አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Saturday, 03 March 2018

አዲስ አበባ የካቲት 24/2010 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መፅደቁ በአገሪቷ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን እንደሚረዳ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ።

ኮማንድ ፖስቱም አዋጁን በጥንቃቄና ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ተግባራዊ እንዲያደርግም ፓርቲዎቹ አሳስበዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በትናንትናው ዕለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈላጊና ወቅታዊ መሆኑን ገልፀዋል።

የተፈጠረው አለመረጋጋትና የፀጥታ ችግር በመደበኛ ህግ መቆጣጠር ባለመቻሉ በዜጎች ደህንነትና በአገሪቷ ሀብት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለማስቆም አዋጁ አስፈላጊ መሆኑን ነው የገለጹት።

የፓርቲዎቹ አመራር አባላት እንደገለፁት፤ በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን የሰላም ዕጦትና የፀጥታ ችግር ለመፍታት ኮማንድ ፖስቱ ማህበረሰቡን ያሳተፈ ጥረት ማድረግ አለበት።

የመላው ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን) ፕሬዚዳንት ልጅ መስፍን ሽፈራው እንደተናገሩት፤ የአገርና የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ የጣለውን ሁከትና ዓመፅ ለማስቆም የታወጀው አዋጅ ህግና ስርዓት ጠብቆ ለሚንቀሳቀስ ዜጋ "ዋስትና እንጂ ስጋት ሊሆን አይችልም"።

የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ አየለ ጫሚሶ በበኩላቸው፤ ሁከትና ብጥብጡ ብሔር ተኮር እና በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ሀብት እያወደመ ነው። ስለዚህ "ይሄንን ለመፍታት ምክር ቤቱ አዋጁን ማፅደቁ ተገቢ ነው" ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ (ኢዴአን) ሊቀ መንበር አቶ ጉዕሽ ገብረስላሴ እንደተናገሩት፤ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር እየደረሰ ያለውን የሰው ህይወትና የሀብት ጉዳት መንግስት በመደበኛ ህግ መቆጣጠር ስላልቻለ የአዋጁ መፅደቅ የሚደገፍ ነው።

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን ታፈሰም "የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰላምና መረጋጋትን በመፍጠር መንግስት የህዝቦችን ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችል ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ መፅደቁ ተገቢ ነው" ይላሉ።

ፓርቲዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ኮማንድ ፖስቱ አዋጁን በጥናትና በጥበብ ተግባራዊ እንዲያደርግም አሳስበዋል።

የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ አየለ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈፃፀም ለመከታተል የተሰየመው ቦርድ "አዋጁ ተግባራዊ ሲደረግ በንፁሃን ዜጎች ላይ እንግልት እንዳይደርስ መስራት አለበት" ነው ያሉት።

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞንም፤ ኮማንድ ፖስቱ  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ኅብረተሰቡን በማሳተፍ በጥበብ እንዲፈፅም አሳስበዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማስፈፀም ኃላፊነት የተሰጠው የኮማንድ ፖስት ፀጥታ ከማስከበር በተጨማሪ የማስተማርና የማነፅ ሥራዎችንም እንዲያከናውን ፓርቲዎቹ አሳስበዋል።

መንግስት አዋጁ ፀንቶ በሚቆይበት ጊዜ ለህዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ የመስጠት ሥራዎች እንዲያከናውንም ፓርቲዎቹ አመልክተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትናንትናው ዕለት በ395 ድጋፍ፣ በ88 ተቃውሞ እና በ7 ድምፀ ተአቅቦ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማፅደቁ ይታወሳል።

Published in ፖለቲካ

ማይጨው የካቲት 24/2010 መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የድርሻቸውን እንደሚወጡ የትግራይ ደቡባዊ ዞን የመንግስት ሠራተኞች አስታወቁ ፡፡

በዞኑ የሚገኙ ከ3 ሺህ 700 በላይ የመንግስት ሠራተኞች የተሳፉበት ለአምስት ቀናት የተካሄደው ውይይት የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል።

ሠራተኞቹ የህወሓት 7ኛ ድርጅታዊ ኮንፈረንስን ተከትሎ የማዕከላዊ ኮሜቴ ባቀረበው የግምገማ ውጤትና የዞኑ ከፍተኛና መካከለኛ አመራር አካላት ባካሄዱት ሂስና ግለሂስ ሰነድ ላይ ተወያይተዋል።

የህዝብ ኃላፊነትን ለግል ጥቅም በማዋል፣ በግልጽነትና ተጠያቂነት ላይ በሚስተዋሉ ችግሮች፣ በመንግስትና በህዝብ ገንዘብና ንብረት ብክነት ፣ በጨረታ፣ በፋይናንስና በበጀት አጠቃቀምና አስተዳደር ጉድለት ላይም ሰራተኞቹ በስፋት መክረዋል፡፡

የዞኑ ህዝብ አደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ገብረትንሳኤ ፍስሃ እንደገለጹት በተለይ የሀሳብ ልዩነትን ያለማስተናገድ፣ እርስ በእርስ ያለመተማመን፣ በመንግስታዊ መዋቅር ላይ ህዝብን መበደል በሠራተኛው ላይ ጎልተው የታዩ ችግሮች ናቸው።

ሠራተኞቹ ሂስና ግለሂስ አካሂደው በውይይቱ መጨረሻ ባወጡት የአቋም መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት፣ በየደረጃው መልካም አስተዳደር ለማስፈን የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

በተለይ የግልጽነትና ተጠያቂነት መርህን በማስፈን የበደሉትን ህዝብ ለመካስ ዝግጁ መሆናቸውን ነው ያስታወቁት።

ከተሳታፊዎቹ መካከል የኮረም ከተማ ሠራተኛ አቶ ሞጎስ ንጉሴ በሰጡት አስተያየት፣ በድርጅቱ የውስጥ ዴሞክራሲ  እንቅስቃሴ እንዲዳከም ድርሻ እንደነበራቸውና በውይይቱ ያለምንም ጎትጓች ራሳቸውን በመገምገም ከድክታቸው መማራቸውን ገልጸዋል።

"ግምገማው ነጻና ግልጽ ስለነበር ከስህተቴ ተምሬ ሕብረተሰቡን በአግባቡና በተሻለ ለማገልገል እንድነሳሳ አድርጎኛል" ያሉት ደግሞ በዞኑ የአፈላ ወረዳ ሠራተኛ አቶ ደስታ ባራኪ ናቸው።

Published in ፖለቲካ

አርባምንጭ የካቲት 24/2010 አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በስነ-ሕንፃና በከተማ ፕላን ያሰለጠናቸውን 37 ተማሪዎች አስመረቀ ፡፡

ዛሬ በተካሄደው የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ እንዳሉት ተቋሙ ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ የዛሬዎቹን ጨምሮ ከ34 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል ፡፡

በአሁኑ ወቅትም ዩኒቨርሲቲው በ74 የቅድመ ምረቃና በ99 የድህረ ምረቃ የትምህርት መርሀ ግብሮች ከ35 ሺህ 700 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማሰልጠን ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዕለቱ ተመራቂዎችም በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀት ከነባራዊ የሥራ ዓለም ጋር በማዋሃድ ኃላፊነታቸውን በብቃትና በታማኝነት እንዲወጡ አስገንዝበዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሀብት ልማት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተርና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶክተር ገረመው ሳህለ በበኩላቸው የሀገሪቱን ፈጣን ዕድገት የሚያስቀጥሉ ምሁራንን ለማፍራት መንግስት ሰፊ ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

በአሁኑ ጊዜ የህዝብ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የከተሞች ዕድገት እየተስፋፋ በመምጣቱ በዘርፉ የመኖሪያ ቤትና መሠረተ- ልማት ዝርጋታ ሥራዎችን ለማሳለጥ የስነ-ሕንፃና የከተማ ፕላን ባለሙያዎች ወሳኝ መሆናቸውን አስገንዝበዋል ፡፡

በመሆኑም የዕለቱ ምሩቃን የማህበረሰቡን ኑሮ ለማሻሻል የሙያ ስነ-ምግባርን ከማክበር ባለፈ እርስ በርስና ከተጓዳኝ ሙያተኞች ጋር ተባብረው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ከዕለቱ ምሩቃን መካከል በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀው በእምነት ካሳዬ የራሱ ጥረት ብቻ ሳይሆን የቤተሰቡና የመምህራን እገዛ በማዕረግ ለመመረቅ እንዳበቃው ተናግሯል።

"በአሁኑ ወቅት ሥራን መጠበቅ ሳይሆን ፈጥሮ መስራት ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ሥራ ፈጣሪ ለመሆን ተዘጋጅቺያለሁ" ብሏል ፡፡

ሌላው የከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂ ምንተስኖት ካሳሁን በበኩሉ እንዳለው በዩኒቨርሲቲ የአምስት ዓመት ተኩል ቆይታው በንድፈ ሀሳብና በተግባር በቂ ዕውቀት አግኝቷል ፡፡

በቀጣይ እውቀቱን በተግባር በመቀየር ለማህበረሰቡ ለውጥ በቅንነትና በታማኝነት እንደሚሰራም ገልጿል።

Published in ማህበራዊ

ነቀምቴ የካቲት 23/2010 በምስራቅ ወለጋ ዞን በመጀመሪያው ዙር በመስኖ ከለማው ማሳ እስካሁን ድረስ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ።

የዞኑ መስኖ ልማት ባለስልጣን ጽህፈት ቤት የመስኖ ኤክስቴንሽን አስተባባሪ አቶ አብዱ ኢፋ እንዳስታወቁት በዞኑ በመጀመሪያው ዙር ከ88 ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለምቷል።

በ17 ወረዳዎች ከለማው ከዚህ መሬት 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

እስካሁን ድረስ በተካሄደው ምርት የማሰባሰብ እንቅስቃሴም ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአትክልትና የአገዳ እህል ተሰብስቦ ለአካባቢው ገበያ እየቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።

ቀሪውን ምርት የመሰብሰቡ ሥራ እስከ መጪው መጋቢት ወር መጨረሻ ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

አቶ አብዱ እንዳሉት የመስኖ ልማቱ የተካሄደው ባህላዊና ዘመናዊ የመስኖ አውታሮችን ጨምሮ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችንና የጉድጓድ ውሃን በመጠቀም ነው።

በልማቱም ከተሳተፉት ከ143 ሺህ ከሚበልጡ አርሶ አደሮች መካከል 14 ሺህ የሚጠጉት ሴቶች መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በመስኖ ልማት ከተሳተፉት መካከል የጎቡ ሰዮ ወረዳ አርሶ አደር ቶላ በንቲ እንዳሉት፣ የውሃ መሳቢያ ሞተር በመጠቀም በአንደኛው ዙር ካለሙት ሦስት ሄክታር ማሳቸው ላይ 520 ሳጥን ቲማቲም አምርተዋል።

የቲማቲም ምርታቸውን ለአካባቢው ገበያ በማቅረብም 312 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ነው የገለጹት።

አርሶ አደሩ ዓምና በቆሎና ጥቅል ጎመን በመስኖ ማልማታቸው አስታውሰው ዘንድሮ ገበያ ተኮር ለሆኑ ምርቶች ትኩረት በመስጠት እያለሙ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በ2 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመንና ቃሪያ በመስኖ ማልማታቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ንጉሣ ተስፋዬ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ጥቅል ጎመን ባይደርስም 50 ሳጥን ቲማቲምና ቃሪያ ሰብስበው ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሦስት ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ በቆሎ፣ አንጮቴና ሌላም እጽዋት በማልማት እስካሁን 75 ኩንታል ምርት በመሰብሰብና ለገበያ በማቅረብ ከ36 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን የተናገሩት ደግሞ የሲቡ ስሬ ወረዳ የለሊሣ ቀበሌ አርሶ አደር አዱኛ ሀምቢሣ ናቸው።

አርሶ አደር አዱኛ በእሼት ደረጃ ከሚገኘው የበቆሎ ማሳቸው ተጨማሪ ገቢ እንደሚጠብቁም ነው የገለጹት።

 

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ የካቲት 24/2010 የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ፡፡

የክልሉ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የሚድያና የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ አቶ ብርሃና ተክሉ  ለኢዜአ እንዳሉት ነዋሪዎቹ በቦንድ ግዢና በስጦታ ድጋፉን ያደረጉት የህዳሴ ግድብ ችቦ ወደ ክልሉ ከገባበት ከየካቲት 1 ቀን 2010 ወዲህ ነው፡፡

ችቦው የአማራ ክልል ቆይታውን አጠናቆ ወደ ትግራይ ክልል ከገባበት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በክልሉ አራት ዞኖች መዘዋወሩን ገልፀዋል፡፡

ነዋሪዎቹም በተደረጀ መልኩና በተናጠል ለግድቡ ግንባታ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ቦንድ ግዢና በስጦታ ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡

ላለፉት አራት ቀናት በትግራይ ደቡባዊ ዞን ቆይታ ያደረገው የህዳሴ ችቦ ትናንት ወደ ትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን መሸኘቱንም አስታውቀዋል፡፡

ችቦው በክልሉ እስከ መጋቢት 7ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ቆይታ የሚያደርግ ሲሆን፣ በቀሩት ቀናት ውስጥ የክልሉ ህዝብ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የከቲት 24/2010 ምሩቃኑ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎች የማምረትና በዘርፉ ብቁ ዜጋ የማፍራት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ በመካኒካል፣ በኮንስትራክሽን፣ በአይሲቲና በኤሌክትሪካል ቴክኖሎጂና ሌሎች ዘርፎች በመጀመሪያ ዲግሪ ለሶስት ዓመት ያሰለጠናቸውን 534 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳህለስላሴ ተካ እንዳሉት ምሩቃን ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በመቅዳት፣ በማሸጋገርና የኢንዱስትሪዎችን ተወዳዳሪነት ለመጨመር በሚደረገው አገራዊ ጥረት የጎላ ሚና አላቸው።

ምሩቃኑ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የተሰማሩ በመሆናቸው ባገኙት ተጨማሪ እውቀት ብቁ ዜጋ በማፍራት ተግባር ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

ተመራቂዎች ወደ ክልላቸው ሲሄዱ በቆይታቸው በእውቀትና በንደፈ ሃሳብ ያካበቱትን እውቀት በአግባቡ እንዲተገብሩም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ኢንስቲትዩቱ ካስመረቃቸው 534 ተማሪዎች መካከል 102ቱ ሴቶች መሆናቸው በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሰራ ላለው ስራ ዋቢ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጣው ወጣት ያረጋል ሌሊሴ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ምሩቅ ሲሆን በስልጠናው በቆየባቸው ጊዜያት በተግባር የተደገፈ ሰፊ እውቀት መቅሰሙን ነው የተናገረው።

"ከዚህ ቀደም ካለኝ እውቀት በተጨማሪ በሳይንስና ዓለማቀፍ ተወዳዳሪ በሆኑ የማሰልጠኛ ቁሳቁሶች ስልጠና አግኝቻለሁ" ብሏል።

"መንግስት በክልሎች በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ያለውን የበቃ የሰው ሃይል እጥረት ለመፍታት እየሰራ ያለው ስራ ጥሩ ነው፤ በቀጣይም ከግብዓት አቅርቦት አንጻር እያጋጠመ ያለውን ችግር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል" ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

ከጋምቤላ ክልል የመጣው ተመራቂ ታምራየሁ ሱርማ በበኩሉ በክልሉ የቴክኒክና ሙያ መምህር የነበረ ሲሆን ባገኘው እውቀት ያስተማረውን ህብረተሰብ ለማገልገል እንደሚሰራ ገልጿል።

በቆይታው የውጭ አገራትን ተሞክሮ ያካተተና በተግባር የተደገፈ ስልጠና በማግኘቱ እውቀቱን ለማሻሻል እንደረዳው ነው የተናገረው።

ኢንስቲትዩቱ በአገሪቷ በፌዴራል የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ብቸኛው ተቋም ሲሆን ከተቋቋመ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ የዛሬዎቹን ሳይጨምር 1 ሺህ 14 ሰልጣኞችን በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ አስመርቋል።

 በ24 የስልጠና መርሃ ግብሮችና በአራት ዘርፎች 7 ሺህ 804 ሰልጣኞችን በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ በቀን፣ በማታና በርቀት መርሃ ግብር በማሰልጠን ላይም ይገኛል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 24/2010 በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ አምስት ቋሚ 'ፕላኔተሪየሞች' እንደሚገነቡ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ አስታወቀ።

ፕላኔተሪየም በምድር ላይ ሆኖ የህዋ አካላት የሆኑት ከዋክብት፣ ጋላክሲዎችና ፕላኔቶች የሚያደርጉትን አጠቃላይ እንቅስቃሴ መመልከት የሚቻልበት ቦታ ነው።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ለሁለት ቀናት የሚያካሂደው 12ኛው ጠቅላላ ጉባዔው ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተጀምሯል።

የሶሳይቲው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብነት እዝራ ለኢዜአ እንደገለጹት በተጠቀሱት ዓመታት አምስት ቋሚ 'ፕላኔተሪየሞች' በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይገነባሉ።

የስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲው ቦርድ በነሐሴ 2009 ዓ.ም ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ለ'ፕላኔተሪየሙ' ግንባታ የመጀመሪያ ምዕራፍ የሆነው የፕሮጀክት ጥናት በጃፓን፣ ስፔንና እንግሊዝ የፕላኔታሪየም ተቋማት መካሄዱን ገልፀዋል።

ከጥናቱ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ የሚሆኑ ተሞክሮዎችና እውቀት እንደተገኘም አመልክተዋል።

ጥናቱ በተካሄደባቸው አገራት ከሚገኙ ተቋማት ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር ከመቻሉ ባሻገር ስለ 'ፕላኔተሪየም' ምንነት ተጨባጭ እውቀት መቅሰም መቻሉንም ነው አቶ አብነት ያብራሩት።

በተጨማሪም ለ'ፕላኔተሪየሞቹ' ግንባታ እውን መሆን የሚያስፈልጉ ወሳኝ ግብዓቶችና የምህንድስና ስራዎችንም ለማወቅ ተችሏል።

በጥናቱ መሰረት የቋሚ 'ፕላኔተሪየሞች' ግንባታው ከሶስት እስከ አምስት ዓመት ባለው ጊዜ መጠናቀቅ እንዳለበትና ለዚሁ የሚሆን ገንዘብም ከአገር ውስጥና ከውጭ አገራት ማሰባሰብ እንደሚያስፈልግ መታወቁን ገልጸዋል።

አንድ ቋሚ 'ፕላኔተሪየም' ለመገንባት 200 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅና ይህም ከስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲው አቅም በላይ በመሆኑ ለመንግስትና ለውጭ አገራት ድርጅቶች ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአንድ ዓመት ሁለት ተንቀሳቃሽ 'ፕላኔተሪየሞችን' ገዝቶ ማስገባትና ስራ ላይ ማዋል የሚቻልበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑንም ነው አቶ አብነት የተናገሩት።

ለዚህም የሚያስፈልገውን የሁለት ሚሊዮን 340 ሺህ ብር የሀብት ማሰባሰብ ስራ በስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲው እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የሀብት ማሳበሰብ ስራው ከተከናወነ በኋላ ለግንባታው የሚያስፈልገው መሬት ጥያቄ ለአዲስ አበባ አስተዳደር እንደሚቀርብ ተናግረዋል።

የራስን 'ፕላኔተሪየም' መገንባት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያስወጣ ቢሆንም፤ አገሪቷ ሳተላይት ለመግዛት ከምታወጣው ወጪ በላይ እንደማይጠይቅ ነው ያስረዱት።

በአሁኑ ወቅት የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፕሮግራም በመጠቀም ድህነትን አሸንፎ ብልጽግና ማምጣት እንደሚያስችል መታመኑ በዘርፉ ከታዩ ትልቅ የአመለካከት ለውጦች ውስጥ ዋነኛው እንደሆነም ነው አቶ አብነት የተናገሩት።

በህብረተሰቡ ዘንድ ኢትዮጵያ በስፔስ ሳይንስ አሳካቸዋለሁ ብላ ያቀደቻቸውን ሃሳቦች እውን ታደርጋለች የሚል የይቻላል እምነት እያደገ መምጣቱንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ በአሁኑ ጉባዔው የስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲውን ቅርጫፍ ጽህፈት ቤቶች የ2009 ዓ.ም በጀት ዓመት ሪፖርት የሚያደምጥ ሲሆን የዘርፉ ተመራማሪዎች የህዋ ሳይንስ ጥናትና ጽሁፍ እንደሚያቀርቡም የወጣው መርሃ ግብር ያሳያል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ሐምሌ 10 ቀን 1996 ዓ.ም በ47 አባላት የተቋቋመ ሲሆን አሁን ከ10 ሺህ በላይ አባላትን አፍርቷል።

 

ሃብታሙ አክሊሉ (ኢዜአ)

 

‘’አድዋ ጫማችንን አውልቀን የምንቆምበት የአፍሪካ የተቀደሰ ስፍራ ነው’’ ዩዌሪ ሙሴቪኒ

ጥንት አባቶቻችን እንደ አንድ መክረው፣ እንደ አንድ ወስነው፣ በአንድ ወኔና ተነሳሽነት እስከ አፍንጫው ታጥቆ የመጣን ወራሪ ሃይል መመከት የቻሉበት የአድዋ ድል በአል እነሆ 122ኛው ዓመት ላይ ደረሰ። እዚህ ግባ በማይባል የጦር መሳሪያ ሳይኖር ነገር ግን የህብረት ክንድ ባጠነከረው ወኔ አባት አያቶቻችን ያስመዘገቡት ድል በአስገራሚነቱ እስካሁንም አነጋጋሪ እንደሆነ ነው። የዛሬ 122 አመት የተፈፀመው የጦር ሜዳ ገድልን በወቅቱ የነበሩ ታዋቂ መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር ብዙ ብለውለታል። በየዓመቱም በሚካሄደው የድል በአል አከባበር ላይ የአፍሪካም ሆነ አለም አቀፍ ሚዲያው ስለ አድዋ ፅፈውና ተናግረው ሊጨርሱ አልቻሉም። በተለያዩ ጊዜያትም አድዋን እያነሱ ለህዝባቸው አልበገር ባይነትንና አሸናፊነትን እያስተማሩበት ይገኛሉ። የሃገር መሪዎች ሳይቀሩ ስለ አድዋ ዘመን ተሻጋሪ አስተያየቶችን ሰጥተውበታል። በተለያዩ ጊዜያት የትኞቹ መገናኛ ብዙሃን ስለ አድዋ ምን አሉ የሚለውን ቀጥለን እንመልከት። 

የአድዋ ድል የአለማችንን ታሪክና ፖለቲካ ከላይ ወደ ታች ግልብጥብጡ እንዲወጣ ያደረገ የኢትዮጵያውያን ብሎም የአፍሪካውያን ድል ነው ሲል ስለ አድዋ  ዘገባው ላይ ያነሳው ኦሪጅንስ ዶት ኮም አውሮፓውያን በአፍሪካውያን ላይ ይዘውት የቆዩትን አመለካከት የቀየረ እንደነበርም አስታውሷል።።

የአድዋ ጦርነት ዝም ብሎ ከተራ ትርክት የሚመደብ ጦርነትም አይደለም በማለት ሃሳቡን ያጠናከረው የድረ ገፁ ፀሃፊ በአንድ ወቅት የአድዋ ጦርነትን አስመልክቶ ብዕሩን ያነሳውን ሬይሞንድ ጆናስ የተባለን ፀሃፊ ሃሳብ ይጋራል። ሬይሞንድ ጆናስ የጦርነቱን የኋላ ዳራ፣ ጦርነቱንና ከጦርነቱ በኋላ የነበሩ ክስተቶችን ግልፅ አድርጎ በብዕሩ የከተበ የታሪክ ፀሃፊ ነው። ፀሃፊው የአድዋን ጦርነትና ከዚያም በኋላ የተገኘው ድል አመጣ ባላቸው ሶስት ጉዳዮች ላይ ተመርኩዞ ይገልፃቸዋል።

እንደ ፀሃፊው አድዋ የቅኝ ገዢነት አስተሳሰብን የገታ የጣሊያን ቅኝ ገዢን ጉልበት በአርበኝነት ተጋድሎ ያሽመደመደ ነው። የወራሪው የጣሊያን ጦርን ቅስም የሰበረ በወቅቱ የነበረውን የጣሊያን ገዢ ሃይል በራሱ ተማሪዎች ‘’ቪቫ ምኒሊክ” እንዲሉ ያስገደደ ድል ነው የአድዋ ድል። የአድዋ ድል በወቅቱ የአፍሪካን አህጉር ይዞ ሲበዘብዝ ለነበረው የቅኝ ወራሪ ሃይል ትልቅ ትምህርትን ያስተላለፈ መሆኑን ፀሃፊው እንደ መጀመሪያ ጉዳይ ያነሳል።    

በሁለተኛነት የአድዋ ድል የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጥበበኛና ሊገለፁ የማይችሉ ታሪካዊ መሪ እንዲሆኑ ያስቻለ መሆኑን ሬይሞንድ ይጠቅሳል። የጦር ጀግኖች ድልን ባጣጣሙበት ቅፅበት ሰዋዊ አስተሳሰባቸውን ያጡና ሌሎች ያልተገቡ ድርጊቶችን ሲፈፅሙ ማየት ሰርካዊ በሆነባት አለም አጼ ምኒልክ ምርኮኞቻቸውን የያዙበትን ሂደት ፀሃፊው ለአድናቆት እንዲንደረደር እንዳደረገው ፅፏል። የባለቤታቸውን የእቴጌ ጣይቱ ብጡል ጠንካራ ድጋፍ ስራ ላይ በማዋል ውጤታማ እንዳደረጋቸውና ይህም የአጼ ምኒልክን ብልህነት የሚያሳይ ነው። የአጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ የጀግንነት ተግባር ስፔንን አንድ ካደረጉት ባልና ሚስት ፈርዲናንድና ኢዛቤላ ጋር በማገናኘት ፀሃፊው ገልፆታል። ህዝቡን ለአንድ አላማ በጠንካራ ተነሳሽነት አንዲተም በማድረግ ለአለም ህዝብ አስገራሚ የድል ብስራትን ያወጁ መሪ መሆናቸውንም ፀሃፊው የአጼ ምኒልክን ብልህነት ከገለፀባቸው ጉዳዮች መካከል ነው።   

ሌላውና ፀሃፊው በሶስተኛነት ያነሳው ጉዳይ የአድዋ ድል ለአፍሪካውያን ብሎም ለአፍሪካ አሜሪካውያን የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ምልክት መሆኑን ነው። የአድዋ ድል አጼ ምኒልክ በትረ ስልጣናቸውን አጠናክረው የሃገራቸውን ነፃነት እንዲያስከብሩ ያደረጋቸው ሲሆን ለፓን አፍሪካን ራዕይ አቀንቃኞች ደግሞ በተምሳሌትነቱ የሚጠቀስ ነው። ለዚህም ይመስላል እኤአ በ1904 የሃይቲው የፓን አፍሪካ ባለ ራዕይ ቤኒቶ ሲልቪያን እንደ ሌላኛዋ ሃገሩ ወደሚቆጥራት ኢትዮጵያ መምጣቱ። ሃይቲ በ18ኛው ክ/ዘመን መባቻ የመጀመሪያዋ የተሳካ የጥቁሮች አብዮት የተካሄደባት ሃገር መሆኗን ፀሃፊው ሳይዘነጋ ያነሳል። የአድዋ ድል በአለም ታሪክ ውስጥ ነጮች ስለ ጥቁሮች እንዲሁም ጥቁሮች ስለ ነጮች ከድሉ በፊት የነበራቸውን አመለካከት የቀየረ ትልቁ የለውጥ መዘውር ነው፤ በማለት ፀሃፊው ሃሳቡን ቋጭቷል።

አፍሪካ ከአድዋ ድል ልትወስዳቸው የሚገቡ ትምህርቶች በርካታ ናቸው ሲል ስለ አድዋ ድል ምስክርነቱን የሚሰጠው የሩዋንዳው ኒው አፍሪካን ጋዜጣ አጼ ምኒልክ በሃገር ውስጥ የነበረባቸውን ልዩነት ትተው በወቅቱ በየራሳቸው የጦር ሃይል የነበራቸውን የየአካባቢ ገዢዎች በማስተባበር አንድ መቶ ሺ ሰራዊት አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ማስድረጋቸውን እንደ አንድ ማሳያ ያነሳል።

ሌላኛው መቅሰም የሚገባው ትምህርት ብሎ ያነሳው ደግሞ አጼ ምኒልክ የባለቤታቸውን እገዛ ቸል አለማለታቸውና በውጫሌ ስምምነት ወቅት የተፈጠረውን ጉዳይ እንዲከታተሉ ሃለፊነቱን ለእቴጌ ጣይቱ መስጠታቸውን ከብልህነት ፅፎላቸዋል። የአፍሪካ ሃገራት የውል ስምምነት (contract agreement) ሲገቡ መውሰድ የሚገባቸውን ጥንቃቄ ለአድዋ ጦርነት በመንሰኤነት የተጠቀሰው የውጫሌ ውል ሂደት ትልቅ ትምህርት ሊሆናቸው እንደሚችል ኒው አፍሪካን ጠቅሷል። ከቅኝ አገዛዝ ነፃ መውጣት በኋላ አፍሪካውያን ከምዕራባውያን ጋር በሚገቡት ጥንቃቄ የጎደለው ውል ሳቢያ የአፍሪካን ሃብት መቀራመቱን የተለመደ አድርገውት እንደቆዩ ዋቢ አድርጓል።    

የአፍሪካን ታሪክ ለመረዳት የአድዋን ጦርነት ታሪክ መገንዘብን ይጠይቃል ያለው ኳርትዝ አፍሪካ በጦርነቱ በሁሉም ሁኔታ የኢትዮጵያውያን አሸናፊነት የታየበት እንደነበር እማኝነቱን ሰጥቷል። ለዚህም ዘ ኒውዮርክ ታይምስ እኤአ ማርች 2 ቀን 1896 ኢትዮጵያውያን በጣሊያናውያን ላይ የፈፀሙትን ታላቅ የጀግንነት ተግባር በሚያወሳውና “Abyssinians defeat Italians: Both wings of Baratieri’s army enveloped in energetic attack.” በሚል ርዕስ ያሰራጨውን ዘገባ በአስረጂነት ተጠቅሞበታል። ሽንፈቱን የተከናነበው የጣሊያን ወራሪ ሃይል 3ሺ የጦር ሃይል አባላቱን ሲያጣ 60 መሳሪያዎችን ጨምሮ በሁሉም የጦር ክፍሉ ላይ ከባድ ኪሳራ እንደደረሰበት ኒውዮርክ ታይምስ በቀጣይ እትሙ ላይ ይዞት ወጥቷል። የኢትዮጵያውያኑ የጦር ሜዳ ውሎ ስኬትና ጀግንነት በበርካታ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በስፋት ተዘግቦ እንደነበርም የታሪክ ድርሳናት ከትበውት ይገኛል።

የኢትዮጵያውያን ድል ቅኝ ገዢዎች በአፍሪካ ላይ የነበራቸውን እሳቤ ከመሰረቱ የቀየረ ከመሆኑም ባለፈ ታላቅ የኋላ ዘመን ታሪካዊና ፖለቲካዊ ክስተቶች እንዲፈጠሩም ያደረገ ነበር። አፍሪካውያን በፀረ ቅኝ አገዛዝ ተጋድሎ ውስጥ በቅኝ ገዢዎቻቸው ላይ ስኬታማ ውጤት ሊያስመዘግቡ እንደሚችሉ የተነበየ ብሎም ያሳየ ድል ነው ሲል ኳርትዝ አፍሪካ ገልፆታል።

የሱዳኑ ሱዳን ትሪቡን በአንድ ወቅት የአድዋ ድልን አስመልክቶ ባስነበበው እትሙ በወቅቱ እጅግ ኋላ ቀር መሳሪያ የታጠቀው የኢትዮጵያ ጦር በአስገራሚ ወኔ በጊዜው ገንዘብ ሊገዛው የቻለውን መሳሪያ የታጠቀውን የጣሊያን ጦር ማሸነፉን ፅፏል። በጣሊያን በኩል ሙትና ቁስለኛ የሆነውን ሃይል ሱዳን ትሪቡን ሟቾቹን 7ሺ እንዲሁም ቁስለኞቹን ደግሞ 1ሺ 500 መሆናቸውን ይገልፅና 3ሺዎቹ መማረካቸውን ያሳያል። እኤአ በ1896 ዓ.ም የኢትዮጵያውያን ጀግንነት ያሳየው የአድዋ ድል የወራሪው የጣሊያን ጦር በሁለቱም የአለም ጦርነቶች ሽንፈትን እንዲከናነብ ጥላውን እንዳጠላበትም ጋዜጣው አክሏል።

የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ በያመቱ ሜይ 25 በሚከበረው የአፍሪካ ቀን ጉባኤ ላይ ተገኝተው ስለ አድዋ በአል ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ምቤኪ የአድዋ ጦርነት የኢትዮጵያ ነፃነት እንዲቀጥል ከማድረጉም ባሻገር ሀገሪቷ በወቅቱ በቅኝ ግዛት እንደተያዙት ሃገራት እንዳልሆነች ያሳየችበትም ጭምር እንደሆነ የገለፁበት ሁኔታ በአፅንኦት ሊጠቀስ የሚገባው ነው።

‘’የበርሊኑ ጉባኤ አፍሪካ በቅኝ አገዛዝ ውስጥ መውደቅ እንዳለባት ሲወስን ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አፍሪካ በቅኝ ግዛት ቀንበር መያዝ የለባትም አሉ፤ ተሳካላቸውም’’ ነበር ያሉት ምቤኪ ተሰብሳቢውን ባስደመሙበት ንግግራቸው።

የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ በአድዋ ድል ክብረ በአል ላይ በተገኙበት ወቅት በአድዋ ድል በአል አከባበር ስነ ስርዓት ላይ በመገኘታቸው ብቻ ክብር እንደሚሰማቸው ተናግረው ለድል በአሉ ምን አይነት ክብር መስጠት እንዳለባቸው እንዲህ ብለው ነበር።

 “…ጫማዬን ማውለቅ ይኖርብኛል ምክንያቱም ይህ የተቀደሰ ስፍራ ነው። አድዋ የአፍሪካ የተቀደሰ መሬት ነው። አድዋ የአፍሪካን የውርደት ሸማ የገፈፈ ነው። አፍሪካ በውጭ ወራሪ ሃይል ተይዛ በቅኝ ግዛት ተይዛ ነበር ብለው የሚያስቡ ሰዎች ሃፍረት ሊሰማቸው ይገባል።”

የአድዋ ድል በአል ከዚህም በበለጠ የተቡ ብዕሮች ሊፅፉለት፣ የሰሉ አዕምሮዎች ጥልቅ ጥናት ሊያደርጉበት፣ ርቱዕ አንደበቶች ሊናገሩለት ይገባል። የአሁኑ ትውልድም ጥንት አባት አያቶቹ የሰሩትን ገድል ከማወቅ በዘለለ በተግባር እንዲኖራቸው ማድረግ ከሁሉም የቀደመ ተግባራችን መሆን አለበት። ደራሲዎቻችን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቻችን፣ አልፎ ተርፎም የፖለቲካ ሰዎቻችን ወጣቱ ትውልድ ሰርክ አባቶቻችን ዘር፣ ቀለም፣ ቋንቋ፣ ሳይገድባቸው የሰሩትን ገድል እንዲገነዘብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

Published in ዜና ትንታኔ

አዲስ አበባ የካቲት 24/2010 የቀድሞውን የድሬዳዋ-ሚኤሶ የባቡር መስመር በመጠገን ወደ ስራ ለማስገባት እየሰራ መሆኑን የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ገለፀ።

የባቡር መስመሩ እንደገና ስራ መጀመር በአዲሱ የባቡር መስመር የማይደረሱትን የምስራቁን የአገሪቱ ከተሞች ወደ መስመሩ ለማስገባት ይረዳል ተብሏል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ተጠሪ አቶ አብዱላዚዝ አህመድ ድርጅቱ ከፍተኛ ጥገናዎችን የሚያከናውኑ የጥገና ማዕከላትና የእውቀት ብቃት ያፈራ በመሆኑ የባቡር መስመሩን ጥገና በራሱ በማድረግ ወደ ስራ ለማስገባት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የቀድሞው የባቡር መስመር ለጥቂት ዓመታት ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም ጥገና በማድረግ ከድሬዳዋ ደወሌ በሳምንት ሶስት ጊዜ በመመላለስ ድሬዳዋ ለሚገኙ ፋብሪካዎች ጥሬ እቃ፣ በመስመሩ ለሚገኙ ከተሞችም የግብርና ምርቶችን የማቅረብ ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።

ጥገናውን በማስፋት ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ መስመር እስከ ሚኤሶ ያለውን 150 ኪሎ ሜትር በመጠገን የመስራት እቅድ መያዙንም ነው የተናገሩት።

የባቡር መስመሩ መጠገን በዚሁ ሳቢያ ለተመሰረቱ ከተሞችና ድሬዳዋ ለሚገኙት የኢንዱስትሪ ዞኖች የትራንስፖርት አማራጭ ይሆናል ነው ያሉት።

በነዳጅ የሚሰሩ ሶስት የህዝብና ስድስት የእቃ ማመላለሻ ባቡሮች መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል። 

ከሚጠገነው መስመር አብዛኛው በተሻለ ደህንነት ላይ እንደሚገኝ፣ መስመሮቹ በኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች እንደሚጠገኑና ከድሬዳዋ አራት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለ ድልድይ ግንባታ ብቻ ከመንግስት እንደሚጠበቅ ነው አቶ አብዱላዚዝ የገለፁት። 

የድሬዳዋ ምክትል ከንቲባ አቶ አብደላ አህመድ በበኩላቸው አስተዳደሩ የቀድሞውን የባቡር መስመር ከአዲሱ የባቡር መስመር ጋር ለማስተሳሰር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

ጥገናው ሙሉ በሙሉ በድርጅቱ ባለሙያዎች የሚሰራ መሆኑን ጠቁመው ይህም ወደ ገንዘብ ቢቀየር 30 ሚሊዮን ብር እንደሚሆን አክለዋል።

የቀድሞው የባቡር መስመር ግንባታ 20 ዓመታትን ፈጅቶ በ1911 ዓ.ም ስራ የጀመረ ሲሆን ስራው ከፈረንሳይ መንግስት ጋር በተደረገ ስምምነት እንደተፈጸመ ይታወሳል።

Published in ኢኮኖሚ

ጎንደር የካቲት 24/2010 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ዘርፉን ደህንነት ለማረጋገጥ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን በጎንደርና ደባርቅ ከተሞች የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ፡፡

የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ መዳረሻ በሆነችው ደባርቅ ከተማ የኢኮ ቱሪዝም ማህበር ሊቀ-መንበር አቶ ማረው ተረፈ እንደተናገሩት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት ለመቆጣጠር አስፈላጊ ነው፡፡

ቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ከሁሉም በላይ ሰላም ይፈልጋል ያሉት አቶ ማረው ባለፈው አመት በደባርቅ አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ ችግር  የቱሪዝም ፍሰት ተስተጓግሎ 8ሺ የማህበሩ አባላት ችግር ላይ ወድቀው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት የማህበሩ አባላት ያገኙት ገቢ ከ700ሺ ብር ያልበለጠ ስለነበር ለማህበሩ ቋሚ ሰራተኞች ወርሃዊ ደሞዝ ለመክፈል ተቸግረው እንደነበር ገልፀዋል፡፡

በዚህ አመት በተፈጠረው ሰላም ባለፉት 6 ወራት ብቻ የማህበሩ አባላት ለቱሪስቶች የተለያዩ አገልግሎት በመስጠት 2 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ የቱሪዝም ዘርፉን ደህንነት ለማረጋገጥ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በጎንደር ከተማ በጉልት ስራ የተሰማሩት ወይዘሮ አስማረች ሲሳይ በበኩላቸው ''ሰላም ከሌለ ነግዶም ሆነ ወጥቶ መግባት አይቻልም፤ ሰላም የሁሉም መሰረት ነው'' ሲሉ ተናግረዋል፡፡

''መንግስት ዜጎቹን የሚጎዳ አዋጅ ያውጃል ብዬ አላስብም'' የሚሉት ወይዘሮ አስማረች የአምናው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በከተማው ሰላም አስፍኖ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

''የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊ ነው'' ያሉት በከተማው የቀበሌ 6 ነዋሪ የሆኑት አቶ አድማስ ደሞዜ ናቸው፡፡

የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ሰላም ያስፈልጋል ያሉት አቶ አድማስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ህዝብ በየደረጃው የሚያቀርባቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ በሚያስችል መልኩ ሊያግዝ ይገባል ብለዋል፡፡

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን