አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 06 March 2018

መቀሌ የካቲት 27/2010 የትግራይ ልማት ማህበር ያስገነባቸው ትምህርት ቤቶች በአቅራቢያቸው ትምህርት ለማግኘት እንዳስቻላቸው ተማሪዎች ገለጹ።

በክልሉ ሰሜን ምዕራብ ዞን የመደባይ ዛና ወረዳ አዲ ባዕረጅ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ ተማሪ ይብራለም ገብረክርስቶስ በሰጠችው አስተያየት ከዚህ ቀደም በአካባቢው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ትምህርት ፍለጋ በየቀኑ የሦስት ሰዓት እግር ጉዞ ታደርግ ነበር ።

" በተለይ መንገዱ ለሴት ተማሪዎች  አስቸጋሪ በመሆኑ በ2007 ዓ.ም የስምንተኛ ክፍል ትምህርቴን እንዳጠናከክኩ ለማቋረጥ ተገደጄ ነበር "ብላለች።

ባለፈው ዓመት ማህበሩ በአካባቢው ያስገነባው ትምህርት ቤት ሥራ በመጀመሩ የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቷን ለመቀጠል መቻሏን ገልጿለች።

"ማህበሩ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት ከማስገንባቱ አንድ ዓመት በፊት በዳስ ውስጥ ለጸሐይና ለአቧራ ተጋልጠን ትምህርታችንን እንከታተል ነበር " ያለው ደግሞ በወረዳው ትኩለ ቀበሌ ገበሬ ማህበር "የጭላጭቕኒ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት" የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ገብረ ሀጎስ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ማህበሩ የገነባው ትምህርት ቤት ሥራ በመጀመሩ ከችግሩ መላቀቃቸውን ተናግሯል።

የቀበሌ ገበሬ ማህበሩ ነዋሪ አቶ ጉዑሽ ታደሰ በበኩላቸው ከቅርብ ዓመታት በፊት በአካባቢው ምንም አይነት ትምህርት ቤት ስላልነበረ እርሳቸው የመማር ዕድል አንዳልነበራቸው አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ሦስት ልጆቻቸውን በአቅራቢያቸው ማስተማር በመቻላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ነው የገለጹት ።

የማህበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ታደለ ሀጎስ እንደገለፁት ማህብሩ በየወሩ ከአባላት በሚሰበስበው መዋጮና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ በጎአድራጊ ድርጅቶች ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ያስገነባቸው ትምህርት ቤቶች ለአገልገሎት በቅተዋል።

ማህበሩ ባለፈው ዓመት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በ174 ሚሊዮን ብር ያስገነባቸው 20 አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት መስጠት እንደጀመሩ ገልፀዋል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 27/2010 የተቋማት ተቀናጅቶ አለመስራትና ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ አለመኖር በመንገድ ሀብት አጠቃቀም ላይ ችግር እየፈጠረ ነው ተባለ።

የባለድርሻ አካላት ተቀናጅቶ አለመስራት በመዲናዋ የመንገድ ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደር ከፍተኛ ተግዳሮት እየፈጠረ መሆኑን የገለፀው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ነው።

ባለስልጣኑ የመንገድ መብት ጥሰትን ለመከላከል የህብረተሰቡና የባለድርሻ አካላት ሚና በሚል የውይይት መድርክ አዘጋጅቷል።

የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት ቢሮው በመንገድ ግንባታና በትራንስፖርት አገልግሎት አበረታች ስራዎች እያከናወነ ቢሆንም ከባለድርሻ አካላት ጋር ተናቦ የመስራት ክፍተት አለበት።

በዚህ ሳቢያም በከተማዋ የመንገድ መብት ጥሰት እየተከሰት ነው።

በፍጥነት እያደገ የመጣውን የተሳለጠ የመንገድ አገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት የባለድርሻ አካላት ተናቦ መስራት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

በውይይት መድረኩ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት የሰሜን አዲስ አበባ መንገድ ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር ኢንጂነር እስማኤል ሰኢድ በቅንጅት የተዘጋጀ የመሰረተ ልማት ዕቅድ ባለመኖሩ ያለ ባለሥልጣኑ ፈቃድ የመንገዶች መቆፈርና መቆረጥ ይካሄዳል።

በህገወጥ የጎዳና ንግድ የእግረኞች መንገድ መዘጋትና የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ቱቦዎች በደረቅ ቆሻሻ መሞላትም ለመንገዶች መበላሸት ተጨማሪ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ስራውን አቀናጅቶ ለመምራት በአዋጅ የተቋቋመ አካል ቢኖርም ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ ችግር ተፈጥሯል የሚሉት ዳይሬክተሩ የችግሩ አለመፈታት ባለስልጣኑን ለአላስፈላጊ ወጪ እየዳረገው ነው ብለዋል።

የባለስልጣኑ የህግ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ፋሲል በለጠ በበኩላቸው ለመስሪያ ቤቱ የተሰጠው የህግ ማዕቀፍ ጠንካራ ባለመሆኑ የመብት ጥሰቱን መከላከል እንዳልተቻለ አስረድተዋል።

በተለይም የሚጣለው ቅጣት የገንዘብ ብቻ መሆኑ የመብት ጥሰት ፈፃሚዎቹ ከስህተታቸው እንዳይማሩ አድርጓቸዋል ነው ያሉት።

በደንብ ደረጃ የተቀመጠውን የህግ ማዕቀፍ በአዋጅ በማርቀቅና እስከ አካላዊ ቅጣት የሚደርስ ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ችግሩን መፍታት እንደሚገባ አቶ ፋሲል ገልፀዋል።

"መብራት ኃይል ወይም ቴሌ ሲቆፍር ለምን ብለን ስንጠይቅ ፈቃድ ያሳዩናል፤ አንዳችን ሰርተን አንዳችን እናፈርሳለን፤ ለምን አንናበብም" ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ግርማ ኤርሚያስ ናቸው።

አሁን ያለው የመንገድ ስራ አካል ጉዳተኞችን ከግምት ያስገባ ባለመሆኑ ባለስልጣኑ "ከእኛ ጋር ተነጋግሮ ፍላጎታችንን ባለመረዳቱ ነው" በማለት ከአካል ጉዳተኞች ማህበር የመጡት አቶ አዲስዓለም በቀለ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ችግሩን ለመፍታት ተናቦ መስራት፣ ስራ ተቋራጮች ዘመናዊ የግንባታ ዘዴዎችን እንዲጠቀሙ ማድረግ፣ ህብረተሰቡን በማስተማር ረገድ መገናኛ ብዙሃን የድርሻቸውን እንዲወጡ የአጭር ጊዜ ስትራቴጂክ ዕቅድ በማውጣት ማቀናጀት ያስፈልጋል ሲሉ ኢንጂነር እስማኤል የመፍትሔ ሃሳብ አስቀምጠዋል።

መድረኩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመስራት የመጀመሪያ መሆኑን የገለፁት የባለስልጣኑ የመንገድ ሀብት አጠቃቀም ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ደመላሽ ገብረስላሴ ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከር ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የትስስር ሰነድ መዘጋጀቱንና የህግ ማዕቀፉን የማሻሻሉም ጉዳይ የታመነበት በመሆኑ ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አክለዋል።

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር  የካቲት 27/2010 በአማራ ክልል የወጣቶች ተዘዋዋሪ  የገንዘብ  ብድር  ዘግይቶ  በመለቀቁ   በገጠር  የሥራ  ዕድል  ፈጠራ   ወጣቶችን  በሚፈለገው ልክ ወደ ሥራ  ለማስገባት  እንዳልተቻለ  የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

  ሆኖም  እስካሁን  በተከናወነው  ስራ  66 ሺህ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተነግሯል፡፡

 በቢሮው የስራተ ጾታና ወጣቶች ጉዳይ ባለሙያ አቶ ማስረሻ በዛብህ ለኢዜአ እንደገለጹት የሥራ ዕድሉ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት የተፈጠረው በአንድ ሺህ 740 ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ ሥራ አጥ ወጣቶች ነው።

 ወጣቶቹ በመስኖ ልማት፣ በእንስሳት እርባታና ማድለብ፣ በተፈጥሮ ሃብት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ዘርፎች መሰማራታቸውንም ተናግረዋል።

 ለወጣቶቹ ከተዘዋዋሪ ፈንድ በጀት 142 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር፣ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ እጥረት ላለባቸው ደግሞ አንድ ሺህ 17 ሄክታር መሬት እንደተሰጠም ገልፀዋል።

 አቶ ማስረሻ እንዳሉት፣ ወጣቶቹ ሥራ ከመጀመራቸው በፊትም ውጤታማ አንዲሆኑ በየአካባቢው ከሚገኙ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል።

 ለሚያለሙት የአትክልትና ለሚያደልቧቸው እንስሳትም የገበያ ችግር እንዳይገጥማቸው ከአካባቢው ሆቴልና ስጋ ቤቶች ጋር የማስተሳሰር ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።

 አቶ ማስረሻ አንዳሉት፣ የወጣቶች ተዘዋዋሪ የገንዘብ ብድር ዘግይቶ መለቀቁ ወጣቶችን በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት ወደሥራ ለማስገባት እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል።  

 በምስራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ የትኖራ ቀበሌ አምስት ሆነው በመደራጀት ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ በወተት ልማት ዘርፍ መሰማራታቸውን የገለጸው ደግሞ አበባ አዲስና ጓደኞቻቸው የወተት ላም ሽርክና ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ምንያህል አድማሴ ነው።

 ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ከተመደበው ተዘዋዋሪ የገንዘብ በድር ባገኙት 900 ሺህ ብርና ራሳቸው በቆጠቡት 100 ሺህ ብር 15 የፈረንጅ ላሞችና ሁለት ጊደሮች በመግዛት የእርባታ ሥራቸውን በማከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 ከሚታለቡት ስምንት የፈረንጅ ላሞችም በቀን 86 ሊትር ወተት ለየትኖራ ወተት ልማት ግብይት ሕብረት ሥራ ማህበር በማስረከብ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን አስረድቷል።

 ማህበሩ በሊትር የሚከፍላቸው ሰባት ብር ዋጋ ዝቅተኛና የላሞችን መኖ የማይሸፍን በመሆኑ በቀጣይ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን መንግስት የገበያ ትስስር እንዲፈጥርላቸውም ወጣት ምንያህል ጠይቋል።

 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ታች አርማጭሆ ወረዳ ጢሻ ቀበሌ የሚኖረው ወጣት ዳዊት ምናለ በበኩሉ ሦስት ሆነው በመደራጀት በመስኖ ልማት መሰማራታቸውን ተናግሯል።   

 ከቤተሰብ ባገኙት ሦስት ሄክታር መሬት በዓመት ለሦስት ጊዜ ያህል ቲማቲም አልምተው ለገበያ በማቅረብ እስከ 135 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ላይ መሆናቸውን ገልጿል።

 በክልሉ በተያዘው የ2010 ዓመት ማጠናቀቂያ ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች ተለይተው ለተመዘገቡ 218 ሺህ ሥራ እጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ታውቋል ፡፡

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ የካቲት 27/2010 የመንግስትን ገንዘብ ለግል ጥቅም በማዋልና በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ወንጀል የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች እስከ 12 ዓመት በሚደርስ ዕኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ መወሰኑን የትግራይ ክልል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ ህዝብ ግንኙነት ኦፊሰር አቶ ወልደገብርኤል ወልደማርያም ለኢዜአ እንደገለጹት ከተከሳሾቹ መካከል ሰረቀ ተስፋዬ የተባለ ግለሰብ የታህታይ አድያቦ ወረዳ ፋይናንስ ጽህፈት ቤት የሂሳብ ሰራተኛ ሆኖ ሲሰራ ባለፈው ዓመት 199ሺህ 154 ብር ለግል ጥቅሙ አውሎ ተገኝቷል፡፡

ግለሰቡ የመንግስት ገንዘብን አጭበርብሮ ለግል ጥቅሙ  በማዋል ክስ የመሰረተበት የክልሉ ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቢ ህግ ድርጊቱን በማስረጃ እንዳረጋገጠበት ነው ኦፊሰሩ ያመለከቱት

ግለሰቡ እንዲከላከል የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እድል ቢሰጠውም ባለመቻሉ ትናንት በዋለው ችሎት በ12 ዓመት ፅኑ እስራትና በሶስት ሺህ ብር እንዲቀጣ  የወሰነበት መሆኑን አስታውቀዋል።

በሌላ በኩልም ተክለብረሃን ኪሮስ የተባለ ግለሰብ ከሁለት ዓመታት በፊት ከሼባ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በዲግሪ የተመረቀ አስመስሎ የሀሰት ማስረጃ ለደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ በማቅረብ በሁመራና በሸራሮ ከተሞች ተመድቦ ሲሰራ መቆየቱን አቶ ወልደገብርኤል አመልክተዋል።

ግለሰቡ በቆይታው የማይገባው 194ሺህ402 ብር ለግል ጥቅሙ ማዋሉ የኮሚሽኑ ዓቃቢ ህግ በማስረጃ አረጋግጦበት ክስ እንደመሰረተበት ጠቁመዋል፡፡ 

ግለሰቡ ክሱን መከላከል ባለመቻሉ የሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትናንት በዋለው ችሎት በዘጠኝ ዓመት ፅኑ እስራትና በሶስት ሺህ ብር እንዲቀጣ የወሰነበት መሆኑን ኦፊሰሩ አስታውቀዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 27/2010 የግል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ለውጭ አገር የስራ ስምሪት ስልጠና የመስጠት ፈቃድ እንዳልተሰጣቸው ተገለጸ።

ይህን የገለጸው የአዲስ አበባ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ስልጠናውን እንዲሰጡ የተመረጡት ተቋማት ሰልጣኞችን ለመቀበል አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቀው እየተጠባበቁ ነው ብሏል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አንዱአለም ዘውዴ ለኢዜአ እንደገለጹት በአዲስ አበባ የእንጦጦ፣ ጄኔራል ዊንጌት፣ ንፋስ ስልክ፣ ምስራቅና የአቃቂ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆችና የልደታ፣ የካ፣ የአዲስ ከተማና የጎፋ ኢንዱስትሪያል ኮሌጆች ለውጭ አገር የስራ ስምሪት ስልጠና የመስጠት ፈቃድ አግኝተዋል።

በመሆኑም ለውጭ አገር ስራ ስምሪት ስልጠና መውሰድ የሚፈልጉ ዜጎች ፈቃድ ካገኙት ተቋማት ውጪ ቢሰለጥኑ ተቀባይነት የማያገኙ በመሆኑ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስታውቀዋል።

የተመረጡት ኮሌጆች በአገር ውስጥ ተመሳሳይ ስልጠናዎች እየሰጡ ሲሆን ብቃታቸው ተፈትሾ ለስምሪቱ አስፈላጊውን ትምህርት መስጠት የሚችሉበት አቋም ላይ መሆናቸው ተረጋግጧል ነው ያሉት።

ኮሌጆቹ በዚህ ዓመት ለውጭ አገር የስራ ስምሪት 13 ሺህ ዜጎችን ለማሰልጠን ዝግጁ በመሆናቸው በቤትና ሕፃናት አያያዝ /ሞግዚትነት/፣ በምግብ ዝግጅትና የቤት ውስጥ መስተንግዶ እንዲሁም በአዛውንቶች እንክብካቤ ትምህርቶችን ይሰጣሉ።

መሰረታዊ የዓረብኛና የእንግሊዝኛ ቋንቋዎችም በስልጠናው የተካተቱ ናቸው።

የጄኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሰልጣኝ ልማት ምክትል ዲን አቶ ታምራት ዘገየ እንደገለጹት ኮሌጁ ለስራ ወደ ውጭ አገር የሚጓዙ ሰዎችን ለማሰልጠን መምህራን በመመደብና የተግባር ትምህርት የሚሰጥባቸውን ቦታዎች በማመቻቸት ዝግጅቱን አጠናቋል።

ቀደም ሲል አጫጭር ስልጠና የመስጠት ልምድ በማካበቱ ይህንን እድል በመጠቀም ለሰልጣኞች አስፈላጊውን ክህሎት በማስጨበጥ ተመዝነው ማረጋገጫ እንዲወስዱ ያደርጋል ብለዋል።

የእንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ዲን ወይዘሮ ሙሉ አፅብሃ እንደተናገሩት ኮሌጁ ስልጠናውን ለመስጠት በቂ የሰው ኃይል፣ ወርክሾፕ፣ የመኝታ ክፍሎችና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን አሟልቶ ሰልጣኞችን እየተጠባበቀ ነው።

ተመሳሳይ አጫጭር ስልጠናዎችን ሲሰጥ በመቆየቱ የተደራጀ ቁሳቁስና የሰው ኃይል እንዳለው ነው የተናገሩት።

ሰልጣኞቹ ለውጭ አገር የስራ ስምሪት የሚያስፈልገውን ስልጠና ከወሰዱ በኋላ የብቃት ማረጋገጫ እንዲያገኙ እንደሚደረግ አክለዋል።

Published in ማህበራዊ

ሀዋሳ የካቲት 27/2010 በወላይታ ሶዶ ከተማ የመንገድ ጥበት ለተሽከርካሪ አደጋ እያጋለጣቸው በመሆኑ መፍትሔ ሊፈለግለት እንደሚገባ ነዋሪዎች ጠየቁ።

ከተማውን አቋርጦ የሚያልፈው ባለአንድ መስመር ጠባብ የአስፓልት መንገድ የተሽከርካሪና የእግረኛ እንቅስቃሴን በአንድ ላይ በማስተናገዱ ለአደጋ ምክንያት መሆኑን  ነዋሪዎቹ ተናግረዋል ።

በአንድ መስመር ላይ መኪናና ሰው በሚያደርጉት ጉዞ የትራፊክ መጨናነቅ በመፍጠር ለተደጋጋሚ የትራፊክ አደጋ መከሰት ምክንያት እየሆነ ነው፡፡

አቶ ተስፋዬ ተገኝ የተባሉ ነዋሪ በሰጡት አስተያየት ''ነገ ትልቅ ቦታ ደርሳ ትጦረኛለች ብዬ  የምጠብቃት ሴት ልጄ በመኪና አደጋ ለህልፈተ ህይወት ተዳርጋለች'' ብለዋል፡፡

በመንገድ ጥበትና የእግረኛ መንገድ ያለመኖር ምክንያት እንደዋዛ እየጠፋ ያለውን የሰው ሕይወት ለመታደግ አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል ።

ሌላው የከተማው ነዋሪና አሽከርካሪ  አቶ አብዲ ሸርፍ በበኩላቸው ላለፉት ስድስት ዓመታት አደጋ ሲያሽከረክሩ ምንም አይነት አደጋ ገጥሟቸው እንደማያውቅ ተናግረዋል ።

"በከተማው ያለው የትራፊክ መጨናነቅ ግን ሁሌም በስጋት እንዳሽከረክር ያደርገኛል " ብለዋል ።

አቶ አብዲ እንዳሉት በከተማው በጠባብ መንገድ ላይ በፍጥነት ማሽከርከር፣ ደርቦ ማለፍ፣ ያለቦታ መታጠፍና ርቀት ጠብቆ አለመጓዝ ለተሽከርካሪ አደጋ ምክንያት ናቸው ።

የዞኑ የትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመቀ ደጀኔ እንደገለፁት የተሽከርካሪ አደጋ ለመቀነስ ምክንያቶቹን ለይቶ መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ ነው ።

በሶዶ ከተማ የመንገድ ጥበት ችግር ለማቃለል ከአዲሱ ሌዊ ሆቴል እስከ እርሻ ጣቢያ ያለውን 5 ኪሎ ሜትር መንገድ ደረጃ ለማሳደግ ከኢትየጵያ መንገዶች ባለስልጣን ጋር ከስምምነት መደረሱን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

የአሽከርካሪዎች ብቃት በተመለከተም ያለውን ችግር ለመቅረፍ 5 ማሰልጠኛ ተቋማት ያላሟላቸው ነገሮች በመኖሩ ተዘግተዋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የ10 ኪሎ ሜትር አዲስ የውጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ ስራ መጀመሩን የገለፁት ሀላፊው ሲጠናቀቅ ለተሽከርካሪ እንቅሰቃሴ አማራጭ በመሆን አሁን በአንድ ዋና መንገድ ላይ የሚስተዋለውን መጨናነቅ እንደሚቀንሰው አመላክተዋል ።

በከተማው በመንገድ ዳር የሚቆሙ ከባድ ጭነት ተሸከርካሪዎችን  ለማስቀረት በ20 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ በ6 ሚሊዮን ብር ወጭ የተሽከርካሪ ማቆሚያ መናኽሪያ ለመገንባት ዝግጅት መደረጉን ሀላፊው አስታውቀዋል ።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ወንጀል መከላከልና ቁጥጥር ዋና ስራ ሂደት ኢንስፔክተር ሃብታሙ አሰፋ እንደተናገሩት በግማሽ ዓመቱ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የ33 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በ32 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል ።

Published in ማህበራዊ
Published in ቪዲዮ

ሀዋሳ የካቲት 26/2010 በደቡብ ክልል በተሽከርካሪ አደጋ የሚደርሰውን የህይወትና የንብረት ጥፋት ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት  የዘርፉ የአመራር  ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ።

በክልሉ የካቲት 28 እና 29 ቀን 2010 አ.ም የሚካሄደውን የመንገድ ደህንነት የንቅናቄ መድረክ አስመልክቶ የክልሉ ትራንስፖርት ቢሮና ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል ።

የክልሉ የትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ስኳሬ ሾዳ እንዳሉት በክልሉ ከሚደርሱ የተሽከርካሪ አደጋዎች ከ80 በመቶ በላዩ በአሽከርካሪዎች የስነምግባር ችግርና የክህሎት ማነስ የሚከሰት ነው ።

በሌሊት የሚደረግ ጉዞና ህገወጥ የህዝብ ትራንስፖርት ስምሪት ለአደጋው መባባስ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ጠቁመዋል ።

በዘርፉ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና የስራ ኃላፊዎች ህግና መመሪያን በአግባቡ በማስፈፀም ለአደጋው መቀነስ  በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

ዘንድሮ በሚካሄደው የህዝብ ንቅናቄ መፍጠሪያ መድረግ በግንባር ቀደም ተሳትፎ እንዲያደረጉ አሳስበዋል ።

በቢሮው የመንገድ ትራፊክ ደህንነትና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር አቶ መርከቡ ታደሰ በበኩሉ በክልሉከፍተኛ የተሽከርካሪ አደጋ የሚደርስባቸውን አካባቢዎች በመለየት አደጋውን ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ጋሞጎፋ፣ ወላይታ፣ ቤንች ማጂ፣ ጌዴኦና ሀድያ ዞኖች እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ስድስት ወራት ከፍተኛ አደጋ የተመዘገበባቸው መሆናቸውን ጠቅሰዋል ።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ በክልሉ በግማሽ አመቱ ከደረሰው 786 አደጋ  421 አደጋ  በእነዚሁ አካባቢዎች የደረሱ ናቸው  ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍስሀ ጋረደው በዚሁ ግዜ እንደተናገሩት ዓምና በክልሉ የተካሄደው የትራፊክ አደጋን የመከላከል ንቅናቄ ስራ ከፍተኛ ለውጥ መምጣት እንደቻለ ጠቁመው ችግሩን ለመቅረፍ አሁንም በትኩረት ሊሰራ ይገባል  ብለዋል፡፡

አንዳንድ የትራፊክ ፖሊሶች ጥፋተኛ አሽከርካሪዎችን ከመምከር ጀምሮ ተገቢውን ቅጣት አለመቅጣቸው ሌላው ለአደጋው መባባስ ምክንያት መሆኑንም  ተናግረዋል ።