አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Thursday, 12 April 2018

አዲስ አበባ ሚያዝያ 4/2010 የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘናዎችን በአዲስ ቴክኖሎጂ መስጠት ሊጀምር መሆኑን የአዲስ አበባ የሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ማእከል አስታወቀ።

 ምዘናው የሚጀምረው ከደረጃ 3 እስከ ደረጃ 5 ባሉ የቢዝነስ ፣ጤና ዘርፍ እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት የሰለጠኑ ተመራቂዎችን እንደሆነ ማዕከሉ አስታውቋል።

 ማእከሉ 'ኮምፒዩተራይዝድ' የብቃት ማረጋገጫ የምዘና ፈተና ስርዓትን አስመልክቶ  ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

 የማእከሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ግደይ ህሼ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት "ከዚህ በፊት ይሰጥ የነበረው ምዘና ኋላ ቀር በመሆኑ ለተለያዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች የተጋለጠ ከመሆኑም ባሻገር ተመዛኞች በቀላሉ ፈተናውን የሚያልፉበት ህገ-ወጥ አሰራርና ልማድ የተንሰራፋበት ነበር።"

 በተለይም በሴት ተማሪዎች ላይ ጾታን መሰረት ያደረገ ትንኮሳ፣የመመዘኛ ፈተናዎች ስርቆት፣ ከመመሪያ ውጪ በሆነ መልኩ ምዘናው ላይ ያተኮረ ስልጠና መስጠት፣የምዘና ውጤት መቀየርና የውጤት መዘግየት ችግሮች የሚታይበት የምዘና ስርዓት እንደነበር አንስተዋል።

 የአዲሱ ዘመናዊ የምዘና ስርዓት ከሰዎች ንክኪ ነጻ መሆኑ ችግሩን ከማስቀረቱ ባለፈ ብቁ ሙያተኞችን ለማፍራት እንደሚያግዝ አቶ ግደይ ተናግረዋል።

 በማእከሉ የሙያ ብቃት ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ ጅላሉ አብደላ በበኩላቸው አሰራሩ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት  በትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ አማራና በአዲስ አበባ በሚገኙ ተመዛኞች አሰራሩ የተተገበሩ ሲሆን "ውጤቱም አመርቂ ሆኗል" ሲሉ ተናግረዋል።

 በተጨማሪም የምዘና ፈተናውን ከመጀመራቸው በፊት የሙከራ ጊዜ የሚሰጣቸው በመሆኑ ተመዛኞች ለፈተናው ይበልጥ ዝግጁ እንዲሆኑ ያስችላቸዋልም ብለዋል።

 ዘመናዊ የምዘና አሰራሩ በፊት በነበረው የምዘና ስርዓት የነበሩ አላስፈላጊ ድርጊቶችን ከማስቀረቱም ባሻገር ተመዛኞች ውጤታቸውን እዚያው የሚያውቁበት ቀልጣፋ የምዘና ስርዓት መፍጠሩን ገልጸዋል።

 አዲሱ የሙያ ብቃት ምዘና የፊታችን ቅዳሜ በከተማዋ ባሉ በሁሉም የመመዘኛ ማእከላት የሚጀመር ይሆናል።

 በአዲስ አበባ ከዋናው የብቃት መመዘኛ ማእከል በተጨማሪ በከተማዋ በአራቱም አቅጣጫ አራት የመመዘኛ  ማእከላት ተቋቁመው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። 

 

 

 

 

Published in ማህበራዊ

ባህር ዳር ሚያዝያ 4/2010 የትዳር አጋሮቻቸው በተለያየ ምክንያት ቢለዩአቸውም ጠንክረው በመስራት ሃብት ማፍራት የቻሉ ሶስት የምግብ ዋስትና እመቤቶች ዛሬ በአማራ ክልል ደረጃ ተሸለሙ፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መልኬ ታደሰ በሽልማት ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለፁት የምግብ ዋስትና በቤተሰብ ደረጃ እንዲረጋገጥ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

ለሴቶች ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግና የግብርና ኤክስቴንሽን ስርዓቱን በማስፋፋት እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱንም ጠቁመዋል።

የትዳር አጋሮቻቸው በፍችና በሞት የተለዩአቸው በርካታ ሴቶችም ቤተሰባቸውን ሳይበትኑ የምግብ ዋስትናቸውን በማረጋገጥ ልጆቻቸውን እያሳደጉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

የእለቱ ተሸላሚዎችም የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ከ542 ሺህ እስከ 814 ሺህ ብር ሃብት ያፈሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ጠንክረው በመስራታቸው ለውጤት ለበቁ የምግብ ዋስትና እመቤቶች የተሰጠው ዕውቅናና ሽልማትም ሌሎችን ሴት አርሶ አደሮች ለማነሳሳት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

በግብርና ልማቱ የምግብ ዋስትና እመቤቶች ስኬት የተገኘውን ልምድና ተሞክሮ በመቀመር ወደሌሎች ሴት አርሶ አደሮች በቀጣይ ለማስፋፋት ቢሮው በትኩረት እየሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ዘላቂነት ያለው የአካባቢ ልማት ትግበራ /ሴዳ/ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግርማ ዳሉ በበኩላቸው የምግብ ዋስትና እመቤቶች ፕሮግራም በእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር፣ በኦክስፋም እና በሴዳ የጋራ ትብብር ላለፉት አምስት ዓመታት እየተተገበረ ይገኛል።

''የትዳር አጋራቸውን በተለያየ ምክንያት ያጡ ሴቶች ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ለውጤት እንዲበቁ በተደረገው ጥረት ላለፉት አራት አመታት በአገር አቀፍ ደረጃ 90 የሚጠጉ የምግብ ዋስትና እመቤቶችን ማስመረቅ ተችሏል''ብለዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በክልል ደረጃ ዛሬ በተካሄደ ስነስርዓት ለሽልማት የበቁት ሦስት የምግብ ዋስትና እመቤቶች ከ10 ሺህ እስከ 20 ሺህ ብርና ዋንጫ፣ የሜዳሊያና የምስክር ወረቀት ሽልማት እንደተበረከተላቸው ተናግረዋል፡፡

ከተሸለሚዎች መካከል ከደቡብ ወሎ ዞን ወግዲ ወረዳ 029 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ኑራ ሁሴን እንደገለጹት ''በአካባቢው በተፈጠረው ድርቅ ባለቤቴ ጥሎኝ ቢሄድም ጠንክሬ በመስራት ሦስት ልጆቼን ማሳደግ ችያለሁ'' ብለዋል።

ከእርሻ ስራቸው በተጓዳኝም በናፍጣ የሚሰራ የእህል ወፍጮ በአካባቢያቸው በመትከል ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ያስቻላቸው ሲሆን አጠቃላይ ሃብታቸውንም 809 ሺህ ብር በማድረስ ለሽልማት መብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከአዊ ዞን ጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ እናትአየሁ አበዛ በበኩላቸው ''ከ10 ዓመት በፊት ባለቤቴ በሞት ቢለየኝም የግብርና ስራየን ሌት ተቀን በመስራት ዘጠኝ ልጆቼን ያለምንም ችግር ማሳደግ ችያለሁ''ብለዋል።

ያላቸውን አንድ ሄክታር ከሩብ መሬታቸውን ገበያ ተኮር በሆኑ የቢራ ገብስ፣ ድንችና ሌሎች ሰብሎችን በማልማት በዓመት እስከ 50 ኩንታል ምርት እንደሚያገኙም ገልጸዋል።

በራሳቸው ጥረት ባከናወኑት ስራም የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ከ814 ሺህ ብር በላይ ሃብት ማፍራት እንደቻሉም አስረድተዋል።

ባለቤታቸው በ1998 ዓ.ም በሞት ቢለዩዋቸውም ያላቸውን ሶስት ሄክታር መሬት በማልማት በዓመት እስከ 70 ኩንታል ምርት በማምረት ስምንት ቤተሰባቸውን ያለምንም ችግር ከማስተዳደር ባለፈ ሃብት ማፍራታቸውን የተናገሩት ደግሞ ከምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ ተሸላሚ ወይዘሮ ንፁህ ወርቁ ናቸው።

በጥረታቸው ያገኙት የገንዘብ፣ የዋንጫ፣ የሜዳሊያና የምስክር ወረቀት ሽልማትም በቀጣይ ጠንክረው በመስራት የተሻለ ደረጃ ለመድረስ ይበልጥ እንዲነሳሱ እንደሚያስችላቸው አስረድተዋል።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 4/2010 የሶዶ-ተርጫ-ኦሞ ወንዝን የጠጠር መንገድ ወደ አስፋልት ደረጃ የማሳደግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ገለፀ።

 በደቡብ ክልል የሚገኘውን የ159 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ አስፋልት ለማድረግ ከ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ተበጅቶለታል።

 የመንገድ ፕሮጀክቱ በሁለት ኮንትራት ተከፋፍሎ እየተካሄደ ሲሆን የሶዶ-ተርጫ የ75 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር መንገድ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ ተገልጿል።

 የመንገዱን ግንባታ ሁናን ሁንዳ የመንገድና የድልድይ ኮርፖሬሽን ዓለም አቀፍ የቻይና ስራ ተቋራጭ፣ የማማከርና የቁጥጥር ሥራውን ደግሞ ኤ.ኢ.ሲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል አማካሪ ድርጅት ይከውኑታል።

 ለስራው የ3 ዓመት ከ5 ወር የጊዜ ገደብ የተቀመጠ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ40 ኪሎ ሜትር በላይ ተከናውኗል። አጠቃላይ ግንባታው በአውሮፓዊያኑ 2018 መጨረሻ ወር እንደሚጠናቀቅም ይጠበቃል።

 ይህን መንገድ በአዲስ መልክ ለመገንባት ያስፈለገው የግልገል ጊቤ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ተጠናቆ ወደ ትግበራ በመግባቱ ቀድሞ በጠጠር መንገድ ደረጃ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው መንገድ በውሃ በመሸፈኑ ነው።

 ሁለተኛውን የሶዶ-ተርጫ /ኦሞ-ተርጫ/ የ83 ኪሎ ሜትር የመንገድ ፕሮጀክት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታውን በማካሔድ ላይ የሚገኘው የቻይና ሬል ዌይ ሰባተኛ ግሩፕ ዓለም አቀፍ የሥራ ተቋራጭ ነው።

 በሌላ በኩል የሚዛን-ዲማ-ቦማ የመንገድ ፕሮጀክት አካል የሆነው ኮንትራት 1 ሚዛን-ዲማ 91 ነጥብ 59 ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ባለስልጣኑ አስታውቋል።

 የመንገዱ ግንባታ የኢትዮጵያ መንግስት በቀረጸው የአራተኛው ዘርፍ ልማት ፕሮግራም የተካተተው የሚዛን-ዲማ ፕሮጀክት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተከናወነ ነው።

 በጠጠር ደረጃ የነበረው መንገዱ በአስፋልት ኮንክሪት በመገንባት ላይ ሲሆን 73 ኪሎ ሜትር ወይም ከ80 በመቶ በላይ ስራው መጠናቀቁን የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ለኢዜአ ገልጿል።

 የመንገድ ፕሮጀክቱ ደቡብና ጋምቤላ ክልሎችን እንዲሁም ኢትዮጵያን ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ   ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆንም አብራርቷል።

 

 

 

 

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 4/2010 በገንዘብና ፋይናንስ ነክ ጉዳዮች ላይ ያተኮረው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ ውይይት ዛሬ ተጀምሯል።

በገንዘብ ነክና ፋይናንስ እንዲሁም በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ዕቅድና ማካተት ላይ ያተኮረው ውይይት በኤክስፐርቶች ደረጃ ነው የሚካሄደው።

ውይይቱ ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን በመጪው ሰኞና ማክሰኞም በሚኒስትሮች ደረጃ ይካሄዳል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ቪክቶር ሄርሰን እንደተናገሩት የአህጉሪቷን ሀብቶች ማንቀሳቀስ፣ ሙስናን መዋጋት፣ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን መከላከልና የአፍሪካ የጋራ መገበያያ ገንዘብ ዝግጅት ውይይቱ በዋናነት ያተኮረባቸው ጉዳዮች ናቸው።

የህጻናት፣ የአካል ጉዳተኞችና አረጋዊያንን ድጋፎች በተመለከተ፣ የስራ እድል ፈጠራ ፈንድ፣ የ9ኛው የአፍሪካ ኅብረት ንዑስ ኮሚቴ የጉምሩክ ዳይሬክተር ጄነራሎች ውይይት ውጤትም ተጨማሪ አጀንዳዎች ናቸው።

በአፍሪካ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ብቻ ለመሰረተ ልማት ግንባታዎችና እድሳቶች እስከ 170 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

በመሆኑም የአፍሪካን እምቅ ሀብት በማንቀሳቀስ በውጭ አገራት ድጋፍና እርዳታ ላይ ያለውን የጥገኝነት ችግር ለመቅረፍ መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል ኮሚሽነሩ።

በአፍሪካ በየዓመቱ 50 ቢሊዮን ዶላር በህገ ወጥ መንገድ እንደሚዘዋወርም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለውን ሙስናን ለመዋጋት ብዙ ስራዎች ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል።

ለውይይቱ አስፈላጊ የሆኑ ጥናቶችና ዶክመንቶች ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው በቀጣዩ ሳምንት በሚኒስትሮች ደረጃ ለሚካሄደው ውይይት ጠቃሚ አስተያየቶችና ግብዓቶች ይገኙበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 4/2010 በኢትዮጵያ የደን ልማት ስራ በሳይንሳዊ መንገድ እየተካሄደ አለመሆኑን የዘርፉ ምሁራን ተናገሩ።

የኢትዮጵያ የደን ባለሙያዎች ማህበር 5ኛ ጉባኤውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ሲሆን በሀገሪቱ እየተከናወነ የሚገኘው የደን ልማት ስራ በአብዛኛው በጥናት ላይ የተመሰረተ አለመሆኑን በመድረኩ ይፋ አድርጓል።

የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ አለሙ ገዛኸኝ እንደተናገሩት በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ቢተከሉም የአካባቢ ተስማሚነት ጥናት ባለመካሄዱና ክትትልና ጥበቃ ስለማይደረግላቸው አብዛኞቹ ሳይፀድቁ ቀርተዋል።

ማህበሩ ችግሩን ለመቀነስ ከአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገርና ጥናቶችን በማካሄድ ሳይንሳዊ የደን ልማት አካሄዶችን ተግባር ላይ ለማዋል እየሰራ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።

የደን ልማት ባለሙያዉ ዶክተር ሙሉጌታ ልመንህ እንዳሉት በኢትዮጵያ ደን የሚገኝባቸው አካባቢዎች እየተመናመኑ በመምጣታቸው አለም አቀፍ በሆኑ የዘርፉ ሳይንሳዊ መመዘኛዎች ደን አለ ብሎ ለመናገር ያስቸግራል ።

ኢትዮጵያ ደን ማልማት የሚያስችል ምቹ መልክአ ምድር ቢኖራትም የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ከመሳሰሉ ለደን ልማት ምቹ ካልሆኑ ሀገራት ሳይቀር የደን ውጤቶችን በከፍተኛ ወጭ ወደ ሀገር ውስጥ እንደምታስገባም ተናግረዋል።

የደን ሀብት የሀገርን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ትልቅ አቅም ቢኖረውም በኢትዮዽያ ያለው ድርሻ ከአራት በመቶ በታች መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  የደን ልማት ባለሙያው ዶክተር ተፈራ መንግስቱ ናቸው።

በቂ የደን ዘር አለመኖር ፣ ለደን ልማት ተስማሚነት ጥናት አለመደረግ ፣ በሳይንስ ያልተደገፈ የችግኝ ተከላና  የደን ባለቤትነት መብት ጉዳይ በሀገሪቱ ደን በከፍተኛ መጠን እንዳይለማ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

መንግስት ለደን ልማት የሚመድበው በጀት አነስተኛ በመሆኑ ቢስተካከል ፣የግል ባለሀብቶች በደን ልማት እንዲሰማሩ ቢደረግ እንዲሁም ከችግኝ ተከላ በኋላ ጠበቅ ያለ የደን ጥበቃ እንዲኖር ባለሙያዎቹ በመፍትሔነት አስቀምጠዋል።

የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዶክተር ገመዱ ዳሌ በበኩላቸው በኢትዮዽያ አሁን ያለውን የ15 ነጥብ 5 በመቶ የደን ሽፋን ለማሳደግ አዋጅ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

የደን ልማት ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ 1065 ደን ከመልማቱ አስቀድሞ የባለቤትነት መብት፣ የሚለማው ደን በአካባቢው የሚኖረው ተስማሚነትና ጠቀሜታ እንዲሁም በመደበኛነት ክትትልና እንክብካቤ የሚያደርግ አካል እንዲኖር ያስገድዳል ብለዋል።

የሚለሙት ደኖች ከሚኖራቸው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በላይ የአካባቢ መራቆትን የሚያስቀሩ፣ በረሃማነት እንዳይስፋፋ የሚያደርጉ ፣  የስርዓተ ምህዳርን ጤንነትን የሚጠብቁና ከውጭ ሀገር የሚገቡ የደን ውጤቶችን የሚተኩ እንዲሆኑ በፀደቀው አዋጅ መካተቱን ሚንስትሩ ገልፀዋል።

ከምንም በላይ ደን ሲለማ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚና አሳታፊ በማድረግም የሀገሪቱን የደን ሽፋን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።

 

 

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 4/2010 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቅጥር ግቢ የሚገኘው የአፍሪካ አዳራሽ እድሳት ሊደረግለት መሆኑ ተገለጸ።

አዳራሹ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፤ የአፍሪካን ባህል፣ ታሪክና የኪነ ህንጻ ጥበብን ባማከለ መልኩ የተገነባ ነው።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቀው፤ እድሳቱ ያስፈለገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያሉትን ተቋማት ለማዘመን በያዘው እንቅስቃሴ መሰረት ነው።

እድሳቱንም ኮሚሽኑ ከአፍሪካ ህብረት፣ ከኢትዮጵያ መንግስትና ከዓለም አቀፉ የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም ዩኔስኮ ጋር በመተባበር እንደሚያስፈፅመው ነው የተገለጸው።

የእድሳት ፕሮጀክቱ ስምምነትም በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል እንደሚደረግም በመግለጫው ተብራርቷል።

ዓለም አቀፍ የስብሰባ አዳራሽ መስፈርትን ባሟላ መልኩ እድሳቱ የሚከናወን ሲሆን፤ እድሳቱ በአዳራሹ የሚገኙና የአፍሪካን ባህላዊና ታሪካዊ ሁነቶችን የሚያሳዩ ንድፎች ይዞታቸውን እንዳይቀይሩ በጥንቃቄ እንደሚከናወን በመግለጫው ተመላከቷል።

የአዳራሹ መታደስም እነዚህን ታሪካዊ ንድፎች ይበልጥ ለቱሪስት መስህብ ግልጽ እንደሚያደርጋቸውም መግለጫው አትቷል።

በተጨማሪም ቋሚ የኤግዚቢሽን ማዕከል እንዲኖረው መደረጉ የቱሪስት መዳረሻነቱን ይጨምርለታል ነው የተባለው።

አዳራሹ  በቅጥር ግቢው ከሚገኙ ሃያ ህንፃዎች አንዱ ሲሆን ከንጉስ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በተለገሰ ቦታ ላይ እ.ኤ.አ. በ1960 የተሰራ ነው።

በአገልግሎቱ ዘመንም ትልቅ አበርክቶ የነበረው ይህ ህንፃ  እ.ኤ.አ. በ1963 ለተመሰረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የትውልድ ቦታም ነበር።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 4/2010 ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አልጀሪያ ዋና ከተማ አልጀርስ አቅራቢያ በተከሰተው  የአውሮፕላን አደጋ ለሞቱት ሰዎች የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ፡፡

ፕሬዝዳንቱ በአደጋው የ257 ሰዎች ህይወት በመቀጠፉ የተሰማቸውን ሃዘን ለአልጄሪያ መንግስት መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የላከው መግለጫ ያሳያል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በራሳቸው፣ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞኪራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ጥልቅ ሃዘናቸውን ገልፀው፤ ለሟቾቹ ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡

አውሮፕላኑ የጦር ኃይሉ ንብረት ሲሆን ከቡተፍሊካ አየር ኃይል ጣቢያ ከተነሳ ከጥቂት ጊዜ በኋላ መከስከሱ ተገልጿል። ከሟቾቹ መካከል አስሩ የአውሮፕላኑ ሰራተኞች ናቸው።

በአደጋው ህይወታቸውን ካጡት መካከል አብዛኛዎቹ የጦር ኃይሉ አባላትና ቤተሰቦቻቸው መሆናቸው በአገሪቷ መከላከያ ሚኒስቴር ተነግሯል።

የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የአገሪቷ መንግስት ለሶስት ቀን የሚቆይ የሃዘን ቀን አውጇል።

 

 

 

Published in ማህበራዊ

ጊምቢ ሚያዚያ 4/2010 ከመደበኛ የእርሻ ስራ በተጓዳኝ በመስኖ ልማት በመሳተፍ በሚያገኙት ገቢ  ተጠቃሚ መሆናቸውን በምዕራብ ወለጋ ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ የልማቱ ተሳታፊ አርሶ አደሮች ገለፁ።

የዞኑ መስኖ ልማት ባለስልጣን በሁለተኛ ዙር የመስኖ ልማት ከ4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።

በዞኑ የመነ ሲቡና ቂልጡ ካራ ወረዳዎች የልማቱ ተሳታፊ አርሶ አደሮች እንደገለፁት ከመደበኛ የእርሻ ስራቸው በተጨማሪ በመስኖ ልማት በመሳተፍ የሚያገኙት ገቢ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

የመስኖ ተጠቃሚነታቸው እንዲጨምር ደግሞ በምርት ማሳደጊያ መጠቀማቸውን እንደ አንድ ምክንያት ያነሳሉ።

የግብርና ባለሙያዎችን ምክረ ሃሳብ ተቀብለው ተግባራዊ ማድረጋቸውም ለስኬታቸው ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳበረከተ ገልፀዋል።

አቶ አዳነ ሀይሉ የውሀ ፓምፕ ተጠቃሚ ሲሆኑ ከአንድ ሄክታር በሚበልጥ መሬታቸው ጥቅል ጎመን፣ ቲማቲምና በርበሬ እንዳለሙ ተናግረዋል።

በመጀሪያው ዙር ከቤት ፍጆታቸው የተረፈውን ለገበያ በማቅረብ ከ140 ሺ ብር በላይ ትርፍ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በሁለተኛ ዙር ልማትም የደረሰ የቲማቲምና ቃሪያ ምርት ለገበያ በማቅረብ ከ20 ሺ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ገልፀው ምርቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ገበያ ሲያቀርቡ ከፍተኛ ገቢ እንደሚያስገኝላቸው ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

የቂልጡ ካራ ወረዳ ለሊሳ ከሚሳ ቀበሌ አርሶ አደር ዱጋሳ ሞሲሳ በዘንድሮ በጋ ነጭ ሽንኩርትና የተለያዩ ቅመማ ቅመም በመስኖ በማልማት ከ10 ሺ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በዚሁ ወረዳ የወንዲ ዳሌ ቀበሌ አርሶ አደር ተስፋ ለታ በቆሎ፣ ደንች፣ ሽንኩርትና ጥቅል ጎመን በባህላዊ መስኖ አልምተው ለገበያ በማቅረብ በሚያገኙት ገቢ ኑሯቸውን ማሻሻል እንደቻሉ ተናግረዋል።

በዞኑ 20 ወረዳዎች በሁለተኛው ዙር የመስኖ ልማት ስራ ከ36 ሺ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የዞኑ መስኖ ልማት ግብርናና ኤክስቴንሽን አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ ዋቅጅራ ናቸው።

በመጀመሪያው ዙር የመስኖ ልማት ስራ ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ከአራት ሚሊዮን 700 ሺ ኩንታል በላይ ምርት እንደተገኘ አስተባባሪው ገልጸዋል።

በመስኖ ልማት ስራው ከ99 ሺ በላይ ወንድና 6 ሺ በላይ ሴት አርሶ አደሮች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ከባለስልጣኑ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 4/2010 በመንግሥት ይዞታ ሥር የነበሩ አራት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ ሊያዘዋውር መሆኑን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ገለጸ።     

ሚኒስቴሩ ይህን የገለፀው የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸሙን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርብ ነው።     

ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ እንደገለጹት በሁለተኛው የእድገትና ትራንፎርሜሽን እቅድ በተቀመጠው ስትራቴጂ መሰረት ወደ ግል ይዞታነት እንዲዞሩ ውሳኔ የተሰጠባቸው የልማት ድርጅቶችን ለማሸጋገር እየተሰራ ነው።

ሽግግሩን በቀሩት የእቅድ ዘመኑ ሁለት ዓመታት ለማጠናቀቅ መታቀዱን ገልጸው በ2010 በጀት ዓመት ቀሪ የልማት ድርጅቶችን ለማዛወር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራትም በእቅድ የተያዙ የልማት ድርጅቶች በቀጥታ ሽያጭና በጋራ ልማት ወደ ግል ይዞታ ለማዛወር የዝግጅት ሥራዎች ተከናውነዋል። 

የብሄራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ፣ የቀንጥቻ ታንታለም ፋብሪካ፣ የፍል ውኃና ላንጋኖ ሪዞርት ሆቴሎች እንዲሁም በግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ሥር የሚተዳደረው የሻሎ እርሻ የዋጋ ትመና ተጠናቋል።

የሆቴሎች ልማት አክሲዮን ማህበርም የዋጋ ትመና እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል። 

የሸበሌ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር፣ የአሰላ ብቅል ፋብሪካና የኢትዮጵያ ቆርኪና ጣሳ አክሲዮንን ወደ ግል ይዞታ ለማዛወር ጨረታ መውጣቱንና የአሰላ ብቅል ፋብሪካ አሸናፊው ተለይቶ 35 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ ተፈጽሞ ውል መፈረሙን አብራርተዋል።   

ከኢትዮጵያ ቆርኪና ጣሳ አክሲዮንና ሸበሌ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበራት ጋር በተያያዘ ሂደቱ ተጠናቆ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለመንግሥት ቀርቧል ብለዋል ሚኒስትሩ።     

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በበጀት ዓመቱ ወደ ግል ይዞታ ከተዛወሩ ውዝፍ ሽያጭና ቀሪ ክፍያ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል።  

ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ በማዛወር ሥራ የተገኙ ልምዶችና የወደፊት ተግባራትን በተሻለ መንገድ ለማከናወን ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የፕራይቬታይዜሽን ፋይዳ ጥናት እየተካሄደ ነውም ብለዋል።  

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶች፣ የማዳበሪያ ፋብሪካዎችና የሌሎች ሜጋ ፕሮክቶች አፈጻጸም መጓተት ለምን በፍጥነት አይፈታም ሲሉ ማብራሪያ ጠይቀዋል።   

ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ሜጋ ፕሮጀክቶች ከመጀመራቸው በፊት የአዋጪነት ዝርዝር ጥናት ስለማይካሄድ ለአፈጻጸም መዘግየት ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

ይህም ከመሰረተ ልማት አቅርቦት ጀምሮ የካሳና የተጠቃሚነት ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ እንዳይመለሱ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ በሚጀመሩ አዳዲስ ፕሮጀክቶች መሰል ችግር እንዳይገጥም ተገቢው ጥናት እንደሚካሄድ አረጋግጠዋል።    

የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) 10 የስኳር ፕሮጀክቶችን ግንባታ ለማከናወን ውል ፈርሞ ወደ ሥራ ቢገባም በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈለገው ልክ ማከናወን እንዳልቻለም ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

የስምንት ፕሮጀክቶች ውል ተቋርጦ በሌላ ተቋረጮች እንዲሰራ መደረጉን ጠቁመዋል።

የስኳር ፕሮጀክቶቹን ወደ ሥራ ለማስገባት በተደረገው ጥረት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከሞላ ጎደል ወደ ሥራ መግባታቸውንም አክለዋል።

ከያዮ ማዳበሪያ ፋብሪካ ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ግምገማ መደረጉን የተናገሩት ዶክተር ግርማ በዚሁ መሰረት የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ የውሳኔ ሀሳብ ለመንግሥት መቅረቡን አስታውቀዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 4/2010 ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እየሰራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ትስስር አስመልክተው ለአገር ውስጥና መቀመጫቸው አዲስ አበባ ለሆነ የውጭ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

ቃል አቀባዩ አቶ መለስ ዓለም በፖለቲካ መስክ ብቻ ተወስኖ የቆየው የአገሪቷና የጎረቤት አገራት ግንኙነት እንደተጠበቀ ሆኖ ለላቀ የኢኮኖሚ መስክ መተሳሰር እየሰራች ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ከጎረቤት አገራት ጋር በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና ቱሪዝም መስኮች የጋራ ተጠቃሚነትን ባማከለ መልኩ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር መፍጠሯን ነው የገለፁት።

ኢትዮጵያ ባለፈው በጀት ዓመት ከ855 ሚሊዮን ዶላር በላይ ምርቶችን ለጎረቤት አገራት ስትሸጥ የጎረቤት አገራት ባለሀብቶችም በ473 የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ተሰማርተው መዋዕለ ንዋያቸውን ማውጣታቸውን ገልጸዋል።

የቀጣናው አገራት ለኢትዮጵያ የወጪ ምርቶች መዳረሻ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ መለስ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳንና ኬንያ ዋነኛ የገበያ መዳረሻዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

እነዚህ አገራት የአትክልትና ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬና ቅመማ ቅመም፣ ስጋና የቁም ከብቶችን ጨምሮ የፋብሪካ ውጤቶችን እንደሚገበያዩም አውስተዋል።

የሱዳን፣ ኬንያና ሶማሊያ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት መስክ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ ያደረጉባቸው 473 ፕሮጀክቶችም ለ13 ሺህ ያህል ኢትዮጵያዊያን የሥራ ዕድል አስገኝተዋል።

ከሱዳን ጋር ከ15 ዓመት በፊት 3 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ የነበረው የንግድ ልውውጥ ወደ 300 ሚሊዮን ማደጉንም ነው ቃል አቀባዩ የገለፁት።

ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ የራስ ገዝ አስተዳደር ጋር የ500 ሚሊዮን ዶላር የወጪ ምርት ገበያ እንዳላት ያብራሩት አቶ መለሰ ይህም ከቻይና ቀጥሎ ሁለተኛው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሱዳናዊያን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ የቻይናን ባለሀብቶች ይከተላሉ።

በቱሪዝም መስክም ከጅቡቲና ሱዳን ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ቱሪስቶች አልነጃሺን የመሳሰሉ የቱሪስት መስህቦችን ለመጎብኘት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቢሆንም ቁጥራቸውን ለማሳደግ የበለጠ መስራት እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።

ኬንያ ጠንካራ የቱሪዝም ዘርፍ ያላት በመሆኑ በሁለቱ አገራት የቱር ኦፕሬተሮች መካከል ትስስር መፈጠሩንም ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ሰላም መረጋገጥ አበክራ እንደምትሰራ ጠቅሰዋል።

ግንኙነቱን ማጠናከር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩን ያወሱት አቶ መለስ የመንግስት ለመንግስት ግንኙነት፣ በመሰረተ ልማት ትስስር የኢኮኖሚ ውህደት ማጣጣም የሚያስችሉ የፖሊሲ ማጣጣምና ህጋዊ የድንበር ንግድን የማበረታታት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

 

 

 

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን