አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 07 March 2018

አዲስ አበባ የካቲት 28/2010 የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር መስራት እንደሚፈልጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሼህ አብዱላሂ ቢን ዛይድ አል ናህያን ተናገሩ።

በቴክኒክ ኮሚቴ ደረጃ የተጀመረው የኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ሁለተኛው የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ዛሬ በዲፕሎማሲ ምክክር ሰነድ ፊርማ ተጠናቋል።

ስምምነቱም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁና በሼህ አብዱላሂ ቢን ዛይድ አል ናህያን ተፈርሟል።

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼህ አብዱላሂ ቢን ዛይድ አል ናህያን እንደተናገሩት በሁለቱ አገሮች መካከል እየተሻሻለ የመጣውን ሁለንተናዊ ግንኙነት ለማሳደግ በቅንጅት መስራት ይሻሉ።

በአገራቱ መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ በማጎልበት ሁለቱንም ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚ ለማድረግ እንፈልጋለን ነው ያሉት።

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ባለሃብቶች በአፍሪካ መዋዕለ ንዋያቸውን የማፍሰስ ሰፊ ፍላጎት ማሳየታቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ተመራጭ መሆኗን አስረድተዋል።

ዛሬ የተፈረመው የዲፕሎማሲ ወይም የፖለቲካ የምክክር ሰነድ በአሁኑ ወቅት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የ500 ሚሊዮን ዶላር የንግድ ልውውጥ ማሳደግ ያስችላልም ብለዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም በስራ ስምሪት፣ በአየር ትራንስፖርትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራዎችም ተጠቃለው በቅርቡ የጋራ ስምምነት  እንዲፈረም ጥረት እናደርጋለን ነው ያሉት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው ሁለቱ አገሮች የጋራ ተጠቃሚ በሚሆኑባቸው ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የተፈረመው የዲፕሎማሲ የምክክር ሰነድ አገራቱ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በአካባቢያዊ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

እ.ኤ.አ በ1973 የተጀመረው የሁለቱ አገሮች የዲፕሎማሲ ግንኙነት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በአካባቢያዊ ጸጥታና ሽብርተኝነትን በመከላከል ላይ ያተኮሩ ስራዎችን መከወን አስችሏል።

በአሁኑ ወቅትም ከ10 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ብር ያስመዘገቡ 135 የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከሚገኙ አራት ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች አንዷ መሆኗን የገለጹት ዶክተር ወርቅነህ፤ በኢትዮጵያ መሰማራት ለሚፈልጉ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ኩባንያዎች በሩ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአካባቢያዊ ጸጥታና ሽብርተኝነትን በመከላከል እንደምትሰራ ሁሉ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችም ከገልፍ አገሮች ጋር ያለውን እሰጥ አገባ በሠላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በቅርበት ትሰራለች ብለዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 28/2010 ሴቶችን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ የንቅናቄው ትግል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የአዲሰ አበባ ሴቶች ማህበር አሳሰበ።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንና የማህበሩ 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ዛሬ ተከብሯል።

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አልማዝ አብርሃ ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን በቀላሉ የተገኘ ድል ሳይሆን፤ በሴቶች እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በተከፈለ ትልቅ መስዋዕትነት እንደሆነ ተናግረዋል።

"በዚህ ታላቅ ቀን የሴቶችን የትግል ታሪክ የምንዘክርበትና የተገኙትንም ድሎች በማስታወስ ለመጪው ዘመን ትግሉ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቃል የምንገባበት ነው" ብለዋል።

የመዲናዋ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ዓለምፀሀይ ኤልያስ በበኩላቸው፤ ሴቶች በሁለንተናዊ ተሳትፎ ከፍተኛ ሚና ያላቸው የማህበረሰቡ አካል መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይም በአገሪቱ አሁን ያለውን አለመረጋጋትና የሰላም እጦት ችግር በመፍታትና ሰላም በማስፈን ረገድ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሴቶች ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ ብርቱካን አደራ ማህበራቸው ሴቶች በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ተሳትፎ የተሻለ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ከፍተኛ ሚና መጫወቱንና በ20 ዓመት ጉዞው በርካቶችን ማብቃቱን ተናግረዋል።

የሴቶች ጥቃት በመከላከልና የተጎዱ ሴቶችና ህጻናት ከጉዳታቸው የሚያገግሙባቸው ሁለት ጊዜያዊ መጠለያዎች አዘጋጅቶ እየሰራም ነው ብለዋል።

በዓለም ለ107ኛ በኢትዮጵ ለ42ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን "በተደራጀ የሴቶች ተሳትፎና ንቅናቄ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን"ሚል መሪ ሃሳብ ተመርጦለታል።

የአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር በሰባት ሺህ አባላት በ1990 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን አሁን ከ300 ሺህ በላይ አባላት አሉት።     

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 28/2010 የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የውጪ ጉዳይና አለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሼህ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ትላንት ምሽት አዲስ አበባ ገቡ።

ሚኒስትሩ በቆይታቸው ከከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽ፣ በቀጣናውና በአለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ የሚወያዩ ሲሆን በአገራቱ መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት በማሳደግ ዙሪያም ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የዘንድሮ የሁለቱ አገራት የጋራ ኮሚሽን ስብሰባም ከየካቲት 26-28 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለ ሲሆን የመጀመሪያው የጋራ ኮሚሽኑ ስብሰባ ከሶስት ዓመት በፊት በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ርዕሰ መዲና አቡዳቢ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

የሁለቱ አገራት ሚኒስትሮች ዛሬ ረፋድ ላይ በሸራተን አዲስ ለጋዜጠኞች በጋራ መግለጫ እንደሚሰጡም ይጠበቃል።

የአገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ከተጀመረ ዘመናት ያስቆጠረ ሲሆን ኢትዮጵያ ቆንስላዋን እ.ኤ.አ በ2004 በዱባይ፣ ኤምባሲዋን ደግሞ በ2014 በአቡዳቢ ከፍታለች።

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ደግሞ እ.ኤ.አ በ2010 ነበር ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ የከፈተችው።

Published in ፖለቲካ

ዲላ የካቲት 28/2010 ወጣቶች ለሁከትና ብጥብጥ ከሚገፏፏቸው አሳሳቾች ራሳቸውን በመጠበቅ ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ የጌዴኦ ብሔር አባገዳ ደንቦቢ ማሮ አሳሰቡ።

የብሔሩ ዘመን መለወጫ የሆነው ዓመታዊ የ"ደራሮ" ክብረ በዓል በጌዴኦ ዞን ቡሌ ወረዳ አጋምሳ ቀበሌ በሚገኘው ኦዳያአ ሸንጎ ተከብሯል፡፡

የብሔሩ ባህላዊ ሥርዐት መሪ አባ ገዳ ደንቦቢ ማሮ በበዓሉ ስነስርዓቱ ወቅት እንደገለፁት ወጣቶች በተሰማሩበት መስክ የሚገጥማቸውን ችግሮች በፀብና ባልተገባ መንገድ ለማስተካከል መሞከር የለባቸውም፡፡

በትዕግስትና በመወያየት ችግሮችን መፍታት ይጠበቅባቸዋል።

ጥያቄዎቻቸውን ተመርኩዘው ለሁከትና ግርግር ከሚገፋፏቸው አሳሳቾች ራሳቸውን በመጠበቅ ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ አሳስበዋል።

ስርቆትን፣ ያለአቻ ጋብቻን፣ አግባብ ያልሆነ ዛፍ ቆረጣንና ሌሎች ከብሔሩ ባህላዊ አስተምህሮ ውጪ የሆኑ ድርጊቶችን መከላከል እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ በበኩላቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋና ባህላዊ እሴቶቻቸውን እንዲያሳድጉና ለትውልድ እንዲያስተላልፉ ምቹ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው በዓሉ ሊከበር እንደቻለ ተናግረዋል፡፡

የጌዴኦ ህዝብ ጠንካራ የሥራና የተፈጥሮ ሀብትን የመንከባከብ ባህሉን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ በመቻሉ አካባቢው ልምላሜውን ጠብቆ እንዲቆይ ማስቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡

"ወጣቱ ትውልድ አባቶቹ ያቆዩለትን ባህላዊ እሴቶች እንዲያሳድግና ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ እንዲያስተላልፍ ለማድረግ ሁላችንም የበኩላችንን ኃላፊነት ልንወጣ ይገባል" ብለዋል ፡፡

የጌዴኦ ዞን ባህል ቱሪዝምና የመንግስት ኩሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ታሪኩ በየነ እንዳሉት የብሔሩ ባህላዊ ክዋኔዎችና ሀገር በቀል እውቀቶች ሰፊ ጥናት ተደርጎባቸውና ዳብረው የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው።

ወጣቱ ትውልድ ባህሉን እንዲያውቅና ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ እንዲችል የባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየም ጨምሮ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንደሚካሄዱም አስረድተዋል፡፡

ቋንቋውን የሥራ ከማድረግ ባሻገር ከዚህ በፊት በኮሌጅ ዲፕሎማ ደረጃ ይሰጥ የነበረው "ጌዴኡፋ" ቋንቋ ዘንድሮ በዲላ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ እየተሰጠ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል የቡሌ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ደሞዜ ደገፉ ከ"ደራሮ" በዓል ባህላዊ ሥርዓቶች ፍቅርን፣ መከባበርንና፣ ለሰላም ቅድሚያ መስጠትን ተገንዝቤያለሁ" ብሏል ፡፡

ክብረ በዓሉ ላይ መገኘቱ አባቶቹ ያቆዩለትን ባህላዊ እሴቶች ይበልጥ ለማወቅና ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ መነሳሳት እንደፈጠረለትም ተናግሯል።

በየዓመቱ በዚህ ወቅት የሚከበረው የብሔሩ ዘመን መለወጫ የ"ደራሮ" በዓል ከሰብል ምርት ማሰባሰብና ከቡና አበባ ማበብ ጋር ተያይዞ የሚከበር ሲሆን ለፈጣሪ ወይም በብሔሩ አጠራር  ለ"መጌኖ" ስለምርቱ ምስጋና የሚቀርብበት ነው፡፡

አበባው ፍሬ እንዲይዝና አርሶ አደሩ ሥራው እንዲባረክለት የሚፀለይበት፤ የባህሉ አባቶች በጉባኤያቸው ስላለፈው ዓመት የሚገመገሙበትና ስለቀጣዩ ዘመን እንዲተገበር የተላለፈው  ውሳኔ የሚያሳውቁበት በዓል ነው፡፡ 

Published in ማህበራዊ

ሀዋሳ የካቲት 28/2010 በሃዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም ዛሬ በተካሄደው የአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ  ወላይታ ዲቻ  የግብጹ ዛማሊክን  ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት አሸነፈ፡፡

ወላይታ ዲቻ ያሸነፈባቸውን ጎሎች ያስቀጠረው  በ15ኛው ደቂቃ ላይ በዛብህ ማለዮ እና በ77ው ደቂቃ ላይ ደግሞ በያሬድ ዳዊት አማካኝነት ነው፡፡

ለዛማሊክ ቡድን ደግሞ 19 ቁጥር ለብሶ የተጫወተው አማድ ፋቲ በ37ተኛ ደቂቃ ላይ ያስቆጠረ  ሲሆን ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያውን ክፍለ ጊዜ ያጠናቀቁት አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት ነበር፡፡

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ብዛት ያለው ስፖርት አፍቃሪና ደጋፊዎች ተከታትለውታል፡፡

የግብጹ ዛማሊክ107 ዓመት እድሜ ያለው ሲሆን ወላይታ ዲቻ ደግሞ በ2005 ዓ.ም እንደሆነ በስፍራው ጨዋታውን የተከታተለው የኢዜአ ሪፖርተር ዘግቧል፡፡

Published in ስፖርት

ደብረማርቆስ የካቲት 28/2010 የማህበረሰብ ጤና መድህን አባል መሆናቸው የሕክምና አገልግሎት በወቅቱ ለማግኘት እንዳስቻላቸው በምስራቅ ጎጃም ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ የደጀን ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

በወረዳው የጥርጭ  ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ  ይሳለሙሽ ጸጋ እንደገለፁት በዓመት አንድ ጊዜ  በከፈሉት 144 ብር  መዋጮ እርሳቸውን ጨምሮ ሦስት የቤተሰብ አባሎቻቸው ሕመም በተሰማቸው ጊዜ ጤና ተቋም በመሄድ ሕክምና እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህ አመት የአባልነት ክፍያው ወደ 240 ብር ቢያድግም እያገኙ ካለው የጤና አገልግሎት አኳያ ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለፁት ወይዘሮ  ይሳለሙሽ፣ ያጋጠማቸው የጆር ሕመም በጤና ጣቢያ ደረጃ ፈውስ የሚገኝለት ባለመሆኑ ወደሆስፒታል መላካቸውን ተናግረዋል ።

የጤና መድን አባል በመሆናቸው ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ የሕክምና አገልግሎት ያለችግር እያገኙ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በወረዳው የሰብ ሸንጎ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ደረሰ ብርሃኔ ናቸው።

ሌሎች አባል የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ላጋጠማቸው ጽኑ ሕመም እስከ 20 ሺህ ብር ወጭ ተሸፍኖላቸው በሆስፒታል ደረጃ ታክመው ሲድኑ ማየታቸውን የገለጹት አቶ ደረሰ፣ አገልግሎቱ ለድሀው ህብረተሰብ ጠቃሚ መሆኑን አረጋግጠዋል ።

እንደ አቶ ደረሰ ገለጻ በጤና ተቋማት ፈጣን አገልግሎት ያለመስጠትና የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት ሊስተካከሉ ይገባል።

የጤና መድህን አባል በመሆናቸው የቤተሰብ አባላት ጭምር ሕመም ባጋጠማቸው ጊዜ ገንዘብ ማፈላለግ ሳያስፈልጋቸው በጤና ጣቢያ እያሳከሙ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በወረዳው የዘመትን ቀበሌ ነዋሪ አቶ መልሴ ታሪኩ ናቸው ።

የደጀን ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ አስማምቸው ጫኔ በበኩላቸው እንደገለጹት ከዚህ ቀደም አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል በሕክምና ወቅት የሚጠየቀውን ክፍያ በመፍራት ሕመም ሲያጋጥመው ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋማት የመምጣት ልምድ አልነበረውም።

በዚህም በቀላሉ ታክመው መዳን ሲችሉ ለጽኑ ሕመም የሚዳረጉ በርካቶች እንደነበሩ ተናግረዋል ።

የጤና መድህን አገልግሎት ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ  አንዴ በሚከፈል የአባልነት መዋጮ  የህክምና አገልግሎት ማግኘት በመቻሉ ህብረተሰቡ ህመም ሲያጋጥመው ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋማት በመምጣት ጤንነቱን እየጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል ።

"በአገልግሎቱ ጤና ጣቢያ ደረጃ አንድ ግለሰብ እንደ ሕመሙ አይነት በአማካኝ ከ100 እስከ 600 ብር የአንድ ጊዜ የህክምና ወጭ ሽፋን ያገኛል " ብለዋል ።

በጤና ጣቢያው የመድኃኒት እጥረት ሲያጋጥም አባላት በገንዘባቸው ለሚገዙት መድኃኒት በሚያቀርቡት ደረሰኝ መሰረት ገንዘቡ እንዲመለስላቸው እየተደረገ መሆኑንም ኃላፊው ገልጸዋል።

ለሕሙማን ፈጣን አገልግሎት በመስጠት በኩል ያለውን ክፍተት በመለየት መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አስተባባሪ አቶ ላቃቸው አበበ በበኩላቸው በዞኑ ከሚገኙ 20 ወረዳዎች በ17ቱ የጤና መድህን አገልግሎት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።

" በወረዳዎቹ 109 ሺህ 400 የህብረተሰብ ክፍሎች በአባልነት ታቅፈው ተጠቃሚ እየሆኑ ነው " ብለዋል ።

በግማሽ ዓመቱ 26 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ከአባላት መዋጮ መሰብሰቡን የገለፁት አስተባባሪው ባለፈው ዓመት 50 ሚሊዮን ብር ወጭ በማድረግ አባላቱ በጤና ጣቢያና በሆስፒታል ደረጃ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን አስታውቀዋል።

Published in ማህበራዊ

ደብረብርሃን የካቲት 28/2010 ሰሜን ሸዋ ዞን በጫጫ ከተማ በክረምት የጎርፍ አደጋ መከላከል የሚያስችል የመፋሰሻ ቦይና የመሸጋገሪያ ድልድይ ግንባታ ባለመከናወኑ ስጋት እንደፈጠረባቸው ነዋሪዎች ገለፁ።

የከተማው መዘጋጃ ቤት በበኩሉ በ4 ሚሊዮን ብር  ከመጋቢት 1 ጀምሮ ግንባታውን ለመጀመር ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል ።

የከተማው ነዋሪ አቶ ከበደ ያዴቴ እንደገለፁት ባለፈው አመት ክረምት ወቅት የጣለ ከባድ ዝናብ ተከትሎ ጎርፍ በመንግስት ተቋማትና በግለሰብ ቤቶች ዘልቆ በመግባት የሀብት ውድመት አድርሷል ።

አደጋው የአንድ ጊዜ ሳይሆን በተደጋጋሚ መከሰቱን የገለፁት አቶ ከበደ ዘላቂ መፍትሄ እንዲበጅለት ለከተማ አስተዳደሩ በተደጋጋሚ ቢያመለክቱም በተግባር የሚገለፅ ስራ አለመሰራቱን ተናግረዋል ።

በዚህ ዓመት የክረምት ወቅት እየተቃረበ ቢሆንም የመከላከያ ስራው ባለመሰራቱ መሰል አደጋ ያጋጥማል የሚል ስጋት እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል፡፡

ዋና ሳጅን ታደሰ ወልደአማኑኤል በበኩላቸው አስተደደሩ በከተማው  ልማት ዙሪያ ነዋሪዎችን በማሳተፍ እየሰራ ባለመሆኑ ባለፈው አመት የተከሰተው የጎርፈ አደጋ ዘንድሮም ያጋጥማል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል ።

"እስካሁን ምንም አይነት የመከላከያ ግንባታ ባለመጀመሩ በነዋሪው ዘንድ ስጋት ፈጥሯል" ያሉት ዋና ሳጅን ታደሰ የከተማውን የጎርፍ ስጋት መከላከል ካልተቻለ እያደገ የመጣውን የኢንቨስትመንት ፍስት ሊገታው እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

የከተማው የመሪ ማዘጋጃ ቤት የማህበራዊ ዘረፍ ኃላፊ አቶ ዳግም እሸቴ  ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ  በከተማው በክረምት የሚያጋጥመውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ሰራዎች እየተሰሩ ቢሆንም ጥቃቱን ማስቀረት ግን አልተቻለም ።

ባለፈው አመት ክረምት የደረሰው የጎርፍ አደጋ በዚህ ዓመት እንዳይደገም ከነዋሪዎችና ከከተማው አስተዳደር በተገኘ 4 ሚሊዩን ብር 1 ኪሎ ሜትር አዲስ የማፍሰሻ ቦይ ግንባታና የ2 ኪሎ ሜትር የነባር ቦይ ጥገና ለማካሄድ ዝግጅት ተደርጓል።

በተጨማሪም የስድስት አነስተኛ ድልድዮች ግንባታ እንደሚካሄድ ተናግረዋል ።

እንደ ኃላፊው ገለፃ በሶስት አነስተኛና ጥቃቅን ማህበራት አማካኝነት የግንባታ ስራው መጋቢት 1 ቀን 2010 ዓ.ም ይጀመራል ።

 

Published in ማህበራዊ

አክሱም የካቲት 28/2010 በመስሪያ ቦታና በውሃ እጥረት የጀመሯቸውን የኢንቨስትመንት ሥራዎች ማስፋፋት እንዳልቻሉ በዓድዋ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ባለሃብቶች ገለጹ።

በከተማው በአልሙኒየም ማምረት ሥራ የተሰማሩት አቶ ተስፋይ ገብረሕይወት ለኢዜአ እንደገለጹት ሥራቸውን ማስፋፋት ቢፈልጉም የመስሪያ ቦታና የውሃ እጥረት እንቅፋት ሆኖባቸዋል።

በ2008 ዓ.ም መጨረሻ ተጨማሪ መሬት እንዲሰጣቸውና መሰረተ ልማት እንዲሟላ ጥያቄ ቢያቀርቡም በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩ ይፈታል ከማለት ውጪ እስካሁን ድረስ ለጥያቄያቸው አዎንታዊ ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል።

"ያለብን የቦታና የውሃ አጥረት እንዲሁም የመንገድ ችግር በየጊዜው ይፈታል እየተባልን በመጠባበቅ ላይ ነን" ብለዋል።

" ለመስሪያ ቦታ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ አካል የለም፤ በከተማ ውስጥ የመሰረተ ልማት ችግሮች አሉ፤ በዚህ ምክንያት ሥራዬን ለማቆም በሚያስችል ደረጃ ላይ ደርሻለሁ " ያሉት ደግሞ የግል ትምህርት ቤት ባለቤት የሆኑት መምህር ኤልያስ ፍስሃ ናቸው።

ካቋቋሙት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተጨማሪ የሕጻናት ማቆያ ማዕከል ለመክፈት ቦታ በነጻ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም ከከተማው መስተዳድር ተጨማሪ ቦታ ሳያገኙ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ከጥቃቅንና አንስተኛ ወደ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ በቅርቡ መሸጋገራቸውን የገለጹት አቶ ሙሴ ሙለይ በበኩላቸው፣ በከተማ መስተዳድሩ የሚደረግ የድጋፍና የክትትል ሥራ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት የሚያበረታታ አለመሆኑን አስታውቀዋል።

የአድዋ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተክላይ ፍስሃዬ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በከተማው ለጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾችና በተለያዩ የማኑፋክቸሪግ ኢንዱስትሪ ለተሰማሩ የግል ባለሃብቶ አገልግሎት የሚውል የመሸጫና የማምረቻ ቦታ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ባለሀብቶች ያነሱትን ተጨማሪ የመሬት ጥያቄ ለመመለስና ለተለያዩ ልማቶች የሚውል ከ18 ሄክታር በላይ መሬት መዘጋጀቱንም ጨምረው ገልጸዋል ።

ይሁንና በማህበራዊ አገልግሎት ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ባለሃብቶች መሬት በግልጽ ጨረታ ብቻ ተወዳድረው የሚያገኙ መሆኑን ነው አቶ ተክላይ ያስረዱት።

በኢንቨስትመንት መመሪያው ለተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫዎች ቦታ በነጻ መስጠት እንደማይቻልም ጠቁመዋል።

ከጥር 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለኢንቨስትመንት የሚውል መሬት በጨረታ እየተሰጠ መሆኑን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ ባለሀብቶቹ በዚሁ አግባብ መሬት በሊዝ መውሰድ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ተክላይ ገለጻ፣ የመሰረተ ልማት አለመሟላትን ተከትሎ ባለሃብቶቹ እያቀረቡት ያለው ችግር  በዚህ ዓመት ይፈታል።

ለውሃ መስመር ዝርጋታ፣ ለመንገድ ግንባታና የጎርፍ አደጋን ለመከላከል 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ወደ ሥራ እየተገባ መሆኑንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

ባለሃብቶቹ በአንድ አካባቢ የሚገኙ መሆናቸው የመሰረተ ልማት ጥያቄያቸውን በተያዘው ዓመት ሰርቶ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል ።

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ የካቲት 28/2010 በምስራቅ ሸዋ ዞን አደአ ወረዳ ድሬ ሾኬ በተባለው ቀበሌ ገበሬ ማህበር በጦር መሳሪያ ጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ  የአንዲት ህጻን ልጅ ህይወት ማለፉን ፖለስ አስታወቀ፡፡

አደጋው የደረሰው በቀበሌ የሚኖሩ እህትና ወንድም ህጻናት ትናንት አስር ሰዓት አካባቢ በመኖሪያ ቤታቸው  መኝታ አልጋ ላይ ተቀባብሎ የተቀመጠ ሚንቶፍ የተባለ የጦር መሳሪያን አግኝተው እየተጫወቱበት እንዳለ ነው፡፡

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት የ12 ዓመቱ ታዳጊ የስምንት ዓመት እድሜ ያላት ታናሽ እህቱ ላይ የጦር መሳሪያውን ደቅኖ በመጫወት ላይ ሳለ  ድንገት ባርቆበት  በተፈጠረው አደጋ ህይወቷ ሊያልፍ ችሏል፡፡

የጦር መሳሪያው ህጋዊ ፈቃድ ያለው ቢሆንም የልጆቹ ወላጆች በጥንቃቄ ካለመያዝ የተነሳ አደጋው መድረሱን አስታውቀዋል፡፡

በቅርቡም በዚሁ ወረዳ ወንድማማች የሆኑ ሁለት ህፃናት ከመኖሪያ  ቤታቸው ያገኙትን የእጅ ቦንብ በድንጋይ  ሲቀጠቅጡ ፈንድቶባቸው ህይወታቸው ማለፉን አስታውሰዋል፡፡

ወላጆች  በጦር መሳሪያ አያያዝና አጠቃቀም ላይ ጥንቃቄ ሊደርጉ እንደሚገባም ኮማንደር አስቻለው አሳስበዋል፡፡

አዲስ አበባ የካቲት28/2010 መንግስት የአበባ ልማት መስኩን በጉድኝት ማዕከላት ለማደራጀትና ፓርኮችን ለማቋቋም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።

ከመቶ በላይ ኩባንያዎችን መሳብ የቻለው ይህ መስክ በተበታተነ መልኩ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኝ ከ3 ሺህ ሄክታር በሚልቅ መሬት ላይ እየለማ ይገኛል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር ባልካቸው መኩሪያ ለኢዜአ እንደገለጹት ይህንን ትልቅ የስራ እድል እየፈጠረና በወጪ ንግዱም አይነተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለን ዘርፍ በተበታተነ እርሻ ማልማቱ ውጤታማ አያደርግም።

የአበባ እርሻ ስራውን በፓርኮች በማቀናጀት ትልቅ ውጤት ማምጣት ይቻላል ያሉት ዶክተር ባልካቸው ለዚህም ለአበባ እርሻ ምቹ የሆኑ አምስት የተለያዩ አካባቢዎች መመረጣቸውን ተናግረዋል። 

ከተመረጡት ቦታዎች መካከል ባህርዳር፣ ሀዋሳ፣ አርባምንጭና በሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ ዜሮ የፈሳሽ ውሃ ማጣሪያ ስርዓት ያላቸው አካባቢዎች መደራጀታቸውን ጠቅሰዋል።

ይህ መደረጉ በዘርፉ ለሚሰማሩ አካላት የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጠት ከማስቻሉ በላይ ምርቶቻቸውን ከዋና ዋና የአገሪቱ ከተሞች ወደ ተለያዩ የምርቱ መዳረሻ አገሮች መላክ የሚያስችል የአየር ትራንስፖርት በቀላሉ እንዲያገኙ ይረዳል ነው ያሉት።

ይሁን እንጂ የአበባ እርሻን በጉድኝት ማዕከላት የማደራጀትና የእርሻ ፓርኮችን የማቋቋም ስራው ውጤታማ እስኪሆን ድረስ አሁን ያለው አሰራር ይቀጥላል ብለዋል።

እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለፃ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅምና የውጭ ንግድ ድርሻውም ከፍተኛ ሆኖ ሳለ በተበታተኑ የእርሻ ቦታዎች መሰራቱ ውጤቱ አነስተኛ በመሆኑ በፓርኮች በማቀናጀት ትልቅ ውጤት ማምጣት ይቻላል።

ለዚህም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት የሚታወቁ ቦታዎች መለየታቸውን ገልፀዋል።

ሆርቲካልቸርና ግብርና ኢንቨስትመንት ባለስልጣን በዚህ ዓመት በተለያዩ አካባቢዎች ለሆርቲካልቸር ኢንቨስትመንት የሚሆን 6 ሺህ ሄክታር መሬት ተዘጋጅቷል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አዱኛ ደበላ እንደገለጹት በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለመሳብ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።

የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቬስተሮች በዘርፉ እንዲሰማሩ ለማስቻል አዲስ የማበረታቻ ማእቀፍ መቀረጹንም ነው የተናገሩት።

የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በዘርፉ ለሚያካሂዱት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የሚያስፈልጋቸውን ካፒታል 30 በመቶ ካቀረቡ ቀሪውን ከልማት ባንክ በብድር የሚያገኙበት አማራጭ የነበረ ቢሆንም አሁን ወደ 15 በመቶ ዝቅ መደረጉን ጠቁመዋል።

የታክስ ዕፎይታ ለኩባንያዎች ሌላው ማትጊያ ሲሆን አንድ ኩባንያ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት 85 ከመቶ ምርት ወደ ውጪ መላክ ከቻለ ለስምንት ዓመት የታክስ እፎይታና እቃዎችን ማስመጣት እንደሚችል ጠቁመዋል።

ይህን በማድረግ አገሪቷ እንደ ኢንዱስትሪ ባሉ መናፈሻዎች ውስጥ የአትክልት እርሻዎችን በማስፋት ኩባንያዎች የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚያስችል ገልፀዋል።

በተጨማሪም ኩባንያዎቹ ምርቶቻቸውን ወደ ዓለም ዋና ዋና የገበያ መዳረሻዎች ለመላክ እንዲችሉ የአየር ትራንስፖርት በቀላሉ ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ለዚህም ሲባል የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ለተሠማሩ ኩባንያዎች ከባህርዳር ቱሌጅ ቤልጄም ቀጥታ የበረራ አገልግሎት እንደሚጀምር ጠቁመዋል።

ይህም ላኪዎች የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጪ በመላክ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ እንደሚረዳ ነው የገለፁት።

ባለፈው ዓመት በዘርፉ 270 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱንና በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራትም ከ130 ሚሊዩን የአሜሪካን ዶላር በላይ መገኘቱንም ገልፀዋል

አትክልትና ፍራፍሬ ከቡናና ሰሊጥ ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ አገሪቱ የውጪ ምንዛሬ ከምታገኝባቸው ምርቶች አንዱ ነው።

 

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን