አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Thursday, 08 March 2018

ጎንደር የካቲት 29/2010 የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ሥራ ለሰብል ምርታማነትና ለወጣቶች የሥራ ዕድል በማስገኘት በኩል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን በሰሜን ጎንደር ዞን የአዲአርቃይ ወረዳ አርሶ አደሮችና ወጣቶች ተናገሩ፡፡

በወረዳው ባለፉት ዓመታት በህዝቡ ተሳትፎ የለሙ ተፋሰሶች ለህብረተሰቡ ዘላቂ ኢኮኖሚዊ ጥቅም የሚሰጡበት አሰራር ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡

በዘንድሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ተሳታፊ ከሆኑ የወረዳው አርሶ አደሮች መካከል ቄስ ዋጋዬ በላይ እንደተናገሩት፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ሥራው ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ እንዲጥል በማድረግ የተሻለ ምርት እንዲያገኙ አግዟቸዋል።

የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራው የመሬት ለምነትን በመጨመሩ ቀደም ሲል እኔ በዓመት የሚያመርቱት ምርት ከስምንት ወር በላይ ቀለብ እንደማይሆናቸውና  አሁን ግን የዓመት ቀለብ የሚሸፍን ምርት እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በለሙ ተፋሰሶች የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ወጣት ሙሃባው ምስጋናው በበኩሉ 12 ሆነው በማህበር በመደራጀት በተፋሰስ ውስጥ በጀመሩት የንብ ማነብ ሥራ ባለፈው ጥቅምት ወር ስድስት ኩንታል ማር ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

ባገገሙ ተፋሰሶች በቋሚ ተክልና በእንስሳት መኖ ልማት ሥራ በመሰማራት እሱና ጓደኞቹ 2 ኩንታል የእንስሳት መኖ ዘር አምርተው በመሸጥ ከ5 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን የገለጸው ደግሞ ወጣት ሰለሞን አስማማው ነው።

" የለሙ ተፋሰሶች ለአካባቢው የገጠር ወጣቶች የሥራ ዕድል እየፈጠሩ ናቸው" ያለችው ደግሞ ወጣት ጥሩዬ ሙሃባው ናት፡፡

በአሁኑ ወቅት በርካታ ወጣቶች በንብ ማነብ፣ በእንስሳት እርባታና በመስኖ ልማት ጭምር በመሳተፍ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ተናግራለች፡፡

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሸጋው ውቤ በበኩላቸው "ተፋሰሶችን በዘላቂነት በማልማትና ማህበረዊ ፋይዳቸውን በማሳደግ ወጣቶችን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ነው " ብለዋል፡፡

በዚህም ባላፈው ዓመት የለሙ ስምንት ተፋሰሶችን ለ56 ወጣቶች በማስተላለፍ በንብ ማነብ ሥራ ተሰማርተው ከማር ምርት ሽያጭ ብቻ ከሩብ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማገኘታአውን ተናግረዋል፡፡

በወረዳው በዘንድሮ የበጋ ወራት በ47 አዲስና ነባር ተፋሰሶች ከ37 ሺህ በላይ ህዝብ የተሳተፈበትና ለ40 ቀናት የሚቆይ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ሥራ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ የካቲት 29/2010 የቅዱስ ዻውሎስ ሚሊኒየም ሆስፒታል ባለፉት ሰላሳ ወራት ለ71 ታካሚዎች የተሳካ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ማድረጉን አስታወቀ።

የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምናው ከአለም አቀፍ ተሞክሮ አንፃር ሲታይ ስኬታማ እንደነበርም ተገልጿል።

በሆስፒታሉ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ክፍል ኃላፊ ዶክተር ብርሀኑ ወርቁ በአለም አቀፍ ደረጃ ዛሬ የተከበረውን የኩላሊት ቀን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

የህክምና ክፍሉ በዓመት በአማካይ ለ25 ታካሚዎች የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ማድረግ መቻሉ በምስራቅ አፍሪካ ካሉ መሰል ተቋማት የተሻለ ያደርገዋል ብለዋል።

የኩላሊት ታካሚዎችን ቁጥር ለመቀነስ ከህክምናው ባልተናነሰ ለቅድመ መከላከል ስራዎች ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ቀዶ ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር እንግዳ አበበ ተናግረዋል።

በአብዛኛው ለህክምና የሚመጡት የጉዳት መጠኑ የተባባሰባቸው ታማሚዎች በመሆናቸው የህመሙን መንስኤ ለማወቅ ሂደቱን አስቸጋሪ እንዳደረገው ዶክተር እንግዳ ተናግረዋል ።

ይህንኑ ለማስቀረት ማንኛውም ሰው ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ የጤና ምርመራ እንዲያደርግ መክረዋል።

በሆስፒታሉ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የተደረገላቸው አቶ አበባው ጌታሁን "ወደ ሆስፒታሉ የመጣሁት በሰዎች ድጋፍ ነበር ከሁለት ወራት በፊት በተደረገልኝ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ጤንነቴ ተመልሶልኛል፣በተደረገልኝ ህክምና ተደስቻለሁ" ብለዋል።

የቅዱስ ዻውሎስ ሚሊኒየም ሆስፒታል የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ክፍል ባለፉት ሰላሳ ወራት የነበረውን አሰራር በማሻሻል የኩላሊት እጥበትን በተመጣጣኝ ክፍያና ታካሚዎች የግል ተግባራቸውን እያከናወኑ ህክምናውን የሚያገኙበት አዲስ አሰራር ሊጀምር መሆኑንም አስታውቋል።

ከውጭ ሀገራት የሚገቡና ለህክምናው የሚውሉ ቁሳቁሶች ግብይት መዘግየት ለስራው እንቅፋት እንደሆነበትና ችግሩን ለመፍታት ቁሳቁሶቹን በሀገር ውስጥ ለማምረት እቅድ መያዙም በመግለጫው ተጠቅሷል።

የኩላሊት እጥበት ህክምና ክፍል ሀላፊው ዶክተር አብዱልመኒም አህመድ ህክምናው በሌሎች አስር ሆስፒታሎች ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑን በዝግጅቱ ላይ ተናግረዋል።

ባህርዳር፣ መቀሌ፣ ወላይታ እንዲሁም በአዲስ አበባ በምኒሊክና ዘውዲቱ ሆስፒታሎች ህክምናውን ለመስጠት መታቀዱን ገልፀዋል።

የኩላሊት ህክምና ያለበትን ደረጃ ለማሳደግ አዳዲስ የትምህርት ዘርፎች እንደሚከፈቱና ተሞክሮውን ለማስፋት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ኃላፊው ጠቁመዋል።

Published in ማህበራዊ

መቀሌ የካቲት 29/2010 በሃገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ አባላት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ900 ሺህ ብር በላይ የቦንድ ግዢ ማከናወናቸው ተገለጸ።

የእዙ አባላት የህዳሴ ግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

የእዙ አባላት የቦንድ ግዢውን የፈፀሙት የህዳሴ ግድብ ዋንጫ በእዙ ስር በሚገኙ የተለያዩ  ክፍሎች  በተዘዋወረባቸው ባለፉት ሶስት ቀናት ውስጥ ነው፡፡

በእዙ የአራተኛ ሜካናይዝድ ክፍለጦር አዛዥ ኮሌኔል ነጋሲ ተስፋይ ዛሬ እንደገለጹት በክፍለጦሩ የሚገኙ አባላትና ሲቪል ሰራተኞች ዋንጫው ወደ ክፍለጦሩ ከመጣ ጀምሮ ከ690 ሺህ በላይ ብር የሚያወጣ ቦንድ ገዝተዋል፡፡

የክፍለ ጦሩ አባል የሆኑት ሻለቃ አለማየሁ ቼሩ በበኩላቸው፣ የህብረተሰቡ የፅናትና የአንድነት መገለጫ የሆነው የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ሰራዊቱ ወዳለበት መምጣቱ ድጋፍን ይበልጥ እንዲያጠናክር ያግዛል ብለዋል።

ላለፉት ስድስት አመታት ከገዙት ቦንድ በተጨማሪ በዛሬው እለትም የአንድ ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ነው ሻለቃ አለማየሁ የተናገሩት።

የህዳሴ ግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ መንግስትና ህዝብ ከሰጡዋቸው ኃላፊነት በተጨማሪ ባላቸው አቅም የቦንድ ግዢ እያካሄዱ መሆናቸው የተናገሩት ደግሞ የእዙ አባል የመቶ አለቃ ጌታሁን ካሳዬ ናቸው። 

የሰሜን ምስራቅ እዝ ቆይታውን አጠናቆ ባለፈው ሰኞ ወደ ሰሜን እዝ የገባው  የህዳሴ ግድብ ዋንጫ በእዙ ስር በሚገኙ የተለያዩ ክፍሎች ለአንድ ወር ያህል ቆይታ ያደርጋል፡፡

ዋንጫው ወደ እዙ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ወደተለያዩ ክፍሎች በተዘዋወረባቸው ባሉት ሦስት ቀናት ውስጥ የሰራዊቱ አባላት የ910 ሺህ ብር ቦንድ ግዢ ማከናወናቸው ለማወቅ ተችሏል።

Published in ኢኮኖሚ

ጋምቤላ የካቲት 29/2010 በጋምቤላ ክልል ከ337 ሺህ የሚበልጡ የአካባቢውን ማህበረሰብና ስደተኞች ተጠቃሚ የሚያደርግ የልማት ፕሮጀክት ተግባራዊ በመሆን ላይ እንደሚገኝ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ።

ፕሮጀክቱ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ነው ተብሏል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ ፕሮጀክቱን አስመልከቶ በተካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ  እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ በክልሉ ካለው ከፍተኛ የስደተኛ ቁጥር ጋር ተያይዞ በአካባቢው ማህበረሰብ ሊደርስ የሚችለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖን ለመከላከል የሚያስችል ነው።

ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ስደተኞቹ በተጠለሉባቸው የጋምቤላ፣የኢታንግ፣ የጎግና የዲማ ወረዳዎች ውስጥ ነው።

"በወረዳዎቹ በአካባቢ ጥበቃ፣ በተለያዩ የገቢ ማስገኛዎች፣ በትምህርት ፣በንጹህ መጠጥ ውሃ ፣ በመንገድ ግንባታዎችና በሌሎች የልማት ዘርፎች ፕሮጀክቱ ትኩረት ያደርጋል"  ብለዋል ኃላፊው።

ኃላፊው እንዳሉት ፕሮጀክቱ ስድተኞቹ በተጠለሉባቸው በነዚሁ ወረዳዎች ሊያደርሱ የሚችሉትን የትምህርት ቤት መጣበብ ፣የውሃና የጤና አገልግሎት መጨናነቅንና በተፈጥሮ የደን ሀብት ሊደረስ የሚችለውን ተጽዕኖ ያቃልላል።

በቢሮው ለሚመራው  ለዚሁ ፕሮጀክት ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በአፍሪካ ቀንድ የስደተኞች ተጽዕኖ ምላሽ የልማት ፕሮጀክት የጋምቤላ ክልል አስተባበሪ አቶ አሊፕ ኡማን በበኩላቸው በስደተኞች ሊደርስ የሚችለውን ተጽዕኖ ለመቀነስ ፕሮጀክቱ የተጀመረው ባለፈው ዓመት አጋማሽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ዘንድሮም ተጠናክሮ  ወደ ሙሉ ትግበራ መግባቱን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ዘንድሮ ስደተኞቹ በተጠለሉባቸው አራት ወረዳዎች የ34 የትምህርት፣ የውሃና የጤና ተቋማትንና የሶስት የቀበሌ አገናኝ መንገዶች ግንባታ እንደሚያከናውን ጠቁመዋል፡፡

40 የሞተር ብስክሌቶችና አምስት ተሽከርካሪዎች ተገዝተው ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው ወረዳዎች መሰራጨታቸውን ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቱ ለአምስት ዓመታት በሚያደርገው ቆይታ ከ337 ሺህ የአካባቢው ማህብረሰብና ስደተኞች በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አቶ አሊፕ አስታውቀዋል፡፡

"ለማስፈፀሚያም ከግማሽ ቢሊዮን ብር የማያንስ በጀት ይፈጃል፤ የሚሸፈነውም በአለም ባንክ ነው" ብለዋል።

በክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ የማህበረሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ባለሙያ አቶ አኩማ ኡኩኝ በሰጡት አስተያየት ስደተኞች በተጠለሉባቸው ወረዳዎች የሚገኙ የጤና ተቋማትን ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በጋራ ስለሚገለገሉ መጨናነቅና የመድኃኒት እጥረት እንደሚያጋጥም ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ችግሩን ከማቃለል ረገድ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን  አመልክተዋል።

"ፕሮጀክቱ በአካባቢው ማህበረሰብና በስደተኞች በተፈጥሮ የደን ሀብቱ ላይ ሊደረስ የሚችለውን ተጽዕኖ ለመቀነስ ያግዛል" ያሉት ዳግሞ በክልሉ የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ የአካባቢ ጥበቃ ዋና የስራ ሄደት ባለቤት አቶ ቤል ኬት ናቸው።

በጋምቤላ ወረዳ አቦል ከተማ በፕረጀክቱ ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ በተዘጋጀው መድረክ የትምህርት፣የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጨምሮ ሌሎችም የሚመለከታቸው የልማት አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የስራ ኃላፊዎችና ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

በጋምቤላ ክልል በሚገኙ ሰባት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ከ408 ሺህ የደቡብ ሱዳን ሰደተኞች ተጠልለው እንደሚገኙ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 29/2010 ሴት የህክምና ተመራማሪዎችን እንደሚደግፍ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የዓለም ሴቶች ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል።

በዩንቨርሲቲው የሴት ተመራማሪዎች ቡድን አለም አቀፍ የሴቶች ቀንን የተለያዩ የምርምር ስራዎችን በማቅረብና በፓናል ውይይት አክብሯል።

የዩንቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በዚህ ጊዜ እንዳሉት፤ ሴት ተመራማሪዎች ያላቸውን እምቅ ሃይል በመጠቀም ለሚሰሩት የምርምር ስራ ተቋሙ በገንዘብና በሃሳብ ድጋፍ ያደርጋል።

"ሴቶች እድሉ ከተሰጣቸው ለአገር ወሳኝ የሆነ ስራ እንደሚሰሩ እሙን ነው" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የዩንቨርስቲው ወጣት ሴት ተመራማሪዎች ቡድን በራሳቸው ተነሳሽነት የሚያከናውኑት የምርምር ስራ ለሌሎች ሴቶች አርዓያ ይሆናል ብለዋል።

በተለይ በህክምናው ዘርፍ የተመዘገበውን ውጤት ለማስቀጠልና ክፍተቶችን ለመሙላት የምርምር ስራዎች ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል።

በተመሳሳይ በዓሉ በኦሮሚያ ባህል ማዕከል ሲከበር "ሴቶች በራሳቸው እንዲተማመኑ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው ሊጎለብት ይገባል" በማለት የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ወይዘሮ ደምቱ ሀምቢሳ ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ባህል ማዕከል ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የመጡ ሴቶች አለም አቀፉን የሴቶች ቀንን አክብረዋል።

በዚህ ዓመት ከሶስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ሴቶችን በቁጠባ የልማት ቡድኖች በማደራጀት ዘጠኝ ቢሊዩን ብር እንዲቆጥቡ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በ2017 ዓ.ም የሴት ልጅ ግርዛት እና ያለእድሜ ጋብቻን ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት አንድ ሶስተኛ የሚሆኑ ሴቶችን ከዚሁ ችግር ነፃ የማድረግ እቅድ ተቀምጧል ብለዋል።

በጤናው ዘርፍ የጡትና የማህፀን ጫፍ  ካንሰርን የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለመግታት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከ16 ሺህ በላይ ሴቶች ቅድመ ምርመራ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

 በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ በመሆን ከተለያዩ ተመራማሪዎችና መሃንዲሶች ጋር የሴቶችን ቀን አክብረዋል።

 የባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስትትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬም ሴቶች በየትኛውም ዘርፍ ተሰማርተው የመስራት አቅም እንዳላቸው ገልጸዋል።

 በባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ጠቃሚ የሆኑ ጥናትና ምርምሮች በማድረግ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ አስፈላጊ ግብዓቶች በማሟላት ለራሳቸው ብሎም ለአገሪቱ ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ ያደረጋል ብለዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 29/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሙሉ በሙሉ በሴት የአቪዬሽን ባለሙያዎች የተመራ አዲስ በረራውን ወደ አርጀንቲና መዲና ቦነስ አይረስ ከተማ አደረገ።

በሴት አብራሪዎቹ ዛሬ ወደ አርጀንቲና ቦነስ አይረስ የተደረገው አዲስ በረራ በአለም አቀፍ ደረጃ ዛሬ የሚከበረውን የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ ነው።

ሴቶች በተሰማሩበት መስክ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉ ማሳያ የሆነው ይህ በረራ ከዚህ በፊት ወደ ታይላንድ፣ ሩዋንዳና ናይጄሪያ በሴቶች ብቻ የተካሔደ በረራ አካል መሆኑም ተመልክቷል።

ይህ በረራ የተከናወነው አውሮፕላን አብራሪዎቹ ፣ቴክኒሻኖች፣ የበረራ አስተናጋጆች፣ መሃንዲሶች፣የትኬት ክፍል ሰራተኞችና በአጠቃላይ ለጉዞው አስፈላጊ በሆኑ ሁሉም መስኮች ላይ ሴቶች ብቻ ተሳትፈውበታል።

አየር መንገዱ በሴቶች ብቻ የተመራ በረራ ሲያካሒድ የዛሬው አራተኛው ሲሆን አላማው ከሀገር አልፎ የአሕጉሪቱን ሴቶች ለማበረታት መሆኑንም የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ተናግረዋል።

ከዛሬ ጀምሮ አየር መንገዱ ወደ አርጀንቲና መዲና ቦነስ አይረስ በሳምንት አምስት ጊዜ በረራውን ያደርጋል ያሉት አቶ ተወልደ ይሕም በደቡብ አሜሪካ ስድስተኛው መዳረሻው መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ መሆኑን የገለጹት አቶ ተወልደ ይህም የአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ያመጣው መሆኑን አስረድተዋል።

አየር መንገዱ እስካሁን ላስመዘገበው ስኬት ሴት የኢቪዬሽን ሙያተኞችና ሌሎች ሰራተኞች አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደነበርም አቶ ተወልደ ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል በበኩላቸው መንግስት በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ካስቀመጣቸው ግቦች ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የትራንስፖርት ዘርፉን እድገት ማፋጠን ነው

በአሁኑ ወቅት አየር መንገዱ በአገሪቱ ለተመዘገበው እድገት ሰፊ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝና ከዚህ ውስጥም ኢትዮጵያ በአበባ ንግድ ከአፍሪካ ሁለተኛ እንድትሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱን አመልክተዋል።

በዛሬው እለት ወደ አርጀንቲና የተከፈተው አዲስ የበረራ መስመር የሕዝብ ለሕዝብ ፣የቱሪዝም ፣የኢንቨስትመንትና የንግድ ግንኙነቱን የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል።

የስታር አሊያንስ አባል የሆነውና 96 አውሮፕላኖች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለያዩ አህጉራት በሚገኙ 110 መዳረሻዎች በመብረር ላይ ይገኛል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 29/2010 የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረተ ድንጋይ የተጣለበትን 7ኛ አመት አስመልክቶ የሚካሄደው የእግር ኳስ ውድድር በአዲስ አበባ  ስታድየም ዛሬ ተጀምሯል።

ዛሬ በተደረገው የመክፈቻ ጨዋታ ሲዳማ ቡና ደደቢትን ሁለት ለዜሮ አሸንፏል።

በመጀመሪያው 45 ደቂቃ ሃብታሙ ገዛኸኝ ባስቆጠራት ጎል እንዲሁም ከእረፍት በኋላ መሃመድ አብዱላጢስ ባገባው ጎል ሲዳማ ቡና ደደቢትን ሁለት ለዜሮ ማሸነፍ ችሏል።

የውድድሩ ሁለተኛ ጨዋታ ዛሬ ከቀትር በኋላ 11 ሰዓት ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክና ኢትዮጵያ ቡናን ያገናኛል።

የሁለቱ ጨዋታ አሸናፊዎች በመጪው እሁድ በሚካሄደው የፍጻሜ ጨዋታ የሚገናኙ ሲሆን ተሸናፊዎቹ የደረጃ ጨዋታ ያደርጋሉ።

የፍጻሜው ጨዋታ እሁድ ከቀኑ 10 ሰዓት ሲካሄድ የደረጃ ጨዋታው  8፡00 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።

ውድድሩ ለ5ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሄራዊ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጋራ አዘጋጅተውታል።

የእግር ኳስ ውድድሩ ዋነኛ ዓላማ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የገቢ ማሰባሰቢያና በግድቡ ዙሪያ ህዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር ነው።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ የካቲት 29/2010 በየካቲት ወር በተካሄደ ግብይት 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ምርት ማገበያየቱን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በተጠቀሰው ወር 65 ሺህ 631 ቶን የቡና፣ የሰሊጥ፣ ነጭ ቦሎቄና አረንጓዴ ማሾ ምርቶችን አገበያይቷል።

በወሩ ከፍተኛው የግብይት ድርሻ የቡና ሲሆን የግብይቱን 45 በመቶ መጠንና 63 በመቶ ዋጋ መያዙን መግለጫው አመልክቷል።

ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና የግብይቱን 59 በመቶ በመጠን እና 53 በመቶ በዋጋ ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዝ ስፔሻሊቲና የአገር ውስጥ ቡና ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።

የሰሊጥ ግብይት በመጠን 44 በመቶ፣ በዋጋ 33 በመቶ በመያዝ በወሩ ግብይት ሁለተኛ ደረጃ የያዘ ሲሆን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር በዋጋ የ45 በመቶና በመጠን የሁለት በመቶ ዕድገት ማሳየቱ ተገልጿል።

በየካቲት ወር ግብይት የማሾ ግብይት ከፍተኛ ለውጥ ያመጣ ሲሆን ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር የግብይት መጠኑ በ80 በመቶ እና ዋጋው በ107 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን መግለጫው ያመለክታል።

በቦሎቄ ግብይትም ነጭ ድቡልቡል ቦሎቄ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ ሲሆን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር በመጠን የ63 በመቶና በዋጋ 73 በመቶ ጨምሯል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በጥር ወር 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በዋጋ፣ 81 ሺህ 830 ቶን በመጠን ያገበያየ ሲሆን የካቲት ላይ በዋጋም በመጠንም ቅናሽ አሳይቷል።

Published in ኢኮኖሚ

ደብረ ብርሃን የካቲት 29/2010 የሰላም እንቅፋቶችን በማስወገድ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የአማራ ክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ የግማሽ ዓመቱን የዕቅድ አፈጻጸም ለመገምገም በደብረ ብርሃን ከተማ ለሦስት ቀናት ያካሄደው መድረክ ተጠናቋል።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጸጋዬ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች ህዝቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በመንግስት በኩል መልስ እንዲያገኙ ድልድይ ሆነው መስራት አለባቸው።

በተለይም በየአካባቢው በከፍተኛ ወጭ እየተከናወኑ ያሉ የመሰረተ ልማት፣የኢንቨስትመንትና ሌሎች ልማቶችን ሕብረተሰቡ በግልጽ እንዲያውቃቸው መረጃውን በአግባቡ ማድረስ እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

የልማት ሥራዎቹ ከዳር የሚደርሱት የተረጋጋና አስተማማኝ ጸጥታ ሲኖር በመሆኑ ሕብረተሰቡ የሰላምን ዋጋ በአግባቡ እንዲረዳ ማድረግ የባለሙያዎቹ አብይ ተግባር መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተለይ ህዝቡ የሚያነሳቸው የልማትም ሆነ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መልስ የሚያገኙት በሰላማዊ መንገድ ሲቀርቡ ብቻ በመሆኑ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች ይህን በማስገንዘብ በኩል በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በተለይ የአፍራሽ ኃይሎችን እኩይ ተግባር ማምከንና ህዝቡ በየጊዜው የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች አመራሩ መቼና እንዴት መፍታት አንዳለበት መጠቆም እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በአማራ ክልል ብዙሃን መገናኛ ድርጅት የስልጠና ጥናት ምርምርና የሚዲያ ዕቅድ ዝግጅት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሐሰን መሀመድ በበኩላቸው በአገሪቱ የብዙሀን መገናኛ ባለሙያዎች የሰላም ትሩፋትንና የሁከት አስከፊነትን ለሕብረተሰቡ በአግባቡ በማስተማር ከጥፋት ሊታደጓቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የባለሙያዎችን የእውቀትና የክህሎት ክፍተት በተጠና መንገድ በመለየት ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመው፣ "በእዚህም ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎች ለሕብረተሰቡ እንዲያደርሱ ይደረጋል" ብለዋል።

በዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ለሰላም ዘገባዎች ሰፊ ሽፋን አለመስጠት፣ ወቅታዊ መረጃዎችን በቦታው ተገኝቶ ፈጥኖ አለመዘገብ፣ የግጭትና የሰላም ዘገባዎች አለመጣጣምና በአንዳንድ ባለሙያዎች የግንዛቤ እጥረት መኖር የተስተዋሉ ክፍተቶች ናቸው።

ክፈተቶቹ ቢኖሩም የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች ከብዙሃን መገናኛ ድርጅት ጋር በቅንጅት በመስራት በተወሰነ ደረጃም የህዝብን ብሶት አውጥቶ በማሳወቅ  መፍትሄ እንዲያገኝ ያስቻሉ ዘገባዎች መሰረታቸውንም አቶ ሀሰን አመልክተዋል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የዜናና ህትመት ዝግጅትና ስርጭት ቡድን መሪ አቶ በእውቀት ደረሰ እንዳሉት፣ የዞኑ ሚድያ የመንግስትን የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ለህዝቡ በማድረስ ለልማቱ መፋጠን እየሰራ ነው።

ከዚህ በፊት የአመራሩን ሀሳብ ብቻ በማራመድ ለአርሶ አድሩ በቂ ሽፋን ይሰጥ አንዳልነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት በዘመናዊ ቴክኖሎጅ በመታገዝ የአርሶ አደሩ ድምጽ እንዲሰማ በመደረግ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

በደሴ ከተማ አስተዳደር የዜናና ህትመት ዝግጅትና ስርጭት ቡድን መሪ ወይዘሮ ማዕዛ ገብረጊዮርጊስ በበኩላቸው በከተማዋ ያለውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል የተለያዩ ሥራዎች አንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

ለሦስት ቀናት የተካሄደው የምክክር መድረክ ያለፉትን ወራት የመረጃ ተደራሽነት አፈጻፀም በመገምገም ለቀጣይ ሰላም መስፈንና የልማት ሥራዎች መጠናከር የሚያግዙ የኮሙዩኒኬሽን አቅጣጨዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 29/2010 ኢትዮጵያ የገጠማትን አለመረጋጋት ለመፍታት መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት መንግስታቸው እንደሚያደንቅ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ተናገሩ።

ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ የሚገኙት ሚኒስትሩ ዛሬ ከኢትዮጵያ አቻቸው ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እና ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ለጋዜጠኞች የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ዶክተር ወርቅነህ በመግለጫው ወቅት እንዳሉት "የሚኒስትሩ ጉብኝት የሁለቱን አገራት ወዳጅነት ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር ክስተት ነው።"

በቆይታቸውም በሁለቱ አገራት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች፣ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና በሌሎች ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እና መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት አስመልክቶ ለቲለርሰን ገለጻ እንዳደረጉላቸውም ተናግረዋል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚስተር ሬክስ ቲለርሰን በበኩላቸው በተመለከቱት ነገር መደነቃቸውን ገልጸው  ሀገሪቱ  እያስመዘገበች  ያለውን ኢኮኖሚያዊ እድገት አድንቀዋል።

ሀገሪቱ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ የምታበረክተው አስተዋጽኦና ለስደተኞች በሯን ክፍት ማድረጓ እንደሚያስመሰግናትም ነው የተናገሩት፡፡,

ኢትዮጵያ ከገጠማት ችግር ለመውጣት እያደረገች ያለው  እንቅስቃሴ የሚደነቅ መሆኑንና በተለይ ደግሞ ለዜጎች ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለማድረግ የሚሰራውን ስራ  መንግስታቸው እንደሚደግፈው አብራርተዋል።

የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ሲባል እስረኞችን ለመፍታት መወሰኑና ከፖሊቲካ ፓርቲዎች ጋር እየተደረገ ያለውን ውይይትም በአዎንታ አንስተዋል።

ህዝቡም "መንግስት እየሰራ ያለው የመታደስና የመለወጥ ስራ ፍሬ እስኪያፈራ በትዕግስት ሊጠብቅና ሊያበረተታ ይገባል" ብለዋል።

የተሟላ ዴሞክራሲ ላይ መድረስ ሂደት በመሆኑም በአጭር ጊዜ ለማሳካት መፈለግም ተገቢ አይደለም ሲሉም ተደምጠዋል።

አገራቸውም ይህን እንደምታበረታታና ድጋፍ እንደምታደርግ ያረጋገጡት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ "ኢትዮጵያውያን ከሁከትና ብጥብጥ በመታቀብ ለለውጥ ከመንግስት ጎን ሊቆሙ” እንደሚገባም ተናግረዋል።

በአገሪቷ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም መንግስት እስከመጨረሻው በጥንቃቄና በኃላፊነት ሊይዘው እንደሚገባ ጠቁመዋል።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 5

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን