አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 10 April 2018

ደብረ ብርሃን ሚያዝያ 2/2010 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ለመጪው የመኸር ወቅት 509 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር ለመሸፈን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

 በመምሪያው የሰብል ልማት ሰርቶ ማሳያ ባለሙያ ወይዘሮ ቦጋለች በልሁ ለኢዜአ እንደገለጹት በምርት ዘመኑ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ።

 እስካሁን በተካሄደ የቅድመ ዝግጅት ሥራም 189 ሺህ 600 ሄክታር መሬት በአርሶ አደሮች ከአንድ እስከ ሦስት ጊዜ መታረሱን ተናግረዋል።

 ለመኸር እርሻ የአፈሩን አይነት መሰረት ያደረገ 653 ሺህ 507 ኩንታል ማዳበሪያ ሲያስፈልግ በአሁኑ ወቅትም 242 ሺህ 239 ኩንታል ማዳበሪያ በሕብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ለአርሶ አደሩ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

 ወይዘሮ ቦጋለች እንዳሉት 17 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ እጅ በእጅ ሽያጭ ለአርሶ አደሩ የደረሰ ሲሆን፣13 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብም ከምርጥ ዘር አቅረቢ ድርጅቶች ጋር በመዋዋል ላይ ናቸው።

 ከእዚህ በተጨማሪ አርሶ አደሩ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ለመኸር እርሻ ሲዘጋጅ መቆየቱን ወይዘሮ ቦጋለች ተናግረዋል።

 በሞረትና ጅሩ ወረዳ በጣሶ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አጥሌ ተፈራ በበኩላቸው እንደገለጹት ሁለት ሄክታር መሬታቸውን በመጪው የመኸር እርሻ በጤፍ፣ስንዴ፣ሽምብራና ምስር ሰብሎች ለማልማት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

 ለዚህም የሚያስፈልጋቸውን በቂ የፋብሪካ ማዳበሪያ ቀድመው ከመግዛታቸው በተጨማሪ፣ አሥር ኩንታል ኮምፖስትና አንድ ኩንታል ምርጥ ዘር ከወዲሁ በማዘጋጀት "የዝናቡን መጣል በመጠባበቅ ላይ እገኛለሁ" ብለዋል።

 አርሶ አደር አድማሱ ጥሩነህ በበኩላቸው ለመኸር ሰብል ልማት የሚውል አንድ ኩንታል ተኩል የተለያየ ምርጥ ዘርና የሚያስፈልጋቸውን ማዳበሪያ ለመግዛት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

 በእርሻ ዝግጅት ሥራው 328 ሺህ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 64 ሺህ የሚሆኑት የመሬት ባለቤት የሆኑ ሴቶች ናቸው።

 በቀጣዩ የመኸር ወቅት ከሚለማው አጠቃላይ መሬት ከ16 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 2/2010 የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን / ሉሲዎቹ / ለአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ወደ ቀጣይ ዙር አልፈዋል።

ሉሲዎቹ በ2011ዓ.ም በጋና አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 11ኛው የአፍሪካ ሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ የማጣሪያ የመልስ ጨዋታቸውን ዛሬ ከሊቢያ አቻቸው ጋር ተጫውተው 7 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፈዋል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሎዛ አበራ 4 ግቦችን ስታስቆጥር ረሂማ ዘርጋው፣ ህይወት ደንጊሶና ሰናይት ቦጋለ አንድ አንድ ግቦችን በማስቆጠር ሉሲዎቹን አሸናፊ አድርገዋል።

ብሔራዊ ቡድኑ በደርሶ መልስ ውጤት 15 ለ 0 ያሸነፈ ሲሆን ፤ ይህም ብሄራዊ ቡድኑ ያሳየውን ብቃት የሚያመላክት ነው።

ሉሲዎቹ ከአልጄሪያና ከሴኔጋል አሸናፊ ጋር በመጪው ግንቦት ይጫወታሉ።

የአፍሪካ ሴቶች  ዋንጫ እንደ አዲስ ከተጀመረ ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሶስት ጊዜ ማጣሪያውን አልፈው በውድድሩ መካፈል ችለዋል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ሚያዝያ 2/2010 በአፍሪካ "የአሜሪካ መጣሽ ተምች"ን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት አሜሪካ የምተሰጠውን ሙያዊ እገዛ አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች።

በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ የአሜሪካ መጣሽ ተምች ግብረ ኃይል አስተባባሪ ሬጊና ኢዲይ በጉዳዩ ዙሪያ አሜሪካ በአፍሪካ እያደረገች ያለውን ድጋፍ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሬጊና ኢዲይ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የአፍሪካ አገሮች ምርትና ምርታማነታቸውን በማሳደግ በምግብ ራሳቸውን ለመቻል የሚያደርጉትን ጥረት ተምቹ እያስተጓጎለ ነው።

ተምቹ ወደ አፍሪካ ከሁለት ዓመታት በፊት መግባቱን ጠቅሰው፤ በ30 የአፍሪካ አገሮች  ከሶስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ የሚሸፍን የበቆሎ ሰብል በአረሙ መጠቃቱን ጠቁመዋል።

ይህም ደግሞ በዓመት እስከ 13 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የገንዘብ ወድመት እንደሚያስከትልና በርካታ የአፍሪካ ዜጎችን ለረሃብና ተያያዥ ችግሮች እንደሚያጋልጥ አስረድተዋል።

አሜሪካም ተምቹን ከአፍሪካ ለማስወገድ ከአገሮቹ መንግሥታትና ከግሉ ዘርፍ ጋር በመሆን ተሞክሮን መሰረት በማድረግ ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎችን በማስተዋወቅ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

እርሳቸው ባደረጉት ገለጻ "አርሶ አደሮች ተምቹን በተመለከተ ያላቸውን እውቀት በማሳደግና ለመከላከል የሚያስችላቸውን ቴክኖሎጂዎች በማጋራት በጋራ እንሰራለን" ብለዋል።

የአፍሪካ አርሶ አደሮች ተምችን ሊቋቋም የሚችሉ የተዳቀሉ ዝርያዎችን መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበው፤ ይህም በሌሎች የዓለም አገሮች ውጤታማ መሆኑን አውስተዋል።

የአሜሪካ አርሶ አደሮች የተዳቀሉ ዝርያዎችን የምርታቸውን 85 በመቶ እንደሚሸፍንም ለአብነት በመጠቆም። 

በሌላ በኩል ከአፈር ሁኔታ ጋር የተገናዘበ የኬሚካል ጸር-ተባይ መድሃኒቶችን አርሶ አደሮች በሥፋት ሊጠቀሙ እንደሚገባም አስተባባሪዋ ያስገነዘቡት።

ይህንንና ሌሎችን ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ አሜሪካ ከአፍሪካ አገሮች ጎን በመቆም ተምቹን ለማጥፋት ርብርብ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን  ተናግረዋል።

የአሜሪካ ተምች  ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ የገባ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ከአምስት ክልሎች በላይ መዛመቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።  

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 2/2010 የገለልተኛ አገራት ንቅናቄ ስብሰባ በአዘርባጃን ባኩ ከተማ መካሄዱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ የአፍሪካን ቡድን ወክለው ባደረጉት ንግግር ግጭትን ለማስወገድ የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ትብብር አስፈላጊነት ገልጸዋል።

አፍሪካ ለገለልተኛ አገራት ንቅናቄ እሴቶችና መርሆዎች መከበር ቁርጠኛ ናት፤ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና በሰለጠነ መንገድ ለመከራከር አፍሪካዊያን አበክረው ይሰራሉ ብለዋል።

ግጭትን መከላከልና የድህረ ግጭት መልሶ ግንባታ ላይ በሚገባ ለመስራት የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከጅቡቲ አቻቸው ሞሃመድ ዓሊ ሀሰንና ከሱዳኑ አቻቸው አምባሳደር ሞሃመድ አብደላ ኢድሪስ ጋር በሁለትዮሽና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በአዛርባጃን የኢትዮጵያ የክብር ቆንስላ ከሆኑት ሴሪሁን አላክባሮቭ ጋርም የሁለቱን አገራት ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

በክብር ቆንስላው አስተባባሪነት የአዘርባጃን የቢዝነስ ቡድን ኢትዮጵያን ይጎበኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

 

 

Published in ፖለቲካ

ጎንደር ሚያዝያ 2/2010 ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶችን ለትውልድ ለማስተላለፍ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የታሪክ ማዕከላትን በማቋቋም ሊሰሩ እንደሚገባ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።

150ኛ ዓመት የዳግማዊ ቴዎድሮስ ዝክረ ሰማዕታት ዓለምአቀፍ ጉባኤ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ዝግጅቶች ዛሬ መከበር ጀምሯል፡፡

በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው እንደተናገሩት የክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች ትውልድን ለመቅረጽ ታሪኮችን አጉልቶ በማውጣት ኢትዮጵያዊ አንድነትን ሊያጠናክሩ ይገባል፡፡

በታሪክ ትልቅ ስፍራና ግምት የሚሰጣቸው አጼ ቴዎድሮስ ለሀገር አንድነት መጠናከር ፣ ለዘመናዊ ስልጣኔና ቴክኖሎጂ መስፋፋት ፋና ወጊ ተግባራት ማከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

"ዩኒቨርሲቲዎች ዘመን ተሻጋሪ ሀገራዊ ታሪኮች ሳይበረዙና ሳይከለሱ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ በማድረግ በኩል የታሪክ ማዕከላትን በማቋቋም ለታሪክ ጥናትና ምርምር ስራዎች ትኩረት ሊሰጡ ይገባል"ብለዋል፡፡

የአጼ ቴዎድሮስ ግለ ታሪክ በጥልቅ ጥናትና ምርምር ላይ በመደገፍ ከህትመት ባለፈ በድራማ፣ በቴአትርና በፊልም ጭምር ተዘጋጅቶ ትውልዱ ታሪኩን እንዲያውቅ በማድረግ በኩል ምሁራን አጥብቀው ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ከቋራ እስከ መቅደላ ያሉትን የአጼ ቴዎድሮስ የታሪካዊ ሥፍራዎች የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራ ከማድረግ ጀምሮ የአጼ ቴዎድሮስ ፋውንዴሽን በመመስረት ሙዚየሞችን ለማቋቋም ትኩረት እንደሚደረግ ዶክተር ሂሩት ተናግረዋል፡፡

"ህጋዊና ዲፕሎማሲያዊ አሰራሮችን በመከተል በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ቅርስ የማስመለሰ ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቢሮው የበኩል ድጋፍ ይደረጋል" ብለዋል፡፡    

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ደላሳኝ መንገሻ በበኩላቸው " በመቅደላ ጦርነት ወቅት በእንግሊዞች ተዘርፈው የተሰወዱ ቅርሶች እንዲመለሱ በማድረግ በኩል ዩኒቨርሲቲው ከአጋር አካላት ጋር ተባብሮ ይሰራል" ብለዋል፡፡

በአጼ ቴዎድሮስ የትውልድ ሥፍራ ቋሚ ኃውልት ከማቆም ጀምሮ ሙዚየም በማቋቋም በየአካባቢው በግለሰቦችና በተቋማት የሚገኙ ቅርሶችን የማሰባሰብና የማደራጀት ሥራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባባል በበኩላቸው አጼ ቴዎድሮስ በቴክኖሎጂና በእውቀት የበለጸገች አንዲት ኢትዮጵያን ለመገንባት ወደፊት ቀድመው በማሰብ ሲታትሩ የነበሩ ታላቅ መሪ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

የዘመኑ ትውልድ ይህ አኩሪ ታሪክ ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ዛሬም እንደትናንቱ ለሀገሩ አንድነትና ክብር በጋራ ሊቆም እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገራት የተጋበዙ ምሁራን አጼ ቴዎድሮስ ከውልደት እስከ ሞት ዘመናቸው ያከናወኗቸውን ታሪካዊ ተግባራት አስመልክቶ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተመልክቷል፡፡

ከእዚህ በተጨማሪ የአጼ ቴዎድሮስን ሕያው ሥራዎች የሚዘክሩ የኪነጥበባዊ ዝግጅቶች የሚቀርቡ ሲሆን የተዘጋጀው የፎቶ አውደ ርዕይም በተሳታፊዎች እንደሚጎበኝ ተመልክቷል፡፡

ለሁለት ቀናት የሚቆየውን የአጼ ቴዎድሮስ 150ኛ ዓመት የዝክረ ሰማዕታት ዓለምአቀፍ ጉባኤ በክልሉ የሚገኙ 10 ዩኒቨርሲቲዎች ከአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋራ በመተባበር ያዘጋጁት ነው።

በጉባኤውም የታሪክ ምሁራን ፣ አርቲስቶች፣ ጋዜጠኞች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የክልልና የዞን አመራሮች ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል፡፡

ዝክረ ጉባኤው ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመቀጠል በደብረታቦርና በመቅዳላ ዩኒቨርሲቲዎች የሚከበር ሲሆን 30 ጥናታዊ ጽሁፎችም ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።   

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 2/2010 በኢትዮጵያ የተካሄደውን ሠላማዊ የስልጣን ሽግግር እንደሚያደንቁና ለአፍሪካም በአርዓያነት ሊወሰድ እንደሚገባው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በላኩት መልዕክት ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኬንያዋን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ሞኒካ ጁማ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯም የፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታን መልዕክት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል።

ፕሬዚዳንቱ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ጋር በአገራቱ መካከል የነበረውን ጠንካራ ወዳጅነት የበለጠ በማጠናከር በጋራ ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት መግለፃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በኬንያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እንዲያደርጉ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ግብዣ እንዳቀረቡላቸውም ተናግረዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ሁለቱ አገራት ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ወዳጅነትና ጉርብትና እንዳላቸው አውስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቀረበላቸው ግብዣ መሰረት ኬንያን ለመጎብኘት ቃል መግባታቸውን ዶክተር ወርቅነህ ገልፀዋል።

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 2/2010 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በከተማዋ ታጥረው በተቀመጡ 138 ቦታዎች ላይ አፋጣኝ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

በከተማዋ ለልማት በሚል ለረጅም ጊዜ ታጥረው የተቀመጡ 138 ቦታዎች መኖራቸውን ቋሚ ኮሚቴው ባደረገው የመስክ ምልከታ አረጋግጧል።

ቦታዎቹ ሳይለሙ የቀሩት ከበጀት እጥረትና ከቸልተኝነት የተነሳ እንደሆነ ተገልጿል።

የቋሚ ኮሚቴው ተወካይ ሰብሳቢ አቶ ጳውሎስ ደጉ ቋሚ ኮሚቴው የቢሮውን የ2010 ዓ ም የዘጠኝ ወር የእቅድ አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በከተማዋ በግል ባለሃብቶች፣ በመንግስት ተቋማትና በዲፕሎማቲክ ተቋማት ጥያቄ እንዲለሙ የተላለፉ በርካታ ቦታዎች ሳይለሙ ለዓመታት ታጥረው ተቀምጠዋል።

ቢሮው ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎችን ከማስመለስና በአልሚዎች ላይ እርምጃ ከመውሰድ አኳያ ያለው ልምድ እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም በሚፈለገው ልክ መጓዝ አለመቻሉን ገልጸዋል።

በግል ባለሃብቶች ለመልማት ከተያዙትና ታጥረው ከተቀመጡት ቦታዎች አብዛኞቹ በሚድሮክ ኩባንያ የተያዙ መሆናቸውን አቶ ጳውሎስ ጠቁመዋል።

'የከተማው መሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ታጥረው ለረጅም ጊዜ ሳይለሙ የተቀመጡ ቦታዎችን ውል በአፋጣኝ በማቋረጥ ለሌሎች ማልማት ለሚችሉ ባለሃብቶች ማስተላለፍ ይገባዋል' ብለዋል።

በቢሮው የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጀማል አሊ በበኩላቸው ቋሚ ኮሚቴው የሰጠው አስተያየት ትክክል መሆኑን ገልጸዋል።

'በግል ባለሃብቶች፣ በመንግስት ድርጅቶችና በሌሎች የውጭ ኤምባሲዎችና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለመልማት የተያዙ በርካታ ቦታዎች ሳይለሙ ታጥረው ይገኛሉ' ብለዋል።

የግል ባለሃብቶች ሊያለሙ ከወሰዷቸው ቦታዎች አብዛኞቹ የሚድሮክ ኩባንያ የያዛቸው መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የመንግስት ተቋማት የያዙትን ቦታ በበጀት እጥረት ምክንያት መገንባት ያልቻሉ፤ የመገንባት አቅም ያላቸው ድርጅቶች ደግሞ በቸልተኝነት ሳይገነቡ የቀሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የግል ባለሃብቶች ለግንባታ ቅድመ ዝግጅት ሳያደርጉ ቦታዎችን ከወሰዱ በኋላ 'ምንም አንሆንም' በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ይዘው ያስቀመጧቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

የሚድሮክ ኩባንያን በተመለከተ 'ባለሃብቱ ሼህ ሁሴን አሊ አላሙዲን ከዚህ በፊት ለአገር በሰሯቸው የልማት ስራዎችና ለዜጎች የሚፈጥሯቸውን የስራ እድሎች ታሳቢ በማድረግ መንግስት ለረጅም ጊዜ ታግሷቸው ቆይቷል' ብለዋል።

በመሆኑም ቢሮው አሁን ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ድርጅቱ አጥሮ የያዛቸው ቦታዎች ውል የሚያቋርጥበትን መንገድ እንደሚያመቻች አስረድተዋል።

በአስራ ስድስት ኤምባሲዎችና በሁለት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለመልማት ተወስደው ሳይለሙ ታጥረው የተቀመጡ  ቦታዎችን በተመለከተ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

እስካሁን 29 የሚደርሱ ቦታዎች የማስመለስ ስራ የተሰራ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው በመንግስትና በግል ድርጅቶች ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎችን በማስመለስ ማልማት ለሚችል ባለሃብትና ድርጅት ለማስተላለፍ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ ሚያዝያ 2/82010 በትግራይ ማዕከላዊ ዞን 100ሺህ ብር የመንግስት ገንዘብ ያባከኑ ሰባት ግለሰቦች በእስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ የተወሰነባቸው መሆኑን  የክልሉ  የስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ወልደገብርኤል ወልደማርያም ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ ገንዘቡን አባክነዋል የተባሉት ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በዓብይ ዓዲ ከተማ  ውሀና ፍሳሽ ጽህፈት ቤት የስራ ኃላፊዎችና  ሰራተኞች ሆነው ሲሰሩ በቆዩባቸው ወቅት ነው፡፡

 በእነዚህ ጊዜያት ለአበልና ለመዝናኛ ዝግጅት 100 ሺህ ብር የመንግስት ገንዘብ አልአግባብ ወጪ በማድረግ ክስ ተመስርቶባቸዋል ።

 የኮሚሽኑ አቃቢ ህግ በሰነድ ማስረጃ በማስደገፍ ያቀረበባቸው ክስ  ግለሰቦቹ ማስተባበል ባለመቻላቸው ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው  የዓብይ ዓዲ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መጋቢት 25 ቀን 2010 ዓ.ም ባዋለው ችሎት የቅጣት ውሳኔ አስታልፎባቸዋል፡፡፡

 በዚህም የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ የነበረው ሞድሮስ መረሳ በ11 ዓመት ጽኑ እስራትና በ3ሺህ ብር፣ የጽሀፈት ቤቱ ኃላፊ ገብረ አረጋይ ገብረ ህይወት በአራት ዓመት ጽኑ እስራትና በ1ሺህ 500 ብር ቅጣት ተወስኖባቸዋል ።

 እንዲሁም የጽህፈት ቤቱ ሰራተኛች ብስራት ገብረ ህይወት በአንድ አመት ከሁለት ወር እስራትና በ1ሺህ ብር፣ ተክለ ብርሀን ብርሀነና ተስፋዬ መሀሪ እያንዳንዳቸው በአንድ ዓመት ከአራት ወር እስራትና በ1ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

 አሸናፊ አብርሀና ጨርቆስ ገብረ ዮሀንስ የተባሉ ሰራተኞች ደግሞ በአስርና በስምንት ወራት እስራትና በ1ሺህ ብር እንዲቀጡ ውሳኔ የተላለፈባቸው መሆኑን አቶ ወልደገብርኤል  አስታውቀዋል ።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 2/2010 በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ና ህዝቦች ክልል የሐዋሳ አየር ማረፊያ- ጥቁር ውሃ የአስፓልት የኮንክሪት ደረጃ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ሂደት እየተፋጠነ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

 በሐዋሳ ከተማ ለተገነባው የአየር ማረፊያ መዳረሻ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የሚገነባው 33 ነጥብ 51 ኪሎ ሜትር መንገድ 592 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪን ይጠይቃል።

 መንገዱ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ለአየር ማረፊያው ምቹ መዳረሻ ከመፍጠር ባሻገር የአካባቢው የግብርና ምርቶችን  ለገበያ ለማቅረብ እንዲሁም ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚወጡ ምርቶችን በቀላሉ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ያግዛል።

 እንደ የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ገለጻ መንገዱ ወደ ሐዋሳ ለጉብኝት የሚሄዱ ቱሪስቶች የተቀላጠፈ የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠትም በላይ በሐይቁ ዙሪያ ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።

 መንገዱ ግንባታ  በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ግንባታው በሚከናወንባቸው መስመሮች ላይ የሚገኙ የመስተዳድር አካላትና ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ አቶ ሳምሶን ጠይቀዋል።

 የመንገድ ፕሮጀክቱ ተጠሪ መሃንዲስ አቶ አስማማዉ ዘወትር በበኩላቸው፤የመንገድ ግንባታው ባለስልጣኑ ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል እያደገበት የሚገኝ በመሆኑ ግንባታው እየተፋጠነ ይገኛል።

 ይሁን እንጂ የመንገድ ፕሮጀክቱ በታቀደለት ጊዜ እንዳይሄድ የወሰን ማስከበር ችግሮች ስጋት መሆናቸውን ይገልፃሉ።

 መንገዱ ባለስልጣኑ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን እሰራዋለው ብሎ ካካተታቸው ፕሮጀክቶች አንዱ ሲሆን የመንገድ ስፋቱ በገጠር 10 ሜትር ነው።

 በከተማ ደግሞ የእግረኛ መንገድን ጨምሮ 23 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን የመንገዱ ግንባታ ሙሉ ወጪው የሚሸፈነው በኢትዮጵያ መንግስት መሆኑ ተገልጿል።

 የመንገዱ ግንባታ የሚከወነው  ከቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ሲሲሲሲ ሲሆን ምህንድስናውን በማማከርና በቁጥጥር ስራው የትራንስፖርት ኮንስትራክሽን ዲዛይን አክሲዮን የተባለ አማካሪ ድርጅት ነው።

 በህዳር ወር 2010 ዓ ም የተጀመረው የዚህ መንገድ ግንባታ ከ18 ወራት በኋላ በመጪው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

       

 

 

Published in ኢኮኖሚ
Tuesday, 10 April 2018 22:37

ገዳ ሁሌ

ሚፍታህ አህመድ ከኢዜአ

በኦሮሞ ታሪክና በጥንቱ የገዳ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ገዳ ሁሌ ከፍተኛ ታሪክና ትልቅ ሥፍራ ያለው ነው። ይህ ተቋም ከፍተኛና ወሳኝ የሆነ የኦሮሞ ማህበራዊ፣ ባህላዊና የፖለቲካም ተቋም እንደሆነ ይገለጻል።

የኦሮሞ ህዝብ  የገዳ ስርአትን በማዕከልነት በባሌ ውስጥ በሚገኘው መዳወላቡን በጋራ ሲጠቀምበት ከቆየ በኃላ በ1450 አካባቢ የገዳን  መታደስ (haroomsa gadaa) በኋላ በየአካባቢው የሚገኙ ኦሮሞዎች መደወላቡ ድረስ ለመመላለስ ያለባቸውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ታስቦ የመጫ  እና ቱለማ ኦሮሞ ዱከም አካባቢ በሚገኘው  ኦዳነቤ ላይ የገዳ ስርዓትን መፈጸም እንደጀመሩ ይነገራል፡፡

በጅማ ዩኒቨርስቲ በኦሮሞ ፎክሎርና ስነጽሁፍ ትምህርት ክፍል የኦሮሞ ባህላዊ ፣ ኃይማኖታዊና ቅርስ ጥበቃ መምህር  አቶ ደሬሳ ዴቡ እንደሚሉት የመጫ ኦሮሞ  የያዘው መሬት ሰፊ ነው ።

 በአሁኑ ጊዜ 9 ዞኖችን ማለትም ምዕራብ ሸዋ  ፣ ደቡብ ምእራብ ሸዋ አራቱ ወለጋ  ፣ ኢሉአባቦር ፣ ቡኖ በደሌ እና የጅማ ዞን የሚገኝበት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህ አከባቢዎች ኦዳነቤ ድረስ በመሄድ የገዳ ጉባኤንና ሌሎች ስርአቶችን ለመፈጸም ስለተቸገሩ   ምዕራብ ሸዋ ኢሉ ገላን ወረዳ ብስል አካባቢ እንዲያከብሩ በድጋሚ መደረጉን ይገልጻሉ፡፡

በርካታ ህጎችን እንዳወጣ የሚነገርለት የመጫ ኦሮሞ መሪ  መካ ቢለም በየአካባቢው የሚገኙ ኦሮሞች በየስምንት አመቱ ብስል ላይ እና መዳወላቡ እየተገናኙ አዲስ የወጡ እና የተሰረዙ ህጎችን እንደዚሁም ሌሎች ጉዳዮች ይዘው በመመለስ ተግባራዊ እንዲያደረጉና በየአካባቢያቸውም የገዳ ቅርንጫፍ  እንዲመሰረቱ ህግ አውጥቷል፡፡

በዚህ መስረት የጅማ ኦሮሞ ከ240 ዓመት በፊት ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ እና አጠቃላይ የውይይት ዘይቤውን የሚመራው ስርአት በጅማ ዞን  በኦሞናዳ ወረዳ በተመሰረተው  በኦዳ ገዳ ሁሌ ስርአት  መሰረት እንዲፈፀም ሆነ ፡፡ በስርአቱ የጅማ ኦሮሞ ይዳኝበታል ። መሪያቸውን ይመርጣሉ፣ ይተዳደሩበታል ። እንደ ሰርግ፣ ለቅሶ፣ ደቦ የመሳሰሉትን ማህበራዊ ጉዳዮች ይፈጸሙበታል፡፡

በፖለቲካው ዘርፍ ደግሞ ኦዳ ጀላ በየ8 አመቱ ወደ መደወላቡ እየሄዱ የተሻሻሉ ህጎችን የሚያመጡበት ፣ኦዳ ጃኒ ቅድመ ዝግጅት የሚያደረጉበት፣ኦዳ ጃለሌ የእርቅ ስነ-ስርአት የሚፈጽሙበት፣ኦዳ ሙርቲ ውሳኔ የሚተላለፍበት ስረዓት የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

ኦደ ሁሌን የመሰረቱት ባቡ ኮዬ የተባሉ ሰው ሲሆኑ በከፍታ ቦታ ላይ የሚፈጸምና ለጅማ ኦሮሞ  አጠቃላይ አገልግሎት የሚሰጥ የገዳ ቅርጫፍ የሆነ ስረአት ነው፡፡

                                      የገዳ ሁሌ ስረአት መዳከም

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የኦሮሞ ጥናት  ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር ተሾመ እገሬ እንደገለፁት የገዳ ሁሌ   ባህላዊው ስርአት ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ  እስከ 1830 አካባቢ ድረስ በጅማ ኦሮሞ ዘንድ በስፋት የሚታወቅና የሚተገበር እንደነበር በታሪክ ሰነዶች ላይ ተመዝገቦ ይገኛል ።

የኃይማኖትና የታሪክ ሊቃውንትም በጉዳዩ ዙሪያ የሚስማሙ መሆኑን ይናገራሉ ፡፡ ይህ የገዳ ስርአት ከ1830 ዓም ገዳማ ጀምሮ አሁን እስካለበት ድረስ እድገት ከማሳየት ይልቅ ጉዞውን ቁልቁል ሆኖ እስከመረሳት የደረሰ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡

ለኦዳ ሁሌ መዳክም ምክንያት ከ1800 ዓ.ም አከባቢ የመጡት  የንጉሳዊያን የአስተዳደር ስርአት በመንስኤነት እንደሚነሳ አቶ ደሬሳ ይናገራሉ፡፡  የንጉሳዊያን ቤተቦችን በተለይ አባዱላዎች ስልጣንን በየስምንት አመቱ እየጠበቁ ለተተኪ ከማስተላለፍ ይልቅ በጠቅላይነት የመያዝ ሁኔታና  በቤተሰብ ማድረጋቸው ለመዳከሙ እንደመንስኤ አንዱ ምክንያት ሆኖ ተጠቅሷል ።

ሌላው በ1902 ዓ.ም አካባቢ በየስምንት አመቱ መደወላቡ ላይ በመሄድ ጉባኤ ላይ የመካፈል ባህል በአዋጅ የመከልከሉ ጉዳይ ለመዳከሙ በምክንያትነት ይነሳል፡፡

የኦዳ ሁሉ ስርዓት በወቅቱ በነበረው አስተዳደር ተፅእኖ ቢዳከምም ማህባራዊ፣ ስነምግባራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን እስካሁን ድረስ የቀጠለበት ሁኔታ አለ፡፡ ለአብነትም   ሬጂ፣ ጂጋ፣ በቀሮ፣ በደቦና በዳዶ አብሮ የመስራት፣  የተጣሉ የሚያስታርቁበትን ባህል   እንደቀጠለ ይገኛል፡፡

                                       ሴቶችና ገዳ ሁሌ

በገዳ ሁሌ ስርአት የአስተዳደር ስልጣን የሚሰጠው ህዝብን ለማገልግል እራሱን ለሰጠ ሰው ነው፡፡ በገዳ ሁሌ የአስተዳደር ኃላፊነት ከባድ ሸክም ነው፡፡ የገዳ ሁሌ ስርአት ተጠናክሮ ተግባራዊ በሚደረግበት ወቅት ምንም አይነት የትራንስፖርት አገልግሎት በሌለበት ሁኔታ እረጅም እርቀትን ተንቀሳቅሶ ማገልገል የሚጠይቅ በመሆኑ  ሴቶች ካለባቸው ማህበራዊ ኃላፊነትና ጫና ጋር ተዳምሮ ወደ ስልጣን አይመጡም ፡፡

ነገር ግን የተለየ ብቃት ካላት የማስተዳደር ስልጠን ይሰጥ እንደነበር  በጅማ ከተማ የአገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ሙህዲን ጀማል ይናገራሉ፡፡ ለአብነትም መካ ኦሌ የተባሉ ብልህ ሴት አባገዳ ሆነው ለስምንት አመት አገልግለዋል፡፡ በስልጣን ዘመናቸውም  በብረት፣ በቆዳ ፣ በሸክላ፤ በሽመና እና በንግድ ስራ ችሎታቸው የሚታወቁ ነገር ግን  በህብረተሰቡ ዘንድ የሚናቁትን የእጅ ባለሙያዎች  ከሰው እኩል መሆናቸውን በሙያቸው ደግሞ ከሌሎች ከማይሰሩት ሰዎች በላይ መሆናቸውን እውቅና የሰጡ የመጀመሪያው አባ ገዳ ሴት መሆናቸውን ይመሰክራሉ፡፡

አባገዳዋ  አዋቂ ሆኖ ከሰው ጋር ከማይማከር  ይልቅ አላዋቂ ሆኖ ከሰው ጋር የሚማከር  ይሻሻል (beekaa namaan hin mari’aannee irra wallaalaa namaan mari’atu wayyaa) በሚል እምነታቸው  በስፋት ይታወቃሉ::

የገዳ ሁሌ ስርአት ከሚታወቅባቸው ባህሪያት አንዱ ሃርሞሳ ገዳ ወይም በገዳ መታደስ  ነው ፡፡ የገዳ ስርአት እንደየወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ እራሱን እያደሰና እየበለጸገ የሚሄድ ስርአት ነው፡፡ በጅማ ኦሮሞ ዘንድ  በስፋት ይተገበር የነበረው የገዳ ስርአት ተዳክሞ ከቆየ በኋላ ጥር 14/2010 ዓ.ም የጅማ ዩኒቭርሲቲ የኦሮሞ ባህል ጥናት ተቋም ከተመሰረተ ከሶስት አመት በኋላ የተዘነጋውን የገዳ ሁሌ ሰርአት ወደ ነበረበት ማህበራዊ መሰረት ለመመለስ ያለመ የምርምር ጉባኤ ተካሄዷል ። የጅማን የገዳ ስርአት የመመለስ ስነስርአትም ተካሔዷል፡፡

በአዲስ የተመሰረተው የገዳ ሁሌ ስርአት በውስጡ ያሉትን ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ ፣ታሪካዊ፣ማህበራዊ፣ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ እሴቶችን በደንብ በማውጣት ከማህበረሰቡ ጋር ለማገናኘት በቀጣይ በትኩረት የመስራትን ግብ በማስቀመጥ ሀሮምሳውን(መታደስን) ጉዞ "ሀ" ብሎ ጅምሯል፡፡ ወደ ነበረበት ከፍታ ለመመለስና  ወደ ተሻለ ከፍታ ለማሸጋገር  የሙህራን፣ የመንግስትና ሁሉንም የህበረተሰቡ ክፍል በንቃት ማሳተፍ ወሳኝ ይሆናል፡፡

 

Published in ዜና ሐተታ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን