲህ ጂግጂጋና አምቦ  በመገኘት ዛሬ ደግሞ በመቀሌ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር  እየተወያዩ ነው፡፡

 

 

Published in ፖለቲካ

ጎንደር ሚያዚያ 5/2010 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት 28 የባዮ ጋዝ ማብላያ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የዞኑ ውሃ መስኖና ኢነርጂ ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ጌታቸው መስፍን ለኢዜአ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ 454 የባዮ ጋዝ  ማብላያ ተቋማት ለመገንባት ታቅዶ የ65ቱ ሥራቸው ተጀምሯል።

"ግንባታቸው ከተጀመሩት ማብላያዎች ውስጥ 28ቱ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል" ያሉት ኃላፊው የ37ቱ ተቋማት ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

የቀሪዎቹን የማብላያ ተቋማት ግንባታ ለማስጀመር የቦታ መረጣ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።

የማብላያ ተቋማቱ በ13 ወረዳዎች የሚገነቡ መሆናቸውን ነው የጠቆሙት።

ሀላፊው እንዳሉት የማብላያ ተቋማቱ እያንዳንዳቸው ከስድስት እስከ ስምንት ሜትር ኪዮብ የከብቶች እዳሪ ማጠራቀም የሚያስችል ጉድጓድ አላቸው። 

"የማብለያ ተቋማቱ የኤሌትሪክ አገልግሎት ባልተዳረሰባቸው የገጠር ክፍሎች በአካባቢው ቁሳቁስና በቀላል ወጪ አማራጭ የኃይል ምንጭ ለማስፋፋት ያስችላሉ" ብለዋል፡፡

"ለአንድ የባዮጋዝ ማብላያ ግንባታ 5 ሺህ ብር ይጠይቃል" ያሉት አቶ ጌታቸው፥ ለተቋማቱ ግንባታ የሚያስፈልገው ወጭ በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ እንደሚሸፈን ጠቁመዋል።

የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎቹ አርሶ አደር ማሩ ተስፋሁንና ወይዘሮ ጥሩዬ ጋሻው በሰጡት አስተያየት በማብላያ ጉድጋዱ የሚመነጨውን ኃይል በመጠቀም በቤት ውስጥ ምግብ ማብሰልና መብራት መጠቀም ጀመረዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ  ባዮ ጋዝ መጠቀም በመጀመራቸው ወጪ እንደቀነሰላቸውና በእንጨት ጭስ ምክንያት የሚያጋጥማቸው የዓይን ጉዳት እንደቀረላቸው ተናግረዋል።

በአለፋ ወረዳ የእሰይ ደብር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አይሸሹም ቸርነት በበኩላቸው ለኃይል ማመንጫነት የዋለውን ተረፈ ምርት፥ በማሳቸው ውስጥ በመጨመር ለምርት ማሳደጊያነት በመጠቀማቸው ለማዳበሪያ ግዥ የሚያወጡት ወጭ እንደቀነሰላቸው ገልፀዋል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባለፉት አራት ዓመታት ከ800 በላይ አርሶ አደሮች የባዮ ጋዝ ኃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

 

አዲስ አበባ ሚያዝያ 5/2010 በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት 10 ወራት ከ60 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የስራ እድል መፈጠሩን የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው እየተገባደደ ባለው የ2010 በጀት ዓመት ለ100 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

በቢሮው የወጣቶች ማብቃትና ተጠቃሚነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ አሻግሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በመደበኛ ብድር፣ በተዘዋዋሪ የብድር ፈንድና ቀጥተኛ የስራ ትስስር በመፍጠር ለከተማዋ ነዋሪ ዜጎች የስራ እድል እየተፈጠረ ነው።

በተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ 5 ሺህ 140 ወጣቶች 140 ሚሊዮን ብር ብድር ወስደው በማኑፋክቸሪንግ፣ በከተማ ግብርናና በሌሎች የተለያዩ የሙያ ዘርፎች ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቁመዋል።

በመደበኛ ብድር 11 ሺህ የሚጠጉ ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

ከ46 ሺህ በላይ የከተማዋ ዜጎች ደግሞ ቀጥተኛ የስራ ትስስር በሚባለውና ብዙም የገንዝብ ብድር በማይጠየቅበት በውሃ ልማት፣ በጽዳትና በሌሎች መሰል ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ መደረጉን አቶ መንግስቱ አመልክተዋል።

ቢሮው ከተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ በማዋል በቀሪዎቹ  ወራት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የቢሮው የስድስት  ወራት አፈጻጸም  ሲገመገም 40 ሚሊዮን ብር ብቻ ለወጣቶች መሰጠቱ በድክመት እንደተገመገመ ያስታወሱት አቶ መንግስቱ  የነበሩ አላስፈላጊ ውጣውረዶችንና ተያያዠ ችግሮችን በመፍታት ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ 100 ሚሊየን ብር ከተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ ለወጣቶች በመስጠት በተሻለ መልኩ የስራ ዕድል ሊፈጠር መቻሉን አስረድተዋል።

የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በማዘጋጀት ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ከተጀመረበት ከባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ጀምሮ ለወጣቶች በተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ ከተሰጠው 140 ሚሊዮን ብር ውስጥ  2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ብድር እንዲመለስ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ሚዛን ሚያዝያ 5/2010 ቤንች ማጂ ዞን የመኤኒት ብሄረሰብ ባህላዊ ምግብ የሆነውን የካቲላ ተክል በዘመናዊ መንገድ  ለማልማት  የሚያስችል ስራ እንደሚከናወን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በብሔረሰቡ ''ካቲላ'' የሚል ስያሜ የተሰጠውና በሳይንሳዊ መጠሪያው ደግሞ ''አማረንተስ'' የተሰኘው ይኸው ተክል በዓለማችን የተለያዩ ሀገራት ለምግብነት እንደሚያገለግል መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎችም ተክሉ የሚታወቅ ቢሆንም በመኤኒት ብሔረሰብ ዘንድ ልዩ ቦታ የሚሰጠውና ከብሔረሰቡ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ባህላዊ ምግባቸው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተክሉን ለማስተዋወቅ በቤንቺ ማጂ ዞን በሜኒኢት ጎልዲያ ወረዳ የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሙስጠፋ አብዱል ሰመድ ''ተክሉ ካለው ምርታማነት፣ ገንቢነትና ተስማሚነት አንጻር በዘመናዊ አመራረት ሊሰራ ይገባል'' ብለዋል፡፡

''በዓመት ሁለት ጊዜ የሚመረት በመሆኑ የምግብ ዋትናን ለማረጋገጥ ያስችላል'' ያሉት አቶ ሙስጠፋ፤ ካቲላ በፕሮቲን ይዘቱም የተሻለ በመሆኑ ለሰው ልጅ የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ተክሉን በብዛት በማምረትም ወደሌሎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች የማስተዋወቅና የማላመድ ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የመኤኒት ጎልዲያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተካ ነጋሽ በበኩላቸው ''የካቲላ ተክል ለመኤኒት ብሔረሰብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያሉትና  የችግር ጊዜ ዋስትና ነው'' ብለዋል፡፡

የመኤኒት ብሔረሰብ የካቲላ ተክልን ከምግብነት ባሻገር ለመድኃኒትነት እንደሚጠቀመው ገልጸው ሦስት ዓይነት የካቲላ ዝርያ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡

 የአመራረት ዘዴ በመቀየር ራሱን ችሎና የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ተጠቅሞ በመዝራት አርሶ አደደሩን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በመኤኒት ጎልዲያ ወረዳ የጫት ቀበሌ አርሶ አደር ዘለቀ ዘውዴ በበኩላቸው ካቲላን ከሌሎች ሰብሎች ጋር አብሮ በመዝራት በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚያመርቱ ገልጸዋል፡፡

ካቲላ በቀላሉ የሚመረት፤ በትንሽ ቦታ ብዙ ምርት የሚያስገኝና ከምግብነት ባለፈም ለመድኃኒትነት እንደሚያውት ተናግረዋል፡፡

በበለጠ በማምረት ተጠቃሚ ለመሆን መዘጋጀታቸውን ገልጸው መንግስት እንደሌሎች የግብርና ውጤቶች ሁሉ በዕቅድ አካቶ ቢሰራ የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ጠቁመዋል፡፡

በወሊድ ጊዜ  የተጎዳ ሰውነታቸውን ለመጠገን ተክሉን እንደሚጠቀሙ የገለፁት ደግሞ ሌላኛዋ የቀበሌዋ ነዋሪ ወይዘሮ ሞካ ቱርሳ ናቸው፡፡

ካቲላን የተመገበ ህፃንም እንደሚፋፋም ያላቸውን ልምድ በመጥቀስ ገልፀዋል፡፡

በብሄረሰቡ ዘንድ ተወዳጅ የሆነው ካቲላ ቤንቺ ማጂ፣ ካፋና ደቡብ ኦሞ ዞኖች የተለመደ ነው፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 5/2010 ለበልግና ለመጪው የመኸር እርሻ የሚውል ከ7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እያሰራጨ መሆኑን የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ባለፈው ዓመት ተከስቶ የነበረውን   የአሜሪካ መጤ ተምች ለመከላከልም የቅድመ ዝግጅት ስራ እየሰራ መሆኑን ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ጠቁሟል።

በእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር የእርሻ ዘርፍ ሚንስተር ደኤታ ተስፋዬ መንግስቴ እንደተናገሩት "ምርትና ምርታማነትን የበለጠ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል"።

ለዚህም በአጠቃላይ በዚህ ዓመት ከሚያስፈልገው 15 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ የ13 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት ግዥው ከተፈጸመው ማዳበሪያ  5 ሚሊዮን እንዲሁም ባለፈው ዓመት ከተረፈው 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በድምሩ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ በሁሉም ክልሎች የማሰራጨት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

ግዥ ተፈጽሞ ወደ አገር ውስጥ ያልገባ ማዳበሪያ በፍጥነት ለማስገባት የማጓጓዝ ስራው በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝም ሚንስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ባለፈው ዓመት በሰብሎች ላይ ተከስቶ የነበረው የአሜሪካ መጤ ተምች እንዳይከሰት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝም አክለዋል።

ባለፈው ዓመት መጤ ተመቹ በ 646 ሺህ 731  ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን የገለጹት ሚንስትር ዴኤታው በዚህ ዓመት ይህ እንዳይሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አጠቃላይ ከነበረው የበቆሎ ምርት ውስጥ 21 በመቶ የሚሆነው በዚህ ተምች መጎዳቱን በማስታወስ።

ዘንድሮ ተምቹ ተመሳሳይ ጉዳት እንዳያደርስ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሰራታቸውንና በተለይም ባለፈው ዓመት የመከላከል ስራው ተደራሽ ባልነበሩ የአፋር፤ ሶማሌና ቤንሻንጉል አካባቢዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ነው በመግለጫቸው የጠቆሙት።

ባለፈው ዓመት ተምቹን ለመካለከል በባህላዊና በዘመናዊ መንገድ ኬሚካልን በመጠቀም የመከላከል ስራዎች መሰራታቸውን አስታውሰዋል።

በተለይም በባህላዊ መንገድ ተምቹን በእጅ ለቅሞ ለማስወገድ የተሰራው ስራ ውጤታማ እንደነበር የገለጹት አቶ ተስፋዬ አሁንም ችግሩ ከተከሰተ ይህ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

በዚህ መንገድ የማይቻልና ከአቅም በላይ ከሆነ ብቻ መጤ ተምቹን ለመካለከል በኬሚካል የማጥፋት ዘዴን እንጠቀማለን ብለዋል።

በእጅ በመልቀም ተምቹን ማስወገድ "ለኬሚካል ግዥ የሚወጣን ወጭ ከማስቀረቱ ባሻገር ሰብሉ እንዳይጎዳም ትልቅ ጠቀሜታ ስላለው ተመራጭ ያደርገዋል" ነው ያሉት።

ለዚህም በክልሎች ከአርሶ አደሩ ጋር ውይይት የማድረግና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስትም ችግሩ ቢከሰት ለመከላከል በሚል የኬሚካልና የመርጫ መሳሪያዎች ግዥ በማከናወን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ 5/2010 የምስራቅ አፍሪካ ልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) በደቡብ ሱዳን ሠላም ሥምምነት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያየ።

ውይይቱ ባሳለፍነው ማክሰኞ የደቡብ ሱዳን የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የደቡብ ሱዳን የኢጋድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ኢስማኤል ዋይስ ከኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀመንበር ተወካዮች ጋር በመሆን ውይይቱን መርተውታል።

ውይይቱ በደቡብ ሱዳን ፓርቲዎች ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች፣ ስለ አስተዳደራዊና የደህንነት አወቃቀርና የሽግግር መንግሥት ስብጥር ላይ ትኩረት አድርጎ ቆይቷል።

ጎን ለጎንም የመንግሥት መዋቅር፣ የኃላፊነት መጋራት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ ብዛትና ስብጥር ዙሪያ በመወያየት ምክረ ኃሳቦች ቀርበው ስብሰባው ተጠናቋል።

በምክረ ኃሳቡ የሽግግር መንግሥቱ ስብጥር የሰላም ስምምነት ማሳለጫ ባለድርሻ አካላትን ታሳታፊ እንዲያደርግ ኢጋድ አቅጣጫ አስቀምጧል።

በሌላ በኩል በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት ትክክለኛ ቁጥጥርና ተጠያቂነት እንዲኖራቸዉ በሚያስችሉና በሌሎች ተዛማች ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ኢጋድ ለደቡብ ሱዳን ሠላም ሂደት የማደረደር ጥረት በአዲስ አበባ እየተደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ ገልጿል።

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 5/2010 በአገር አቀፍ ደረጃ በ2010 ዓ.ም የመኸር ወቅት ከ300 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት መሰብሰቡን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ምርቱ የተሰበሰበው በአነስተኛ የግል ገበሬዎች ታርሶ በምግብ ሰብሎች ከተሸፈነ ከ 12 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ መሆኑም ተገልጿል።

ኤጀንሲው የመኸር ምርት መሰብሰቡን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በኤጀንሲው የስታስቲክስ ጥናቶችና ቆጠራዎች ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አማረ ለገሰ እንዳሉት፤ ምርቱ የተሰበሰበው ከአገዳ፣ብርዕ፣የጥራጥሬ፣የቅባት እህሎች፣ በአትክልት፣ ስራ-ስርና እንሰትን ጨምሮ ጊዜያዊና ቋሚ ሰብሎች ነው ፡፡

ይህም ደግሞ ከአነስተኛ የግል ገበሬዎች የተገኘው የምርት መጠን ከአምናው የመኸር ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ 5 ነጥብ 42 በመቶ ወይም 15 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ጭማሪ አሳይቷል።

ከምግብ ሰብሎች ከፍተኛ ጭማሪ የታየው ደግሞ በጥራጥሬ ሰብሎች ሲሆን ለአብነትም ጤፍ፣ስንዴ፣በቆሎ፣ዳጉሳና ሩዝ ሲሆኑ ይህም ወደ 5 ነጥብ 83 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ምክትል ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

በዘንድሮው የመኸር ወቅት እንዲሁ የብርዕና አገዳ ሰብሎች ምርት ከአምናው ጋር ሲወዳደር 5 ነጥብ 49 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም ዘንድሮ የተገኘው የቅባት ሰብሎች ምርት አምና ከተገኘው ምርት ጋር ሲነጻጸር የ1 ነጥብ 89 ጭማሪ አለው ብለዋል።

ባለፈው አመት በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች የዘነበው ዝናብ በቂ በመሆኑና አርሶ አደሮች በመስመርና በመስኖ የማልማት ባህላቸው ማደጉ ለምርቱ መጨመር ምክንያት እንደሆነም ምክትል ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

የኤጀንሲው የግብርና፣ የተፈጥሮ ሃብትና ከባቢ ስታስቲክስ ዳይሬክተር አቶ ሃበክርስቶስ በየነ እንዳሉት "በኦሮሚያ ክልል በሰብል የተሸፈኑ ማሳዎች የመሬት ስፋት በጂፒኤስ በተገኘ መረጃ የተሰበሰበ ሲሆን በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ ሜትርና ኮምፓስን በመጠቀም የማሳ ልኬቱ ተግባራዊ ሆኗል።"

የ2010 ዓ.ም የመኸር ሰብል ምርት ግምት በመኸር ወቅት ከአነስተኛ የግል ገበሬዎች ብቻ የተገኘ መረጃ ሲሆን  የበልግ ወቅት እርሻን፣የሰፋፊና መካከለኛ ንግድ እርሻዎችን የሚመለከቱ መረጃዎችን እንደማያካትትም ተገልጿል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 5/2010 በእርግዝና ወቅት በፎሊክ አሲድ እጥረት በህፃናት ላይ የሚከሰተውን የአንጎል ህብለሰረሰር መጎዳት (ስፒና ቢፊዳ) ለመከላከል የጤና ባለሙያዎችና ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ ማግኘት እንደሚገባቸው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለፀ።

በሚኒስቴሩ የሚኒስትር ዴኤታ ጽህፈት ቤት ኃላፊና አማካሪ ዶክተር ዳንኤል ገብረሚካኤል እንደገለፁት፤ በፎሊክ አሲድ እጥረት ምክንያት ተጎድተው የሚወለዱ ህጻናትን ቁጥር ለመቀነስ የጤና ባለሙያዎችና እናቶች ስለ በሽታው በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል።

በመውለድ እድሜ ላይ የሚገኙና ነፍሰ ጡር ሴቶች ወደ ጤና ተቋማት በሚሄዱበት ጊዜ የፎሊክ አሲድን መውሰድና የጤና ባለሙያዎች የሚሰጧቸውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ችግሩን ለመከላከል በጤና ኤክስቴሽን ባለሙያዎች አማካኝነት ለህብረተሰቡ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን በመስጠትና እናቶች ጤናማ አመጋገብ እንዲኖራቸው በማስተማር በኩል ሰፊ ሥራ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የጤና ባለሙያዎችና ህብረተሰቡ በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ዶክተር ዳንኤል ገልጸዋል።

የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ዳሬክተር  አቶ ያዕቆብ ሰማን በበኩላቸው በፎሊክ አሲድ እጥረት ምክንያት በህጻናት ላይ የሚከሰተውን በሽታ ቀድሞ ለመከላከል ሆስፒታሉ ከሁለት ዓመት በፊት ህክምናውን መስጠት መጀመሩን አስታውሰዋል።

ከ15 እስከ 49 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ፎሊክ አሲድንና በፎሊክ አሲድ የበለጸጉ ምግቦችን በመውሰድ በሽታውን መከላከል እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር በመሆን በፎሊክ አሲድ እጥረት ምክንያት በህፃናት ላይ የሚከሰተውን በሸታ ለመከላከል የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ለጤና ባለሙያዎች ሰጥቷል።

በውሃ የሚሟሟውና ቫይታሚን ቢ9 በመባል የሚታወቀው የፎሊክ አሲድ ንጥረ ነገር የሰው ልጆች ሰውነት ጤናማና አዲስ ህዋስ ለመስራት የሚጠቅም ነው።

ፎሊክ አሲድ በበቂ መጠን ያላገኙ ነፍሰ ጡር እናቶች የሚወልዷቸው ልጆች ስፒና ቢፊዳ በተባለ የነርቭ እክል ከተጠቁ ያልተለመደ እብጠት በጀርባቸውና አንገታቸው ላይ ይከሰታል።

በዓለም ላይ ከሚወለዱ 1 ሺህ ህጻናት መካከል ከ2 እስከ 3 የሚደርሱ ህፃናት ከዚህ ጉዳት ጋር አብረው ይወለዳሉ።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገሮች ቁጥሩ ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 5

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን