አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 05 March 2018

አዲስ አበባ የካቲት 26/2010 የህትመት ኢንዱስትሪውን ችግሮች የሚፈታ የኮርፖሬት አደረጃጀት ማቋቋም እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ተናገሩ።

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ የህትመት ዘርፉን ችግሮች መፍታት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መክረዋል።

ኢትዮጵያ 70 በመቶ የህትመት ፍላጎቷን በውጭ አገራት የምታሳትም ሲሆን ይህም ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ እየዳረጋት በመሆኑ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠቁሟል።

የህትመት ኢንዱስትሪውን ክፍተት ለመሙላት በዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶች የኮርፖሬት አደረጃጀት ማቋቋም እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

በውይይቱም የኢትዮጵያን የወረቀት ህትመትና የአሳታሚነት ኢንዱስትሪ ችግሮችን በተመለከተ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት፣ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር አለመኖር፣ የግብዓትና የአደረጃጀት ችግሮች ዘርፉ በሚጠበቀው ልክ እድገት እንዳያስመዘግብ ማድረጋቸውን የሚያሳይ መነሻ ጽሁፉ ቀርቧል።

በጽሁፉ ላይ በተደረገ ውይይት የመድረኩ ተሳታፊዎች የውጭ ህትመትን ለማስቀረት ኢንዱስትሪውን አቀናጅቶ ማሰራት የሚያስችል የኮርፖሬት አደረጃጀት እንደሚያስፈልግ አጽንዖት ሰጥተው አስተያየታቸውን አቅርበዋል።

ጽሁፉን ያቀረቡት በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የቢዝነስ ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታሁን ነጋሽ እንደተናገሩት የህትመት ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ ከተዋወቀ በርካታ አመታት ቢያስቆጥርም የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት አልቻለም።

''የዘርፉ ዋና ተልዕኮ የወጪ ንግድን በመደገፍ ከውጭ የሚገቡ ጥሬ እቃዎችን በማስቀረት አገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ ታስቦ ቢሆንም ከውጭ ገበያ ጥገኝነት መላቀቅ አልተቻለም'' ብለዋል፡፡

የህትመት ኢንዱስትሪን፣ የቀለም ምርትን፣ የወረቀት ምርትንና የአሳታሚነት ዘርፎችን አጣምሮ የያዘ ኮርፖሬሽን በማቋቋም ዘርፉን የበለጠ ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኮርፖሬት አደረጃጀት መቋቋሙ ሁለንተናዊ አቅምን በመገንባት አገሪቱ ለህትመት ዘርፉ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ መቀነስ እንደሚችል ምክትል ዋና ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው በአገሪቱ የህትመት ቴክኖሎጂ በግልጽ ስትራቴጅካዊ አቅጣጫ ተደግፎ ባለመሰራቱ የተፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም።

በዚህ ሳቢያ አገሪቱ ለህትመት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በውጭ ምንዛሬ ከሌሎች አገሮች ለመግዛት እንደተገደደች ተናግረዋል።

ችግሩን ለመፍታት ከአገር ውጭ የሚታተሙ ህትመቶችና ሚስጢራዊ ህትመቶችን በአገር ውስጥ ማተም እንዲቻል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

''የአገር ውስጥ የህትመት ዓቅምን ለማሳደግ ለረጅም ዓመታት በህትመት ዘርፍ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውን የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የካፒታል አቅም ከ8 ሚሊዮን ወደ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ማሳደግ ተችሏል'' ብለዋል።

በተጨማሪም ከውጭ የሚገቡ የወረቀት ምርቶችን በአገር ውስጥ ማምረት እንዲቻል መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ዘርፉ የበለጠ እንዲጠናከር የጋራ የኮርፖሬት አደረጃጀት ተቋቁሞ መሰራት እንዳለበት ከባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

የህትመት ዘርፍ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ እድሜ እንዳስቆጠረ መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 26/2010 እስራኤል በዘመናዊ ግብርና ዘርፍ ያላትን የካበተ ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል የጀመረችውን ሥራ አጠናክራ እንደምትቀጥል የአገሪቷ የእርሻና የገጠር ልማት ሚኒስትር ዩሪ አሪል ገለጹ።

የእስራኤል የእርሻና የገጠር ልማት ሚኒስትር ዩሪ አሪል በኢትዮጵያ የሦስት ቀናት ጉብኝታቸውን ትላንት የጀመሩ ሲሆን በዛሬው ውሏቸው ከተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመወያየት ላይ ናቸው።  

ሚኒስትሩ ትላንት ማምሻውን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ "እስራኤል ባለፉት ስልሳና ሰባ ዓመታት በመስኩ ያስመዘገበችው ውጤት ለኢትዮጵያም የግብርናው መስክ ቀጣይ እድገት እንደ አንድ ግብዓትነት ያገለግላል" በማለት ገልጸዋል።

እስካሁንም በእስራኤል ጥሩ ምርት መሰብሰብ የተቻለባቸው የአትክልትና የፍራፍሬ ዝርያዎች ለኢትዮጵያ በማስተዋወቅ በዘርፉ ያላትን ልምድ እያካፈለች ነው ያሉት።  

ከእስራኤል በመምጣት የተዋወቀው የአቮካዶ ዝርያ ከኢትዮጵያ አየር ሁኔታ ጋር ተገናዝቦ፤ በከፍተኛ ጥራት ተመርቶ ለውጭ ገበያ በመቅረቡ አገሪቷ ተጠቃሚ መሆኗን ለአብነት ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል "በአሳ እርባታና በተለይም በኮምፒዩተር በታገዘ የመስኖ ሥራ ላይ ያሉ ልምዶችን እያካፈልን ነው" ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህ ስራ በቀጣይም ተጠናክሮ አንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ውኃን በአግባቡ አንዴት መጠቀም እንደሚቻልና ጨዋማ ውኃን አንዴት ማጣራት እንደሚቻልም ያላቸውን ልምድና ክህሎት ለማጋራት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘርፉ እስራኤል በርካታ የምርምር ባለሙያዎች ባለቤት መሆኗን ጠቁመው በዚህም ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ለማድረግ የሥልጠና መርኃ ግብር በማዘጋጀት በጋራ እንሰራለን ብለዋል። 

ይህም በዘርፉ ያለውን የምርምር ውጤት ኢትዮጵያ እንድትቀምር በማድረግ የእውቀት ሽግግር ለማረጋገጥ ሁነኛ ዘዴ መሆኑን አስረድተዋል።

ጎን ለጎንም በሁለቱ አገራት መካከል የትብብር አድማሱን ለማስፋት የተደረሱ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ገቢራዊ ለማድረግ ሥራዎችን እንሰራለን ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በእስራኤል ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከእስራኤሉ አቻቸው ቤንጃሚን ኔትንያሁ ጋር በዘርፉ በትብብር ለመሥራት የደረሱበት ሥምምነት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም አንስተዋል ሚኒስትሩ።

ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት እስራኤል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2014 የግብርናው ዘርፍ ለአጠቃላይ አገራዊ ምርት ያለው ድርሻ 3 ነጥብ 3 በመቶ ነበር።

ምንም እንኳን ዘርፉ ለበርካታ እስራኤላዊያን መተዳደሪያ ባይሆንም አገሪቱ እስከ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስውን የውጭ ንግድ ገቢ እንደምታገኝበት ግን መረጃዎች ያሳያሉ።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 26/2010 ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር በማህበራዊ ዘርፎች ያላትን ጠንካራ ግንኙነት በኢኮኖሚና ንግድ ዘርፎችም ለማድረግ እንደምትሰራ በኢትዮጵያ የአገሪቷ አምባሳደር ሚስ ቪልማር ቶማስ ገለጹ።

አምባሳደር ሚስ ቪልማር እንደተናገሩት፤ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በማህበራዊ ዘርፎች ጠንካራ ግንኙነት ቢኖራትም በኢኮኖሚና በንግዱ ዘርፍ ያን ያህል የጠነከረ ትብብር የላትም። በዘርፉ ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ የሚያስችሉ እድሎች ላይ ትኩረት አድርጋ ትሰራለች።

ለዚህም የኩባ መንግስት አገራቱ በኢኮኖሚና በንግድ ያላቸው ግንኙነት እንዲያድግ ጠንካራ ቁርጠኝነት እንዳለው ተናግረዋል።

ሁለቱ አገሮች በኢኮኖሚና በንግድ ያላቸው ግንኙነት ማሳደግ ከቻሉ በአጠቃላይ ያለውን "የሁለትዮሽ ትብብር ይበልጥ ያሻሽለዋል" ብለዋል ሚስ ቪልማር።

ሁለቱ አገሮች በጤናና በትምህርት ጥሩ የሚባል ግንኙነት እንዳላቸው ጠቁመው፤ በዘርፉ የኩባ ህክምና ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በተለያዩ ሆስፒታሎች ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉና የኩባ አስተማሪዎችም ወደ አገሪቷ በመምጣት ስልጠና እየሰጡ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በቀጣይም ኩባውያን የህክምናና የትምህርት ባለሙያዎች "ለኢትዮጵያ የሚያደርጉት ሙያዊ ድጋፍ ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

ኢትዮጵያና ኩባ ታሪካዊና በደም የተሳሰረ ግንኙነት እንዳላቸው አመልክተው፤ ከ40 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ  የሶማሊያ ጦር ለመደምሰስ በተደረገው ጦርነት የከፈሉት መስዋዕትነት ዋነኛ ማሳያ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ወረራውን ለመመከት ከተሳተፉት የኩባ ወታደሮች መካከል 163 መሞታቸውን አስታውሰው፣ በጦርነቱ የሞቱትን ለማስታወስ መጋቢት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚገኘው የኩባ ኤምባሲ የመታሰቢያ በዓል እንደሚከበርም ጠቁመዋል።

አምባሳደር ሚስ ቪልማር የአገሮቹ የወደፊት ግንኙነት የበለጠ እንደሚጠናከር ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ሆነው ከተሾሙ አንድ ዓመት ከሶስት ወር ያስቆጠሩት ሚስ ቪልማር በቀሪ የአምባሳደርነት ቆይታቸው የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ለማሳደግ የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ኩባ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.ኤ.አ. በ1977 እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የኩባ አቻቸው ራኦል ካስትሮ ባቀረቡላቸው ግብዣ መሰረት ባለፈው ጥር በአገሪቷ ይፋዊ የሆነ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

Published in ፖለቲካ

ባህር ዳር/ደብረ ማርቆስ/ሽሬ የካቲት 26/2010 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የዕለት ተዕለት ሥራቸውን በተረጋጋ መንገድ ለማከናወን እንዳስቻላቸው የደጀንና የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በምስራቅ ጎጃም ዞን የደጀን ወረዳ የኮንቸር ሳሳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ያለው ወርቅነህ እንዳሉት በሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ እርሳቸውን ጨምሮ ማህበረሰቡ የተረጋጋ ኑሮ እንዲመራ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

አዋጁ ከመታወጁ በፊት በሌሎች አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት ምክንያት በደጀንና አካባቢው ስጋት ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል ።

"አዋጁ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ ስጋቱ ተወግዶ የአካባቢው ሰላማዊ እንቅስቃሴ በአንፃራዊነት እየተሻሻለ መጥቷል" ብለዋል።

በወረዳው የቀበሌ 01 ነዋሪ አቶ ይበልጣል አለሙ በበኩላቸው ከአዋጁ በፊት በተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ሁከትና ግርግር ወደአዲስ አበባ የሚያስኬድ መንገድ በመዘጋቱ ከባህር ዳርና ከጎንደር የሚመጡ ተሽከርካሪዎች ለቀናት ደጀን መቆማቸውን አስታውሰዋል።

በሌላ አካባቢ የነበረው ሁከትና ግርግር ወደአካባቢው ይመጣ ይሆን በሚል ስጋት የእለት ተለት እንቅስቃሴያቸው እንዲገታ ማድረጉን ገልፀዋል።

" አዋጁ ከታወጀ በኋላ ስጋታችን እየቀነሰ በመምጣቱ ሥራዬን እየሰራሁ እገኛለሁ" ብለዋል ።

አዋጁ ጊዜያዊ መፍትሄ የሚሰጥ መሆኑን አቶ ይበልጣል ገልጸው፣ መንግስት ጎን ለጎን ለሕዝቡ ዘርፈ ብዙ ጥያቄ ምላሽ በመስጠት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መስራት እንዳለበት አመላክተዋል።

በተመሳሳይ በባህር ዳር ከተማ በጫማ ማስዋብ ሥራ የሚተዳደረው ወጣት አሰፋ መለሰ በበኩሉ ለኢዜአ እንደገለጸው የአዋጁ መጽደቅ በፈጠረው አንፃራዊ ሰላም  ከስጋት ነፃ ሆኖ ስራውን እንዲሰራ አስችሎታል።

ሰላም ከሌለ ወጥቶ መግባት እንደማይቻል ጠቁሞ፣ ወጣቱ ከጥፋት መንገድ በመቆጠብ ለሰላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባ መክሯል።

በመጠጥ ማከፋፈል ንግድ ሥራ የተሰማራው ወጣት ገረመው አሰፋ በበኩሉ እንደተናገረው የፀደቀው አዋጅ ለህዝቡ ደህንነትና የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ ነው።

የአማራ ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ወጣት አባይነህ መላኩ በበኩሉ አዋጁ ሀገሪቱ እንድትረጋጋና ሰላሟ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

" የአዋጁ ተግባራዊ መሆን መንግስት ወጣቱና ህዝቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደርና የሥራ አጥነት ችግሮች ትኩረት ሰጥቶ ለመፍታት መልካም አጋጣሚ ይፈጥርለታል " ብሏል ።

ማህበሩ ወጣቱ የሚያነሳውን የገንዘብ ብድር፣ የቦታ አቅርቦትና የገበያ ትስስር ችግሮች ለመንግስት በማቅረብ እንዲፈቱለት የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ  አመላክቷል።

በሌላ በኩል አስተያየታቸውን ለአዜአ የሰጡ የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ነጋዴዎች አዋጅ መታወጁ መሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት ላይ እጥረት እንዳይከሰት አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ከነጋዴዎቹ መካከል ወይዘሮ አብርኽት ተክሉ እንዳሉት፣ ከዚህ ቀደም ተከስቶ በነበረው ሁከት የትራንስፖርት አገልግሎት በመቋረጡ በከተማው የሸቀጣ ሸቀጥ አቅርቦት ላይ እጥረት እንዲከሰት ምክንያት ሆኖ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህም የእለት ስራቸው ተስተጓጉሎ መቆየቱን ነው የገለጹት።

" የዕለት ተዕለት ኑራችን በንግድ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የሰላም መኖር የሕልውናችን መሰረት ነው " ያሉት ወይዘሮ አብርኽት፣ የአዋጁ መጽደቅ ለሰላም አስፈላጊ በመሆኑ እንደግፈዋለን ብለዋል።

አቶ ታረቀ ኃይለ የተባሉ ነጋዴ በበኩላቸው የአዋጁ መጽደቅ የንግድ ሥራቸውን በአግባቡ ለማካሄድ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።

Published in ፖለቲካ
Published in ቪዲዮ

ሶዶ የካቲት 26/2010 ትናንት በወላይታ ሶዶ ሁለገብ ስታዲየም የተካሄደው የ5ኛ ሳምንት የኢትዮጽያ የወንዶች ቮሊ ቦል ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ወላይታ ድቻና ጣና ባህር ዳር ተገናኝተው የወላይታ ድቻ ቮሊ ቦል ቡድን ሦስት ዜር አሸነፈ።

የወላይታ ድቻ በሦስቱም የጨዋታው ክፍሌ ጊዜያት 25 ለ 22 ፣ 25 ለ23 እንዲሁም የሦስተኛውንም ዙር  25 ለ23 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ነው ሦስት ለዜሮ ተጋጣሚውን ሊረታ የቻለው።

በሦስቱም የጨዋታ ክፍሌ ጊዜ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ ፉክክር በማሳየት ተመልካችን አዝናንተዋል።

“የጣና ባህር ዳር ቮሊ ቦል ቡድን ዋና አሰልጣኝ ምንይችል የኔዓለም ተጋጣሚያችን ጥሩ ስብስብ ያለውና ጠንካራ ቡድን ከመሆኑም ባለፈ በቴክኒክና በልምድ ስለሚበልጠን ልንሸነፍ ችለናል” ብለዋል

“የዘንድሮ አቋማችን መልካም ቢሆንም አዲስ ወደቡድኑ የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ያለመላመድና ያላቸውን አቅም አውጥተው አለመጠቀማቸው የሚያስቆጭ ነው” ያሉት አሰልጣኙ ከጨዋታው ለቀጣይ ትምህርት የሚሆኑ ነገሮችን መቅስማቸውንና ወደ አሸናፊነት እንደሚመለሱ ተናግረዋል።

የአከባቢው ማህበረሰብ የድጋፍ አሰጣጥና ለኳስ ያለው ፍቅር እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል።

“የወላይታ ድቻ ቮሊ ቦል ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሻምበል ጳውሎስ ሹከ በ2009 ዓመት የነበርንበትን ደረጃ ገምግመን ድክመታችንን ለመሸፈን ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ ከክለቡ አመራርና ደጋፊዎች ጋር በትጋት የሰራነው ሥራ ውጤት ነው “ ብለዋል፡፡

"የእያንዳንዱን ተጋጣሚ ቡድን ድክመትና ጥንካሬ በመገምገም ነው ወደጨዋታ የምንገባው" ያሉት አሰልጣኝ ሻምበል ጳውሎስ፣ ተጨዋቾቹ  ምን ማድረግ እንዳለባቸው የተነገራቸውን መተግበራቸው ለማሸነፋቸው አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

"በዛሬው ጨዋታ ብናሸንፍም የሚያኮራ አይደለም፤ በዓመቱ አሸንፈን ዋንጫ ለማንሳት ካለን ዕቅድና አቅም አንጻር ሊሰሩ የሚገቡ የቤት ሥራዎች እንዳሉ ተምረንበታል" ብለዋል። 

በርካታ ደጋፊዎች ስታዲየሙ ተገኝተው ስፖርታዊ ጨዋነት በተላበሰ ሁኔታ ቡድኖቻቸውን አበረታተዋል፡፡

Published in ስፖርት

የካቲት 25/2010 ኢትዮጵያ በበርሚንግሃሙ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሁለት ተጨማሪ  ወርቅ ሜዳሊያዎችን አገኘች፡፡

ዛሬ ምሽት 12፡35 በተካሔደው የወንዶች 3000 ሜትር ፍጻሜ ዮሚፍ ቀጀልቻና ሰለሞን ባረጋ ተከታትለው በመግባት የወርቅና ብር ሜዳሊያ ባለቤት ሆነዋል፡፡ 

በወንዶች 1500 ሜትር ደግሞ ሳሙኤል ተፈራ ውድድሩን በበላይነት አጠናቆ የኢትዮጵያን የወርቅ ሜዳልያ ብዛት ወደ አራት ከፍ አድርጎታል፡፡

በርቀቱ የተሳተፈው አማን ወቴ ውድድሩን አራተኛ ሆኖ ሲጨርስ በ3000 ሜትር የተሳተፈው ሀጎስ ገብረህይወት ደግሞ በኬንያዊው ቤትዌል ብሪገን ተቀድሞ ውድድሩን አራተኛ ሆኖ ጨርሷል፡፡

በ800 ሜትር ሴቶች የተወዳደረችው ሃብታም ዓለሙም ውድድሯን በአራተኝነት አጠናቃለች፡፡

 አሜሪካ በ6 ወርቅ፣ 10 ብርነና 2 ነሐስ ውድድሩን በበላይነት ስታጠናቅቅ ኢትዮጵያ ደግሞ በ4 ውርቅና 1 ብር ሜዳሊያዎች ሁለተኛ ሆናለች፡፡

የኢትዮጵያ የምንጊዜም ተቀናቃኟ ጎረቤት ኬንያ በውድድሩ 1 የነሐስ ሜዳሊያ ብቻ አግኝታ ውድድሩን 24ኛ ሆና አጠናቃለች፡፡

Published in ስፖርት

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን