አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Friday, 09 March 2018

አዲስ አበባ የካቲት 30/2010 በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የሦስት አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ቆይታ የአገሪቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲጠናከር እድል መስጠቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተናገሩ።

ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የሦስት አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሰሞኑን በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት በተመለከተ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የሦስቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ጉብኝት በውጭ ጉዳይ መስክ ታሪካዊ ክስተት ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ነው ብለውታል። 

በተለይም የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭና የአሜሪካው አቻቸው ሬክስ ቲለርሰን ጉብኝት አገሪቱ የኃያላንን ቀልብ መያዝ የምትችል አገር መሆኗን ያሳያል ነው ያሉት።

ያም ሆኖ የሁለቱ ሚኒስትሮች ጉብኝት ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በማያያዝ የተለያዩ ትርጉሞች ቢሰጡትም ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው አስረድተዋል።

እንዲያውም የሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ከአጋጣሚ ያለፈ የተለየ ምክንያት የለውም በማለት ገልጸዋል።

በአንጻሩ የሦስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉብኝት ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማሳደግ እድል እንደሰጣት ነው የጠቆሙት።

ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጋር የተደረገው ምክክር ቀደም ሲል በምጣኔ ኃብት ዘርፍ ያሉትን ግንኙነቶች ይበልጥ ለማጠናከርና በተለይም የበርበራ ወደብ የ19 በመቶ ድርሻ እንድንይዝ ያስቻለ ነው ብለዋል።

ይህም የሶማሊያን ሉአላዊነት እንዲሁም ኢትዮጵያ በጂቡቲ ያላትን የዋና ወደብ ተጠቃሚነት በማይጋፋ መልኩ ተፈጻሚ ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

ከአሜሪካ ጋርም በተመሳሳይ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ መደረሱን ጠቁመው አገራቱ አንድ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው አገራት ናቸው ብለዋል። 

ጎን ለጎንም በርካታ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ እንደሚኖሩና ይህም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት ውይይት በአገራዊ ጉዳይ እንዲሁም ቀጠናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን አንስተው መወያየታቸውን ተናግረዋል።

ሩሲያን በተመለከተም ከአቻቸው ጋር ለረጅም ዓመታት የቆየውን የሁለቱን አገራት ታሪካዊ ግንኙነት ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ጠቅሰዋል።  

ሩሲያ በቀድሞ ሶቪየት ኅብረት ከተጠራችበት ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በመደገፍ እየሰራች ያለች መሆኗን ገልጸው አሁንም በተለያዩ ጉዳዮች ግንኙነቱ መጠናከሩን አስረድተዋል።

አሁን ደግሞ ወደ ሞስኮ የቀጥታ በራራ ለማስጀመርና ለሰላማዊ ጉዳይ የሚውል የኑክሌር መርኃ ግብርን ፕሮጀክት በኢትዮጵያ በጋራ ለማልማት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

 

 

 

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 30/2010 ሩሲያ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከል ማድረግ እንደምትፈልግ የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ገለጹ።

ፕሬዘዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ከሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ማሳደግ በሚችሉባቸው በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ትምህርት፣ ባህል፣ በሰላም ጉዳዮች ላይ በብሔራዊ ቤተ መንግስት መክረዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም እንዳሉት፤ ሩሲያ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከል የማድርግ ፍላጎት አላት።

 

 የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የልህቀት ማልከል ማድረግ የፈለጉት በአህጉሪቱ የተሻለ አቅምና ተቀባይነት እንዳላት በማመን ነው ብለዋል።

ፕሬዘዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመም ሩሲያ ያቀረበችውን የልህቀት ማዕከል የመገንባት ጥያቄ በአዎንታ መቀበላቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ሁለቱ አገሮች ያላቸው ግንኙነት በዳግማዊ አፄ ሚኒልክ ዘመንም እንደነበር የገለጹት ቃል አቀባዩ፤ በወቅቱ በአድዋ ጦርነት ላይ የሩሲያ ቀይ መስቀል ማህበር ድጋፍ አድርጎ እንደነበር ገልጸዋል።

ይህን ታሪካዊ ግንኙነት የእድሜውን ያህል የዳበረ አለመሆኑና የሁለቱ አገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች ተጠናክሮ እንዲቀጥል በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል ብለዋል።

እስካሁን ከ13 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በሩሲያ የትምህርት እድል ማግኘታቸውንና ቀጣይም ተጨማሪ ነፃ የትምህርት እድል በመስጠት በዘርፉ ያለው ግንኙነት እንዲጎለብት የሁለቱም አገራት ፍላጎት መሆኑንም አቶ መለስ ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላቭሮቭ ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ አገልግሎት ለመጠቀም በምታደርገው ጥረት ሩሲያ ድጋፍ እንደምታደርግ መግለጻቸውን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ለምታደርገው አስተዋፅኦ ሩሲያ ድጋፍ እንደምታደርግ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ በኢትዮጵያውያን ብቻ የሚፈታ እንጂ ሌሎች አገሮች ጣልቃ የሚገቡበት ጉዳይ አለመሆኑን መግለፃቸውን ቃለ አቀባዩ ተናግረዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 30/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ለማጠናከር በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ተወያዩ።

በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ዳሳለኝ ጋር በትምህርት፣ በባህልና ቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንት ዙሪያ አብሮ ለመስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተመካክረዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ሁለቱ አገሮች የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤቶች በመሆናቸውና የሚጋሯቸው በርካታ እሴቶች ስላሏቸው በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ያለውን ትብብር አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በትምህርት ዘርፍ የሚያደርጉትን ትብብር ለማጠናከር የነጻ የትምህርት ዕድል ማመቻቸትና የሁለቱን አገሮች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትብብር ለማጠናከር ይሰራል።

የኢትዮጵያና የሩሲያ የኢንቨስትመንት ትብብር የሚጠበቀውን ያህል ባለመጠናከሩ ይህንኑ ሁኔታ ለመቀየር የሩሲያ ባለሀብቶች በስፋት በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ ተብሏል።

በዓለም አቀፍ ጉዳዮች የሁለቱን አገሮች ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ አብሮ ለመስራት ውይይት አኳሂደዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 30/2010 35ኛው የሞሐ ፔፕሲ አዲስ አበባ የክለቦች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የፊታችን ሰኞ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚጀመር ተገለጸ ።

ውድድሩን የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የሞሐ የለስላሳ መጠጦች ማምረቻ በጋራ የሚያዘጋጁት ሲሆን ለክለብ አትሌቶች የውድድር ተሳትፎ በመፍጠር ይታወቃል።።

የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ መኮንን ውድድሩ በዓመቱ ለማካሄድ ከታቀዱት 11 ውድድሮች መካከል አንደኛ ነው ብለዋል።

ውድድሩ ክለቦች የአትሌቶቻቸውን አቋም የሚፈትሹበትና የሚገመግሙበት መሆኑንም ጠቅሰዋል ።

ከመጋቢት 3 ቀን ጀምሮ የሚካሄደው የክለቦች ሻምፒዮና  ለሰባት ተከታታይ ቀናት የሚደረግ ይሆናል ተብሏል።

ውድድሩ ከ100 ሜትር እስከ 10 ሺህ ሜትር ባሉ ርቀቶችና በሌሎች የሜዳ ላይ ተግባራት እንደሚከናወንም ተገልጿል።

በመክፈቻው እለት ሁለት የፍጻሜና ሌሎች የማጣሪያ ውድድሮች እንደሚከናወኑ ከወጣው መርኃ ግብር ለመረዳት ተችሏል።

በውድድሩ ከ30 ክለቦች የተወጣጡ ከ1 ሺህ በላይ አትሌቶች ይካፈላሉ።

 

Published in ስፖርት

መቀሌ የካቲት 30/2010 የሕዳሴው ግድብ ዋንጫ ወደ መቀሌ ከተማ መግባትን ተከትሎ በአራት ቀናት ውስጥ 20 ሚሊዮን ብር ከነዋሪዎች በቦንድ ግዥ መሰብሰቡ ተገለጸ።

የመቀሌ ከተማ መስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዘመንፈስቅዱስ ፍሰሃ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የሕዳሴ ዋንጫውን ወደከተማው መምጣትን ተከትሎ ከከተማው ህዝብ 15 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር።

122ኛውን የዓድዋ ድል በዓልና የህወሓት ምስረታ ቀንን ምክንያት በማድረግ በተሰራው የቅስቀሳ ሥራ ከዕቅዱ አምስት ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው ገንዘብ በቦንድ ግዥ መሰብሰበብ መቻሉን ተናግረዋል። 

የቦንድ ግዥውን ለማከናወን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ላሳዩት ቀልጣፋና  ቅን አገልግሎት ኃላፊው ምስጋናቸውን ጨምረው አቅርበዋል።

የ500 ብር ቦንድ በመግዛት ለግድቡ ድጋፍ ያደረጉት በከተማው የቀዳማይ ወያነ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አባል ሳጅን ጉዕሽ ተክለሃይማኖት፣ በፀጥታ ማስከበር ብቻ ሳይሆን በልማት ሥራም ተሳትፏቸው በማጠናከር ሀገራዊ ኃላፊነታቸው ለመወጣት ሲሉ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ በሚደረገው ቀጣይ ድጋፍም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በመቀሌ ሃውልት ክፍለከተማ የሚኖሩትና በጅምላ ንግድ ሥራ የሚታዳደሩት አቶ ተመስገን አበራም በበኩላቸው የ10 ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት ለግድቡ ግንባታ ያላቸውን ድጋፍ አሳይቷል።

"በየጊዜው ችግር እየፈጠሩ ያሉትን የውጭና የአገር ውስጥ ፀረ ሰላም ኃይሎችና ድህነትን ማሸነፍ የምንችለው የልማት ፕሮጀክቶችን በማፋጠን ነው" ያሉት አቶ ተመስገን፣ ወደፊትም ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል 

ሌሎች አቅም ያላቸው ባለሃብቶችም ለግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አቶ ተመስገን ጠይቀዋል።

የሕዳሴ ግድብ ዋንጫ በትግራይ ክልል መዘዋወር ከጀመረ ከየካቲት 1 ቀን 2010 ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ህዝቡ በስጦታና በቦንድ ግዢ 40 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል።

የሕዳሴ ግድብ ዋንጫ በአማራ ክልል የነበረውን ቆይታ አጠናቅቆ ወደ ትግራይ ክልል መግባቱ ይታወሳል።

Published in ኢኮኖሚ

ጋምቤላ የካቲት 30/2010 በጋምቤላ ክልል በግብርና ኢንቨስትመንት ሥራ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሰው ኃይል እጥረትና የመንገድ መሰረተ ልማት ለሥራቸው እንቅፋት እየፈጠረባቸው መሆኑን ገለጹ።

የከልሉ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ፤ የመንገዶች ባለስጣን ቢሮዎች በበኩላቸው የባለሃብቶችን ችግር ለመፍታት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ባለሀብቶች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በአካባቢው የጉልበት ሠራተኛና የመንገድ መሰረተ ልማት ችግር በግብርና ልማት ሥራቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል በኢታንግ ልዩ ወረዳ በግብርና ልማት ከተሰማሩት ባለሀበቶች መካከል አቶ ኃይሌ አዲስ እንዳሉት፣ የሰው ኃይል እጥረትና የመንገድ ችግር ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናውን ችግር እየፈጠረባቸው ነው።

በአካባቢው በቂ የሰው ኃይል ባለመኖሩ ከሌሎች ክልሎች ሠራተኛ በማምጣት ችግሩን ለማቃለል ጥረት ቢደረግም ችግሩ አለመቃለሉንና በእዚህም የጥጥ ምርታቸው እስካሁን ድረስ ሳይሰበሰብ ለብክነት በመዳረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ኃይሌ እንዳሉት፣ ደረጃውን የተጠበቀ የበጋና ክረምት መንገድ አለመኖር የግብርና ግብዓቶችን ለማስገባትም  ሆነ ምርታቸውን ለገበያ ለማቅረብ ችግር እየፈጠረባቸው ነው።

የመንግድ ችግርና የሠራተኛ እጥረት በምርት መሰብሰብም ሆነ በሰብል ልማት ሥራቸው ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን የገለጹት ደግሞ በእዚሁ ወረዳ በግብርና ኢንቨስትመንት ሥራ የተሰማራው የአብራሃልኝ የግል እርሻ ልማት ተወካይ አቶ አባይነህ አየለ ናቸው።

የሚመለከተው የመንግስት አካል ያሉባቸው ችግሮች የሚፈቱበትን ሁኔታ እንዲያመቻችላቸው ባለሀብቶቹ ጠይቀዋል።

በኢንቨስትመንት የሥራ ዕድል የተፈጠረለት የአካባቢው ወጣት ጅምስ ሬክ በበኩሉ፣ ባለሀብቶች በተፈጠረው የሥራ ዕድል በቀን 150 ብር እየተከፈለው በመስራት ላይ መሆኑን ተናግሯል።

በክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሠራተኛ አገናኝና ስምሪት የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ፒተር ላም በክልሉ የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች በባለሀብቶች የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎችን የመጠቀም ባህል ብዙ አለመዳበሩን ተናግረዋል።

ቢሮ የአካባቢውን ወጣቶች ግንዛቤ በማሳደግ የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችን በመቅሰም ወደ ራሳቸው ሥራ እንዲገቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ተናገረዋል።

ባለሃብቶት የእያጋጠማቸው ያለውን የሰው ኃይል እጥርት ለጊዜው ለማቃለል ሲባልም ከሌሎች ክልሎች ሠራተኛ እንዲያመጡ ቢሮው የድጋፍ ደብዳቤ እየጻፈላቸው መሆኑንም አቶ ፒተር ጨምረው ገልጸዋል።

የክልሉ ገጠር መንገዶች ባለስጣን ተወካይ አቶ ተስሏች ቾል በበኩላቸው፣ ባለሃብቶች በመንገድ ዘርፍ ያቀረቡት ቅሬታ ትክክለኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ችግሩን በጊዜያዊና በዘለቄታ ለመፍታት በክልሉና በፌደራል መንገዶች ባለስልጣን በኩል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስጣን በአሁኑ ወቅት አራት የጠጠር መንገዶችን በአስፓል ደረጃ እያሻሻለ መሆኑንና በኢታንግ ልዩ ወረዳ ያለውንም የመንገድ ችግር ለመፍታት የዲዛይን ሥራ እያከናወነ መሆኑን አቶ ተስሏች ተናግረዋል።

ችግሩን በጊዜያዊነት ለማቃለልም በአሁኑ ወቅት የጥገና ሥራ እየተሰራባቸው ያሉ መንገዶች መኖራቸውንም ነው የገለጹት።

Published in ኢኮኖሚ

የካቲት 30/2010 ኢትዮጵያና ሩስያ በኢነርጂ ፣ ንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ፡፡

የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከሩስያው አቻቸው ሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር በሁለትዮሽና አካበቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

ዶክተር ወርቅነህ ከውይይቱ በኋላ እንዳብራሩት ሁለቱ ሀገራት በኃይል አቅርቦት በተለይም በኒውክሊየር ኃይል፣ ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ እንዲሁም  በትምህት ዘርፎች ተባብረው ለመስራት ተስማምተዋል፡፡

ስምምነቱ ለሰላማዊ ጥቅም የሚውል የኒውክሊየር ኃይል በጋራ ማበልጸግን እንደሚያካትትም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሞስኮ ለመብረር በዝግጅት ላይ መሆኑን ያብራሩት ዶክተር ወርቅነህ ይህም የሁለቱን አገራት የህዝብ ለህዝብ፣ የንግድና እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ያሳድገዋል ብለዋል።

የሩስያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በበኩላቸው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳላት ጠቅሰው ግንኙቱን በንግድ እና ኢንቫስትመንት ይበልጥ ለማሳደግ እንደምትፈልግ ገልፀዋል።

በአካበቢ ሠላምና በባለብዙ ወገን አጀንዳዎች ላይ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ተበባራ እንደምትሰራም ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

“ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” የሚለውን መርህ ሀገራቸው እንደምትደግፍ የገለጹት ላቭሮቭ  የኢትዮጵያ ጉዳይ  የሚመለከተው ኢትዮጵያውያንን ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

ሩሲያ ለኢትዮጵያ 162 ሚሊዮን ዶላር የዕዳ ስረዛ ያደረገች ሲሆን እስከ አሁን አስራ ሶስት ሺህ ኢትዮጵያውያን በሩሲያ በተለያዩ ዘርፎች ትምህርተቸውን ተከታትለዋል።

ሁለቱ ሀገራት 120 ዓመታትን የተሻገረ ጠንካራና ታሪካዊ ግንኙነት አላቸው፡፡

 

ምንጭ፡- የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 30/2010 አንዳንድ ማህበራዊ ልማዶች ስርዓተ ጾታን የማረጋገጥ ሂደትን አሁንም እያደናቀፉ እንደሚገኙ ተገለጸ።

ዓለም አቀፍ የሴቶችን ቀን በማስመልከት በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አዘጋጅነት 'ማህበራዊ ልማዶችና ስርዓተ ጾታ በኢትዮጵያ' በሚል ርዕስ የመወያያ ጽሁፍ ቀርቦ ከአጋር አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።

የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት የሴቶች መብት ተሟጋችና የሴታዊነት ድርጅት አስተባባሪ ዶክተር ስሂን ተፈራ እንደተናገሩት፤ ''የጾታ እኩልነት መከበር ራሱን የቻለ የማህበራዊና ፖለቲካዊ ግብ ከመሆኑም በላይ ሚዛናዊ ለሆነ የስነ ህዝብ እድገት መሳካት የጎላ አስተዋጽኦ አለው።"

"በኢትዮጵያ የጾታ እኩልነትና መብቶችን ለማስጠበቅ መልካም ጅምሮች ቢኖሩም፤ አሁንም በርካታ ሴቶች ካሉባቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መላቀቅ አልቻሉም" ብለዋል።

የሴቶች ተሳትፎ ከወንዶች እኩል ያለማየት፤የቤት ውስጥ ስራዎችና ልጆችን የመንከባከብ ሃላፊነት የሴቶች ነው ብሎ ማሰብ የሚታዩ ልማዳዊ ድርጊቶች መሆናቸውን አንስተዋል።

በተጨማሪም ህብረተሰቡ ለጾታዊ እኩልነት ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆን ችግሩ በሚፈለገው ደረጃ እንዳይቀረፍ እንዳደረገው ጠቅሰዋል።

እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2016 በአገሪቷ የተሰራውን የኢትዮጵያ የስነ ህዝብ ጤና ዳሰሳ ጥናት ጠቅሰው እንደተናገሩት፤ ሴቶች አሁንም ድረስ በጤና፣ በትምህርት፣ ያለእድሜ ጋብቻና በስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ዙሪያ ያሉባቸው ችግሮች አለመቃለላቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ ሴቶችን ወደፊት እንዳይመጡ እያደናቀፉ ያሉ ማህበራዊ ልማዶች ስርዓተ ጾታን የማረጋገጥ ሂደቱን እየፈተኑት መሆኑን ጠቁመዋል ።

በዳሰሳ ጥናቱ የሴቶች የተገደበ የውሳኔ ሰጭነት ሚና እልባት ያላገኘ አጀንዳ ሆኖ መቀጠሉንም ዶክተር ስሂን ገልጸዋል።

በአገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች 57 በመቶና በከተማ ደግሞ 16 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች አሁንም ድረስ የመደበኛ ትምህርት እያገኙ አለመሆኑን ተናግረዋል።

በአገሪቱ 61 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች በመጀመሪያ ጋብቻቸው ጉዳይ ምንም የመወሰን ድርሻ እንደማይሰጣቸው ጠቁመው፤ በገጠር አካባቢዎች ሴቶች ትዳር የሚይዙበት አማካይ የእድሜ ጣሪያ 17 ነጥብ 1 ዓመት መሆኑን ጥናቱ አካቷል።

እንደ ዶክተር ስሂን ገለጻ፤ ይህ መሆኑ የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ገና በርካታ ስራዎች መስራት እንደሚገባ የሚያሳይ ነው።

በዚህም የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ማህበራዊ ልማዶች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ቀላል ባለመሆኑ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሚወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን በትክክል ተግባራዊ ማድረግና ሁሉም አካላት ለጾታ እኩልነት መረጋገጥ የድርሻውን መወጣት እንደሚገባውም አሳስበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ አካላትም የጾታ እኩልነት ለማረጋገጥ እንቅፋት ከሚሆኑ ማህበራዊ ልማዶች በመውጣት አጋርነታቸውን በማሳየት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

 

Published in ማህበራዊ

 

አዲስ አበባ የካቲት 30/2010 አፍሪካ በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ሩስያ ድጋፍ እንድታደርግ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ጠየቁ።

ትላንት ምሽት ለይፋ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት የሩስያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ጋር በአህጉራዊና አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ተወያይተዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፈቂ ማህማት በዚህ ጊዜ እንዳሉት የዓለማችን ሁለተኛዋ ግዙፍ የህዝብ በዛት ያላት አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት ይገባል።

የመንግስታቱ ድርጅት የለውጥ ማሻሻያ የአፍሪካን ፍላጎት ያማከለ ሊሆን እንደሚገባ የጠቆሙት ሊቀ መንበሩ ሩስያም ለአፍሪካውያን ፍላጎት መሳካት ድጋፍ እንድታደርግ ጠይቀዋል።

ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረው የአፍሪካና ሩስያ ወዳጅነት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባውም ሊቀመንበሩ  በውይይቱ ወቅት ለሰርጊ ላቭሮቭ አንስተውላቸዋል።

የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው ሩሲያ አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት እንደምትሰራ ገልጸዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፀጥታው ምክር ቤት የሚደረገው ማሻሻያም አፍሪካን ያካተተ ሊሆን እንደሚገባ ላቭሮቭ አጽኖት ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ አፍሪካን ባላካተተ መልኩ በምክር ቤቱ የሚደረገው ማሻሻያ ተቀባይነት እንደሌለውና ሩስያ የአፍሪካ ህብረት የሚያቀርበውን የውክልና ጥያቄ ስትደግፍ መቆየቷን አውስተዋል።

 

 

Published in ፖለቲካ

ሚዛን የካቲት 30/2010 በሚዛን አማን ከተማ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የአንድ ሰው ሕይወት አለፈ፡፡

የቤንች ማጂ ዞን ፖሊሲ መምሪያ የትራፊክ አደጋ ማደራጃ ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር አበራ አለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በሚዛን አማን ከተማ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የአንድ ሰው ሕይወት አልፏል፡፡

አደጋው ትናንት ምሽት 5፡00 ሰዓት ላይ የደረሰው በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ ሾንጋ ወንዝ አካባቢ ነው፡፡

ከሚዛን ወደ አማንና ከአማን ወደ ሚዛን በተቃራኒ አቅጣጫ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ "ኮድ 4-02162 ደህ" እና "ኮድ 4- 02569 ደህ " የመንግስት ተሽከርካሪዎች በመጋጨታቸው ምክንያት አደጋው ሊከሰት ችሏል።

ምክትል ኢንስፔክተር አበራ እንዳሉት ምንም እንኳ የአደጋው መንስኤ በፖሊስ እየተጣራ ቢሆንም ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር ለአደጋው መንስኤ ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት አለ፡፡

በአደጋው የአንደኛው መኪና አሽከርካሪ ሕይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ በሌላኛው ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ቲቺንግ ሆስፒታል ሕክምናውን በመከታትል ላይ ይገኛል፡፡

በአንደኛው ተሽከርካሪ የተሳፈረ አንድ ግለሰብ ላይም ቀላል ጉዳት መድረሱን ምክትል ኢንስፔክተር አበራ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን