አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Sunday, 01 April 2018

መጋቢት 23/2010 የትግራይ ክልል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ለተማራማሪ ወጣቶችና የጤና ባለሙያዎች የስልጠና ድጋፍና እውቅና መስጠቱን አስታወቀ።

ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለሃገር እድገትና ልማት መፋጠን ያለውን ፋይዳ አስመልክቶ ቢሮው ለወረዳ ምክር ቤት አባላት፣ አፈ ጉባኤዎችና የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ያዘጋጀው የአቅም ግንባታ ስልጠና በአክሱም ከተማ ተካሂዷል።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር አብረሃ ኪሮስ በስልጠናው መድረክ እንዳሉት፣መስሪያ ቤታቸው በተያዘው የበጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 280 ለሚሆኑ ተማራማሪ ወጣቶች የተለያዩ ሙያዊ ድጋፍና እውቅና ሰጥቷል።

በክልሉ በሚገኙ 32 ሆስፒታሎች ውስጥ ለሚሰሩ የህክምና ባለሙያዎችም ከጨረር አደጋ ራሳቸውን መከላከል እንዲችሉ የአጠቃቀም ትምህርትና ስልጠና መስጠቱን ተናግሯል።

በክልሉ የሚገኙ 28 ኮሌጆችን ጨምሮ ለተለያዩ ተቋማት አገልግሎት ሊውሉ የሚችሉና በሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ አራት ሺህ ያህል መረጃዎችን ማሰራጨታቸውንም ጠቅሰዋል።

የከተማና የገጠር ልማት  ለማፋጠን የሚያግዙ ስድስት ዓይነት የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራዊ ተደርጓል ዶክተር አብረሃ እንደገለጹት፡፡

በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተደገፈ ፈጣን ልማት ለማረጋገጥ በየደረጃው የሚገኙ የምክር ቤት አበላት በህዝብና መንግስት የተጣለባቸው ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የዓድዋ ከተማ ምክር ቤት አባል መምህር አስመላሽ አሳየሀኝ በበኩላቸው በከተማው የሚገኙ የሙያና ቴክኒክ ማሰልጠኛ ማዕከላት የሳይንስና ምርምር ስፍራ እንዲሆኑ የምክርቤት አባላት ክትትልና ድጋፍ እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የታህታይ ማይጨው ወረዳ ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ መኮንን  ወልደስምኦን" በሳይንሳዊ መንገድ መስራት ፈጣን ልማትና እድገት ማረጋገጥ እንደሚቻል አመላካች የሆኑ የፈጠራ ስራዎችን ጀምረናል" ብለዋል።

ወጣቶችና ምሁራን የሀገር እድገትና ብልፅግና ለማፋጠን የሚያስችሉ ምርምሮችን እውን በማድረግ ኃላፊነታቸው ሊወጡ እንደሚገባ ያመለከቱት የምክር ቤት አባላቱ  ይህንን በመደገፍም የድርኛቸውን እንደሚወጡ ተናግረል፡፡

በዓድዋ ከተማ ምክር ቤት የሴቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ መምህርት ያለም ገብረስላሰ እንዳሉት ስልጠናው እያንዳንዱ ስራ በሳይንሳዊ መንገድ እንዲታሰብና በተግባርም እንዲተረጎም የሚያችል ግንዛቤ ያስጨበጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በተካሄደው ስልጠና ትኩረት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል የኮሪያ ተሞክሮ በኢትዮጵያ፣ የክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በልማት ያለውን ፋይዳ የሚሉት  ይገኙበታል።

በስልጠናው ከ14 የክልሉ ወረዳዎች የተውጣጡ ከ180 በላይ የወረዳ ምክር ቤት አባላት፣ አፈ ጉባኤዎችና የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ተሳትፈዋል፡፡

 

ባህርዳር መጋቢት 23/2010 በምዕራብ ጎጃም ዞን በ2010/2011 የምርት ዘመን ከ550 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብል ለማልማት የእርሻ ስራ እየተካሄደ ነው፡፡

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ስሜነህ አያሌው ለኢዜአ እንደገለጹት ከዚሁ መሬት ውስጥ እስካሁን 342 ሺህ ሄክታር መሬት ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ዙር ታርሷል፡፡

በምርት ዘመኑ ከሚለማው መሬት ከ242 ሺህ ሄክታር በላይ ለኢንዱስትሪ ግብዓት በሚውል ሰብል በኩታ ገጠም እርሻ የሚካሄድ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በኩታ ገጠም እርሻ የሚሳተፉ አርሶ አደሮችንና የሚለማውን መሬት ቀድሞ የመለየቱ ስራም ከወዲሁ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

አቶ ስሜነህ እንዳሉት አጠቃላይ የሰብል ምርታማነትን በአማካኝ አሁን ካለበት በሄክታር 39 ኩንታል ወደ 44 ኩንታል ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ ነው።  

"የምርት ጭማሪውን ለማሳካትም ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ እየተካሄዱ በሚገኙ የመኽር ሰብል ንቅናቄ መድረኮች በእርሻ ድግግሞሽ፣ በግብዓት አጠቃቀም፣ በተባይ አሰሳና መከላከል ላይ ያተኮረ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል" ብለዋል።

በመጪው የመኽር ወቅት በዞኑ በተለያየ ሰብል ለማልማት በዕቅድ ከተያዘው ከ550 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት 24 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል፡፡

በዞኑ ጃቢጠህናን ወረዳ የማና ውስጠጉልት ቀበሌ አርሶ አደር ብርሃኔ ካሴ በሰጡት አስተያየት ያላቸውን ሶስት ሄክታር መሬት በመኽሩ ወቅት ለማልማት የእርሻ ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

በየዓመቱ በባለሙያዎች የሚሰጣቸውን ስልጠና መሰረት አድርገው የእርሻ መሬታቸውን የምርት ማሳደጊያ ግብዓት ተጠቅመው የተለያየ ሰብል በማልማት ተጠቃሚ መሆን እንደጀመሩ ጠቁመዋል።  

የሰብል ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችል ስልጠና በየዓመቱ በባለሙያዎች እንደሚሰጣቸው የገለጹት ደግሞ በዚሁ ወረዳ የወንጌ በርቀኝ ቀበሌ አርሶ አደር ህብስቱ ንብረት ናቸው።

የሚወስዱትን ስልጠና መሰረት አድርገው የእርሻ ማሳቸውን ደጋግመው አርሰው በማለስለስ የተለያየ ሰብል በማልማት ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን በ2009/ 2010 የምርት ዘመን ከለማው 551 ሺህ ሄክታር መሬት ከ23 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱ ታውቋል፡፡   

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 23/ ኒጀር በ 2019 ለምታስተናግደው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቡሩንዲ አቻው 2-0 ተሸንፏል፡፡

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሔደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የቡሩንዲዎቹ ሞሀመድ ጁማና ሻካ ቢያቤኑ የማሸነፊያ ግቦችን ከመረብ አዋህደዋል፡፡

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት ብሔራዊ ቡድን ባሳየው ከፍተኛ የቅንጅትና የመናበብ ችግር በሜዳው ላይ ለሽንፈት ተዳርጓል፡፡

ከሶስት ሳምንት በኃላ የመልስ ጨዋታው በቡሩንዲ ሜዳ ተካሂዶ በደርሶ መልስ የሚያሸንፈው ቡድን ከሱዳን ብሔራዊ ቡድን ጋር ይገናኛል፡፡

Published in ስፖርት

አርባምንጭ መጋቢት 23/2010 ወላጆቻቸውን ያጡና ተንከባካቢ የሌላቸው ችግረኛ አረጋዊያንን ለመርዳት ባለሀብቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ፡፡

ሜሪ ጆይ የልማት ማህበር ኢትዮጵያዊያን ለኢትዮጵያዊያን በተሰኘው ፕሮግራሙ በአርባምንጭ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡

የማህበሩ መስራችና ስራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት ሜሪ ጆይ ትብብር አርባምንጭ ከተማ የሚገኙ ባለሀብቶችና የመንግስት ተቋማት በማስተባበር ከ30 በላይ ህጻናትንና አረጋዊያን መርዳት ጀምሯል፡፡

"ከችግሩ አንጻር ስራው ትንሽ ነው" ያሉት ሲስተር ዘቢደር ወላጆቻቸውን ያጡና ተንከባካቢ የሌላቸው አረጋዊያንን ለማገዝ የሚደረገው ጥረት  እንዲጠናከር ባለሀብቶች ከመንግስት ጋር ተቀናጅተው እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአካባቢው ባለሃብቶችና  የመንግስት አካላት ለዚሁ ድጋፍ በአርባ ምንጭ ከተማ ለመገንባት በታቀደው የአረጋዊያን ማዕከል ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጠቁመዋል፡፡

የጋሞ ጎፋ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ፀጋነሽ እንግዳ በበኩላቸው የሜሪ ጆይ በጎ ሥራ የዞኑን ችግር በመፍታት ረገድ ትልቅ ድርሻ ያለው በመሆኑ ለዓላማው መሳካት ከወትሮው  በተሻለ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ የተሳታፉት አርቲስት ችሮታ ከልካይ "ዛሬ ለችግር የተጋለጡ ህፃናት ካልተንከባከብናቸው ነገ የሀገራችን ችግር እንደሚሆኑና ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ የሀገር አለኝታ ማድረግ ይጠበቅብናል" ብሏል፡፡

ወላጆቿን በሞት ያጣችው የ17 ዓመቷ ታዳጊ ምጥነሽ ጉልማ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ሜሪ ጆይ በሚያደርግላት ድጋፍ ያቋረጠችውን ትምህርት መቀጠሏን ተናግራለች፡፡

በየወሩ ከሚሰጣት 300 ብር በተጨማሪ ሌላ የገቢ ማስገኛ ስራ ላይ በመሰማራትና ጠንክራ በማመር ዶክተር የመሆን ፍላጎት እንዳላትም ገልጻለች፡፡

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ሶዶ መጋቢት 23/2010 የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለሶዶ ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ተማሪዎች የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ፡፡

ድጋፉን ያደረጉ በምህንድስና ሳይንስ ኮሌጅ የሃይድሮሊክስና የውሃ ሃብት አስተዳደር  የ3ኛ ዓመት 100  ተማሪዎች ናቸው፡፡

በኮሌጁ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት  ተማሪ ካሳሁን ሰይፉ እንደገለጸው ዓይነ ስውራን ተማሪዎች ሆነው በርካታ ችግሮች እንዳሉባቸው በመስማት ከኪሳቸውና የተለያዩ ገቢ ማግኛ ዘዴዎችን በመጠቀም  ባሰባሰቡት ከ20 ሺህ ብር በላይ ቁሳቁስ ገዝተው ለግሰዋል፡፡

ከለገሷቸው ቁሳቁሶች መካከል ቅባት፣ ጫማዎች ፣አልባሳትና የንጽህና መጠበቂያ የሚገኙበት ሲሆን በተጨማሪም ግቢያቸውን ፣ የመማሪያ ክፍላቸውን በማጽዳት፣ ልብሳቸውን በማጠብና ሌሎችንም አገልግሎቶችን በመስጠት ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ከተማሪዎቹ መካከል አንዱዓለም ዳንሳ በሰጠው አስተያየት የዕረፍት ቀናቸውን በመጠቀም ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ለአካል ጉዳተኞቹ ድጋፍ በማድረጋቸው መደሰቱን  ገልጿል፡፡

የኮሌጁ ተወካይ ዶክተር ሞሲስ ሶሙ በበኩላቸው የተቸገሩትን መርዳት በዕድሜ፣ በአቅምና በተለያዩ አመለካከቶች ልዩነት የሌለበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባልተለመደ መልኩ ተማሪዎቹ በራሳቸው ተነሳስተው በአጭር ቀናት ድጋፉን በማሰባሰብ ዓይነ ስውራን ተማሪዎችን ለማገዝ ያሳዩት መነሳሳት የሚበረታታ መሆኑ ጠቁመው  ድጋፉ ቀጣይነት እንዲኖረው ጥረት አንደሚያደርጉ አመልክተዋል፡፡

በሶዶ ዓይነ በስውራን ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል ተማሪ እህቴናት ባሳዝን ተማሪዎቹ ያደረጉላቸው ድጋፍ የሚፈልጉትና በዚህም ደስተኛ መሆኗን ገልጻለች፡፡

የወላይታ ሶዶ ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ኑሩ በድሩ "ትምህርት ቤቱ ከአቅም ማነስ የተነሳ የልጆቹን ፍላጎት ለማሟላት በተቸገርን ሰዓት ከተማሪዎቹ የተደረገው ድጋፍ አስታዋሽ እንዳላጣን ያመላክታልና ደስ ብሎኛል" ብለዋል፡፡

ልጆቹ ከቤተሰብ ርቀው የሚኖሩ በመሆናቸው ፍቅር የሚሰጥ ሲያገኙ ከፍተኛ ደስታ እንደሚሰማቸው ጠቅሰዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት በ1957 ዓ.ም. የተቋቋመ ሲሆን ብዙዎችን በማስተማር ለቁም ነገር እንዳበቃና በአሁኑ ወቅትም 55 ተማሪዎች እንዳሉት ተመልክቷል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2010 ወጣት ዮሐንስ ታደሰ በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ነው፤ ተወልዶ ያደገውም በዚሁ ክፍለ ከተማ ዘነበ ወርቅ አካባቢ ነው።

ወጣቱ ከልጅነት ዕድሜው ጀምሮ በአካባቢው በሚገኘውና ቁልቋል ሰፈር በሚባለው ሰፈር ባለ ሜዳ  የእረፍት ጊዜውን ያሳልፋል።                          

ዛሬ ግን በልጅነቱ ቦርቆ ያደገበት፣ በጨርቅና  በላስቲክ ኳስ የተጫወተበት ሜዳ ግንባታ እየተካሄደበት በመሆኑ ቤቱ ለመቀመጥ ተገዷል።

የአካባቢው ልጆች መጫዋቻ የነበረው ሜዳ ለግንባታ ስራ መዋሉ በወጣት ዮሐንስ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ነዋሪዎችም ቅሬታ ፈጥሯል።

አቶ የማነህ ታደሰ እንዳሉት ቦታው ብዙ ወጣቶች የሚዝናኑበትና ጊዜያቸውንም የሚያሳለልፉበት እንደነበር ገልጸው አሁን ወጣቶቹ በየሰፈሩ ተቀምጠው ለመዋል መገደዳቸው እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል፡፡

የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወጣቶች ጽህፈት ቤት የወጣት ማዕከላትና ስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ልማት ቡድን መሪ አቶ ወንድወሰን ጥላሁን ቦታው ክፍት ሆኖ በመቆየቱ እንጂ በመሪ ፕላኑ ላይ ለስፖርት ማዘውተሪያ የተተወ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከወጣቶቹ ጥያቄ በፊት ደረጃውን የጠበቀ የስፖርት ማዘውተሪያ ለመገንባት ተፈልጎ የነበረ ቢሆንም ማስተር ፕላኑ ለስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ የማያመላክት በመሆኑ መቅረቱንም ተናግረዋል።

የአስኮና የመድሃኔዓለም አካባቢዎቹ ወጣቶች አለምሰገድ ሌምቤቦ እና አስረስ ማሞም  ችግሩ በየአካባቢያቸው እንዳለ ነው የተናገሩት።

የከተማዋ ስፖርት ቢሮ የወጣት ማዕከላትና የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ንዑስ የስራ ሂደት መሪ አቶ ብርሃኑ ባዩ ችግሩን በፕላን ኮሚሽን በተቀመጠው መሰረት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በተለያዩ ወረዳዎች፣ ክፍለ ከተሞችና የጋራ መኖሪያ ቦታዎች ላይ  በማስተር ፕላኑ መሰረት ሶስት በአንድ ፣ ሁለት በአንድ ሜዳዎች እየተገነቡ መሆኑን ገልጸዋል።

በፕላን ኮሚሽን ለስፖርት ማዘውተሪያ ከተቀመጡ ቦታዎች መካከል ለሌላ ዓላማ የዋለ አለመኖሩንም ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ቀድሞውኑ በመኖሪያ ቦታነት የተያዙና በመልሶ ማልማት ላይ የሚገኙ ተጨማሪ የስፖርት ማዘውተሪያ የሚገነባባቸው እንደ ልደታ፣ ኮልፊ ቀራኒንዮና አራዳ ክፍለ ከተሞች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ ፕላን ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ለአለም ብርሀኑ በመዲናዋ ሁሉም ወረዳዎች የስፖርት ማዘውተሪያ የሚሆኑ ቦታዎች በማስተር ፕላኑ መቀመጣቸውን ገልጸዋል።

መሪ ፕላኑ በዋናነት ያሉትን መጠበቅ ላይ ትኩረት አድርጎ የተሰራ ሲሆን ትላልቅ የስታዲየምና የጎልፍ መጫዋቻዎችንም በአዲስ መልክ  ያካተተ ነው።

በከተማዋ እየተገነባ ካለው ብሄራዊ ስታዲየም በተጨማሪ ለቡ አካባቢ ትልቅ ስታዲየም ማሰራት የሚችል ቦታ በማስተር ፕላኑ ላይ መኖሩን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ጀርባም ለጎልፍ መጫወቻ አገልግሎት የሚውል ቦታ በማስተር ፕላኑ ተቀምጧል ነው ያሉት።

ይህም ወደፊት ስታዲየምና ሌሎች የስፖርት ማዘውተሪያዎችን መገንባት ሲያስፈልግ  የቦታ ችግር  እንዳያጋጥም ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ 633 የስፖርት ማዘውተሪያዎች ሲኖሩ 344 ያህሉ በመንግስት ቀሪዎቹ ደግሞ በግል ተቋማት፣ በመኖሪያና በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ መሆናቸውን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

Published in ስፖርት

አዳማ  መጋቢት 23/2010 ኢትዮጵያ በደን ሀብቷ አምቃ ለምትይዘው በካይ ጋዝ ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ የካርበን ሽያጭ ገቢ ለማግኘት በድርድር ላይ መሆኗን የአካባቢ ደን ልማትና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ የፖሊስ ህግና ደረጃዎች  ዳይሬክተር ዶክተር አየለ ሄገባ ለኢዜአ እንዳሉት ሀገሪቱ ወደ አካባቢ አየር ንብረት የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ  በደን ሀብቷ አምቃ በመያዝ እያበረከተች ያለው አስተዋፆኦ ከፍተኛ ነው።

"በአሁኑ ወቅት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም እየተተገበረ ከለው የአርንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በተጓዳኝ ሀገሪቱ ከደን ሀብቷ ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ ወደ ካርበን ሽያጭ እየገባን ነው "ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባላት የደን ሀብት አምቃ የምትይዘው የካርበን መጠን ልክ የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማስቻል መንግስት በድርድር ላይ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

በመጀመሪያው ዙር የካርበን ሽያጭ የድርድር ስምምነት 20 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ እንድታገኝ መግባባት ላይ መደረሱን  ጠቅሰው "እየተካሄደ ባለው ሁለተኛው የድርድር ምዕራፍ ደግሞ 30 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንድታገኝ እየሰራን እንገኛለን "ብለዋል።

ይህም  በተለይ በኦሮሚያና በደቡብ ህዝቦች ክልል የሚገኘው የደን ሀብት  በካይ ጋዝን በመቀነስ ሂደት ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ከግምት ውስጥ ያስገባ የካርበን ሽያጭ ለማከናወን እንደሆነ ተናግረዋል።

"ከካርበን ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በደን ሀብቱ አካባቢ ያሉት አርሶ አደሮች ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን ጨምሮ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል "ብለዋል።

ለአፈፃፀሙ አመቺ የሆኑ የፖሊሲዎች የህግ ማዕቀፎችና አሰራሮች እየተዘጋጁ መሆኑንም ዶክተር አየለ ገልጸዋል።

ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ሀገሪቱ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ስትራቴጂ በመንደፍ በሙሉ አቅሟ እየገበረች መሆኑንም ዶክተር አየለ አመላክተዋል፡፡

በሀገሪቱ እየተከናወነ ባለው የአፈርና ውሃ እቀባ የተጎዳ መሬት ከንኪኪ ነፃ ማድረግና መልሶ እንዲያገግም በተደረገው ጥረት በተፈጥሮ ሀብት ልማት ላይ አመርቂ ውጤት መምጣቱን ጠቅሰዋል።

በህዝቡ ባለቤትነት እየተከናወነ ባለው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ የሀገሪቱ የደን ሽፋን ከነበረበት 3 በመቶ ወደ 15 በመቶ ማደጉን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ የደን ልማትና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አጌና አንጁሉ ናቸው።

አሁን በዘርፉ የታዩትን መሻሻሎች አጠናክሮ ለማስቀጠል በእፅዋት ሀብት ልማት ላይ እየተከናወኑ ያሉ የጥናትና የምርምር ሥራዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።

በዚህም የተፈጥሮ ሀብት ልማትና እንክብካቤን ከዘመቻ ሥራ በማውጣት በህብረተሰቡ ዘንድ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2010 ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ የፖለቲካ ባህል ሊቀየርና ሊስተካከል እንደሚገባ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ፖለቲከኞች ገለጹ።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ "በአመጽና በአብዮት አይፈታም" ይላሉ አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው።

በአገሪቷ የሚስተዋለው የፖለቲካ ባህል ችግር "ለተፈጠረው የሰላም ዕጦት ጠንቅ ሆኗል" የሚሉት አቶ ልደቱ፤ በምክንያታዊነት የሚመራ ጤናማ የመደማመጥና የመደራደር የፖለቲካ ባህል እንደሌለ ተናግረዋል።

ለአገር ሰላምና መረጋጋት የሚበጀው መፍትሔ ደግሞ ሁሉም ፖለቲከኞች አሸናፊ የሚሆኑበት በምክክርና በድርድር ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ባሕል ሲዳብር ነው ባይ ናቸው።

'ፖለቲካ ህዝብን የመምራት ጥበብ ነው' የሚሉት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ትግስቱ አወሉ፤ መደማመጥ የሰፈነበት የፖለቲካ ስርዓት ካልተዘረጋ በጉልበት ሰላምን ማስፈን እንደማይቻል ይገልጻሉ።

የቅንጅት ለአንድነትና ለፍትሕ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አየለ ጫሚሶ በበኩላቸው፤ ሰላምን ማረጋገጥ የሚቻለው በቅድሚያ ራስን ከሰላም ጋር ማስታረቅ ሲቻል እንደሆነ ገልጸው፤ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮች፣ የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብና የዴሞክራሲያዊ መብቶች አለመከበር በአገሪቷ ለተፈጠረው የሰላም ዕጦት ችግር መንስኤዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ፖለቲከኞቹ የሰላም ዕጦት መንስኤዎችን ለመፍታት የጋራ ውይይት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ የሕዝብን ጥያቄዎች በመፍታት ሰላምና መረጋጋት ማስፈን የሚቻለው ከጽንፈኝነት የተላቀቀ የፖለቲካ አስተሳሰብና ባሕል ሲዳብር መሆኑን ነው የተናገሩት።

Published in ፖለቲካ

መቀሌ መጋቢት 23/2010 በህዝቦች መካከል ግጭትን ለመቀስቀስ አሉቧልታ እንደመሳሪያ አድርገው የሚጠቀሙ አሳሳቾችን ለመታገል ዝግጁ መሆናቸውን የመቀሌው

ህዝባዊ የሰላምና የልማት ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡

ተሳታፊዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት ተመሳሳይ ህዝባዊ ኮንፍረንሶች በሌሎችም ክልሎች ቢዘጋጅ የህዝቦችን አንድነትና ሰላም ይበልጥ እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን የተወከሉ የኮንፍረንሱ ተሳታፊ አቶ ባበየ አባጋሮ አቶ በሰጡት አስተያየት በኮንፍረንሱ ያገኙት  ትምህርት ተጠቅመው በህዝቦች መካከል መቻቻልና ሰላም እንዲኖር የበኩላቸው እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡

እስካሁንም በህዝቦች መካከል ግጭት አለመኖሩን ጠቅሰው አሉቧልታ እንደመሳሪያ ጠቅመው ግጭት ለመቀስቀስ የሚሞክሩ አሳሳቾችን እንደሚታገሉና ልማትን እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡

በየጊዜው ህዝባዊ ኮንፍረንሶች ቢኖሩ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድም ለመፍታት እንደሚበጅና ግጭት ቀስቃሾች  ክፍተት ማግኘት እንማይችሉ የተናገሩት ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዘጠን የተወከሉ አርሶ አደር ሲሳይ ታደሰ ናቸው፡፡

ህዝቡ በጋራና በነጸ የሚወያይበት ተመሳሳይ ህዝባዊ ኮንፍረንስ በሌሎችም ክልሎችም ቢዘጋጅ የህዝቦችን አንድነትና ሰላም ይበልጥ እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ የተወከሉ አርሶ አደር ለማ ደሱ በበኩላቸው የትግራይ ህዝብ ወርቅ በወርቅ እንዳሸበረቀ ተደርጎ የሚነዛው ወሬ መሰረተ ቢስ እንደሆነ በስፍራ በመገኘት ማረጋገጣቸውንና እንደዚህ ዓይነት  አሳሳቾች በጋራ ለመታገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

"ኮንፍረንሱ ሰላምን  ለማስጠበቅ ጠቃሚ ነው ፤የሀገሪቱ የተረጋጋ  ሰላም ፣ ልማትና ዴሞክራሲ ወደ ቀድሞ ይዞታው እንደመለስ እፈልጋለሁ " ያለው ደግሞ  ከሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የተወከለው ወጣት አሕመድ ካፌ ነው፡፡

ከአርባምንጭ ከተማ የመጡት ወይዘሮ አዩ ብርሀኑ በሰጡት አስተያየት "ስለ ትግራይ የሚወራው አሉቧልታና ትግራይ መጥቼ በአካል ያረጋገጥትኩት ነገር ሰማይና ምድር ነው "ብለዋል፡፡

የክልሉ ህብረተሰብ ድህነትን ለማሸነፍ የሚተጋ እንጂ ከሌላው የሀገሪቱ ህዝብ የተለየ ጥቅም እንዳገኘ ተደርጎ የሚወራው ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ 

የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮች የተሳተፉት የመቀሌው ህዝባዊ የሰላምና  የልማት ኮንፍረንስ ለአራት ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ባለ አስራ አምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ትናንት ማምሻውን እንደተጠናቀቅ ቀደም ብሎ ተገልጿል፡፡

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2010 ሰላም የሁሉም ኃይማኖቶች አስተምህሮ መሆኑን የኃይማኖት አባቶች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ እንዳሉት "ሠላም ለመንፈሳዊም ሆነ ለዓለማዊ ኑሮ መሰረት መሆኑን ምዕመኑ በቅጡ ሊረዳ ይገባል" ።

"በሰው ልጆች መካከል ሠላምና ፍቅርን መስበክ የዕምነት ተቋማት አስተምህሮ ነው" የሚሉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼኸ መሀመድ አሚን ጀማልም የአቡነ ማትያስን ሀሳብ ይጋራሉ።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ እየሱስ ፕሬዝዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ በበኩላቸው "ለአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ቤተ-ዕምነቶች የሠላም መልዕክተኛነት አገልግሎታቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል" ብለዋል።

ትውልዱም በኃይማኖቶች አስተምህሮ ውስጥ ቀዳሚ የሆነውን የሠላምን አስፈላጊነት በመገንዘብ ከምንም በላይ አገሩን ማስቀደም እንዳለበትም የኃይማኖት አባቶቹ አሳስበዋል።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን