አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 11 April 2018

አዲስ አበባ ሚያዚያ 3/2010 'ወቅታዊ የኑሮ ሁኔታን መሰረት ያደረገ የክፍያ ማሻሻያና የመስሪያ ቁሳቁሶች ተሟልተው መቅረብ አለባቸው' ሲሉ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ጠየቁ።

በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ 12 ነዋሪና በአካባቢ ጥበቃ ስራ ላይ ተሰማርተው ስምንት ቤተሰብ የሚያስተዳድሩት አቶ ዝናቤ አዳነ፥ በፕሮግራሙ መሰረት የተሰጣቸውን ስራ በማከናወን የሚያገኙት 1 ሺህ 200 ብር በቂ እንዳልሆነ አመልክተዋል።

አቶ ዝናቤ ገንዘቡ ከወቅቱ የኑሮ ሁኔታ አንጻር በቂ ባለመሆኑ የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን የክፍያ ማሻሻያ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ነዋሪ የሆኑትና የጽዳት ስራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ብርቄ በሻህውረድ ከሰኔ ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ ስራውን ቢጀምሩም፥ የደህንነት መጠበቂያ፣ ቱታ፣ ማስክና የእጅ ጓንት በበቂ ሁኔታ ባለመሟላቱ የጽዳት ሰራተኞቹ ለከፍተኛ የጤና እክል መዳረጋቸውን ተናግረዋል።

በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ አንድ ነዋሪና በከተማ ግብርና ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ መሐመድ አሊ ለግብርና ስራ አስፈላጊ መሳሪያዎች እስካሁን አለመሟላታቸውን ያነሳሉ።

"መንግስት እየደጎማችሁ ነው በሚል አከራዮች የቤት ኪራይ እየጨመሩብን ነው። የምናገኛት 1ሺህ200 መቶ ብር ናት ይህ ገንዘብ በቂ አይደለም" ያሉት አቶ መሐመድ ከተማ አስተዳደሩ የኢኮኖሚ ሁኔታውን መሰረት በማድረግ ለዚህ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ፥ ሰራተኞቹ ያነሱት የክፍያ ማሻሻያ ጥያቄ ተገቢ በመሆኑ በ15 በመቶ ከፍ ለማድረግ ከዓለም ባንክ ጋር እየተነጋገሩበት መሆኑን ጠቁመዋል።

ሰራተኞቹ ለሚያከናውኗቸው የተለያዩ ተግባራት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን በማሟላት ችግሩን በአጭር ጊዜ ለመፍታት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

በፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች የተነሱ የጤና እንክብካቤ አገልግሎት ጉዳይ የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ውይይት አድርጎበት አቅጣጫ እንደሚቀመጥ አመልክተዋል።

ከስራ አድል ፈጠራው በተጨማሪ ተጠቃሚዎቹ ከሚያገኙት ገንዘብ ላይ በመቆጠብ የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም እንዲኖራቸው ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከንቲባ ድሪባ ኩማና ሌሎች የአስተዳደሩ የስራ ሃላፊዎች በመዲናዋ የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚዎች እያከናወኗቸው ያሉ ስራዎችን ዛሬ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 3/2010 በክልሎች ህዝቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነት የሚያጎለብት 'የመንግስታት ግንኙነት ፖሊሲ' መዘጋጀቱን የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ሙሉጌታ ውለታው እንደገለፁት፥ በፌዴራሉና በክልል መንግስታት መካከል ያለው አንድነትና ወንድማማችነት በሚፈለገው ልክ የጎለበተ አይደለም።

በመሆኑም በክልል መንግስታት መካከል የሚስተዋለውን ችግርና አለመግባባት በዘላቂነት ለመፍታት የመንግስታት ግንኙነት ፖሊሲ ተዘጋጅቷል።

ፖሊሲው የዜጎችን አብሮነትና ወንድማማችነት ከማሳደጉ ባሻገር ግንኙነቱን ለማሻከር የሚንቀሳቀሱ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚያስችል ነው የጠቆሙት።

በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው ይህ ፖሊሲ፥ ለህዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ቀርቦ ሲፀድቅ ተግባራዊ ይሆናል ነው ያሉት።

ሀገሪቱ በመደበኛና መደበኛ ባለሆነ አካሄድ የክልል መንግስታት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስታደርግ ብትቆይም የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልቻለችም ብለዋል አቶ ሙሉጌታ።

ተጀምሮ የተቋረጠው የምስራቅ ኢትዮጵያ ክልሎች (ኦሮሚያ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ አፋር፣ ሐረሪና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር) የእርስ በእርስ ግንኙነት መደበኛ በሆነ መንገድ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በክልሎች መካከል የነበሩ ግንኙነቶች ቀጥለው ቢሆን ኖሮ በኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት አይከሰትም ነበር ነው ያሉት።

በቀጣይ መቋቋም የሚገባቸው አደረጃጀቶች ካሉ እንዲቋቋሙና የተቋቋሙትም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ይደረጋል ብለዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 3/2010 የፌዴራልና የክልል መንግስታትን ግንኙነት ለማጎልበት ከአገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚዛመድ ስርዓት ከሚከተሉ አገሮች ልምድ እንደሚወሰድ የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ገለጸ።

የፌዴራል ስርዓት የሚከተሉት ጀርመንና ናይጄሪያ የመንግስታት ግንኙነት አወቃቀር ስርዓት ተሞክሯቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤትና ለሚኒስቴሩ ተወካዮች አቅርበዋል።

በዓለም ላይ 40 በመቶ የሚሆነውን ህዝብ የያዙት 28 አገሮች የፌዴራል ስርዓትን የሚከተሉ ናቸው።

የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ውለታው እንደገከጹት ውስንነት ቢኖረውም በፌዴራልና በክልል መንግስታት መካከል መቀራረብና አንድነት እንዲጎለብት የህዝብ ለህዝብ መድረኮች እየተዘጋጁ ነው።

በዚህም ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣሙ የፌዴራል ስርዓት የሚከተሉ አገሮችን ልምድ በመቅሰም የክልሎች ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር ይደረጋል።

ጀርመንና ናይጄሪያ ካቀረቡት የመንግስታት ግንኙነት ተሞክሮ መካከል አገሪቱ ከምትከተለው ፖሊሲ፣ ከህዝቡ ባህል፣ ቋንቋና እምነት ጋር ተስማሚ የሆኑት እንደሚወስዱ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

የጀርመን የፌዴሬሽን አወቃቀር በክልል መንግስታት የጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የመንግስታቱን ግንኙነት ለማጠናከር ቅድሚያ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ናይጄሪያ የምትተገብረው እንደ ምርጫ ቦርድ፣ የፍትህ አካላትን ማጠናከርና ገለልተኛ ማድረግ እንዲሁም የወሰን ጉዳዮችን ማንነትን መሰረት በማድረግ ምላሽ መስጠትም ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይነት አላቸው።

ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጋር ተያይዞ እያደገ የሚሄድ የመንግስታት ግንኙነት ስርዓት እንገነባለን ብለዋል።

በረጅም ጊዜ ልምድ የተገኘውን የጀርመን የመንግስታት አወቃቀርና አስተዳደርን መሰረት አድርጎ የተቋቋመው የናይጄሪያ የክልል አመሰራረት የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ማንነት መሰረት አድርጎ ከተዋቀረው የክልል አደረጃጀት ጋር አብሮ አይሄድም ብለዋል።

በመሆኑም እነዚህን ከአገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይሄዱ ጉዳዮች በመተው ከኢትዮጵያ የፌዴራል አወቃቀር ጋር የሚሄዱትን እንደ ህንድና ስዊዘርላድ ያሉ አገሮች ልምድ እንወስዳለን ነው ያሉት።

የፎረም ፎር ፋውንዴሽን ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ጆርጅ ሚልብሬድት በመንግስታት መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር አገሮች ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት የመንግስታት ግንኙነት ፖሊሲ ማውጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ሁሉም አገሮች የሚገነቡት የመንግስታት ግንኙነት የፌዴራልና የክልል መንግስታትን ማቀራረብና የክልሎችን የጋራ ጥቅም መሰረት ማድረግ አለባቸውም ብለዋል።

Published in ፖለቲካ

ጎንደር ሚያዚያ 3/2010 በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ መዳረሻ የሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚያስተዋውቅ ፎረም በደባርቅ ከተማ ሊካሄድ ነው፡፡

"ሰሜን ጎንደርን ለማልማት በጋራ እንሩጥ’’ በሚል መሪ ቃል የፎረሙ አካል የሆነ የ10 ኪሎ ሜትር ታላቅ የሩጫ ውድድርም ተዘጋጅቷል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የኢየኢንቨስትመንት ፎረሙን ለማካሄድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከአካባቢው ተወላጆችና ባለሀብቶች ጋር  በጎንደር ከተማ የምክክር ተካሄዷል ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አምሳሉ ደረጀ በወቅቱ እንደገለፁት የኢንቨስትመንት ፎረሙ ሚያዚያ 13 እና 14 ቀን 2010 ዓ.ም በዞኑ ዋና ከተማ ደባርቅ ይካሄዳል፡፡

"የፎረሙ ዋና አላማ በብሄራዊ ፓርኩ መዳረሻ የሚገኙ ኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጪ ባለሀብቶች ወደ አካባቢው መጥተው እንዲያለሙ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ነው " ብለዋል ።

የአካባቢውን የእንስሳት ሀብት፣ የእጣን ምርት፣ የቅባት ሰብሎችና ሌሎች የግብርና ኢንቨስትመንት አማራጮችን በስፋት በማስተዋወቅ ለአካባቢው እድገትና ልማት ባላሀብቶችን መሳብ የፎረሙ አለማ መሆኑን ገልፀዋል ።

በፎረሙ ከ500 በላይ የአካባቢው ተወላጆችና አልሚ ባለሀብቶችን ጨምሮ ከፌደራል ከክልልና ከዞን የተጋበዙ ከፍተኛ አመራሮች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡

ፎረሙን ምክንያት በማድረግ አካባቢው ለአትሌቲክስ የስፖርት ውድድርና ስልጠና ያለውን ምቹ የአየር ንብረት ለማስተዋወቅ የሚያግዝ የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር እንደሚካሄድ አመላክተዋል፡፡

መነሻና መድረሻውን ደባርቅ ከተማ በማድረግ በፓርኩ ክልል በሚገኘው የሊማሊሞ ጠመዝማዛ መንገድ በሚካሄደው ውድድር ታዋቂ አትሌቶችና ቱሪስቶችን ጨምሮ ከ5ሺህ በላይ የአካባቢው ስፖርት አፍቃሪዎች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡

ከውድድሩ የሚገኘው ገቢ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የአትሌቲክስ ኢንስትራክተር ለነበሩት ለእንዳልክ ቀለመወርቅ መታሰቢያነት ለሚገነባው የአትሌቲክስ መንደር የሚውል መሆኑ ተመልከቷል።

እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለፃ በፎረሙ ማብቂያ በደባርቅ ከተማ አዲስ ለሚገነባው ባለ ሰባት ፎቅ  የአስተዳደር ህንጸ የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ -ስርአት ይከናወናል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በቅርቡ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም የአካባቢው ህብረተሰብ በተገኙበት ሚያዚያ 15 ቀን 2010  እንደሚመረቅ ታውቋል።

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ ሚያዚያ 3/2010 በትግራይ ደቡባዊ ዞን ኦፍላ ወረዳ ለመዋቢያና ለሳሙና መቀመሚያ የሚውል የ"ሮዝ ደማሲና " ጥሬ  ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ሮዝ ደማሲና  በተባለ የእርሻ ኢንቨስትመንት በተሰማሩ ባለሀብት  እየተዘጋጀ ያለው ይሄው ጥሬ ምርት በ10 ሄክታር መሬት ላይ በማልማት ነው፡፡

" ሮዝ ደማሲና "  የአበባ ተክል መሆኑንና ከተክሉ የሚገኘው ጥሬ ምርት በዘይት መልክ ተዘጋጅቶ ሙሉ በሙሉ ወደ አውሮፓ ገበያ የሚላክ መሆኑን ባለሀብቱ  አቶ አታክልቲ ስዩም ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡ 

በኦፍላ ወረዳ ለኢንቨስትመንት በተሰጣቸው  መሬት ላይ የተከሉት የሮዝ ደማሲና ችግኝ ለምርት በመድረሱ ወደ አግሮ ፕሮሴሲንግ ስራ ለመሸጋር ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡

ባለሃብቱ እንዳሉት ምርቱ  በአንፋሎት ኃይል በመጭመቅ ወደ ዘይትነት ለመለወጥ የሚያስችል ማሽኖች ተተክለው ሙከራ ተደርጓል፤ ውጤታማም ነው፤ ዘይቱ   ለተለያዩ የመዋቢያ ቅባቶችና ለሳሙና መቀመሚያ የሚውል ነው፡፡ 

በአሁኑ ወቅት ምርቱ  በዓለም ገበያ ተፈላጊነት እንዳለውና አንድ ኪሎ የሮዝ ደማሲና ዘይት እስከ 12ሺህ ዩሮ  እንደሚሸጥ ነው ባለሀብቱ የተናገሩት፡፡

የእርሻ ኢንቨስትመንቱ  ለማስፋት ፍላጎት እንዳላቸው ያመለከቱት  ባለሀብቱ ከሁሉም በላይ በአካባቢው ያሉ ከ200 በላይ አርሶ አደሮች  አበባውን በማምረት ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት መስጠታቸውንም አስታውቀዋል፡፡

በ20 ሚሊዮን ብር ካፒታል የሚንቀሰቃሱት ባለሀብቱ በቅርብ ቀናት   ውስጥ የማምርት ስራ እንደሚጀምሩ ጠቅሰው  የከርሰ መሬት ውሀ በመጠቀም በመስኖ ልማትና በእንስሳት እርባታም መሰማራታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ባለሀብቱ እስከአሁን ለሀያ አምስት የአካባቢው ነዋሪዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡

የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ነዋሪዎች መካከል አርሶ አደር ከማል ካህሳይ በሰጡት አስተያየት  ባለሀብቱ በአካባቢው በተሰማሩበት የአበባ እርሻ ልማት ላይ በመሳተፍ በወር 2ሺህ ብር እየተከፈላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

ወጣት የብሪ ተስፋዬ በበኩሏ  የአስረኛ ክፍል ትምህርቷን አጠናቃ  ስራ ስታፈላልግ ባለሀብቱ ባመቻቹት  እድል በመጠቀም በወር 900 ብር እየተከፋለት እየሰራች መሆኑን ተናግራለች፡፡  

የክልሉ የግብርና ምርቶች ፕሮሜሽን ኤጀንሲ ተጠባባቂ ስራ  አስኪያጅ  አቶ ዘርአጽዮን ፍሰሃ ጥሬ ምርቱን  አቅራቢ አርሶ አደሮች አቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

የ "ሮዝ ደማሲና" ተክል የአካባቢን ጥበቃን የማጠናከር አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡

ከሮዝ ደማሲና አበባ  በእንፋላት የሚጨመቅ ዘይት በሀገሪቱ  በደብረ ብርሀን ከሚገኘው  የእርሻ ልማት ቀጥሎ የኦፍላ ወረዳ ሁለተኛው ፕሮጀክት መሆኑም ተመልክቷል፡፡

በደቡባዊ ዞን ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማንቀሳቀስ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ 95 ባለሀብቶች  ለ2ሺህ900 ወገኖች  የስራ መፍጠራቸውን  የዞኑ ገጠር መሬት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ ኪዱ ፍትዊ ገልጸዋል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር ሚያዝያ 3/2010 በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሀገር ለስራ የሚሄዱ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አጫጭር የሙያ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን የአማራ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው የሰው ሃይል ጥናትና የስራ ስምሪት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንጌ ለኢዜአ እንደገለጹት ስልጠናው እየተሰጠ ያለው በክልሉ በተመረጡ 13 ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ነው።

የባህ ዳር፣የደሴ ወይዘሮ ስህንና የደብረ ታቦር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ስልጠናውን ከሚሰጡ ተቋማት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

በተያዘው ዓመት በፍቃደኝነት ከተመዘገቡ 525 ወጣቶች መካከል 392ቱ በቤት አያያዝና በህጻናት እንክብካቤ ከአንድ እስከ ሶስት ወር የፈጀ በተግባር የተደገፈ ስልጠና ወስደው በሙያ ምዘና ማለፋቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ። ዳይሬክተሩ እንዳሉት ኮሌጆቹ ስልጠናውን የሚሰጡት ከክፍያ ነጻ  ነው ።

በደሴ ወይዘሮ ስህን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ስልጠና ወስደው የሙያ ምዘና ካለፉ መካከል ወጣት ሰዓዳ መሀመድ በሰጠችው አስተያየት የተሰጠን ስልጠና ለስራ በምንሄድበት የውጭ አሰሪ ሀገራትን ነባራዊ የስራ ሁኔታ ከግምት ያስገባና በተግባር የተጋዘ ነው  ብላለች ።

 የተሰጣት ስልጠና ውጭ ሀገር ሂዳ ያለምንም ስጋት በብቃት ስራዋን እንድታከናውን እንደሚያስችላት ተናግራለች ።

በኮሌጁ የተሰጣት ስልጠና ለምትሰራው ስራ በቂ ግንዛቤ እንዳስጨብጣትና በራሶ እንድተማመን እንዳደረጋት የተናገረቸው ደግሞ  ወጣት ዓለም እሸት ናት።

"በኮሌጁ በህጋዊነት ወደ ውጭ ሀገር ሂደው ሰርተው ለመለወጥ ለሚፈልጉ ዜጎች ያለምንም ወጭ የሙያ ስልጠና መሰጠቱ ለዜጎች አማራጭ በመፍጠር እንዲበረታቱ የሚያደርግ ነው " ብላለች ።

ወደ ውጭ ሀገር ለስራ የሚሄዱ ዜጎች ለሚሰሩት ስራ እውቅና ኖሯቸውና ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል በ2006 ዓ.ም የወጣው የውጭ ሀገር ጉዞ መመሪያ ተቋርጦ ቆይቶ በአዋጅ 923/2007 መሰረት ዘንድሮ መከፈቱ ይታወቃል።

Published in ማህበራዊ

አምቦ ሚያዝያ 3/2010 የአካባቢያቸውን ሰላምና  ልማት በዘላቂነት ለማስቀጠል ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻቸውን እንደሚወጡ በአምቦ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ነዋሪዎቹ ይህንን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ዛሬ በአካባቢው በተገኙበት ወቅት አቀባበል ሲያደርጉ ነው፡፡

መንግስት ለውጥ ለማምጣት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ደቻሣ ገለታ  ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ወደ አምቦ በመምጣታቸው መደሰቱን ገልጾ ይህም "ለከተማዋ የወደፊት ዕድገት ተስፋ የሚሰጥ የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው "ብሏል፡፡

ከመንግስት ጎን በመቆም የሀገራቸውን ብሎም የአካባቢያቸውን ሰላምና  ልማት በዘላቂነት ለማስቀጠል የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ እንዲሳካ የሚደግፍ መሆኑን ገልጿል፡፡

ህዝቡም በጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ የተጣለበትን ሰላም የማስጠበቅ እና ዘላቂ ልማት የማረጋጋጥ አደራ በብቃት እንዲወጣ መደገፍ እንደሚገባውም ጠቁሟል፡፡

አቶ በላይ ታደሰ የተባሉት ነዋሪ በበኩላቸው " የከተማዋ ነዋሪዎች ያላቸውን አንድነት እና መግባባት ለልማት ማዋል ይኖርባቸውል" ብለዋል፡፡ 

ለዘላቂ ሰላምና እድገት በተደረጃ አግባብ ህዝቡ እንዲተጋ ፍላጎታቸው መሆኑን ጠቅሰው በእሳቸውም በኩል ለለውጥ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

" መንግስት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት በተነሳበት በዚህ ወቅት የአምቦ ከተማ እና አካባቢዋ ሴቶችም ልማቱን በማገዝ ረገድ የድርሻችንን መወጣት ይኖርብንል"  ያለችው ደግሞ ወጣት ሰናይት ሚደግሣ ናት፡፡

አዲሱ አመራርም የህዝቡን ጥያቄ በመስማት ፈጣን ምልሽ መስጠት እንደሚጠበቅበት ያመለከቱት አስተያየት ሰጪዎቹ ችግሮች ተፈትተው የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ  ከመንግስት ጎን በመቆም እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡

ዶክተር አብይ አህመድ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሰየሙ ወዲህ ጂግጂጋ በመገኘት ዛሬ ደግሞ በአምቦ ከተማ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር  የተወያዩ ሲሆን በተመሳሳይ ወደ መቀሌም እንደሚያቀኑ ይጠበቃል፡፡

 

 

 

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 3/2010 የግብርና ምርቶችን በባለቤትነት ማስመዝገብ ካልተቻለ ኢትዮጵያ በዘርፉ ልታገኝ የሚገባትን እድገትና ጥቅም ልታጣ እንደምትችል ተጠቆመ።

ይህ የተገለፀው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሳይንስ፣ መገናኛና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤትን የዘጠኝ ወራት ሪፖርት በገመገመበት ወቅት ነው።

ኢትዮጵያ በሌሎች አገሮች የሌሉ የእህል፣ የእፅዋትና የእንስሳት ሃብት ቢኖራትም በባለቤትነት ባለመመዝገባቸው አገሪቱ ማግኘት የምትችለውን ጥቅም እያሳጣት ነው ብሏል ቆሚ ኮሚቴው ።

በቅርቡ አገሪቱ ያጣችው የጤፍ ባለቤትነት የግብርና ምርቶች በባለቤትነት የማስመዝገብ ክፍተት ስለመኖሩ ማሳያ ነው ተብሏል ።

የአእምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤት በዕቅድ አፈጻጸሙ የግብርና ምርቶችን ባለቤትነት የማስመዝገብ ሂደት ክፍተት የታየበት ነው።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው መለስ እንደገለፁት፤ የግብርና ምርት የሆነውን ጤፍ ቀደም ሲል በባለቤትነት በአገር ውስጥና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ማስመዝገብ ባለመቻሉ ሌሎች ተቋማት የባለቤትነት መብቱን ሊወስዱ ችለዋል።

አሁንም የግብርና ምርት የሆኑ የተለያዩ የቡና ምርቶች፣ የጤፍና የእዕፅዋት ዝርያዎች ቢኖሩም ምዝገባ እንዳልተደረገላቸው ሰብሳቢው ጠቁመዋል።

ግብርና መር የሆነውን የኢኮኖሚ እድገት ለማፋጠንና ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ የአገሪቱን የግብርና ውጤቶች ባለቤትነት ማስጠበቅ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ነው ቋሚ ኮሚቴው ያሳሰበው።

ተቋሙ በበኩሉ የነዚህን ምርቶች ባለቤትነት ለማረጋገጥ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም አንዳንድ የህግ ማዕቀፎች አለመሟላትና ለአሰራር ምቹ አለመሆን ችግር እየፈጠሩ እንደሆነ አስታውቋል።

ችግሩን ለመቅረፍም የፖሊሲና አዋጆች ረቂቅ አዘጋጅቶ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት መላኩን ገልጿል።

የተቋሙ ተወካይ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤርምያስ የማነብርሃን እንዳሉትም የግብርና ምርቶችን ባለቤትነት ለማረጋገጥና የሚገኘውንም ጥቅም ለማሳደግ ከማሳ ጀምሮ ያሉ ሂደቶች ከታሪካዊ ዳራቸው ጭምር የማጥናት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ሂደትም በቅርቡ የተለያየ ዝርያ ያላቸው የቡና፣ የጤፍ፣ የጤና አዳምና የጭሳጭስ እፅዋት ምዝገባ በቅርቡ ይካሄዳል ብለዋል።

 

ሚያዚያ/2010 በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ሂሳባቸውን በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎች ለማቅረብ አራት የልማት ድርጅቶች ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ገለፀ።

ዝግጅታቸውን ያጠናቀቁ ድርጅቶች ብሄራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ናቸው።

የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጋሼ የማነ የ5 ዓመት ስትራቴጂ በማዘጋጀት የዓለም አቀፍ የሂሳብ አያያዝ ደረጃዎችን ለመተግበር ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

በሚኒስቴሩ የኮርፖሬትና ፋይናንስ አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ መሰለች ወዳጆ በበኩላቸው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፣ ብሄራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ፣ የኢትዮጵያ ብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን የፋይናንስ ሪፖርታቸውን በዓለም  አቀፍ ደረጃዎች ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የበጀትና ፋይናንስ ዳይሬክተር አቶ መለሰ ስሜነህ ተቋማቸው የፋይናንስ ሂሳቡን ረቂቅ ሪፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃዎች ማውጣቱን ጠቁመዋል።

ዳይሬክተሩ እንደሚሉት የድርጅቱ አመራር ቁርጠኝነትና የተወከሉ ኮሚቴዎች ከፍተኛ ጥረት በአዲሱ የፋይናንስ ሪፖርት ስርዓት ትግበራ ላይ ውጤት አስገኝቷል።

የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዲኤታዋ ወይዘሮ መሰለች ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር የፋይናንስ ሪፖርታቸውን በማዘግየት የሚታወቁ የስኳር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ዲዛይንና ቁጥጥር ስራዎች ኮርፖሬሽን  አሁንም በዓለም አቀፍ ደረጃዎች ትግበራ ወደ ኋላ  ቀርተዋል ነው ያሉት።  

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የፋይናንስ ዋና መምሪያ ስራ አስፈፃሚ  ወይዘሮ መዓዛ መድምም በበኩላቸው ተቋሙ በ2010 የፋይናንስ ሪፖርቱን በዓለም አቀፍ ደረጃዎች ለማውጣት እየሰራ መሆኑን  ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን፣ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና ፍል ውሃ አገልግሎት ድርጅትን ጨምሮ ዘጠኝ ድርጅቶች ድጋፍ ቢደረግላቸው ሰኔ 30 ላይ የፋይናንስ ሪፖርታቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃዎች ሊያቀርቡ እንደሚችሉ መለየታቸውንም ወይዘሮ መሰለች ተናግረዋል።

ተንጠልጣይ ሂሳቦችን ያለመወሰን፣ የቦርዶች በመደበኛ ጊዜ አለመገናኘት፣ ስለአሰራሩ በቂ ግንዛቤ አለመኖሩና የባለሙያ እጥረት ተቋማቱን ወደ ኋላ እንዲቀሩ አድርጓቸዋል ብለዋል ።

በዚህ ዓመት መተግበር የማይችሉ ተቋማት እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚወሰን ገልፀው ሚኒስቴሩም አሁን የደረሱበትን ደረጃ በማየት ሪፖርቱን በአዲሱ አሰራር እንዲያዘጋጁ ግፊት ያደርጋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጋሼ እንደተናገሩት ለዓለም አቀፍ የሂሳብ አያያዝ ደረጃዎች ትግበራ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር  የምታደርገውን ሂደት ለማጠናከር፣ በአሰራር ላይ ግልፅነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን እንዲሁም የልማት ድርጅቶችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ አዲሱ የሂሳብ አያያዝ ስርዓት ሚናው የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 3/2010 የፍትህ የህግ ምርምርና ስልጠና ኢኒስቲትዩት ከማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ለማጎልበት መስራት እንደሚጠበቅበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢኒስቲትዩቱን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ዛሬ ተመልክቷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት እንደተናገሩት፤ ከፌዴራል እስከ ክልል የተቋቋሙ ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ቢኖሩም ከኢኒስቲትዩቱ ጋር ያላቸው ቅንጅታዊ አሰራር የተጠናከረ ባለመሆኑ በሚፈለገው ደረጃ አገልግሎት መስጠት አልቻሉም።

በዚህም የማህበራዊ ፍርድ ቤቶችን አገልግሎት የሚሹ ዜጎች ተገቢውን አገልግሎት እያገኙ አለመሆኑንም  ቋሚ ኮሚቴው ባደረገው የመስክ ምልከታ ማረጋገጡን ነው የሚናገሩት።

ማህበራዊ ፍርድ ቤቶቹ ለህብረተሰቡ የሚሰጡት የህግ አገልግሎት የጎላ ቢሆንም ኢኒስቲትዩቱ ለፍርድ ቤቶቹ የሚያደርገው ድጋፍና ክትትል በቂ አይደለም።

የማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ሙያተኞችን ለማብቃት የረጅምና የአጭር ጊዜ ስልጠና መስጠትና አስፈላጊውን ግብአት ከማሟላት አኳያ ኢኒስቲትዩቱ ክፍተት ይስተዋልበታል።

ክፍተቱ ኢኒስቲትዩቱ ከማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሰራር ዝቅተኛ እንደሆነ እንደሚያመላክት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጠቁመዋል።

የኢኒስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን አበበ በበኩላቸው የፍትህ፣ የህግ ኢኒስቲትዩትና የህግ ምርምርና ስልጠና ኢኒስቲትዩትን፣ የፍትህ የህግ ምርምርና ስልጠና ኢኒስቲትዩት የሚለውን ስያሜ በመስጠት አንድ ተቋም በመደረጋቸው ተቋሙን በማደራጀት ስራ ላይ ተጠምዶ እንደነበር አብራርተዋል።

ተቋሙን በማደራጀት ስራ ላይ ትኩርት በማድረጋቸው ለማህበራዊ ፍርድ ቤቶች በቂ ድጋፍና ክትትል አለማድረጋቸውን ገልጸው በቀጣይ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ክልል የተሰጣቸው ስልጣን የተለያየ በመሆኑ በጋራ ለመስራት እንደማይመች ያስረዱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የተሰጣቸውን የፍርድ አሰጣጥ ስልጣን ምክር ቤቱ በድጋሚ እንዲመለከተው ጠይቀዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላትም ኢኒስቲቲዩቱ የህዝብ ክንፍን አለመለየቱ፣ በክፍት የስራ መደቦች ላይ ሙያተኞችን በመቅጠር የሰው ኃይልን አለሟሟላቱንና ሊወገዱ የሚገባቸውን ንብረቶች በወቅቱ አለማስወገዱን በእጥረት ተመልክቷል።

በሴቶች፣ በኤች አይ ቪ /ኤድስ ስርጭትና መከላከል ላይና የአካል ጉዳተኞች ደህንነት ላይ የተመዘገቡ ውጤቶች በጥንካሬ የሚታዩ መሆናቸውን የቋሚ ኮሚቴው አባላት ጠቁመዋል።  

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን