አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Sunday, 04 March 2018

ሰመራ የካቲት 25/2010 በአፋር ክልል እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የነዋሪዎችን ግንዛቤ ለማሳደግ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ የኃይማኖት አባቶችና መምህራን ገለጹ።

የክልሉ ንግድ፤ ኢንዱስትሪና ትራንስፖርት ቢሮ ከተለያዩ ወረዳዎች የተወጣጡ የኃይማኖት አባቶችና ትምህርት ቤቶች መምህራን ጋር የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በጋራ መስራት በሚችሉበት ዙሪያ ላይ ያዘጋጀው የአንድ ቀን የውይይት መድረክ በሎግያ ከተማ ትናንት አካሄዷል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ከአሚበራ ወረዳ የመጡት ሼክ ሃቢብ ሙስጠፋ እንደተናገሩት የሰው ህይወትን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ሁኔታዎችን መከላከል የመንግስት ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የኃይማኖት አባቶችም መንፈሳዊ ተልዕኮ ነው።

በአካባቢያቸው ለትራፊክ አደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉትን እንደ ትርፍ ሰው መጫንና ተያያዥ ችግሮችን ለመቀነስ ተሳፋሪዎችና አሽከርካሪዎች ህግ አክብረው እንዲንቀሳቀሱ በመምከር  የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ከአይሳኢታ ወረዳ የመጡት ቀሲስ ተስፋየ ወርቁ በበኩላቸው "በአካባቢያቸው ጫት እየቃሙ በማሽከርከር የሰዎችን ህይወት ለአደጋ የሚያጋልጡ አሽከርካሪዎችን ማስተማርና መምከር ከዕምነት አባቶች የሚጠበቅ ተግባር ነው" ብለዋል።

ለዚህም የበኩላቸውን ለመወጣት ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

የሎግያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ሃቢብ ኡትባን ተማሪዎቻቸው ለትራፊክ አደጋ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ትምህርት ቤቶቹ የመንገድ አጠቃቀም ስርዓትን ለማስተማር  የጀመሩትን ስራ እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል፡፡

የተማሪ ትራፊኮችን በመመደብ ችግሩን ለመፍታት  የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ የገለጹት ደግሞ ከአሚበራ ወረዳ ወረር ሁለተኛ ደረጃ ትምርት ቤት የመጡት መምህር ጥበቡ አበራ ናቸው፡፡

የክልሉ ንግድ፤ ኢንደስትሪና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ድሂሉ በክልሉ የትራፊክ አደጋ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ እያደረሰ የሚገኘው ጉዳት አሳሳቢ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

"ለዚህም ከአቅም በላይ መጫናን ከተገቢው ፍጥነት በላይ ማሽከርከር ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው" ብለዋል።

ቢሮው የትምህርት ተቋማትና የኃይማኖት አባቶች  በህብረተሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተሰሚነትና ቅርበት ተጠቅመው የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል በጋራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በውይይቱ ከተለያዩ የክልሉ ወረዳዎች የተወጣጡ ከ120 በላይ የትምህርት ቤት መምህራ፣ አመራሮችና የኃይማኖት አባቶች ተሳትፈዋል።

Published in ማህበራዊ

ድሬደዋ የካቲት 25/2010 የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ በመድኃኒትና በህክምና መሣሪያዎች አቅርቦት ረገድ እያከናወናቸው የሚገኙትን አበረታች ሥራዎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ማጠናከር እንዳለበት ተመለከተ፡፡

ኤጀንሲው በድሬዳዋ  ለሶስት  ቀናት ያካሄደው የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ሲያጠናቀቅ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አሚር አማን እንዳሉት ኤጀንሲው በሀገሪቱ ለሚገኙ ጤና ተቋማት መድኃቶችና የህክምና መሣሪያዎችን በተሻለ መንገድ በማቅረብ አበረታች ሥራ እከናውኗል፡፡

በበጀት አመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት መድኃኒቶችና የህክምና መገልገያዎችን ገዝቶ ለማሰራጨት ካቀደው  ውስጥ  64 በመቶውን በመፈፀም ኤጀንሲው ካለፉት ዓመታት የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡን አመልክተዋል፡፡

የክትባት መድኃኒቶችን ስርጭት 74 በመቶ በሚሆኑ የሀገሪቱ ወረዳዎች ማዳረስ መቻሉና 99 የጤና ተቋማትን ተደራሽ ማድረጉን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል፡፡

ኤጀንሲው በስድስት ወራቱ የህክምና መሳሪያዎችና መገልገያዎችን በ42 የጤና ተቋማት በመትከል ህብረተሰቡ የተሟላ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ማመቻቸቱን ተናግረዋል፡፡   

ኤጀንሲው በቀጣይ መድኃኒትን ከክምችትና ከብክነት በማዳን በፍጥነትና በተቀናጀ መንገድ ወደ ጤና ተቋማት የማቅረብ ፣ በቅርንጫፎቹ የሚስተዋሉ የአፈጻጸም ልዩነቶችን የማጥበብ፣  ሙስናና ብልሹ አሠራርን  በማስተካከል ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ለዚህም  አጀንሲው የጀመረው የለውጥ እንቅስቀሴ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

የኤጀንሲው ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር ሎኮ አብርሃም ኤጀንሲው የጀመራቸውን የለውጥ መሣሪያዎች በተቀናጀ መንገድ በመተግበር ዕቅዱን ለማሳካት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የተተገበሩት አሠራርና አደረጃጀቶች ይከሰቱ የነበሩ የግዥ መጓተቶችን በማስቀረት የመድኃኒት አቅርቦት ሳይቆራረጥ ለተጠቃሚው እንዲደርስ ማስቻሉን ጠቁመዋል፡፡

"በተለይ በመጋዘን የሚከማቹ መድኃኒቶችን በፍጥነት ወደ ተጠቃሚው ለማድረስና ክፍተቶችን በማሻሻል የሚባክን መድኃኒትን አሁን ካለበት 1 ነጥብ 1 በመቶ ለመቀነስ ይሰራል "ብለዋል፡፡

ለዚህም የመድኃኒት ማከማቻ መጋዘኖችን ጥራት የማሻሻል እና የባለሙያዎችን አቅም የማሳደግ ሥራ እንደሚከናወንም ዶክተር ሎኮ ጠቁመዋል፡፡

የኤጀንሲው የስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የተመዘገቡ ውጤቶችን በመጠበቅና የተስተዋሉ ክፍተቶችን በማረም ከአጋር አካላት ጋር ተቀናጅተው የተሻለ ሥራ ለማከናወን እንደሚሰሩ በግምገማው መድረክ ገልጸዋል፡፡

የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ  በጀት ዓመቱ  14 ቢሊዮን በሚጠጋ ብር መድኃኒቶች፣ የህክምና መሳሪያዎችና መገልገያዎችን ገዝቶ በሀገሪቱ ለማሰራጨት አቅዶ በስድስት ወራት ውስጥ  ከ6 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ግዥ በፈጽሞ ማሰራጨቱም አጀንሲው አስታውቃል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 25/2010 የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ችግር የሚፈቱ ቴክኖሎጂዎች ማቅረባቸውን የ8ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ተሳታፊ ተቋማት ገለጹ።

የአዋሬ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አሰልጣኝ አቶ ክንፈ አደሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አዳዲስ ቴክኖጂዎችን መቶ በመቶ በመቅዳት ያመረቷቸውን ማሽነሪዎች  በማሳያነት  አቅርበዋል።

በዚህም ቴክኖሎጂዎቹ በተሻለ ጥራትና በዝቅተኛ ዋጋ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ተደራሽ እንዲሆኑ እያደረግን ነው ብለዋል።

የአራዳ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የፈርኒቸር አሰልጣኝ ለጥቃታቸው አዘነ በኮሌጁ ውስጥ የሚሰሯቸው የተቀዱ ቴክኖሎጂዎች ለተጠቃሚዎች ማራኪ በሆነ ዲዛይን የሚቀርቡ መሆናቸውን ይናገራሉ።

በተጨማሪም ኢንተርፕራይዞች የተጠቃሚዎችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ የተለያዩ ዲዛይን ጨምረው በማምረት ኅብረተሰቡ በሚፈልገው መንገድ እንዲያገኝ ያግዛሉ ብለዋል።

የአዋሬ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ የስራ ፈጠራ እና ንግድ ስራ አመራር አስተባባሪ ወይዘሮ ማለዳ ጌቱ በበኩላቸው የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎች  የኢንተርፕራይዞችን ችግር መነሻ ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም የምናቀርባቸውን የቴክኖሎጂ ቅጂዎች ችግራቸውን መሰረት አድርገን ለምንሰራላቸው ኢንተርፕራይዞች ስለምናስረክብ የተጠቃሚ ችግር አይገጥመንም፤ ኢንተርፕራይዞቹም ችግሯቸውን በቀላሉ በመፍታት እንረዳቸዋለን ብለዋል።

በኤግዚቢሽኑ ላይም ከ14 በላይ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ቅጂዎችን በማሳያነት ለተጠቃሚ ኢንተርፕራይዞች ማቅረባቸውንም ገልጸዋል።

አሰልጣኞቹ ከዚህ በላይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማቅረብ ቢቻልም የመብራትና የኢንተርኔት መቆራረጥ እንዲሁም የገንዘብ እጥረት ተግዳሮቶች እንደሆኑባቸው ገልጸው፤ በቀጣይ የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲያበጅላቸው ጠይቀዋል።

8ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ''ቴክኒክና ሙያ ለህዳሴያችን'' በሚል መሪ ሀሳብ ከየካቲት 26 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በኤግዚቢሽን ማዕከል ይከበራል።

Published in ኢኮኖሚ

ዲላ የካቲት 25/2010 በጌዴኦ ዞን  ቡሌ እና ይርጋጨፌ ወረዳዎች18  ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የተገነባው 22 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ትናንት ተመረቀ፡፡ 

በሁለቱ ወረዳዎች መንገዱን የገነባው የደቡብ  ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንገዶች ባለሥልጣን ዲላ ዲስትሪክት ነው፡፡

የዲስትሪክቱ  ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባሊ ሞኬ በምረቃው ወቅት እንደገለጹት መስሪያ ቤታቸው በከፊል ሲዳማ እና በከፊል ሰገን ህዝቦች ዞን እንዲሁም ሙሉ በሙሉ በጌዴኦ ዞን  የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

በአካባቢዎቹ በተያዘው የበጀት ዓመት ታቅደው እየተከናወኑ ካሉት ውስጥ ለምረቃ የበቃውና 22 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው  የጋርቦተ - ኢዲዶ - ራጴ መንገድ አንዱ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

በጌዴኦ ዞን  ቡሌ እና ይርጋጨፌ ወረዳዎች የተገነባው ይሄው መንገድ 17 ሚሊዮን 850 ሺህ ብር ወጪ እንደተደረገበትም ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ  መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታከለ ጌታቸው በበኩላቸው በተያዘው የበጀት ዓመት ባለስልጣኑ ለሚያከናውናቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች መንግስት አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር መመደቡን አስታውቀዋል።

በበጀት ዓመቱ ሁለት ሺህ 170 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታና ሶስት ሺህ 500 ኪሎ ሜትር ጥገና ለማከናወን ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡

እስካሁን ያለው አፈፃፀም 65 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡

በቡሌ ወረዳ አርሶ አደር በቀለ ኢጆ በመንገድ ምረቃው ወቅት እንደገለፁት እንዳሁኑ የመንገድ መሰረተ ልማት ባልተስፋፋበት ወቅት ምርታቸውን ወደ ከተማ ለማድረስና  ለገበያ ለማቅረብ በፈረስ ጭነው ከአምስት ሰዓታት በላይ ይጓዙ ነበር ፡፡

አርሶ አደር በቀለ ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው መንገድ እስከበራፋቸው መኪና ማስገባት ስለሚያስችል ምርታቸውን በቀላሉ ለገበያ ለማቅረብ እየረዳቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መንገድ ባለመኖሩ ወላዶችንና በጠና የታመሙ ሰዎችን በቃሬዛ ተሸክመው ወደ ጤና ተቋማት ይወስዱ እንደነበር  በማስታወስ የገለጹት ደግሞ  የይርጋጨፌ ወረዳ አርሶ አደር ታደለ ብላቴ ናቸው፡፡

"መንግስት ይህንን  ችግራችንን ተመልክቶ ምቹ መንገድ ስለሰራልን ተደስቻለሁ "ብለዋል ፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ጭሮ የካቲት 25/2010 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በጊዜያዊ  መፍትሄነት አስፈላጊ ቢሆንም  የህዝቡን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት አተኩሮ መስራት እንዳለበት በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሂርና ከተማ አስተያየት ሰጪዎች አመለከቱ፡፡

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የከተማዋ ነዋሪ አቶ  መላኩ ነጋሽ ለኢዜአ እንደገለጹት አዋጁ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታዩ ያሉትን አላስፈላጊ ሁከቶችንና ስጋቶችን በማስቀረት የህዝብ ሰላም ለማስጠበቅ  ፋይዳው የጎላ ነው።

ሆኖም "አዋጅ ማወጅ ብቻ የህዝቡን ጥያቄ ስለማይፈታ መንግስት በየደረጃው ያሉትን አመራሮች በማብቃት የህዝቡን ጥያቄ በዘላቂነት መመለስ አለበትም "ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ በተለይ ወጣቱ መብቱን እና ግዴታውን በማወቅ ካልተፈለገ ሁከትና ግርግር በመቆጠብ ከመንግስት ጎን በመቆም ለችግሩ የመፍትሄው አካል መሆን እንዳለበት ያመለከቱት ደግሞ ወይዘሮ ሳሊያ ጀማል የተባሉት የከተማዋ  ነዋሪ ናቸው፡፡

ወጣቱ በስሜታዊነት ተነሳስቶ ችግር ውስጥ ሳይገባ ጥያቄውን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እያቀረበ መጓዝ የሚበጅ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

"አዋጅ ህዝብን በዘላቂነት ማረጋጋት አይችልም ፤ ከዚህ ይልቅ መንግስት የህዝቡን ጥያቄ በማዳመጥ ለህዝቡም ሆነ ለወጣቱ መልስ መስጠት አለበትም" ብለዋል

የነገ ሀገር ተረካቢ የሆነው የወጣቱም ሆነ ጠቅላላ የህብረተሰቡ ጥያቄ የሆነው በመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር በዘላቂነት ለመመለስ መንግስት በትኩረት መስራት እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

ወጣት ይታያል ከተማ በበኩሉ መንግስት ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በጊዜያዊ መፍሄነት አስፈላጊ ቢሆንም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት   ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ጠንክሮ መስራት እንዳለበት አመልክቷል፡፡

"በሃገሪቱ የታወጀው አዋጅም ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከአደጋ ለመጠበቅና ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት መሆኑን ወጣቱ መረዳት አለበት "ያሉት ደግሞ ሌላ የሂርና ከተማ ነዋሪው አቶ ይመር አበበ ናቸው።

በየደረጃ ያሉት የመንግስት አካላትም በአዋጁ ላይ ለወጣቱም ሆነ ለሌላው  ህብረተሰብ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

በሂርና የግል ትምህርት ቤት አስተማሪ የሆኑት መምህር አበበ ቸኮል እንዳሉት አዋጁ ወቅታዊና ሀገራዊ ሁኔታን ግምት ውስጥ ያስገባ ቢሆንም ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም፡፡

መንግስት የሕዝቡን ጥያቄዎችና መሰረታዊ ፍላጎቶች በተገቢው ሁኔታ አጢኖ ተገቢ ምላሽ በመስጠት ለዘላቂ ሰላምና መፍትሄ ማተኮር እንዳለበትም አመልክተዋል።

መንግስት ማንኛውንም የህዝብ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ጀምሮ ለሀገር አንድነትና ደህንነት ስጋት በሆኑ ጉዳዮች   ዘለቄታዊ የሆነ መፍትሔ መስጠት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባው አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

ነገሌ የካቲት 24/2010 በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን እራሳቸውን ለማወቅ በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረት  የደም ምርመራ የሚያደርጉ ሰዎች  ቁጥር መጨመሩን የዞኑ የጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት  ገለጸ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ክፍል ባለሙያ አቶ ጎዳና ጀልዴሳ እንዳሉት  ባለፉት ስድስት ወራት ከ73 ሺህ በላይ ሰዎች  የኤች አይ ቪ ኤድስ የደም ምርመራ አድርገዋል፡፡

ይህም  ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ1 ሺህ 800 ሰዎች ብልጫ ያለው ነው፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት በፍቃደኝነት የደም ምርመራ ካደረጉ ሰዎች መካከል 452 ቫይረሱ በደማቸው  ተገኝቶባቸዋል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ 389  የጸረ ኤች አይ ቪ ኤድስ መድኃኒት መጠቀም መጀመራቸውን ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡

ባለሙያዋ እንዳመለከቱት በሽታውን ለመከላከል በዞኑ  በተያዘው የበጀት ዓመት 148 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች በፈቃዳቸው  ነጻ የደም ምርመራ እንዲያደርጉ በ16 የጤና ተቋማት ትምህርታዊ ግንዛቤ እየተሰጠ ይገኛል፡፡

በጉጂ ዞን እስካሁን ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ 4 ሺህ 327 ሰዎች የጸረ ኤች አይ ቪ ኤድስ መድኃኒት ተጠቃሚ ናቸው ተብሏል፡፡

ወጣት ስንታየሁ በየነ የነገሌ ከተማ  ቀበሌ ዜሮ አንድ ነዋሪ ሲሆን በነገሌ ቦረና ሆስፒታል ነፃ የደም ምርመራ በማድረግ ራሱን ማወቁን ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት ገልጿል፡፡

" ከ10 ጊዜ በላይ ተመርምሬ ራሴን አውቄያለሁ" ያለው ወጣቱ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታትና ለመከላከል ሌሎች ወጣቶችም እንዲመረመሩ ለማድረግ  የድርሻቸውን እንደሚወጣም ጠቅሷል፡፡

የዚሁ ከተማ ዜሮ አንድ  ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሮማን ኩምሳ እንዳሉት  ምርመራውን በማድረግ ራሳቸውን ካወቁ በኋላ የጸረ ኤች አይቪ መድኃኒት መጠቀም ጀምረዋል፡፡

ራሳቸውን ካወቁ በኋላ በጤና ባለሙያዎች በተሰጣቸው ምክር መድኃኒት በመጠቀም ከቫይረሱ ጋር ቢኖሩም መስራትና መውለድ እንደሚችሉ ግንዛቤ ማግኘታቸውን አመልክተዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 25/2010 በ17ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲከስ ሻምፒዮና አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ሁለተኛ የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሯ አስገኝታለች።

በበርሚንግሃም እየተካሄደ የሚገኘው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር አራተኛ ቀኑን ይዟል።

ገንዘቤ ትላንት በተካሄደው በ 1 ሺህ 500 ሜትር የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር ሁለተኛ የወርቅ ሜዳሊያዋን አግኝታለች።

በዚህም ለሀገሯ ከፍተኛ የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግባለች።

እስካሁን ከተደረጉ 13 የፍጻሜ ውድድሮች መካከል ኢትዮጵያ በ3 ሺህ ሜትርና  በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች ውድድሮች ተካፍላለች።

ገንዘቤ የትናንት ምሽቱን  የ1 ሺህ 500 ሜትር ውድድር በቀዳሚነት ለማጠናቀቅ የፈጀባት 4 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ ከ27 ማይክሮ ሴኮንድ ነው።

ገንዘቤ ዲባባ በየ 2 ዓመቱ በሚካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር ያለፉትን አራት ተከታታይ ውድድሮች የተካፈለች ሲሆን  በአራቱም ዓመታት የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሯ አስገኝታለች።

ከስምንት ዓመት በፊት በቱርክ ኢስታንቡል በተደረገው ውድድር በ1 ሺህ 500 ሜትር የተጀመረው ድሏ ከዚያ በኋላ በተደረጉት ሶስት ውድድሮች ላይ በተካፈለችባቸው የ3 ሺህ ሜትር ውድደር ሶስቱንም የወርቅ ሜዳሊያዎችን ለሀገሯ አስገኝታለች።

በዚህ ዓመት እየተደረገ ባለው ውድድር በ3 ሺህ ሜትር ለሶስተኛ ጊዜ ከማሸነፏም በላይ በ1 ሺህ 500 ሜትርም በማሸንፍ በአንድ ውድድር ላይ ሁለት ወርቅ ማገኘት ችላለች።

አትሌት ገንዘቤ በውድድሩ ማሸነፏን ተከትሎ በቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድሩ 5ተኛ ድሏን በማስመዝገብ በኢትዮጵያ ታሪክ ብዛት ያለው የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሯ በማምጣት በኩል አዲስ ክበር ወሰን አስመዝግባለች።

ይህም እስካሁን ሀገራቸውን ወክለው በቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ከተካፈሉና በዓለም አደባባይ ከፍ አድርገው ካስጠሩት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ቀዳሚ አድርጓታል።

እስካሁን  በዚህ ሻምፒዮና ተካፍለው የሀገራቸውን ስም ካስጠሩ አትሌቶች መካከል አትሌት መሰረት ደፋር 4 ወርቅ  አንድ ብርና አንድ ነሀስ እንዲሁም አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎች ያመጡ አትሌቶች ናቸው።

አትሌት ገንዘቤ በዚህ ውድድር ላይ ከተሳተፉ አትሌቶች ጋር በቁጥር ደረጃ ሲቀመጥ በወርቅ ብዛት አንደኛ በሜዳሊያ ብዛት ደግሞ ከመሰረት ደፋር ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃነት ያስቀምጣታል።

17ኛው የበርሚንግሃም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬም ሲቀጥል ኦትዮጵያውያን ሌላ የወርቅ ሜዳሊያ ያመጡበታል ተብሎ የሚጠበቀው  የ3 ሺህ ሜትር ወንዶች ፍጻሜ ይደረጋል።

በዚህ ውድድር ላይ ሀገራቸውን ወክለው የሚወዳደሩት አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ ሰለሞን ባረጋና ሀጎስ ገብረ ህይወት ናቸው።

በተመሳሳይ ዛሬ በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች አትሌት አማን ወጤና ሳሜኤል ተፈራ እንዲሁም በ800 ሴቶች አትሌት ሀብታም አለሙ  ሀገራቸውን ወክለው በፍጻሜው ውድድር ይካፈላሉ።

Published in ስፖርት

አዳማ የካቲት 25/2010 በምስራቅ ሸዋ ዞን አድአ  ወረዳ ሁለት ህፃናት ከመኖሪያ  ቤታቸው ያገኙትን የእጅ ቦንብ በድንጋይ  ሲቀጠቅጡ ፈንድቶባቸው ህይወታቸው ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው  አለሙ ለኢዜአ እንደገለፁት አደጋው የደረሰው ትናንት ቀን አስር ሰዓት አካባቢ በአድአ ወረዳ ቀልቢ ስላሴ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ነው፡፡

ህጻናቱ  በዚሁ ቀበሌ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ያገኙትን ኤፍ ዋን የተባለ የእጅ ቦንብ  በድንጋይ እየቀጠቀጡ ፈንድቶባቸው ህይወታቸው ያለፈው ህጻናት አንደኛው  12 ዓመትና ታናሹ ደግሞ የስድስት ዓመት እድሜ የነበራቸው ናቸው።

"ቦንቡ በግለሰቡ መኖሪያ ቤት እንዴት ሊገኝ እንደቻለ ፖሊስ በማጣራት ላይ ይገኛል " ብለዋል ኮማንደር አስቻለው።

ማንኛው የጦር መሳሪያ ህፃናት በማይደርሰበት ቦታ መቀመጥ እንዳለበትና ህጋዊ ፍቃድ ያለው መሆን እንደሚገባው ጠቅሶ ህፃናቱ ያገኙትን ነገር አንሰቶ መቀጥቀጥ እንደሌለባቸው በቤተሰቦቻቸው ሊመከሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

Published in ማህበራዊ

ደሴ/አሶሳ የካቲት 25/2010 የዜጎችን ደህንነት እንዲጠበቅና የንብረት ጉዳት እንዳይደርስ  የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አማራጭ መፍትሄ  በመሆኑ እንደሚደግፉት በከሚሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ እና አሶሳ  ከተሞች አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ፡፡

በከሚሴ ከተማ የዜሮ አምስት ቀበሌ ነዋሪ አቶ የሱፍ አሊ ለኢዜአ እንዳሉት በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተፈጠረው ረብሻ በሰዎችና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡

የንግዱ ማኅበረሰብና የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ተንቀሰቅሰው መነገድና መማር ተቸግረው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

አዋጁ  መጽደቁ ሀገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ በማገናዘብ  በሰውና በንብረት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት የሚያስቀር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚሁ ከተማ የቀበሌ ዜሮ ሁለት ነዋሪው  አቶ ከሚስ ሰይድ በበኩላቸው  አዋጁ  ዘግይቶም ቢሆን መጽደቁ የሀገሪቱን ሰላምና አንድነት ያረጋግጣል ብለው እንደሚያምኑ  ገልጸዋል፡፡

" የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ ሀገሪቱ ወደ ቀደሞ ሰላሟ ይመልሳታል " ያሉት ደግሞ በኮምቦልቻ ከተማ የዜሮ አራት ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዝናቡ ሻረው ናቸው፡፡

በተለይ ወጣቱ ሀገሪቱን የማተራመስ ዓላማ ይዘው ለተነሱ የውጭ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆን ያስችላል ብለው እንደሚያምኑ አመልክተዋል፡፡

የደሴ ከተማ ነዋሪው አቶ ትዕዛዙ እንግዳው በሰጡት አስተያየት የተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከመደገፍ ባለፈ ከተቃውሞ እስከ ድምጽ ተአቅቦ አቋማቸውን ማንጸባረቃቸው የዴሞክራሲ ስርዓት በሀገሪቱ እያበበ መምጣቱን እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ከአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች መካከል በንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ ሃሰን አህመድ የፀጥታ ችግር በመኖሩ ሸቀጦችን ከአዲስ አበባ ለማስመጣት ተቸግረው እንደነበር ገልፀዋል፡፡

ሸቀጦችን አስጭነው በማስመጣት ላይ ሳሉ ለቀናት መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት ለተጨማሪ ወጪና ለእንግልት ሲዳረጉ መቆየታቸውን ጠቁመው "የአዋጁ መታወጅ በዋናነት የዜጎችን ህይወት ለመጠበቅ ይረዳል" ብለዋል፡፡

ተቀዛቅዞ የነበረውን የንግድ ስራቸውን በተሻለ ሁኔታ ለማከናወን አስተማማኝ ሰላም መኖር ስላለበት የአዋጁ መታወጅ መልካም  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ አብዱራሂም አልማሙር የተባሉት ነዋሪ በበኩላቸው "የፀጥታ ችግሩ ዜጎች ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ የደህንነት ስጋት ውስጥ እንዲገቡ ያደረገ በመሆኑ አዋጁ አስፈላጊ ነው" ብለዋል፡፡

አዋጁ ተግባራዊ ከሆነ በኋላም የተወሰኑ ለውጦች እንዳሉ መታዘባቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የፀጥታ ችግሩ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ላይ ተፅዕኖ ያሳደረ እንደነበር በማስታወስ የገለጹት ደግሞ  አቶ እንድሪስ አልማሃዲ የተባሉት የከተማዋ ነዋሪ ናቸው፡፡

አርሶ አደሮች ምርታቸውን ወደ ገበያ እንዳያወጡ፣ ወደ ሌሎች ክልሎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በመግታቱ ችግሩ እሳቸው ላይ ጭምር  ተጽእኖ ማሳደሩን ጠቁመዋል፡፡

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ  የዜጎችን ደህንነት እንደጠበቅና የንብረት ጉዳት እንዳይደርስ  አማራጭ መፍትሄ በመሆኑ እንደሚደግፉት አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት25/2010 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የህዝብን ህይወትና ንብረት ከጥፋት ከመታደጉም በላይ ለሚነሱት ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

መንግስት ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ያወጀውን አዋጅ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀ ሲሆን፤ አዋጁ መታወጁ  ተገቢ እርምጃው መሆኑን ነው አስተያየት ሰጪ ነዋሪዎች የገለጹት።

ከነዋሪዎቹ መካከልወይዘሮ እመቤት እንደሻውና  አቶ ግርማይ ታረቀኝ እንደገለጹት "የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ባይታወጅ ኖሮ አገሪቷ ወደባሰ የህይወትና የንብረት መጥፋት ቀውስ ውስጥ ልትገባ ትችል ነበር" ብለዋል ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈጥሮ የነበረውን አለመረጋጋት ወደ ነበረበት "ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ የሚያስችል ነው"ም ብለዋል።

ሃጂ ኦመር ሰይድ ሙሃመድ እና መላዕከ ብርሃን ግርማ ሞልቶት የተባሉት ነዋሪዎች በበኩላቸው አዋጁ ጊዚያዊ መረጋጋትን ከማምጣት ባለፈ መንግስትና ህዝብ በተፈጠረው ችግር ላይ በሰላም እንዲወያዩና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያመጡ "ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል" ሲሉም ተናግረዋል። 

በተለይም መንግስት ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ በመስጠት በኩል ጠንክሮ ሊሰራ እንደሚገባና ህዝቡም ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

መንግስት ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ የመከላከልና የመጠበቅ፣ የአገርን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር በሚል ያወጣውን አዋጅ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዋጁን አስፈላጊነት መርምሮ በ395 ድምጽ ድጋፍ፣ 88 ተቃውሞ እና በ7 ድምጸ ተአቅቦ ማጽደቁ ይታወሳል።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን